Wednesday, June 10, 2015

ኢህአዴግ በምርጫው አገኘሁት ያለውን ውጤት ለማብሰር የያዘውን የድጋፍ ሰልፍ እቅድ በፍርሃት ሰረዘ

Amharic

ሰኔ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከኢህአዴግ ጽ/ቤት ለመላ አገሪቱ በወረደ ጊዚያዊ አደረጃጃት፣ በመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች እንዲሁም በተለያዩ የግንባሩ ጽ/ቤቶች በተሰጠ መመሪያ መሰረት የተዋቀረው የድጋፍ ሰላማዊ
ሰልፍ ኮሚቴ የድጋፍ ሰልፍ የማድረግ እቅዱን ሰርዟል። ምርጫው ፍጹም ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መሆኑን ህዝቡ በድጋፍ እንዲመሰክር እና ሚዲያዎቹ በቀጥታ እንዲዘግቡት መመሪያ ከወረዳ በሁዋላ፣ የኢህአዴግ ምክር ቤት ተሰብስቦ ሰላማዊ
ሰልፉ እንዲደረግ አይመከርም ሲል በሙሉ ድምጽ ውሳኔ አሳልፏል።
ምክር ቤቱ ለእቅዱ መሰረዝ በምክንያትነት ያቀረበው በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የክልል ከተሞች ኢህአዴግ የህዝቡን ድምጽ አላገኘም የሚል ነው። የድጋፍ ሰልፍ መጥራት በራሳችን ጊዜ የተቃውሞ ሰልፍ እንደመጥራት ይቆጠራል ያለው ምክር
ቤቱ ፣ በአዲስ አበባ አይ ኤስ ኤስን ለማውገዝ በተጠራው ሰልፍ ላይ የታየውን በምሳሌነት አቅርቧል።
መንግስት በጠራው ሰልፍ ላይ ጥላቻውን ለማሳየትና ድንጋይ ለመወርወር ያልተሸነፈ ህዝብ፣ በድጋፍ ሰላማዊ ሰልፉ ሊፈጥረው የሚችለው ሁከት ከፍተኛ ሊሆን ይችላል ሲል ምክር ቤቱ ስጋቱን ገልጿል።
ውጤቱን አንቀበልም ያሉ የተቃዋሚ አመራሮችን “ጸረ ሰላም” የሚሉና ሌሎችንም ስድሞች ከመስደብ መታቀብ እንደሚገባም ወስኗል።
የኢህአዴግ አመራሮች የድጋፍ ሰልፉን ለመሰረዝ ያቀረቡት ሌላው ምክንያት በውጭ አገር መንግስታት በኩል የሚቀርበው ወቀሳ በርዷል የሚል ነው። ከውጭ የሚመጣው ተቃውሞ ግፊቱ እስካልጨመረ ድረስ በውሳኔው እንደሚጸና የገለጸው
ምክር ቤቱ፣ ነገር ግን ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ ከስጋት ውጭ ነው ብሎ መናገር እንደማይቻልና ቅድመ ዝግጅት አድርጎ መቀመጥ አስፈላጊ መሆኑን አስምሮበታል።
በድጋፍ ሰልፍ ስም የሚነሳውን ተቃውሞ የፈራው ኢህአዴግ፣ ደጋፊዎቹን ለማመስገን ሲል በተጠናከረ ጥበቃና ክትትል በአዲስ አበባ ስታዲየም ብቻ ከሰኔ 17 በሁዋላ የምስጋና ዝግጅት ለማድረግ አስቧል።
የኢህአዴግን ውጤት የቀየሩት የገጠር ካድሬዎች በተለየ ለአምስተኛው ድል ምስጋናውን ይወስዳሉ ያለው የኢህአዴግ ምክር ቤት ፣ ስጋቶቻችንን ሁሉ ለማለፍ የቻልንበት ዘዴ በጥናት ይመለስ ብሎአል። ሁሌም ኢህአዴግን ከውድቀት የሚታደገው ያልተማረው አርሶ አደር ነው ሲል ግንባሩ ፣ በገጠር አርሶ አደር ካድሬዎች ላይ ያለውን አመኔታ ገልጿል።
ምክር ቤቱ፣ ኢህአዴግ የተማረውን ክፍል ድምጽ አለማግኘቱን አረጋግጦ፣ ግንባሩ በተማረው የህብረተሰብ ክፍል ላይ መስራት አለበት ብሎአል።
በምርጫው ለሰማያዊና ለተቃዋሚዎች የተሰጡ የምርጫ ድምጾች፣ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በስርዓት የተሞሉና አንዱም እንኳ ዋጋ አልባ ያልሆኑ ሲሆኑ፣ በተቃራኒው ግን ኢህአዴግ ካገኘው ድምጽ እኩል፣ ዋጋ አልባ የሆኑ ድምጾች
መኖራቸውና ለኢህአዴግ የተሰጡ ድምጾች ናቸው በሚል የተያዙት በራሱ ኢህአዴግ የተማረውን ክፍል በተቃዋሚው መነጠቁን የድምጽ አሰጣጡ በራሱ መስካሪ ነው ይላል። በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች የንብ አርማ ብቻ ያለበት የድምጽ
መስጫ መቅረቡ በድምጹ ላይ ልዩነት ከመፍጠር ታድጎናል ብሎአል።
በገጠር ቀበሌዎች ለምሳሌ በአዊ ዞን አንድም የተቃዋሚ ታዛቢ እንዳይኖር የተወሰደው እርምጃ እና ቀድሞ ለመጨረስ የተደረገው ስራ በግልጽ ከሚደረግ፣ በቀላሉ ድምጽ ማግኘት የሚቻልበትን አማራጭ መጠቀም ይቻል ነበር ሲል ገምግሟል።
የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ከሚወዳደሩበት ጣቢያ ድረስ በመሄድ ድምፅ መስጠታቸው፤ ታማኒነት ያለው የምርጫ ቦርድ በሚንስትር ማዕረግ መቋቋሙ፤ በምርጫ ፉክክሩ ከተሳተፉት 58 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥም በርካቶቹ የምርጫውን
ሂደትና ጊዜያዊ ውጤቱን በፀጋ መቀበላቸውን በአወንታዊነት ሲያነሳ፣ የተሻሻለው የምርጫ ሕግ በአንድ የምርጫ ጣቢያ መመዝገብና መምረጥ ያለበት መራጭ ከአንድ ሺሕ በላይ መሆን የለበትም ቢልም፣በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በርከት ያሉ
የምርጫ ጣቢያዎች ከአንድ ሺሕ በላይ ነዋሪዎችን በማስመረጥ ሕጉን መጣረሳቸው ታይቷል ብሎአል፡፡
በድምፅ መስጫ ጣቢያ ቆጠራ ሲደረግ፣ድምፅ ለመስጠት የተመዘገበው ሕዝብ ብዛትና የተሰጠው ድምፅ ሳይጣጣም ቢቀርም፣ በታዛቢነት የተገኙ የፓርቲ ተወካዮች ምንም ዓይነት ተቃውሞ አለማንሳታቸው እንደ መልካም ጎን ልናየው የምንችለው
ነው ሲል ድርጊቱን አወድሷል፡፡
የኢህአዴግ ምክር ቤት ግምገማውን የካሄደው ከክልሎች የቀረቡለትን የግምገማ ውጤት ተንተርሶ ነው።
ዘንድሮ በተካሄደው ምርጫ ኢህአዴግ መቶ በመቶ በሆነ ድምጽ በማሸነፍ የአፍሪካን ሪከርድ መስበሩን መረጃዎች ያሳያሉ። ዋነኞቹ ተቃዋሚዎች ምርጫው ቀልድ ነበር ሲሉ አጣጥለውታል። የአፍሪካ ህብረት በምርጫው በርካታ ግድፈቶችን
ማየቱን በሪፖርቱ ቢያመለክትም፣ የምርጫውን ታአማኒነት እንደማይቃወም ገልጿል። የምርጫ 97 የአውሮፓ ህብረት የታዛቢዎች ቡድን መሪ የነበሩት ወ/ሮ አና ጎሜዝ የምርጫውን ውጤት አስቂኝ ብለውታል።

No comments: