በኢትዮጵያ መሰረታዊ የንግግርና የመሰብሰብ ነጻነት ጨምሮ የፖለቲካ ምህዳሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጠበበ መሄዱን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ።መቀመጫውን በብሪታኒያ ለንደን ያደረገው ታዋቂው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከዋሽንግተን ቢሮ እሁድ ግንቦት 14 /2008 ዓ.ም ሜይ 22 /2016 ኢትዮጵያን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ የኢህአዴግ መንግስት የንግግርና የመሰብሰብ ነጻነትን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የከለከለበት ደረጃ ላይ መድረሱን አትቷል።
“ወደተሳሳተ መንገድ ማዝገም፥ እየተዘጋ ያለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር” በሚል ርዕስ ድርጅቱ ባሰራጨው ጽሁፍ፣ የኢህአዴግ መንግስት በኢትዮጵያ እየፈጸመ ነው ያለውን ህገወጥ ተግባር ኮንኗል። መንግስት በሚያደርጋቸው ማናቸውንም አገራዊ ጉዳዮችን መጠየቅ፣ ወይም ተቃውሞ ለመግለጽ መሞከር የማይቻል መሆኑንም አምነስቲ ኢንተርናሽናል በመግለጫው አስፍሯል።
በተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች መከበርና፣ በህግ የበላይነት መስፈርቶች ኢትዮጵያ በመጨረሻዎቹ አገራት ተርታ እንደምትገኝ፣ በፍሪደም ሃውስ “ነጻ ያልሆነች አገር”፣ በWorld Justice Project Rule of Law Index ደግሞ በመንግስት ስልጣን፣ በመሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ከፍተኛ ውድቀት የሚታይባት አገር እንደሆነች መግለጻቸውን ይኸው ተቋም ሁለቱን ተቋማትን እና ሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶችን ዋቢ በማድረግ በጹሁፉ ዘርዝሯል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተዘግተዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በእስር ቤቶች በሃሰት ክስ እየማቀቁ ይገኛሉ፣ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞች በግዳጅ እስር ቤት መወርወራቸውንና መደብደብደባቸውን ቀጥሏል ሲል አምነስቲ በመግለጫው አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ጸረ-ሽብር ህግን በመጠቀም ጋዜጠኞችና ሌሎች ተቃዋሚዎችን ዝም ማሰኘቱን መቀጠሉን፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ የኦፌኮ ተቀዳሚ ም/ፕሬዜዳንት አቶ በቀለ ገርባ፣ የአኝዋኩ የመሬት መብት አቀንቃኝ አቶ ኦኬሎ አኳይ ኦቻላን የመሳሰሉ ዜጎች የመንግስትን ፖሊሲ በመቃወማቸው ብቻ ለእስር እንደተዳረጉና እነዚህ ሶስቱ የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰድ ባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከሚሰቃዩት በሺዎች ከሚቆጠሩ ዜጎች እንደምሳሌ የሚጠቀሱ ናቸው ሲል አምኒስቲ በመግለጫው አትቷል።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የጋዜጠኛ ሙያውን በአግባቡ በመስራቱና በመንግስት ላይ ሂስ የሚያቀርቡ ጋዜጠኞች እንዲታሰሩ የሚደነግገውን ህግ በመቃወሙ 18 አመት በግፍ ተፈርዶበት እንደሚገኝ መግለጫው አብራርቶ፣ በተመሳሳይ መልኩ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባም፣ ባለፈው ክረምት አሜሪካ በተጓዙ ጊዜ NPR ለተባለ ሬዲዮ እንደተናገሩት ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉት ጉዞ በአገሩ ድጋፍ ለሌለው መንግስት የተሳሳተ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ በመናገራቸው እንዲሁም እሳቸው ከአሜሪካ ወደኢትዮጵያ ሲመለሱም በነጻነት እንደሚኖሩ ጥርጣሬ ውስጥ ነኝ በማለታቸው አሁን 4 በ 5 ሜትር በሆነች ጠባብ ክፍል ከ21 እስረኞች ጋር እንደታሰሩ በአምነስቲ ዘገባ ተመልክቷል። አቶ በቀለ የተከሰሱትም ክስ እንደተለመደው በሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በተወገዘው በጸረሽብር ህጉ እንደሆነና የእስሩ ዓላማም የተቃዋሚውን ድምፅ ለማዳፈን እንደሆነ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘግቧል።
የኖርዌይ ዜግነት ያላቸው አቶ ኦኬሎ አኳይ ኦቻላም ከደቡብ ሱዳን ጁባ ከተማ ከሁለት አመት በፊት ተጠልፈው ባለፈው ሚያዚያ ወር የ9 አመት እስራት እንደተፈረደባቸው ሪፖርቱ ገልጾ፣ አቶ ኦኬሎ የመሬት ቅርምት በከፍተኛ ሁኔታ ከሚካሄድበት፣ ዜጎች ያለፈቃዳቸው በሚፈናቀሉበት ጋምቤላ ክልል ፕሬዚደንት ሆነው እንደሰሩም አስታውሷል። አቶ ኦኬሎ ከደቡብ ሱዳን ተጠልፈው ወደ ኢትዮጵያ ተወስደው እንደሌሎች ኢትዮጵያውያን እስረኞች ሁሉ እሳቸውም በጸረ-ሽብር ህግ እንደተከሰስሱ እና የ ዘጠን አመት እስር እንደተፈረደባቸው ገልጿል። በመረጃ ግብዓትነት የቀረበባቸው ደግሞ እሳቸው በብቸኝነት ታስረው በነበሩ ጊዜ ለፖሊስ ሰጡት የተባለው ቃል ሲሆን፣ አቶ ኦኬሎ በምርመራ ወቅት ስቃይ (ቶርቸር)ና ድብደባ እንደተፈጸመባቸው መረጃ እንዳለው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በአቶ ኦኬሎ ላይ የተላለፈው ፍርድም የኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓትና የህግ የበላይነት ምን ያክል የዘቀጠ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ሲል መግለጫው አትቷል።
ኢህአዴግ በቅርቡ አዳዲስ ህጎችን እያረቀቀ እንደሆነ ያመለከተው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለጫ፣ ድርጊቱ የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚዎችን የማፈን ዘመቻውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ማሳያ ነው ብሏል። በተመሳሳይ ሁኔታ፣ በአሁኑ ሰዓት በመንግስት እየተደረገ ያለው የትምህርት ዕድል፣ የመንግስት ስራና አገልግሎት በፓርቲ አባልነት ብቻ መሆኑ፣ ዜጎች በኢህአዴግ ፖሊሲ በግድ እንዲታነጹ መደረጋቸው፣ በዜጎች ላይ እየተደረገ ያለው ከልክ ያለፈ ቁጥጥር ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ ምንም አይነት ውይይት እንዳያደርጉ ፍርሃት እንደፈጠረባቸው በድረ-ገጹ ባስተላለፈው መግለጫ አስታውቋል።
የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈፅም ማንኛውም መንግስት ተጠያቂ መደረግ እንዳለበት በዘገባው ያሰመረው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ገንዘብና ድጋፍ የሚሰጡ አገሮችም፣ ለሰብዓዊ መብትና መከበር ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው አበክሮ አሳስቧል። በመንግስት የሚፈጸም ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሃይል ወደተመላበት የትግል ስልት ሊያመራ ስለሚችል፣ ለአጭር ጊዜ ጥቅም ተብሎ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽምን መንግስት መደገፍ ችግር ይጋብዛል ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል አመልክቷል። የሰብዓዊ መብት በሚጣስባቸው ሃገራት ህዝብ በድህነት ይሰቃያል፣ የድንበር ግጭት ይባባሳል፣ የህግ የበላይነት ፈተና ውስጥ ይወድቃል እንዲሁም በአጠቃላይ አካባቢውን ሰላም ያሳጣል ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ለኢትዮጵያ እርዳታ የሚሰጡ አገሮች ለሰብዓዊ መብት ቅድሚያ እንዲሰጡ በዘገባው አሳስቧል። source http://amharic.ethsat.com/
No comments:
Post a Comment