ኅዳር 24 ቀን 2006 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ ማኅበረ ቅዱሳን ከሳውዲ አረቢያ ተመላሽ ወገኖቻችንን ለመደገፍ ቀጣይ ሥራዎችን እንደሚሠራ አስታወቀ፡፡ አቶ ምሕረተአብ ሙሉጌታ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራልና የጊዜያዊ ጣቢያው ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተባባሪ ከስደት ተመላሾችን አቀባበል በተመለከተ ሲገልጹ “ከመንግሥት ጥረት ጎን ለጎን የተለያዩ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት፤ ማኅበራትና በጎ አድራጊ ግለሰቦች ከስደት ተመላሽ ወገኖቻችንን ለመርዳት ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ 79ሺህ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 49 ሺሕ ወንዶች፤ 26ሺሕ ሴቶች እንዲሁም ከ3ሺሕ በላይ ሕፃናት ናቸው፡፡”በማለት ገልጸዋል፡፡ አስፈላጊውንም ምዝገባና መስተንግዶ እየተደረገላቸው ወደየትውልድ ቀዬአቸው የመመለስ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ምሕረተአብ ማኅበረ ቅዱሳንና ሌሎችም ማኅበራት እያደረጉ ላሉት ወገኖቻችንን የመርዳትና የመደገፍ ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ አቶ መስፍን መንግሥቱ “ኢትዮጵያዊያን ለኢትዮጵያዊያን” በሚል ከነጋዴው ኅብረተሰብ የተቋቋመ ማኅበር አስተባበሪ ሲሆኑ ቦሌ በሚገኘው ጊዜያዊ የስደተኞች መቀበያ ጣቢያ ሲያስተባብሩ አግኝተናቸው ላቀረብንላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ “የተፈጠረው ድንገተኛ ችግር እጅግ አስደንጋጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ወቅት ተባብረን ፈጣን ምላሽ መስጠት ይጠበቅብናል፡፡ በዚህም መሠረት ወገኖቻችንን ለመርዳት ተሰባስበን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዶክተር ቴዎድሮስ አድኀኖም ደብዳቤ በማስገባት ድጋፍ መስጠት እንደሚገባን ተወያተናል፡፡ የተቀደሰ ዓላማ በመሆኑም ወደ ተግባር መግባት ትችላላችሁ በማለት ፈቃድ ሰጥተውናል፡፡ ስደተኞቹ መግባት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በአጭር ሰዓት ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ከመስተንግዶ ጀምሮ እየሠራን እንገኛለን” ብለዋል፡፡ ከስደት ከተመለሱት መካከል ስሟን መግለጽ ያልፈለገች አንዲት እኅት በሳውዲ አረቢያ ስለነበረው የሥራዋ ሁኔታ ስትገልጽ “ከሀገሬ ከወጣሁ ሁለት ዓመት ሆኖኛል፡፡ ሁለት ሕፃናት ልጆቼን ትቼ ያልፍልኛል ብዬ ነበር አወጣጤ፡፡ ነገር ግን እዚያ የገጠመኝ እጅግ አስከፊ ሁኔታ ነበር፡፡ ከአሰሪዬ ቤት ውጪ ለሦስት ቤቶች በነጻ እንድሠራ አድርጋኛለች፡፡ ለምን ብዬ በጠየቅሁበት ወቅት ደብድባኝ ጎኔን ኦፕራሲዮን እሰከመሆን ደርሻለሁ፡፡ ሃያ አራት ሰዓት ያለማቋረጥ እንድሠራ ስታደርገኝ ቆይታለች፡፡ ከዚህ ሥቃይ በሀገሬ ልሙት ብዬ ነው የመጣሁት” በማለት ተናግራለች፡፡ |
Wednesday, December 4, 2013
ማኅበረ ቅዱሳን ከስደት ተመላሾችን ለመደገፍ እንደሚሠራ አስታወቀ
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment