June 13, 2013
እንደሚታወቀው
በአንድ ሃገር የኤኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ክንውኖች የቀን ተቀን ለውጥ ውስጥ የህብረተሰብ ተሳትፎ(አስተዋጾ)
ጉልህ ሚና አለው፡፡ እንዲሁም በሂደትቱ ውስጥ የሚያጋጥሙ አገራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ጉዳዮችም ይሁኑ ወይም በተቃራኒው
የሚከሰት ተፈጥሯዊም ሆነ በመልካም አስተዳድር ችግር ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮች ከህብረተሰብ ጫንቃ ላይ
አይወርድም፡፡ ይህ ስለሚታወቅ ሃላፊነት የሚሰማቸው፣ ለሃገርና ለሕዝብ ታማኝ የሆኑ፣ በሕዝብ ይሁንታ ስልጣን
የያዙ መንግስታት ያላቸው ሃገሮች በየትኛውም ሃገራዊ እንቅስቃሴ ላይ ሕዝባቸውን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ
በማድረግ በቤሔራዊ ስሜት የታነፀ በሃገሩ ጉዳይ የማያመነታ ህብረተሰብ ይገነባሉ፡፡ የእንደኛ አይነቶቹ የሃገርና
የሕዝብ ፍቅር የሌላቸው አምባገነን መሪዎች ግን እንኳን የሃገርህ ጉዳይ ያገባሀል ብለው ሊያሳትፉት ቀርቶ የሕዝብን
የመናገርና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ ተፈጥሮዊ መብቱን ገፈው ሃገሪቱን የቁም እስር ቤት አርገዋታል፡፡
በሕዝብ
ላይ የሚፈፅሙትን ኢሰብአዊ የሆነ የመብት ጥሰትን የተቃወመ፣ ሕዝብ እየተፈናቀለ ሃገር ሲቸበቸብ ኢትዮጲያ
የኢትዮጲያዊያን ነች ብለው የተቃወሙትን፣ የእምነት ነፃነታቸውን አናስነካም ብለው በሰላማዊ መንገድ መብታቸውን
የጠየቁና በሌላም ሃገራው ጉዳይ ላይ እንደ ዜጋ ይመለከተናል ያሉትን የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይ የተማረውን ክፍል
ስም እያወጡ በየማጎሪያው በእስር በማሰቃየትና ገሚሱንም በማሳደድ ኢትዮጲያ የምንላትን የሁላችን የሆነች ታላቅ
ሃገር በሞኖፖል በመቆጣጠር የአንድ ግለኛ ቡድን የግል ሃብት አረገዋታል፡፡
ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት
ለሃገርና ለሕዝብ የተሻለ ሃሳብ አለን የሚሉትን የተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎችን ጨምሮ የሞያ ስነምግባራቸውን ጠብቀው
አምባገነኑ ስርዓት በሕዝብና በሃገር ላይ የሚፈፅመውን ግፍና በደል በብእራቸው ያጋለጡ ጋዜጠኞችን በጅምላ ለሱ
የሚመቸውን ስም እያወጣለቸው በየማጎሪያ ካምፑ የወረወራቸው እጅግ ብዙ የህሊና እስረኞች አሉ፡፡ ከህፃን ልጁ ተለይቶ
በእስር የሚማቅቀው እስክንድር ነጋ፣ እውነት በመፃፏ ከነህመሟ በእስር የምትማቅቀው እርዮት አለሙ፣ በዘረኛው
ቡድን ላይ የሰላ ሂስ በማቅረቡ በአሸባሪነት ተፈርጆ በእስር የሚሰቃየው ወጣቱ ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌ እንዲሁም
በቀለ ገርባና ኦልባና ሌሊሳን ጨምሮ ብዙ ምርጥ የሃገር ልጆች በዚህ ዘረኛ ቡድን ግፍ እየተፈፀመባችው ይገኛሉ፡፡
ለዚህ
ሁሉ በሃገርና በህዝብ ላይ ለሚደርሰው እንግልትና መዋከብ ምንም እንኳን የመንግስትን እርካብ የተቆናጠጡት
ገዢዎቻችን ከተፈጥሮ ባህሪያቸው አንፃር የፈለጉትን ያሻቸውን ቢያደርጉም በየግዜው በህዝብ ላይ የሚያደረሱትን ሰቆቃ
የየሰሞኑ መነጋገሪያ ከማደረግ በዘለለ ህዝብ እንደ ህዝብ በደል በቃኝ፣ ግፍ በቃኝ፣ መሰደድ በቃኝ፣ መታሰርና
መገረፍ በቃኝ፣ ከሃብትና ከቀዬ መፈናቀል በቃኝ ብሎ በተለይ በሃገር ቤት ያለው የበደሉ ገፈት ቀማሽ የሆነው ወገን
ለለውጥ ጥግ ድረስ ለትግል አልተዋቀረም፡፡ ሃገርና ህዝብን ከዚህ እኩይ ስርዓት መታደግን ለተወሰኑ የህብረተሰብ
ክፍሎች ብቻ የሚተው አይደለም የልቁኑም ወያኔን ለመታገል ቆርጠው ከሚሰሩ የህዝብ ሃይሎችን በመቀላቀል ትግሉ
የሚጠይቀንን ሁሉ የምንሆንበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡
ኢትዮጲያ የነማን፣ የማን እንደሆነች ማወቅ
የሚቸግርበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ጥቂት ዘረኛ ቡድኖችና ሆድ አደሮች የነገሱባትና ፈላጭ ቆራጭ ሆነው የቅንጦት ኑሮ
የሚኖሩባት፣ ብዙሃኑ ለሃገርና ለዳር ድንበሩ መከበር ከጥንት ጀምሮ አጥንቱን ከስክሶ ደሙን አፍስሶ ባቆያት ሃገር
ላይ የበይ ተመልካች ሆኖ በርሃብና በእርዛት በሚኖርባት ሃገር ናት፡፡
እናም ይህ ዘረኛ የወያኔ ስርዓት
እንዲያበቃለትና ዘመን እንዳይሻገር እነሱ እንደሚሉን ጥቂቶች(ኢምንቶች) ሳንሆን እልፍ አእላፍ ሆነን ለነፃነታችን፣
ለሃገራችን አንድነትና ለወደቀው ክብራችን ብለን በአንድነት እንነሳ፡፡ ኢትዮጲያ የኛ የብዙሃን እንጂ የጥቂት ዘረኛ
ቡድን መፈንጫ አትሁን!!!!!!!!!!
ኢትዮጲያን እግዚሀብሔር የባርክ!!!!
No comments:
Post a Comment