Friday, June 17, 2016

የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት ተጠያቂነትና ግልጽነት እንዲኖረው ጠየቀ


 (ሰኔ 9 ፥ 2008)
የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ሃላፊዎች የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት ተጠያቂነትና ግልጽነት የሚታይበት እንዲሆን አሳሰቡ።
የህብረቱ የሰብዓዊ መብት ምክትል ፕሬዚደንት የሆኑት ፊዴሪካ ሞግሪኒ በቤልጅየም ብራሰልስ ጉብኝት እንያደረጉ ካሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር በኦሮሚያ ክልል ስለተካሄደው ተቃውሞና ተያያዥ ፖለቲካዊ ጉዳዮች መምከራቸውን የአውሮፓ ህብረት አስታውቋል።
ህብረቱ እያካሄደ ካለው የልማት ፕሮግራም ጎን ለጎን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የመከሩት የህብረቱ የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ ሃላፊዎች የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት ተጠያቂነትና ግልጽነት እንዲሁም ሁሉን አሳታፊ መሆን እንዳለበት ጥሪ ማቅረባቸውን ከመግለጫው ለመረዳት ተችሏል።
የአውሮፓ ፓርላማ በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ ህብረቱ የተለያዩ እርምጃዎችን እንዲወስድ የሚያስችል ሃሳብ በቅርቡ ማፅደቁ ይታወሳል።
የአውሮፓ ህብረት ሰብዓዊ መብት ምክትል ፕሬዚደንት የሆኑት ፌዴሪካ ሞጌሪኒ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታና ሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ዋናኛ አጀንዳ በማድረግ ከጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር መምከራቸው ታውቋል።
ምክትል ፕሬዚደንቷ በኦሮሚያ ክልል ከተቀሰቀሰው ተቃውሞ ጋር በተገኛኘ ለእስር ተዳርገው ስለሚገኙ ሰዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሰፊ የዝግ ውይይት ማካሄዳቸውን ህብረቱ ገልጿል።
ሁለቱ ወገኖች ረቡዕ ትብብራቸውን ለማጠናከር ስምምነት ቢፈራረሙም በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ስርዓትና ዴሞክራሲ ዋነኛ አጀንዳ ሆነው መቅረባቸውን ለመረዳት ተችሏል።
ከሁለት ወር በፊት የአውሮፓ ህብረት እርምጃን እንዲወስድ የውሳኔ ሃሳቦችን ያቀቀረበው የአውሮፓ ፓርላማ ህብረቱ ለሃገሪቱ የሚሰጠውን ድጋፍ የሰብዓዊ መብት መከበርን መሰረት በማድረግ መሆን እንዳለበት ማሳሰቡ ይታወሳል።                                                                     source http://amharic.ethsat.com/

No comments: