በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለውን ተቃውሞ ተከትሎ በቅርቡ ተጨማሪ 3ሺ ሰዎች ከተለያዩ የክልሉ ከተሞች በቁጥጥር ስር መዋላቸው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ረቡዕ ገለጠ።
ባለፈው ሳምንት ከሃገር እንዳይወጡ የታገዱትና የኮንግረሱ ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና የመንግስት ባለስልጣናት ለተፈጸመው ግድያና ወከባ በቅርቡ ይቅርታን ቢያቀርቡም እስራቱ ተባብሶ መቀጠሉን ለኢሳት በሰጡት ቃለ-ምልልስ አስታውቀዋል።
ይኸው የእስር ዘመቻም በወለጋ፣ አምቦ፣ አርሲ፣ ምስራቅ ሃረርጌ እና ሌሎች የኦሮሚያ የክልል አካባቢዎች መፈጸማቸውን ዶ/ር መረራ አስረድተዋል።
በቅርቡ ለእስር የተዳረጉት 3ሺ ሰዎች በአሁኑ ወቅት ያሉበት ሁኔታ እንደማይታወቅና በቤተሰብም ዘንድ እንደማይጎበኙ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት ቃለ-ምልልስ ገልጸዋል።
በዚሁ የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ማክሰኞ ዘገባን ያቀረበው የፈረንሳይ የቴለቪዥን ጣቢያ (ፍራንስ 24) በክልሉ ያለው ተቃውሞ ተጠናክሮ መቀጠሉንና ነዋሪዎች በፍርሃት ውስጥ መሆናቸው መዘገቡ ይታወሳል።
ይኸው ውጥረት ተባብሶ መቀጠሉን ያረጋገጡት ዶ/ር መረራ ጉዲና በነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታን አስነስተው የነበሩ የፌዲራል የጸጥታ ሃይሎች አሁንም ድረስ በተለያዩ ከተሞች ሰፍረው እንደሚገኙ አመልክተዋል።
የአለም ትኩረትን ስቦ የሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ በትንሹ ለ200 ሰዎች መሞት ምክንያት የሆነ ሲሆን ቁጥራቸው በአግባቡ ሊታወቅ ያልቻለ ሰዎችም ከባድ የመደብደብ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸውም የሰብዓዊ መብት ተቋማት የፓርቲ አመራሮች ይገልጻሉ።
የመንግስት ባለስልጣናት ተቃውሞ እልባት አግኝቷል ቢሉም ችግሩ አሁንም ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች መቀጠሉን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል። source ኢሳት (መጋቢት 21 ፥ 2008)
No comments:
Post a Comment