የካቲት ፳፫(ሃያሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የብረታብረት ኢንዱስትሪዎች ከኃይል አቅርቦት መቆራረጥ፣ ከአቅርቦት ማነስ እንዲሁም ከውጪ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ በሙሉ አቅማቸው ማምረት አለመቻላቸውና ለኪሳራም እየተዳረጉ መሆናቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
የብረታብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሰሞኑን በግዮን ሆቴል የ2007 ግማሽ ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለባለድርሻ አካላት ባሳወቀበት ወቅት እንደተጠቀሰው በብረታበረት ዘርፍ ወደ 60 የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች የሚገኙ ሲሆን እነዚህ ኢንዱስትሪዎች በዋንኛነት ከኃይል አቅርቦት መቆራረጥና ከአቅርቦት ማነስ ጋር ተያይዞ ከማምረት አቅማቸው እያመረቱ የሚገኙት 41 በመቶ ያህል ብቻ ነው፡፡
አንዱስትሪዎቹ በጠቅላላው 129 ነጥብ 6 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ያላቸው ቢሆንም መንግስት በትክክል ማቅረብ የቻለው 69 ነጥብ 6 ሜጋዋት ብቻ ነው፡፡ ፋብሪካዎቹ ቀሪ 60 ሜጋዋት ገደማ የኃይል አቅርቦት ክፍተት እንዳለባቸውና ይህም ችግር መቼ እንደሚፈታ እንደማይታወቅ ተጠቁሞአል፡፡
እነዚህ ፋብሪካዎች የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በማሟላት ለኢክስፖርት እንዲያመርቱ በመንግስት በኩል ፍላጎት ቢኖርም በዋንኛነት ከኃይል አቅርቦት ጋር ተያይዞ ይህ ሊሳካ እንዳቻለ ታውቆአል፡፡
በተጨማሪም ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅም እንዳያመርቱ እንቅፋት ከሆኑት ችግሮች መካከል የግብአት አቅርቦትና የመሰረተ ልማት ችግሮች፣ የባንክ ብድር አለመመቻቸት፣ ተጠቅሰዋል፡፡
ለፋብሪካዎቹ 131 ሺ ቶን ጥሬ ዕቃ ከውጪ ሀገር ገዝቶ ለማቅረብ በኢንስቲትዩቱ በኩል ፍላጎት ቢኖርም በባንክ በኩል የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ባለመቻሉ አለመሳካቱን እንዲሁም በተመሳሳይ ሁኔታ ከስድስት ኢንዱስትሪዎች የቀረበ የ17 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ በምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ ሊፈቀድ አለመቻሉ በችግርነት ተነስቶአል፡፡
በብረታብረት ኢንዱስትሪ ዘርፉ በዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተቀመጠው ዕቅድ አለመሳካቱ ብቻ ሳይሆን የችግሮቹ መወሳሰብ ባለሃብቱን ተስፋ በማስቆረጥ ከዘርፉ እንዲወጣ ሊያደርግ እንደሚችል፣ አዳዲስ ባለሃብቶችንም
ሊያሸሽ እንደሚችል አንዳንድ የሰብሰባው ተሳታፊዎች ስጋታቸውን ገልጸውልናል፡፡ በኢትዮጵያ የሚታየው የውጭ ምንዛሬ እጥረት በብረት እንዱስትሪው ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዘርፎች እንደሚታይ ኢሳት በቅርቡ ዘግቧል።
No comments:
Post a Comment