Tuesday, February 9, 2016

ሁለተኛው ምዕራፍ ተመስገን ደሳለኝ (ከዝዋይ ማጎሪያ)

 እጅግ ኋላቀር ከሆኑ ትናንሽ የገጠር ወረዳዎች አንስቶ እስከ ታላላቅ ከተሞች ድረስ በኦሮሚያ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት የመጀመሪያውን ምዕራፍ ከሞላ-ጎደል በአሸናፊነት ተወጥቷል፡፡ በድሉ በመጠኑም የምንኩራራው (አንገታችንን ቀና የምናደርገው) የወደቁ ሠማዕታት የከፈሉትን ዋጋ ሳንዘነጋ ነው፡፡ በዚህ አውድ ፖለቲካዊ ድል ብዬ የምዘክረው የ “ማስተር-ፕላኑ” ዕቅድ መሠረዙን ብቻ አይደለም፡፡ በውሳኔው ስር የሰደደው የወያኔ ግትር ባሕሪም (የአስተዳደር ዘይቤ) ለቡርቦራ መጋለጡን ጭምር በመገምገም ነው፡፡ ክስተቱም የ1966ቱን አብዮት ዋዜማ ያስታውሰኛል፡፡ በወቅቱ የአፄው መንግሥት የተቃውሞ ንቅናቄ በፈጠረበት ጫና አጣብቂኝ ውስጥ በመቀርቀሩ “ሴክተር ሪቪው” የተሰኘ አዲስ የትምህርት ፖሊሲውን ሲሰርዝ፤ በነዳጅ ዋጋ ላይ ሊጨምር ያሰበውንም ታሪፍ ለመተው ተገዷል፡፡ በዚህም የተበረታታው የለውጥ ኃይል ዘውዳዊውን ሥርዓት ለመገርሰስ ከወራት የበለጠ ጊዜ አላስፈለገውም ነበር፡፡ በኦሮሚያ ጎበዛዝት ክፉኛ የተፈተነው ወያኔም የቆመበት ጠርዝ በግርድፉ ሲታይ ከ66ቱ ዋዜማ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ይህ ግን እንደ አዛውንቱ ንጉሥ የመጨረሻ ቀናት ጡንቻው ሙሉ በሙሉ ዝሏል ማለት አይደለም፡፡ ከዚህ በኋላ ማዛሉ፣ አልፎም ተርፎ የመቃብሩን ካንቻ ማጥበቁ የመጀመሪያውን ምዕራፍ ያህል አስቸጋሪ (ከባድ) አለመሆኑን መጠቆም እንጂ፡፡ የሁለተኛው መርሃ-ግብር ሕዝባዊ እምቢተኝነት “ማስተር ፕላኑ” መሠረዙን አመስግኖ ሲያበቃ (በብሉይ አብዮቱ ዋዜማም የንጉሡ አስተዳደር ያፀደቃቸውን ፖሊሲዎች ለመሻር የተገደደበትን ኩነት ተከትሎ “እግዜር ይስጥልኝ” በሚል ርዕስ ከግራ-ዘመም ቡድኖች የአንዱ አመራር አባል መጣጥፍ አዘጋጅቶ እንደነበረ ዛሬ ማስታወስ ባልቻልኩት ድርሳን ላይ ማንበቤን አልዘነጋውም፡፡) በዋናነት መነሳት ያለበት አጀንዳ ምንድን ነው? የሚለውን በአዲስ መስመር ጨርፈን እናያለን፡፡ ቀዳሚው እንዲህ ዓይነቱን የክልሉን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ህልውና ተፈታታኝ ዕቅድ ያለአንዳች ሕዝባዊ ውይይት ማብራሪያና ለመተግበር የሞከሩ፤ ሙከራውንም በዝምታ ያዩ ባለሥልጣናት ከሥልጣናቸው እንዲሻሩ ማድረጉ ላይ ቢያተኩር ቅቡል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህም ርዕሰ-መስተዳድሩ ሙክታር ከድር፣ ረዳቶቹና አማካሪዎቹ በቸልተኝነት የሚከሰሱ ሲሆን፤ ተከታዩ የፕላኑ ነዳፊዎችን ይመለከታል፡፡ በጋራ ደግሞ ሹማምንቱ ለጠፋው ሕይወት፣ ለደረሰው አካል ጉዳት፣ ለወደመው ንብረት…… ኃላፊነቱን ወስደው በወንጀል እንዲጠየቁ መቀስቀሱ እና ማሳመፁ የሁለተኛው ምዕራፍ ትግል ባንዲራ መሆን ይችላል፡፡ ይህንን ለማደላደልም ልሂቃን እና አክቲቪስቶች ከወዲሁ የመጀመሪያውን ተሞክሮ ገምግመው ጠንካራ ጎኑን በማዳበር፣ ድክመቱን አርመው መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አጀንዳው የታሰሩ የንቅናቄው ተሳታፊዎች ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ እንዲፈቱ፣ ጭካኔ የተጠናወተውን ጅምላ ጭፍጨፋ ያዘዙ ባለሥልጣናትም ሆኑ የተገበሩት በሙሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ፤ እንዲሁም መንግሥት ለሟች ቤተሰቦች ካሳ እንዲከፍል ማስገደድን ጭምር ማካተቱን ሁሉም በግልፅ በሚገባው መንገድ ማብራራቱና ማስረፁ አስፈላጊ ነው፡፡ በጥቅሉ ሊመለሱ የማይችሉ ጉዳዮችን እያነሱ የመታገያ ጥያቄዎች ማድረጉ ከሰላማዊ ትግል ስልቶች መካከል የሚመደብ መሆኑም መዘንጋት የለበትም፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም የተገኘውን ፖለቲካዊ ድል በተለይ ለተርታው አማፅያን አጉልቶና አፍታቶ ማስረዳቱ የመሪዎቹ ግዴታ ነው፡፡ ብዙሃኑ የዕቅዱ መሠረዝ የአገዛዙ ችሮታ ወይም በራሱ አገላለፅ ‹‹የሕዝብን ፍላጎት ማክበር›› ሊመስለው ይችላልና (ወሳኔውንም በዚህ መልኩ ወደ መሬት ለማውረድ የሥርዓቱ የፕሮፓጋንዳ ማሽኖች ምን ያህል እንደለፉ ልብ ይሏል፡፡) ሌላው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች አስተዋፅኦ ወሳኝነትን ማስታወስ እወዳለሁ፡፡ የዚህ ትኩስ ኃይል አበርክቶ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም የላቀ ነው፡፡ ምክንያቱም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በቋንቋ ተናጋሪነታቸው በብሔር የተከፋፈሉ ከመሆናቸውም በዘለለ፣ አብዛኞቹ በዕጣ-ምደባ መሠረት ከትውልድና ከመኖሪያ መንደራቸው ርቀው በመምጣታቸው ምክንያት በሚማሩበት ከተማ ካለው ሕብረተሰብ ጋር ግንኙነታቸው የጠበቀ አይደለም፡፡ ስለዚህም ተቃውሞውን ከትምህርት ቤታቸው ቅፅር ግቢ ውጪ የማሻገር ዕድላቸው የመነመነ ነው፡፡ በግልባጩ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እዛው በቀዬአቸውና በማሕበረሰባቸው ውስጥ ሆነው ስለሚማሩ ቤተሰቦቻቸውን፣ ዘመድ ጓደኞቻቸውን….. በአጠቃላይ አካባቢያቸውን በቀላሉ ከጎናቸው ማሠለፍ አያዳግታቸውም፡፡ ይህ ደግሞ የአመፁን አድማስ በሚፈለገው መጠን ያስፋፋዋል፡፡ እናም መላው አብዮታውያን፣ ተማሪዎቹ ከወዲሁ አስተባባሪዎቻቸውን መርጠው በሕቡዕ እንዲደራጁ ማብቃቱ ለነገ የሚሉት የቤት ሥራ አይደለም፡፡ (በያ ትውልድ ትግልም ከ1964ዓ/ም ጀምሮ ሕዝባዊ ቁጣ የተጋጋመውም ሆነ በከፊል የተመራው በየትምህርት ቤቱ በተመሠረቱ “የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ሸንጎ” (High school councils) እንደነበር ዘመኑን የሚያወሱ በርካታ ትርክቶች አትተዋል፡፡) በመጨረሻም ኦሮሚኛ ተናጋሪ ያልሆነው ኢትዮጵያዊ ሚናስ ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ ሊተኮርበት ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ይህን መሠሉን ተቃውሞ ተቆጣጥረው ከመሩት ታሪካዊ ተልዕኮውን ሲጨርስ ወደ አብዮታዊ ትግል ማደጉ ተፈጥሮአዊ (አይቀሬ) በመሆኑ ከፖሊሲ ማሻሻያ ያለፈ ውጤት ሊያስገኝ የሚችልበት አጋጣሚ የበዛ ነው (የኢኮኖሚው ድል በተስፋና በአመፅ ትዕምርትነትም (symbolic) ጭምር ማገልገሉ ሳይረሳ ማለት ነው፡፡) በአናቱም ንቅናቄው በኢትዮጵያችን ሰማይ ሥር (ያውም ሁሉን ረግጦ በሚገዛ ቡድን ላይ) እስከሆነ ድረስ በየትኛውም ቋንቋ ተናጋሪ ቢገደብ እንኳ መንፈሱና ውጤቱ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የማይዳስሰው የሕብረተሰብ ክፍል የለም፡፡ ስለዚህም የየብሔሩ ቅቡል ልሂቃን ባሻቸው ሥፍራ (“ሰባተኛው ሠማይ” ላይም ቢሆን) ተሰባስበው ቢያንስ በስልት ደረጃ የሚደጋገፍ የጋራ ግንባር (ኮሚቴ) በመፍጠር ተቃውሞውን በየክልላቸው ማዛመቱ ታሪክ የጣለባቸው ኃላፊነት ይመስለኛል፡፡ የሰሜን ጎንደሩን ስምየለሽ ክስተት እና የድንበር ጉዳይ አማርኛ ተናጋሪውን የማስተባበሪያ አጀንዳ በማድረግ መጠቀምንም እመክራለሁ (በእንዲህ ዓይነቱ በግላጭ በሚሰራጭ መጣጥፍ ዝርዝር ነገሮችን ማንሳት አገዛዙን ማንቃት ነውና ሃሳቤን እዚሁ ጋር እገታለሁ፡፡) ከዚህ ባለፈ ሁለተኛው ምዕራፍ እንዲያጠነጥንባቸው ከላይ የተጠቀሱትን ጥያቄዎች ይዘት ብቻ በመመዘን ጉዳዩ የኦሮሞ የግሉ ነው ብዬ ራስን በዝምታ መግራት (በተመልካችነት ማስቀመጥ) የማይታረም ስህተት ከማስከተሉም ሌላ ወርቃማውን ዕድል ሊያመክነው ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በጠቅላይነት ሳር-ቅጠሉን በመጠርነፍ የተካነው ኢህአዴግ ተጠናክሮ የሚወጣበትን ጉልበት በቀላሉ እንዲጎናፀፍ ያደርገዋል፡፡ ድል ለሠፊው ሕዝብ! ኢትዮሚድያ -                                                        Source     Ethiomedia.com February 9, 2016

No comments: