Friday, March 13, 2015

የግዲቾ ብሄረሰብ አባላት ያነሱትን ተቃውሞ ተከትሎ ፖሊሶች አንድ ሰው ገድለው 8 አቆሰሉ

My CMS

መጋቢት ፬(አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የግዲቾ ብሄረሰብ አባላት ተቃውሞውን ያስነሱት መሬታቸው ለትምባሆ ተክል እርሻ ለአንድ ባለሀብት መሰጠቱን ተከትሎ ነው።
በደቡብ ክልል በጋሞጎፋ ዞን በምእራብ አባያ ወረዳ የሚኖሩት ቁጥራቸው እስከ 5 ሺ የሚደርሱ የብሄረሰቡ አባላት፣ ቀደም ብሎ በአባያ ሃይቅ መካከል በሚገኘው ደሴት ይኖሩ ነበር። ደሴቱ በሃይቁ ሙሉ በሙሉ መሸፈኑን ተከትሎ የብሄረሰቡ አባላት ሃንቲ ወደ ሚባል አጎራባች ቀበሌ በመሄድ ኑሮአቸውን ሲገፉ ቆይተዋል።
ይሁን  እንጅ የዞኑ ምክር ቤት የእርሻ መሬታቸውን ለ4 ኢንቨስተሮች በመስጠቱ፣ ነዋሪዎቹ በእርሻ መሬት እጦት ሲሰቃዩ ቆይተዋል። ባለፉት ጥቂት ወራት ደግሞ የብሄረሰቡን አባላት ሙሉ በሙሉ በሚያፈናቅልና መድረሻ በሚያሳጣ ሁኔታ ፣ መሬታቸው ለአንድ ትምባሆ አምራች ኢንቨስተር ተሰጥቷል።
ነዋሪዎቹ  በተወካይ ሽማግሌዎች አማካኝነት አቤቱታቸውን ለዞኑና ለክልል ምክር ቤት አባላት ሲያቀርቡ ቢቆዩም፣ በየደረጃው ካሉ ባለስልጣናት ያገኙት መልስ ግን ስድብ ብቻ ነው።
ባለፈው ማክሰኞ አዲሱ ባለሃብት ወደ አካባቢው በመሄድ ደኖችን  መመንጠር ሲጀምር በአካባቢው የነበሩት ሴቶችና ህጻናት በመጮህ ተቃውመዋል። የአካባቢው ፖሊሶች ፈጥነው በመድረስ በጩኸት ሲቃወሙ ከነበሩት መካከል አንዷን አሮጊት ክፉኛ መደብደባቸውን፣ ጨኸቱን ሰምተው የተሰባሰቡት ወንዶችም ተቃውሞአቸውን መግለጻቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል።
ፖሊሶች ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ያገኙትን ሁሉ ከመደብደብ አልፈው ጥይቶችን በመተኮስ አንዱን የብሄረሰቡ አባል በ4 ጥይቶች አናቱን መትተው ሲበታትኑት፣ 8ቱን ደግሞ ክፉኛ አቁሰለዋቸዋል። አንደኛው ሰው አንጀቱ አካባቢ ተመትቶ የህክምና እርዳታ እያገኘ ቢሆንም፣ ላይተርፍ ይችላል ተብሎአል። ሌሎች ደግሞ እጅና እግራቸው መሰባበሩን የአይን እማኖች ለኢሳት ተናግረዋል።  
“በጣም የሚያሳዝነው” ይላሉ ነዋሪዎች፣ “ሟቹ ለ6 ሰአታት ያክል መንገድ ላይ ወድቆ አስከሬኑ እንዳይነሳ መደረጉ ነው”።
የብሄረሰቡ አባላት በከፍተኛ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ መሬታቸው በጉልበት ለባላሀብቱ ከተሰጠ፣ ወደ ከተሞች ተሰደው የጎዳና ተዳዳሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይናገራሉ።
በጉዳዩ ዙሪያ የጋሞጎፋ ዞን ፖሊስ ጽ/ቤትን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። 

No comments: