Friday, April 15, 2016

በኦሮምያ ዜጎች መገደላቸውን አላቆሙም


ሚያዚያ ፯(ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ገዢው ፓርቲ ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴ የሆኑትን ቫይበር እና ዋት ስ አፕ የመሳሰሉትን በመዝጋት በኦሮምያ ክልል የሚፈጸሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይፋ እንዳይሆኑ እያደረገ ነው በሚል ትችት እየቀረበበት በሚገኝበት በዚህ ጊዜ፣በክልሉ የሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት መቀጠሉን ነዋሪዎች ለኢሳት ተናግረዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ በጉጂ ዞን አዶ ሻኪሶ ወረዳ ሙጋድ ቀበሌ ውስጥ የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን አጠናቆ ወላጆቹ ቤት ይኖር የነበረው ግርማ ገልጁ ኪጋ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሎአል፡፡ ወጣቱ ቀደም ብሎ በደህንነቶች ሲፈለግ እንደነበር የገለጹት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ሚያዚያ 5 ቀን 2008 ዓም አንድ ታርጋ በሌላት ነጭ መኪና የተጫኑ የደህንነት አባላት ከምሽቱ አንድ ሰአት ላይ ወጣት ግርማን አስቁመው በጩቤ ከወጉት በሁዋላ፣ እንደገና ከወደቀበት ተነስቶ ለማምለጥ ሲሞክር በጥይት ደብድበውታል፡፡የጥይት ሩምታውን የሰሙ የአካባቢው ነዋሪዎች ፣ ወደ ቦታው ሲሄዱ፣ ደህንነቶች ጥይት በመተኮስ ህዝቡ እንዳይቀርብ ያደረጉ ሲሆን፣ ወዲያውኑ ሙዋቹን ይዘው ወደ ክብረመንግስት ወይም አዶላ ሆስፒታል በመውሰድ ጥለውታል፡፡
ወላጆቹ አስከሬኑን ሆስፒታል ሄደው የወሰዱ ሲሆን፣ የቀብር ስነስርአቱም ትናንት በመጋዶ ቀበሌ ልዩ ስሙ ሶዱ በሚባል ቦታ ላይ ተፈጽሞአል፡፡
ነዋሪዎች እንደሚሉት ደህንቶች ከምሽቱ 12 ሰአት በሁዋላ በእየቤቱ ሳይቀር እየገቡ ህዝቡን በማስፈራራት ላይ ናቸው፡፡ሌሊቱን እንደሚዳቁዋ እየባነን ነው የምናሳልፈው የሚሉት ነዋሪዎች፣ ከምሽቱ 12 ሰአት በሁዋላ መንቀሳቀስ እንደማይቻል ይገልጻሉ፡፡
በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚታሰሩ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡
መንግስት ተቃውሞውን በሃይል ለማቆጣጠር ሙከራ ቢያርግም በአንዳንድ አካባቢዎች አሁንም አልፎ አልፎ ተቃውሞዎች ይካሄዳሉ፡፡
በክልሉ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ እስ 300 የሚደርሱ ሰዎች በመንግስ የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸው በተለያዩ የሰብአዊ መብት ድርጅቶችና የመገናኛ ብዙሃን መዘገቡ ይታወቃል፡፡                      source http://amharic.ethsat.com/

No comments: