Feb 05, 2015
ጥር ፳፰(ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ህብረቱ ጥር 27፣2007 ዓም በብራሰልስ ቤልጂየም የአውሮፓ ህብረት ጽ/ቤት ውስጥ ለ3 ሰአታት ባደረገው የኢትዮጵያ የሰአብአዊ መብት ግምገማ በኦጋዴን ክልል እና በተቀሩት የኢትዮጵያ ግዛቶች በዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ሰቆቃ የአውሮፓ ህብረትና አባል መንግስታት በዝምታ መመልከታቸውን ማብቃት አለበት የሚል ውሳኔ አስተላልፈዋል።
ስብሰባውን ያዘጋጁት የህብረቱ የሶሻሊስትና የዲሞክራቲክ ፓርቲዎች ጥምር ህብረት ፣ ውክልና አልባ ህዝቦች ተቆርቋሪ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው።
በስብሰባው ላይ የኦጋዴን ክልል ፕ/ት አማካሪ የነበረና በክልሉ የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በመረጃ በማጋለጥ ላይ የሚገኘው ወጣት አብዱላሂ ሃሰን፣ ተቀማጭነቱ በጄኔቫ የሆነ የአፍሪካ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ባልደረባ፣ አቶ አብዱላሂ ሙሃመድ፣ የኦጋዴን ሴቶች ተወካይ ፣ ጋዜጠኛና የክሬት ትረስ ዳይሬክተር ግርሃም ፌብልስ፣ እንዲሁም በኦሮሞ ሴቶች ላይ የሚደረሰውን ሰቆቃ በማስመልከት ጥናት ያካሄዱት፣ ዶ/ርባሮ ቀኖ በቪዲዮ የተደገፈ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
እንግሊዛዊው ግራሃም ፌብልስ በኢትዮጵያ 2 አመታት ቆይታቸው የታዘቡትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተለይም በኦጋዴን ክልል በሴቶች ላይ ተፈጽሟል ያሉትን አስገድዶ መድፈር ወንጀል የታዳሚውን ስሜት በነካ መልኩ አቅርበዋል። በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በዜጎች ላይ ሽብርን እያኬደ ነው ያሉት ሚ/ር ፌብልስ የዚህ ሶቆቃ ፈጻሚዎች፣ ከአውሮፓ ህበረትና መንግስታት በእያመቱ ከፍተኛ የገንዘብ እርዳታ የሚያገኙ መሆናቸው እጅግ የሚያሳዝነው ነው ብለዋል።
በጉባኤው ላይ የኦጋዴን ነጻነት ግንባር ተወካይ ዶ/ር ባዳል አህመድ እና አርበኞች ግንቦት7 ተወካይ አቶ አበበ ቦጋለ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸመ ነው የሚሉትን የሰብአዊና የፖለቲካ መብቶች እረገጣና አስከፊ ሰቆቃ በእየተራ አቅርበዋል።
የአውሮፓ ህብረትን ወክለው በስብሰባው ላይ የተገኙት ወ/ሮ አና ጎሜዝና የእንግሊዝ የፓርላማ ተወካይ ወ/ሮ ጁሊ ዋርድ በየተራ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ መንግስት ከ60 በመቶ በላይ በጀቱን ከአውሮፓ ህበረት እየተቀበለ ዜጎች ላይ እየፈጸማቸው ያለው አስከፊ ሰቆቃዎችን አውሮፓ ካሁን በሁዋላ በዝምታ ማየት የለባትም ካሉ በሁዋላ፣ ኢትዮጵያኖች በአገራቸው እየተፈጸመ ያለውን አፈናና ጭቆና የውች ማህበረሰብ ያስቆምልናል ብለው ከመጠባበቅ ለራሳቸው ነጻነት ልዩነቶቻቸውን በማቻቻልና መለስተኛ ፕሮግራም በማዘጋጀት ህብረት ፈጥረው በአንድነት መታገልና ለለውጥ መነሳት አለባቸው ብለዋል።
የአውሮፓ ህብረት በዘንድሮው ምርጫ ላይ ታዛቢዎችን እንዳይልክ የወሰነው የኢህአዴግ መንግስት በየ5 አመቱ የሚያደርገውን የተሳሳተ ምርጫ በማጀብ ህጋዊነት ለማሰጠት እንደከዚህ በፊቱ ለመተባበር ፈቃደኛ አለመሆኑን ለመግለጽ ሆኖ ሳለ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ግን ህበረቱ በገጠመው የበጀት ችግር ምክንያት ታዛቢ አልክም ብሎአል ብሎ የጀመረው ቅስቀሳ መሰረተ ቢስና የተለመደ ህዝብን የማዘናጊያ ወሬ እንደሆነ ገልጸዋል። የአመቱን 60 በመቶ የሚሸፍን በጀት የሚሰጠው ህብረቱ፣ ኢትዮጵያን የመሰለ ስትራቴጂክ አገር፣ ህብረቱ የገንዘብ እጥረት ገጥሞታል ብሎ ማሰብ ራስን እንደማታለል ይቆጠራል ብለዋል።
ህብረቱ ምርጫው ከመደረጉ ከሚቀጥለው ወር በፊት የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችንና ሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን በስፋት የሚያሳትፍ ትልቅ ጉባኤ በሚያዚያ ወር ላይ ለመጥራት በዝግጅት ላይ እንዳለ በዚህ ስብሰባ ላይ ተገልጿል።
አንዳንድ የፓርላማ አባላት በዚህ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደግብጽ ህዝብ ሆ ብሎ በመነሳት ከመዒው ግንቦት ምርጫ በፊት አምባገነንነትን ከራሱ ትከሻ ላይ ለማውረድ መነሳት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሚቀርብበት የሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ አቋሙን እንዲገልጽ ቢጋበዝም ፣ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ የሆነ ቤልጂየማዊ ዜጋ የሆነ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ሰራተኛ የተገኘ ሲሆን ስራውም መረጃ መሰብሰብ እንጅ አስተያየት መስጠት አለመሆኑን ገልጾ፣ ምንም ንግግር ሳያደርግ ወጥቷል። sourse esate
No comments:
Post a Comment