Thursday, April 14, 2016

እነ አቶ ዓለማዬሁ መኮንን በድጋሜ ተቀጠሩ


ሚያዚያ ፮(ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ በሽብርተኝነት የፈጠራ ውንጀላ ታስረው በሌሊት ወደ አዋሳ የተወሰዱትና ከመጋቢት 20፣ 2008 ዓም ጀምሮ በአዋሳ ፖሊስ ኮሚሽን ግቢ ታስረው የሚገኙት የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት ም/ሊቀመንበርና የዞኑ ጽ/ቤት ኃላፊ መምህር ዓለማዬሁ መኮንን ፣ የኦህዲኅ አባል አቶ አብርሃም ብዙነህና የቀድሞ አንድነት የዞኑ ተጠሪ የነበሩት አቶ ስለሺ ጌታቸው ፖሊስ የጠየቀባቸውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጨርሰው ሚያዚያ 05 2008 ዓም ፍርድ ቤት ቀርበው ለሚያዝያ13/08) ተቀጥረዋል ፡፡
በችሎት ላይ የተገኙት የኦህዲኅ አባላትና የታሳሪዎች ቤተሰቦች እንደገለጹት ፖሊስ መረጃ የማሰባሰብና የምርመራ ሥራውን አላጠናከኩም በሚል የ14 ቀን ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ በመጀመሪያ ‹‹ ጥያቄው አግባብ ያለመሆኑን፣ባልተሰበሰበ መረጃና ባልተደረገ ምርመራ ተጠርጣሪዎችን ማሰርም ሆነ እዚህ ድረስ ማምጣት ከህግ አሰራርም ሆነ ከሰብዐዊ መብት አኳያ አግባብ አለመሆኑን ›› በመጥቀስ ፖሊሶችን ከገሰጸ በኋላ ፣ ‹‹መዘንጋት የሌለበት እነዚህ ሰዎች በጠባብ ቦታ ነው ያሉት ፣ እኛ ደግሞ በሰፊው፣ ስለዚህ የተጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ ምን የተለየና ተጨማሪ ነገር ለማድረግ ነው ?›› ሲል ጠይቋል፡፡ ፖሊስ በሰጠው መልስ- የሰው ማስረጃዎችና ተጨማሪ መረጃዎች እያሰባሰብን ያለነው ከዞኑ- ጂንካ በመሆኑ ከቦታው ርቀትና ከዞኑ ፖሊስ ጋር ስለምንሰራ ነው ብሎአል፡፡ አቶ ዓለማዬሁ በበኩላቸው ‹‹ ከጅምሩ የታሰርነውና ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ ወደሌለበት ያመጡን ያለአግባብ ነው፣ አሁን እየተጠየቀ ያለው የጊዜ ቀጠሮም ምንም በሌለበት እንዲሁ ለማንገላታት ነውና ፖሊስ አለኝ የሚለውን ማስረጃና የምርመራ ውጤት ያቅርብ ፣ ይህ ካልሆነ ፍርድ ቤቱ በነጻ ያሰናብተን ዘንድ እንጠይቃለን››ሲሉ አመልክተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም ወገን ካደመጠ በኋላ ‹‹ የአንድ ሳምንት ጊዜ ይበቃችኋል›› በሚል ለመጪው ሃሙስ ሚያዝያ 13, 2008 ዓ.ም. ፖሊስ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን አሰባስቦ፣ ምርመራውን አጠናቆ እንዲያቀርብ ሲል ቀጠሮ ሰጥቷል ፡፡ በተጨማሪም በዛሬው ችሎት ታሳሪዎች ከመያዛቸው አስቀድሞ ቤታቸው ሲፈተሸ የነበሩ እማኞች በችሎት ያለመቅረባቸው ተረጋግጧል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢሳት እነ ዓለማዬሁ ከመታሰራቸው ጥቂት ቀናት በፊት በዞኑ ውስጥ በኢንቨስትመንት ስም የሚፈጸመውን የመሬት ቅርምት፣ ይህም በዞኑ ልማት ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖና የመሬት ቅርምቱ ከ98 ከመቶ በላይ የተፈጸመው በህወኃት አባላትና ደጋፊዎች መሆኑንና በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ ዓለማዬሁና የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ አስተያየት መስጠታቸውን መዘገቡ ይታወሳል ፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ የዞኑ መስተዳድር በዞኑ ነዋሪዎች የተቋቋመ ‹ነጻ› በሚባል የልማት ማህበር ጋር የገንዘብ ማሰባሰቢያ ባዛር ለማዘጋጀት ህዝቡን በመቀስቀስ ላይ መሆኑን፣ ለዚሁ ባዛር መምህራንን ለማሳመን በየትምህርት ቤቱ …..በመሰብሰብ ያወያየ ሲሆን ፣ ከመምህራን የተለያዩ ጥያቄዎች መነሳታቸውንና ለዚህም በቂ መልስ መስጠት ባለመቻሉ ለሌላ ጊዜ ሰፊ ውይይት ለማድረግ በመወሰን ስብሰባዎቹ ማብቃታቸውን መምህራን ገልጸዋል፡፡ በተለያዩ ት/ቤቶች በተደረጉ ስብሰባዎች ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል ፣ ከዚህ በፊት በተደረገው ባዛር የተሰበሰበው ገንዘብ አጠቃቀምና በገንዘቡ ለመስራት የተነደፉ ፕሮጀክቶች ክንውን /አፈጻጸም ሪፖርት ሳይቀርብ ስለሌላ ባዛር ማቀድ አግባብ ነውን ፣ ሌላ ዕቅድ ከማሰባችን በፊት ከዚህ በፊት በህዝብ ሃብት የተገዙ የኮንስትራክሽን መሳሪያዎች / ዶዘርና ግሬደር፣ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ/ ያለአገልግሎት የቆሙት ለምን እንደሆን በግልጽ ይታወቅ፤ ከዚህ በፊት በህዝብ ገንዘብ የተገነባው ስታዲዬም ከፍተኛ ገንዘብ ወጣበት ተብሎ በተነገረ በወራት ውስጥ መደርመሱ/መፍረሱ ይታወቃል፤ ይህ ሁኔታ እንዲጣራ ጥያቄ ቢቀርብም መልስ ባልተሰጠበት እንደምን ሌላ ባዛር ማዘጋጀት ታሰበ ፣ በተመሳሳይ በዕቅድ ተጀምሮ የተቋረጠው የጂንካ ቤቶ-ሜላ መንገድ የተቋረጠበት ምክንያት አሳማኝና ግልጽ ምክንያት ባልቀረበበት በባዛር ስም ከህዝብ ለምን ገንዘብ መሰብሰብ ተፈለገ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
አንድ መምህር -እውነት ዛሬ ላይ ለጂንካ ከተማ የሚያስፈልገው የምግብ እህል ነው ወይስ የሽንት ቤት መምጠጫ መኪና- ለመሆኑ ምን ተበልቶ ? የሚል ጥያቄ አንስተው በተሰብሳቢው ከፍተኛ ጭብጨባ ተችሮኣቸዋል፡፡
መምህራኑ ‹‹ ማናችንም የዞናችንን ልማት እንፈልጋለን፣ ከፍላጎት ባለፈም በአቅማችን መሳተፍና አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለብን እንረዳለን፤ ግን በልማት ስም ገንዘብ እየተሰበሰበ ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ የሙስና ደላላና ተጠቃሚ ግለሰቦችና ባለሥልጣናት ኪስ ማደለቢያ ሊውል አንፈቅድም ›› ብለዋል፡፡
ይህንኑ ባዛር በሚመለከት የኦህዲኅ የዞን ጽ/ቤት ምክትል ተጠሪ መምህር እንዲሪስ መናን በሰጡት አስተያየት ‹‹ ተመሳሳይ ጥያቄዎች እርሳቸው በሚያስተምሩበት ት/ቤትም በተደረገ ስብሰባ ላይ መነሳታቸውን አረጋግጠው፣ እንደ ህዝብና የዞኑ ነዋሪ ልማቱን የምደግፍ ነኝ፣ በመምህራን የተነሱት ጥያቄዎች በቂና አሳማኝ መልስ ማግኘት እንዳለባቸው አምናለሁ›› ከዚህ ባለፈ እንደ ፖለቲከኛ ‹‹ ይህ የአካባቢ ልማት ጉዳይ በቅርብ ጊዜ በዞናችን በኢንቨስትመንት ስም በህወኃት አባላትና ደጋፊዎች የተፈጸመው የመሬት ቅርምት ከተጋለጠና የህዝብ ውይይት አጀንዳ ከሆነ በኋላ እንዴት መጣ ፣ ለሽፋን የታሰበ ፖሮፖጋንዳ ይሆን ? በዚህ ጉዳይ የታሰሩ የእነ አቶ ዓለማዬሁ ጉዳይስ በዚህ ወቅት በዝምታ የሚታለፍ ነውን ? ከዚህ የልማት ኃሳብና ዕቅድ በፊት በዞናችን የሚታዩ ማህበራዊ ምስቅልቅሎች / የዜጎች መፈናቀል፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መሻከር – የቦዲና የኮንሶ ግጭት /፣ የሃመር ወጣቶች ያነሱትን የፍትህ ጥያቄ ተከትሎ ከመንግስት ታጣቂ ኃይሎች ጋር የተገባው ቅራኔ ያስከተለው የህይወት መጥፋት፣ አካል መጉደል፣ የንብረት ውድመት፣የወጣቶች ከቀዬኣቸው መሰደድ፣….በአጠቃላይ ከዞኑ ነዋሪዎች የሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበርና በህዝብ የተነሱ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አለባቸው ፣ የህዝብ ብሶት ያሰሙ መሪያችን፣ አባልና የከተማው ነዋሪ በሃሰት ውንጀላ ከቤተሰብና ከዞናቸው ህዝብ ተነጥለው በእስር እየማቀቁ ባሉበት ይህን ለምን ? ብለው ሳይጠይቁ ‹ነጻ› ነን በሚል ስለልማት ቢሰብኩ በህዝብ ተቀባይነት ማግኘት አይታሰብም፡፡ ብለዋል፡፡
የኦህዲኅ ሊቀመንበር በሰጡት አስተያየት ደግሞ “ብዙ ከበሮ ተደልቆለት ከወራት በላይ ዕድሜ ከሌለው ድንጋይ ድርዳሮ በፊት የዜጎች መብትና የሰው ሃብት ልማቱ፣ የባለሥልጣናት ተጠያቂነት መቅደም አለበት፣ ለረጅም ጊዜ በተደጋጋሚ የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎች መመለስ፤ ሙስናው መገደብ…. አለበት፣ ስለቀጣዩ ብዙ ከማለታችን በፊት ካለፈው ምን ተምረናል ለሚለው ግልጽና በቂ መልስ ማግኘት፣ ፍላጎታችንና የልማት ጥያቄዎቻችን በአግባቡ ቅደም ተከተል ሊቀመጥላቸው ይገባል›› ብለው እንደሚያምኑና እነዚህ በሆኑበትና በተሟሉበት ‹‹ ህዝብ በአንድ ልብ፣በአጭር ጊዜ ተዓምር የመስራት አቅም እንዳለው በጽኑ አምናለሁ›› ብለው መናገራቸውን ከስፍራው የደረሰን ሪፖርት ያመለክታል፡፡                                                                                       source http://amharic.ethsat.com/ 

No comments: