አክሎግ ቢራራ (ዶር)
ክፍል ሁለት
“ውኅ እየጠማው ያባዪን ልጅ
እሚያዘጋጅለት ቢጠፋ
እሚያበጃጅ
ለልማት የሚያመቻች
ዓባይን
አኮላሽቶለት ፈንጂውን”
ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው፤ ዐባይ--ፈንጅ የቀበረ ውሃ
ኢትዮጵያ ታላቅና ሃብታም ለመሆን የምትችል አገር ናት። የተፈጥሮ ሃብቷ፤ አቀማመጧና የሕዝብ ስርጭቷ ለታላቅነቷ የማይገኙ
ምሰሶዎች (Social Pillars) ናቸው። ሆኖም፤ ይህ የአገርና የማህበረሰብ ታላቅነት መሰረት ጎሳዊና አምባገነናዊ የሆነ ስርዓት ባመጣው
ጦስና ቀውስ እየባከነ ነው። ህወሓት ከተመሰረተበት ጀምሮ የተካውን መንግሥትና ሌሎችን በማዋረድ፤ በማጋለጥ፤ በማጥላላት፤
በማሰር፤ በመግደልና ከሃገር በማባረር ሃያ ሶስት ዓመት ገዝቷል። የጥቂቶችን ኪስ በሚያሳፍር ደረጃ ሞልቶ፤ ቢያንስ ሃያ አምሥት
ቢሊዮን ዶላር ከሃገር ተዘርፎ ወደ ውጭ ሃብታም አገር ባንኮች እንዲዘዋወር አድርጓል። ይኼን ሲያደርግ ደጋግሞ የሚነግረን ተግባሩ
ሁሉ ለጭቁን ሕዝቦች፤ ለድሃዎች ጥቅም የሚል ፕሮፓጋንዳ እየተጠቀመ ነው። ኢትዮጵያ የብዙ ምሁራን፤ ጠበብቶች፤ ሰራተኞች፤ አገር
ወዳዶች ወዘተ አገር ብትሆንም ዛሬ የተማረና አገሩን ለማልማት የሚችል የተማረና የሰለጠነ የሰው ኃይል ድሃ ሆናለች። በሃያ አንደኛው
መቶ ክፍል ዘመን ተቀባይነት የሌለው በኢትዮጵያ ተከስቷል። ገዢው ፓርቲ ኢትዮጵያውያንን በጎሳ እየከፋፈለ፤ እያሰረ፤ እያባረረ፤
እያደኼየ፤ ኃይላቸውን እያባከነ፤ ተስፋ እያስቆረጠ፤ መብታቸውን እየገገፈፈ፤ ተሰደው የውጭ ምንዛሬ እንዲልኩ እያደረገ ከሕንድ፤
ከቻይናና ከሌሎች አገሮች የሰው ኃይል፤ የቀን ሰራተኞች ጨምሮ፤ ይሽምታል። ኢትዮጵያውያን ሊሰሩት የሚችሉትን በውጭ አገር
ሰዎች ያሰራል። አገሪቱ የማትችለውን ደሞዝና አበል ይከፍላል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተማረውና ያሰለጠነው የሰው ኃይል፤ በተለይ
ወጣቱ ትውልድ በአገሩ የመስራትና የስራ እድል የመፍጠር አቅምና መብቱ ስለታፈነ ወደ መካከለኛው ምስራቅ፤ ሰሜንና ደቡብ ሱዳን
ወዘተ ይጎርፋል። የሳውዲ፤ በቅርቡ የኩዌት መንግሥትና ሌሎች በኢትዮጵያውያን የቀን ሰራተኞች ላይ የወስዱት አሳፋሪ እርምጃ
በግልፅ ያሳየን አስደናቂ እድገት ታሳያለች የምትባለው አገራችን የኢትዮጵያውያንን የስራ፤ የገቢና የኑሮ ፍላጎት ለማሟላት አለመቻሏን
ነው። በተደጋጋሚ እድገቱ የጥቂቶች መጠቀሚያ ሆኗል የምለው ለዚህ ነው።
አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በኑሮው፤ በመብቱ፤ በመንግሥቱና በተፈጥሮ ሃቡቱ ለማዘዝ አይችልም። በአገር ቤት መሬት ለመመራት፤
ቤት ለመግዛት፤ የግል ተቋም ለመመስረት የሚችለው ገቢና አቅም ያለው ዲያስፖራ፤ በአብዛኛው የገዢው ፓርቲ አጋር ሆኗል ለማለት
ይቻላል። በዓለም ድሃ፤ የሕዝባቸው ጤና ያልተጠበቀበትና ኋላ ቀር ከሆኑ አገሮች መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ የተማረ የሰው
ኃይል ድሃ መሆኗን በአንድ ምሳሌ አቀርበዋለሁ። የካናዳው ኩሶ ኢንተርናሽናል ባደረገው ጥናት ከ1990-2006 ዓም ባለው ጊዜ ብቻ
ኢትዮጵያ ካሰለጠነቻቸው 3,700 የህክምና ባለሞያዎች 700 ብቻ አገር ቤት ይሰራሉ። ሶስት ሽህ የሚሆኑት ወጥተው ሌሎች
ሕብረተሰቦችን፤ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ያገለግላሉ። በሌሎች ሞያዎች የተሰማራነውም ተመሳሳይ ሚና አለን። ገዢው ፓርቲ
ፈቃድና ፓሥፖርት በመስጠት ቀልጣፋ ነው። መብትን በመግፈፍ የሰለጠነ ነው። የሚፈልገውን ያገኛል። የሚፈልገው ሁለት ነገሮች
አሉ። አንድ የውስጥ ተወዳዳሪና ተቃዋሚ እንዳይኖር። ሁለት ወደ ውጭ የሚጎርፈው የሰው ኃይል የውጭ ምንዛሬ እንዲልክና ለገዢው
ፓርቲ ደጋፊ እንዲሆን። ብንቀበልም ባንቀበልም ይህ እቅድ እየሰራ ነው። የእድገቱ አድናቂ ከሆኑት ውስጥ ሃብትና ቤት ያለው
ዲያስፖራ የመጀመሪያውን ደረጃ ይዟል። ከመቶው ዘጠናው የኢትዮጵያ ሕዝብ የነፍስ ወከፍ ገቢ ዓለም ባንክ ካወጣው በቀን አንድ
ዶላር ከሃያ አምስት ሳንቲም በታች መሆኑን ረስቶታል ወይንም አያየውም። ስለዚህ ነው፤ “ዓባይ ዓባይ ዓባይ” የሚለው አነጋጋሪ
አርእስት ከስርዓቱ አፋኝነት ጋር አብሮ መታየት አለበት የምለው።
የማይካደው ሃቅ አቅም ያለው ዲያስፖራ በሚሰጠው ፈቃድ፤ የገዢው ፓርቲና ተወካዮቹ በወሰኑለት ዋጋና በሚያመቻቹለት ኩንትራት
ቤት ይሰራል ወይንም ይገዛል። የመሬትና የቤት ዋጋ ከኢትዮጵያ የማምረትና የገቢ አቅም ጋር ሲመጣጠን “እግዚዖ ምን መጣ”
የሚያስብል መሆኑን ተራው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቀዋል። ዋጋው ለምን ከፍ እንደሚልና በአገር ቤት ያለውን ገቢው የማይፈቅድ
ወገኖቹን እንዴት እንደሚጎዳ ለመገንዘብ ዛሬ ዘመናዊዋ አዲስ አበባ የማን ከተማ እንደሆነች ማየቱ ብቻ ይበቃል። መካከለኛው
መደብና ድሃው ተመልካች እንጅ ባለሃብት አይደለም። ገዢው ፓርቲ ብልጥ መሆኑን ለመገመት አያስቸግርም። ቤትና ሌላ የቁሳቁስ
ሃብት ያለው በውጭ የሚኖረው ዲያስፖራ የሚሰራውን ቤት ለእረፍት፤ ለጡሮታና ለኪራይ ይጠቀምበታል። የአብዛኛው ዲያስፖራ 2
ባህል ከሃገሩ ጋር የተቆራኘ ስለሆነ ከዚህ ዓለም ሲለይ ወይንም ክፍ ቀን ሲገጥመው ትቷት ወደመጣባት “አገሬ ላኩኝ” እንደሚል ብዙ
ታዛቢዎች ይናገራሉ። ይህ ለገዢው ፓርቲ አመች ነው። ዙሮ ዙሮ የመሬት ሃብቱና በግምብ ላይ የፈሰሰው መዋእለ- ንዋይ የራሱና
የደጋፊዎቹ እንደሚሆን አስልቷል። ገዢው ፓርቲ የተፈጥሮ ሃብት የበላይ እስከሆነ ድረስ የግል ሃብት ዋስትና አይኖረውም። የግል
ሃብት በሕግ የተከበረ አለመሆኑን በተደጋጋሚ አይተናል። መካከለኛ መደቡና ድሃው ለኑሮው መሻሻል አስተማማኝ ሁኔታ የለውም።
ባጭሩ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠረው ስደተኛ ሊገነዘበው የሚገባው ስደትና የስደት ባህል የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም፤ ዘላቂነት፤
ማህበራዊ አንድነትና ፈጣን እድገት እንደበከለው ነው። ስርዓቱ የጥቂቶች አገልጋይ እስከሆነ ድረስ የአገሪቱ የተፈጥሮ ኃብት፤ ዓባይን
ጨምሮ ይባክናል። ጥገና እንጅ አገር ወለድ ልማት አይኖርም። የዚህ ትንተና አስኳል ሃሳብ ከድህነት ነጻ የሆነ፤ በራሱ የሚተማመን፤
መብቱ የተከበረ፤ በመንግሥቱ ላይ ለማዘዝ የሚችል ሕብረተሰብ እስካልተመሰረተ ድረስ ኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶቿን ለመከላከል፤
ጥቅሟን ለማስከበር፤ ደህንነቷን ለመጠበቅ የምትችል መሆኗ ያጠራጥራል። የዓባይ ባለቤትነት ዋስትና ከአገሪቱ ሕብረተሰብ
መቀራረብና አንድነት ጋር አብረው የሚሄዱ ሆነው ይገኛሉ።
ዓባይን በተመለከተ በቁጥር አንድ ያቀርብኩት መሰረታዊ የፖሊሲ አቋም የአባይ ወንዝና ውሃ የኢትዮጵያ መሆኑን ነው። ይህ
አያከራክርም። የተሃድሶ ግድብ ከስሙ በስተቀር የህወሓት/ኢህአዴግ አጀንዳ አይደለም። የኢትዮጵያ ተከታታይ መንግሥታት
የታገሉበት፤ ኢትዮጵያውያን የሞቱበለት፤ የውስጥና የውጭ ተፃራሪዎች ስኬታማ እንዳይሆን ያገዱት ወሳኝ የተፈጥሮ ሃብት ነው።
የባህር በርም ተመሳሳይነት አለው። ዓባይ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን መታወቂያ፤ የአገሪቱ የወደፊት እድል ወሳኝ ሃብት መሆኑን
አሳስባለሁ። ሆኖም፤ የተፈጥሮ ሃብት ዘላቂነትና ህይወት ለዋጭነት ከስርዓቱ አሳታፊነትና ፍትሃዊነት ተለይቶ ሊታይ አይችልም።
ህወሓት በበላይነት የፈጠረውና የሚመራው ስርዓት አፋኝ፤ ከፋፋይና አግላይ ነው። ኢትዮጵያዊነቱ የማያሻማ የሆነውን የትግራይን
ሕዝብ ከወንድሞቹ፤ ከእህቶቹ፤ ከጎረቤቶቹ ወዘተ ለመለየት የሞከረ ጠባብ ቡድን ዙሮ ዙሮ መጋለጡ አይቀርም። ዛሬ በግልፅ በምድር
ላይ የሚታየው ሁኔታ የጎሳዊው ስርዓት የኢትዮጵያውያንን ጥንክርና መሰረት፤ ማለትም አብሮ፤ ተቻችሎና ተከባብሮ አገርን የመጠበቅና
ለጋራ ጥቅም የማልማት እሴቶች ከስሩ አናግቷቸዋል። ጠንካራ ኢትዮጵያንና ከድህነት አሮንቃ የተላቀቀ፤ ራሱን የቻለ ማህበረሰብ
ለመመስረት የሁሉም ህብረተሰብ ክፍሎች ሰብአዊ መብት መከበር አለበት። ፍትህ የሌለበት እድገት ጥቅም ለተወሰኑ የፖለቲካ
ኃይሎችና ወዳጆቻቸው መሆኑን ባለፉት ሃይ ሶስት ዓመታት አይተናል። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሕግ ፊት ያልተገደበ እኩልነት
መብቱ ነው። የአባይን ጥቅም ማህበራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያውያን ሰብአዊ መብትና የተፈጥሮ ሃብት ባለቤትነት ግልፅና ተቋማዊ
በሆነ መንገድ በሕግ መታወቅ አለበት። የመንግሥት ስርአቱ አሳታፊና ፍትሃዊ ካልሆነ ግድቡን አጼ ፋሲል፤ አጼ ዘረያእቆብ፤ አጼ
ተከለኃይማኖት፤ አጼ ዮሃንስ፤ አጼ ቲዎድሮስ፤ አጼ ምኒልክ፤ አጼ ኃይለ ሥላሲ፤ ደርግ ወይንም ጎሰኛው ህወሓት/ኢህአዴግ ቢሰሩት
ድህነትን፤ ኋላቀርነነትንና ጥገኛነትን ከስሩ ሊገረስሰው አይችልም። ባለፉት ሃያ ሶስት ዓመታት እንደታየው የተፈጥሮ ሃብት ልማት
ጥቅም ለተወሰኑ ባለስልጣናትና ወዳጆቻቸው ይሆናል። ወሳኙ የስርዓቱ ፍትሃዊነት ነው። ስርዓቱ ካልተለወጠና የሕዝብ መብትና
ስልጣን ተቋማዊ ካልሆነ ፍትሃዊነት አይኖርም። ፍትሃዊ ስርዓት በቀላሉ አይመሰረትም። መተባበርን ይጠይቃል። ጥቃቅን ልዩነቶችን
ወደ ጎን ትቶ ለዓላማ አንድነት አብሮ መስራት የጊዜው ተቀዳሚ ጥያቄ ነው።
ይህ እንዳለ ሆኖ፤ የማንኛውም አገር ዘላቂና ፍትሃዊ እድገት የሚያሳየው አስኳል ጉዳይ አለ። ዓባይ ወይንም ሌላ አንጋፋ የተፈጥሮ
ሃብት የኢትዮጵያውያን ሃብት ነው ሲባል፤ በመጀሚሪያ ኢትዮጱያ የምትባል አንድ አገር መኖሯን መቀበልን ይጠይቃል። ህወሓት
ከጅምሩ ይህ እሴት እንዲጠፋ አድርጓል። ኢትዮጵያዊ የሚባል ዜግነት የጋራ መታወቂያ መሆኑን ማስተጋባት ግዴታ ይሆናል። ይህ
ካልሆነ የዓባይን ጥቅም ማህበራዊ ለማድረግ ሕልም ይሆናል። ተጠቃሚው ዛሬ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነቱን የያዘው የጎሰኛ ቡድን
መሆኑ አይቀርም። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ስል፤ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር/ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ምንም ገደብ የሌለው፤ በሕግ
የተረጋገጠ የመወሰን፤ የመሳተፍ፤ የመንቀሳቀስ፤ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ሃብትና ንብረት የመያዝ ወዘተ እኩልነትና ተሳትፎ
ይኑራቸውና ሲኖራቸው ማለቴ ነው። አንዱ የበላይ አንዱ የበታች፤ አንዱ ስልጣንና ሃብት ያለው፤ ሌላው ድሃና ተመልካች ወዘተ የሆነ
ስርዓት ከሆነ ስርዓት ፍትሃዊ ሊሆን አይችልም። የሚወልዳቸው ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ፤ ለውጭ አገር ኃይሎች የሚጠቅሙ ክፍተቶችን
ነው። ከዚህ በፊት ተፈጥረዋል። ዛሬም እየተፈጠሩና ስር እየሰደዱ ነው። አግላይነትና አፈና የእነዚህና ተመሳሳይ ችግሮች ፈጣሪ ነው።
የተገለለ ግለሰብ ለመብቱ መከራከር አይችልም። ኢ-ሰብአዊ፤ አግላይ፤ አፋኝና ጨካኝ የሆነ ስርዓት ቆይቶም ቢሆን አለመረጋጋትን፤
የእርስ በርስ ጦርነትን፤ መከፋፈልን፤ እልቂትን፤ ተገንጣይነትን፤ ሽብርተኛነትን ወዘተ ይፈጥራል። ይህ አባባል ከአየር ላይ የተቀሰመ
አይደለም። ቢያንስ ባለፉት አምሳ ዓመታት ታይቷል።
የኢትዮጵያውያን የመንታ ጉዞ
የዓባይ ባለቤትነት ጉዳይ መንታ ጉዞ ያሳያል። የኢትዮጵያ ሕጋዊና ተፈጥሯዊ የዓባይ ባለቤትነት በአንድ በኩልና የኢትዮጵያ ሕዝብ
የፍትህ ጥያቄ በሌላ በኩል። የዓለም ሁኔታ፤ የአካባቢው የኃይል አሰላለፍ ስእል፤ የአሁኑ ስርዓት አፋኝነት የሚያሳየው ሃቅ አለ። በአንድ
በኩል ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በፈተና ላይ ናቸው። የሚያሳየው የዓባይን ይገባኛልነት (አግባብ ያለው ተልእኮ) አስተማማኝነትና
ዘላቂነት ባለው ተቋማዊ ደረጃ ስኬታማ ለማድረግ አስቸጋሪ መሆኑን ነው። የዚህ ማነቆ መነሻ ኢትዮጵያውያን፤ ልክ ባለፉት አምሳ
ዓመታት እንደታየው ሁሉ፤ ዛሬ በባሰ ሁኔታ መብታቸው ተገፎና ታፍኖ የራሳቸው የተፈጥሮ ኃብት ባለቤት አይደሉም። ሌላው ቀርቶ
በራሳቸው የግል ህይወት ለማዘዝ አይችሉም። የሚኖሩት አንድ በአምስት በሚል የሰለላና የቁጥጥር ሰንሰለት ነው። አባት በልጁ፤ ሚስት
በባሏ፤ ወንድም በእህቱ፤ ጓደኛ በጓደኛው፤ ተማሪ ባሰተማሪውው ላይ እንዲሰልል የሚያደርግ ስርዓት የማህበረሰብ ድክመት እንጅ
ጥንክርና አይፈጥርም። የሚፈጥረው የእርስ በርስ አለመተማመንን ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የመጀመሪያውን የተፈጥሮ ሃብታቸው 3
ባለቤትነት ግብ ለማረጋገጥ ሁለተኛውን ግብ፤ ማለትም፤ ሰብአዊ መብታቸውን ማስከበርና ዲሞክራሳዊ አገዛዝ ለመመስረት መሯሯጥ
ተቀዳሚ ተግባራቸው ሆኖ ይገኛል። ይኼም ስኬታማ ሊሆን የሚችለው በተናጠልና በተከፋፈለ መንገድ በሚደረግ ትግል አይደለም።
ለመከፋፈል የሚሰጥ ምክንያት የሚያገለግለው ገዢውን ፓርቲና የውጭ ኃይሎችን ጥቅም ብቻ ነው። መለያየት ድህነትን አያጠፋም።
የህብረተሰብ አብሮና ተሳስሮ መስራት (Social cohesion) ድህነትን ይቀንሳል። እየቆየ ያጠፋዋል። ለሁሉም ቤት የምትሆን፤ ፍትሃዊ፤
አሳታፊ፤ በሕግ የበላይነትና በእውነተኛ እኩልነት የምትዳኝ ኢትዮጵያን ለመገንባት ከተፈለገ (በኔ ግምት አስፈላጊና ሊተገበር የሚችል
ዓላማ ነው) መሰረታዊ ለውጥ ፈላጊዎች ሁሉ ገዢው ፓርቲ በፈጠረላቸው የልዩነት ወጥመድ መበከላቸውን ማጤንና ለዚህ ወጥመድ
መፍትሄ መፈለግ አለባቸው። መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ፍላጎት ካለ ባለፈው--በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥትና በደርግ---
የተከተልናቸውን የሥልጣን ሽሚያዎች የፖለቲካ ባህል ማስወገድ ግዴታ ነው። መሰረታዊ ለውጥ ከተገኘ በኋላ ሊፈቱ የሚችሉ
ልዩነቶች አሉ። ለጊዜው እነዚህን ልዩነቶች ወደ ጎን ትቶ አብሮ፤ ተቻችሎ፤ ተከባብሮ በጋራ መታገል የወቅቱ መሪ ጥያቄ ነው። ለዚህ
ግብ የሚታገሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ መቀበልና መደገፍ አለብን።
ዘላቂነት ያለው ለሁሉም የሚያገለግል የስርአት መሰረታዊ ለውጥ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ቁልፍና የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው
ካልን፤ ከሚያለያዩን ይልቅ የሚያቀራርቡን እሴቶች ከፍተኛነት ማስተጋባት ጠቃሚ ነው። ከማንኛውም አቅጣጫ በሚመጣ የጥላቻ
ርእዮት አእምሯችን “ካልተዘጋ” በስተቀር፤ ኢትዮጵያ የምትባል የሰው ፍጥረት (humankind) መንስኤ መሆኗን መቀበል ለሁላችንም
ኩራት ነው። ጥንታዊ የስልጣኔ ፋና ከሆኑ ጥቂት አገሮች---ቻይና፤ ግብፅ፤ ሜሶፖታሚያ፤ ግሪስ፤ ኢታሊ (የሮማን ግዛት) መካከል አንዷ
መሆኗን መቀበል ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ያኮራል። የልዩ ልዩ ኃይማኖቶች፤ በተለይ የክርስትና፤ የእስልምናና የአይሁዳዊ እምነቶች
መዲና መሆኗ አብሮ፤ ተከባሮና ተቻችሎ የመኖር መስፈርት ስለሆነ ለሁላችንም የመንፈስና የሞራል ጥንካሬ ይሰጠናል። ሌሎች አገሮች
ለማድረግ ያልቻሉትን ማድረግ ቀላል አይደለም። ቀላል ቢሆን እስካሁን በተሰራ ነበር። ተስፋ ሳይቆርጡ ጥረት ማድረግ የጥንካሬ
መለኪያ ነው። እነዚህ የእምነት ልዩነቶች ለፖለቲካ ስልጣን ማሽከርከሪያ እንዳይሆኑ መጣር የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሃላፊነት ነው።
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከኃይማኖት፤ ከጎሳ፤ ከገቢ ወዘተ በላይ ናችው ብለን ከተነሳን አገራችንና ሕብረተሰቡ ይጠነክራሉ።
ኢትዮጵያ በነጻነቷ ኮርታ ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የሚያኮራ ምሳሌ መሆኗን ማስተጋባት ጎሳዊ አይደለም። ብሄራዊ ነው። ብዙ የአፍሪካ
አገሮች የኢትዮጵያ መታወቂያ የነበረውን ሰንደቅ ዓላማ ለአገሮቻቸው አግባብ ባለው ሁኔታ ተቀብለዋል። የደቡብ ሱዳን፤ የጃማይካና
ሌሎች ሕዝቦች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እንደሚያኮራ መለያ ተቀብለውት አናያለን። ኢትዮጵያ ከክርስቶስ ልደት በፊት በግምት
ከ400 እና 300 የኖረው የግሪኩ የታሪክ ትምሕርት አባት ተብሎ የሚታወቀው ሄሮዶተስ በአካባቢው ተጉዞ ስለ ኢትዮጵያ እውቅና
ያየውን ለታሪክ መዝግቧል። በወቅቱ የእትዮጵያ ግዛትና ድንበር በሰሜን ግብፅን፤ በሰሜናዊ ምስራቅ ቀይ ባህርን፤ የመንን፤ ደቡብ
ሳውዲ አረቢያን ወዘተ እንደሚሸፍን ጽፏል። ኤ.ደ ሰሊንኮርት ከግሪክ ወደ እንግሊዝኛ በ1954 በተረጎመው “ሔሮዶተስ--የታሪክ
ባለሞያው” በተባለው መጽሃፉ የኢትዮጵያውያንን ዓለም ዓቀፍ የሕዝብ ስርጭት ግልጽ በሆነ መንገድ አስቀምጦታል። “በምስራቅ
የሚገኙት ኢትዮጵያውያን በፔርዢያ የጦር ኃይል ውስጥ ገብተው ከህንዶች ጋር ያገለግላሉ፤…እነዚህ ኢትዮጵያውያን፤ ከቋንቋቸውና
ከፀጉራቸው መለያ በስተቀር በደቡብ ከሚገኙት ወገኖቻቸቸው አይለዩም… ተመሳሳይ ልምድና ባህርይ አላቸው…በሊቢያ (አፍሪካ)
የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ፀጉራቸው ከርዳዳ፤ ሰውነታቸው ቀጠን ያለ” ወዘተ ነው ይላል። ከእርሱ በፊት የኖረው የግጥም ደራሲና
ፈላስፋ ሆመር በኦዲሲ (The Odyssey) ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን እውቅና ሰጥቶ እንዲህ ብሏል። “በፅሃይ ሙቀት የተቃጠሉ
የሚመስሉ ጥቁር ወንዶች፣ አ ኢቶፒ (ኢትዮጵያውያን) ከምእራብ ሊቢያ (አፍሪካ) እስከ ምስራቅ ሜሶፖታሚያ (ዛሬ የመካከለኛው
ምስራቅ የሚባለው) ተሰራጭተው ይገኛሉ...” ብሏል። ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ቤት የምትሆን ስርዓቷ ፍትሃዊ የሆነች ኢትዮጵያን
እንፍጠር የሚለው መሰረታዊ የክርክር ነጥብ ከዚህ ከኢትዮጱያ ታሪካዊ ሂደት ተከታታይነት የተለየ አይደለም። ይህ የወደፊት ታላቅነት
ድልድይ ወይንም መሰረት ምልክት ነው።
በኢትዮጵያ ታሪክ የተለያዩ “በፅሃይ ሙቀት” የተቃጠሉ ኢትዮጵያውያን ከሊቢያ (አፍሪካ እስከ ፔርሽያ/ሕንድ ድረስ ተሰራጭተው ነበር
ሲባል ለአንድ ጎሳ ብቻ እውቅና የሚሰጥ አይመስለኝም። ነዋሪዎቹ ትግሬ፤ አማራ፤ አፋር፤ ኦሮሞ፤ ሶማሌ፤ ወላይታ፤ ድብልቅ ወዘተ
ሊሆኑ ይችላል። ማን ምን እንደሆነ ጅናቸውን መርምረን አልደረስንበትም። ማንም ታላቅ አገር ዜጋውን ለመለየት “ጅንህ ምን ይሆን”
ብሎ የጠየቀ የለም። የሞከረው ሂትለር አይሁዶችን ለማጥፋት ሲል ነበር። ሞክሮ በመጨረሻ ራሱን አጥፍቷል። የሰው ፍጥረት ከአፋር
ሸለቆ ተጀመረ የሚለው ብቻ የኢትዮጵያውያን ጥንታዊይነትና፤ በመጠነኛ ደረጃ፤ ስርጭት መረጃ ሊሆነን ይችላል። ይህ ሰብአዊ
ፍጥረት እንደ ጉልቻ በአንድ ቦታና አገር አይቀመጥም። ህያው ስለሆነ ይፈጥራል። ይንቀሳቀሳል። ከሌላው ጋር ይዋለዳል ወዘተ። ይህ
የአፋር ክልል በረከት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚያኮራ የታሪክ ምእራፍ ነው። ይህ በሳይንስ የተረጋገጠ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ
የተባለችውን ታሪክ የመዘባትን አገርና ለሁሉም የዜግነት መታወቂያ የሆነውን ኢትዮጵያዊነት አንቀበልም የሚለው የጎሰኞች አዲስ ታሪክ
ፈጠራ የሚጠቅመው ለራሳቸውና ለውጭ ኃይሎች እንጅ ለኢትዮጵያውያን ሊሆን አይችልም። ኢትዮጵያውያን “እኛን በጎሳ
አትከፋፍሉን” የማለት መብት አለን። ዓባይ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃበት ነው ከተባለ ኢትዮጵያዊነት መለያችን ነው ለማለት ደፍረን
ድምጻችን ማሰማት አለብን። ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚመኙት ያለፈው እንዳይደገም ፍትሃዊ ስርዓት መገንባትን ይመስለኛል።
ተከታታይ ትውልድ የሚመኘውና የሚያስፈልገው ጥላቻን አይደለም። ለዚህ የሚያደርሰው ሁሉን አስተናጋጅ ጥበባዊ አመራርና
ስራዓት ነው። በሰላም፤ በእኩልነት፤ በነጻነት፤ በፍትህ፤ በሕግ የበላይነት መኖርን ነው። ከፍጹም ድህነት መላቀቅን ነው። የስደት ባህልን
ማቆም ነው። እነዚህ አብሮ የመኖርና አብሮ ፍትሃዊ ስራዓት የመገንባት ቅድመ ሁኔታዎች የሚያመለክቱት ድህነትን ተባብሮ ለማስወገድ
እንደሚቻል ነው። መተባበር ኢትዮጵያውያን የተፈጥሮ ሃብታቸው ባለቤት መሆን መብታቸው እንደሆነ ስኬታማ ያደርጋል። ቤትና
ንበረት ከገዢው ፓርቲ የሚለመን ጉዳይ አይደለም። የኢትዮጵይውያን መብት ነው። መብት በልመና አይገኝም። ሕብረተሰቡ ከአንድ 4
ላይ ሆኖ ለመብቱ ከቆመ የማይቀር ነው። ገዢው ፓርቲ “እኔ ጥቅማችሁን አከብራለሁ” የሚልበት የፖለቲካ ጨዋታ ወቅት የሚያልፈው
እርስ በርስ የሚካሄደው ባለፈው ላይ ብቻ ትኩረት የሚሰጥ የመከፋፈል ፖለቲካ ባህል ሲያቆም ይመስለኛል።
ኢትዮጵያ የምትባል አገር ጥንታዊና ታሪካዊ አይደለችም የሚለው አዲስ ሰው ፈጠር ታሪክ መሰረተ ቢስ መሆኑን የኢትዮጵያ የታሪክ
ሊቃውንት በሰፊው እንደጻፉት ይታወቃል። ይህ የሚያኮራ የታሪክ አቀራረጽ እንዳለ ሆኖ፤ ፈረንጆች የፃፉትን ስንመለከት ፕሮፌሰር
ማርቲን በርናል ስለ ጥቁር ሕዝቦች፤ በተለይ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የፃፈው “Black Athena: The Afro-Asiatic Roots of
Classical Civilization,” Volume I, 1987 ለዚህ ክፍል አግባብ አለው። የአውሮፓና የአረብ የታሪክ ፀሃፊዎች የጥቁሮችን ስልጣኔ፤
የአገር ምስረታ፤ የዘመናዊነት አስተዋፆ ፈፅሞ እንደሌለ አድርገዋታል የሚል ማስረጃና ትንተና ይሰጣል። “በኔ ጥናትና ምርምር የጥቁር
አፍሪካና ኤዢያ ስልጣኔና ባህል በምስራቅ አፍሪካ ሸለቆ (East African Rift Valley) “የበረዶው ዘመን (The Ice Age)” ተብሎ
በሚታወቀው ከክርስቶስ በፊት ከብዙ መቶ ምእተ ዓመታት በፊት ነው።” ዛሬ የአፋር ክልል ተብሎ በሚጠራውና በአካባቢው
የተመሰረተው ባህልና ስልጣኔ ነዋሪዎች የእርሻ፤ የአደን፤ የከብት እርባታና ሌሎች የኢኮኖሚና የአይነት ንግድ ተግባሮችን ልምድ
እንዳደረጉ ያሳያል። ይህን ልምድ በየሄዱበት አስራጭተዋል። ለምሳሌ፤ እነዚህ ነዋሪዎች ከቀያቸው ተንቀሳውሰው ወደ ቻድ ኃይቅ፤
ማግሬብ (ሞሮኮ፤ ቱኒዢያ፤ አልጀሪያ) የአባይን ወንዝ ተከትለው ወደ ሱዳንና ግብፅ፤ በሰሜን ምስራቅ ወደ አረቢያ (ዛሬ ሳውዲ
አረቢያ፤ የመንና የገልፍ አገሮች) ወደሚባሉት ተሰራጭተዋል። ብዙ ኢትዮጵያውያን ከአረቦች ጋር የተቀላቀሉትና አረብ የሚመስሉት
ኢትዮጵያውያን ወደ የመን፤ ደቡብ ሳውዲ አረቢያና ሌሎች የዓረብ አገሮች ስለተንቀሳቀሱና ዓረቦች ወደ ኢትዮጵያ ስለመጡ ነው።
ሲንቀሳቀሱ ልምዳቸውን አበርክተዋል። ከነሱም ተምረዋል። በበርናል አባባል፤ “ኢትዮጵያውያንና ሌሎች አፍሪካውያን ግብፅ
በሚገኘው የአባይ ሸለቆ ተሰራጭተዋል። ከነዋሪዎች ጋር ተጋብተው ተዋልደዋል። ለግብጾች ስልጣኔ ከፍተኛ በረከት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ነገሥታት በተደጋጋሚ ግብፅን ለመያዝ ሞክረዋል።” ግብጾች ይኼን የኢትዮጵያውያንን፤ የአፍሪካውያንን በረከት ተቀብለው
አያውቁም። የሚቀበሉት ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ህብረተሰቦቻቸውን ከድህነት፤ ከጥገኝነት፤ ከኋላ ቀርነት ነጻ ሲያወጡ ብቻ
ነው። ነጻ ለማውጣት ደግሞ የመንግሥት ስርአቶቻቸው ለሕዝብ አገልጋይና ተጠሪ መሆን አለባቸው።
“The image of the Ethiopian King who marched into Egypt and on to Susa would seem to be based on
the Ethiopian conquorers of Egypt 716-695 BC…and 689-664 BC.” የኢትዮጵያ በረከት ወንዧ ብቻ አይደለም ማለት
ነው። የእርሻ ልምድ፤ የጌጣጌጥ ስራ፤ የጦርና ጎራዴ ስራ፤ የሸክላ ስራ፤ የንግድ፤ የግድብና ህንጻዎች ስራ ወዘተ ልምዶችን እንዳበረከተች
ጥናቱ ያሳያል። “ የተፈጥሮ ሃብቷ የተወሰነ ስለሆነ፤ ግብፅ ጥገኛ አገር ናት። በራሷ ቅመማ ቅመም፤ የዝሆን ጥርስ፤ ወርቅ፤ እንቁ፤ ወዘተ
አታመርትም። እነዚህ የተገኙት ከኢትዮጵያና ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ነው።” ይህ እውነት ከሆነ አውሮፓውያንና አረቦች ለምን እውነቱን
አልተቀበሉም ብለን የመጠየቅ መብትና ግዴታ አለብን? መልሱን አንባቢ ያስብበታል የሚል እምነት አለኝ። በርናል የደመደመው በቂ
ይመስለኛል። “I refuse to accept the (European and Arab) basic social-Darwinist premise that the conquest
or domination through violence (slavery, colonialism) somehow makes a people or linguistic group
morally or creatively better than those who are conquered or dominated….Early European Bronze Age
Civilization derived in some way from the skills of earlier metal working cultures of Southeast Asia and
North-East Africa of which Ethiopia is a part.” በሁሉም አቅጣጫ ሲታይ፤ የጥቁር ሕዝቦች አስተዋጾ እንደሌለ ተቆጥሯል።
ይህ የታሪክ ድለዛና ክህደት ኢትዮጵያንና ሌሎችን የጥቁር አፍሪካ አገሮችና ሕዝቦች ለመቆጣጠር፤ ታሪክ፤ ማንነት ወዘተ እንደሌላቸው
ለማድረግ ረድቷል። የጎሳ ፖለቲካ መሪዎች ኢትዮጵያ “የመቶ ዓመታት ታሪክ ብቻ ነው ያላት” ሲሉ የሚጋሩት ሃቅ የጠላቶቿን ነው።
ማንነታችን አለማወቅ ያስከተለው ከባድ ዋጋ
በአፍሪካ የዘመናዊ ትምህርት ሲስፋፋ የተዛባውን ለአውሮፓና ለአረቦች አድልዎ የሰጠውን (Euro-Arab centric) ሂደት
አላስተካከለውም። የኔ ትውልድ በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ የትምኅርት ገበታ ላይ በነበረበት ወቅት የአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት
ትኩርት የሰጠው ሃሁን ወዘተ ማወቅን ነበር። ህይወት ለዋጭና ለተከታታይ ትውልድ ወሳኘ የሆነው ትምኃርት ከታሪክ፤ ከባህል፤
ከልምድ፤ ከአካባቢ፤ ከተፈጥሮ ሃብት፤ ከተከታታይ መንግሥታት፤ ከኢትዮጵያ ብሄር/ብሄረሰብና ሕዝቦች አብሮ መኖር ጋር ወዘተ
ያለውን ትሥስር (Organic link) አላስተማረንም። አገራችን በሚመለከት በድንቁርና አድገናል ለማለት ይቻላል። የአባይን ወንዝ
ሳናውቅ ስለ አማዞን፤ ስለ ኢንደስ ጋንጀስ እንማር ነበር። ስለ ኢትዮጵያ የተለያዩ የሁሉም ብሄር/ብሄረሰብና ኃይማኖት ወርቃማ
ባህሎች፤ ልምዶች፤ ቋንቋዎች፤ ታሪኮች፤ ስልጣኔዎች ምንም ሳናውቅ ስለ ግሪኮች፤ ሮማኖች፤ እንግሊዞች፤ ፈረንሳዮች፤ አሜሪካኖች
ወዘተ ታላቅነት ተምረናል። በተከታታይና በልዩ ልዩ ቀውጢ ወቅቶች ኢትዮጵያን የታደጉ ከሁሉም ብሄር/ብሄረሰቦች የተወጣጡ
የታላላቅ ኢትዮጵያዉያንን ምንነት አልተማርንም። ዛሬ ወጣቱ ትውልድ ስለሃገሩ ከሚያውቀው ይልቅ ስለ እንግሊዝ የእግር ኳስ
ጨዋታ ሊግ ያውቃል። ሁላችንም በአጠቃላይ የአጼ ምኒልክን የአድዋ ጀብድና ድል ብናውቅም፤ ለድሉ ውጤት ከፍተኛ አስተዋፆ
ያደረጉት ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ጀግኖችና አገር ወዳዶች መሆናቸውን በሚገባ አልተረዳንም። በፋሽስት ወረራ
ዘመን ግራዚያኒን ለመግደል እቅድና ሙከራ ካደረጉት አገርና ነጻነት ወዳድ ኢትዮጵያውያን መካከል የኤርትራ ተወላጆች የሆኑት
ኤርትራን ለቀው አዲስ አበባ ይማሩ የነበሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል። Ethiopia 1937: the Plot to Kill Graziani, Addis
Ababa University, 2010 የኢትዮጵያውያንን አገር ወዳድነት፤ ጀግንነትና ቆራጥነት ያመለክታል። ሞገስ አስገዶምና አብርሃ ደቦጭ
ቆራጥ ከሆኑ ጀግኖች መካከል ከፍተኛ ደረጃ የያዙ ናቸው። የግድያውን ዝግጅትና አፈጻጸም ከሚያምኗችው ኢትዮጵያውያን ጋር ሆነው 5
በጥበብና በምስጢር ያካሄዱት ያስደንቃል። ያኮራል። ሞገስ ለተባባሪው ጀግና አብርሃ “ራስክን ለክብርህ መሰዋት አለብህ” ያለው
ተከታታይ ትውልድ ሲያስታውሰው ይኖራል። ኢትዮጵያ እነዚህን የኤርትራ ተወላጅ የመሰሉ አገር ወዳድ፤ ደፋርና ጀግና
ኢትዮጵያውያን ከኦሮሞው፤ ከትግሬው፤ ከደቡቡ፤ ከወላይታው፤ ከአፋሩ፤ ከሶማሌው፤ ከጉራጌው ወዘተ እንደነበሯት አውቃለሁ።
አሁንም እንዳሏት እገምታለሁ። ስለነዚህ መነጋገር ማቆማችን የወደፊቱን ትውልድ እንደሚጎዳው አሳስባለሁ። በምንለያይባቸውም
ለወደፊቱ ትውልድ ስንል ደፍረን በመከባበር እንወያይ። ከእኛ በላይ ለወጎኖቻችን የሚያስብ ሊኖር አይችልም።
ህወሓትና ሌሎች ጎሰኞች ያደረጉትና የሚያደርጉት የሚያሳዝነውና የወደፊቱን ትውልድ የሚያሰጋው ብዙውን ያለፈ ታሪክ በጥላቻ፤
በመበረዝ፤ በሽሙጥ አይነት ወሬ በሚበይን (በሚፈርድ) መነፅር እንድናይ ተገደናል። የማይካደው ግን ማንም ከደረታችን ላይ ሽውጥ
አንግቦ ተጣሉ፤ ተፋጁ ያለን አላገኘሁም። ፈቅደንና ዝም ብለን የኢትዮጵያን ሥብጥር ሕዝብ ብሄራዊ አንድነት ወደ ጎን ትተነዋል።
ማንኛውም አገር ያለጦርነት አልተመሰረተም። ጦርነት የውጭም የውስጥም ነው። የእንግሊዙ ፈላስፋ ቶማስ ሆብስ ስለ ሰላም፤
ጦርነትና የማእከላዊ መንግሥት ምስረታ ግንኙነት “Leviathan” ንን የጻፈው ስለ እንግሊዞች የእርስ በርስ ጦርነት የመሰከረውን
ለማመን ያልቻለውን እልቂት ለተከታታይ ትውልድ ለማስተማር ነው። በዓለም ታሪክ ውስጥ ተመሳሳይና የባሱ እልቂቶች ተካሂደዋል።
የሮማን ቅኝ ገዥዎች ግሪኮችን፤ ጣሊያኖችንና ሌሎችን ባላቸው መሳሪያ በገፍ ጨፍጭፈዋል። አቲላ ዘ ሃንና ጀንጅስ ካን ብዙ ሚሊዮን
ሰላማዊ ሰዎች ጨፍጭፈዋል። ቻይናዎች ታላቁን ግንብ የገነቡት ከእልቂት ለመዳን ነበር። ይኼም ሁኖ ቻይና ከውስጥ የእርስ በርስ
ጦርነት አልዳነችም። አገሪቱን እንደገና ለመመስረትና ዘመናዊ ለማድረግ የእርስ በርስ ጦርነት ጡፋል። ብዙ ሚሊዮን ሕዝብ
ተጨፍጭፏል። እንግሊዞች ዓለምን ሲገዙ በአፍሪካ፤ በመካከለኛው ምስራቅና በሕንድ አገር የጨፈጨፉት ሕዝብ ብዛት አይታወቅም።
ብዙ ሚሊዮንና ጭካኔ እንደነበረበት ይታወቃል። ፈረንሳይዎች በአልጀሪያ ሕዝብ ላይ ያደረሱት እልቂት እስከዛሬ ያነጋግራል። ቱርኮች
የጨፈጨፉት የአርመን ሕዝብ ብዛት በሚሊዪን ይቆጠራል። አሜሪካ ግዛቷን ስታስፋፋና ዘመናዊ አገር ስትመሰርት የጨፈጨፈችው
የነዋሪዎቹ ሕንዶች ብዛት በብዙ ሚሊዮን ተገምቷል። ግዛት፤ መሬት፤ ህይወት፤ ስልጣኔ የነበራቸው ሕንዶች አልቀዋል ለማለት
ይቻላል። ስፓኒሾች የላቲን አሜሪካንና የካሪቢያንን ነዋሪ ሕዝቦች ጨፍጭፈዋል። አውሮፓውያን እስከ ሃያ ስድሰት ሚሊዮን የሚቆጠሩ
ጥቁር አፍሪካውያንን ከቤታቸው አስገድደው በባርነት ወስደዋል። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩት በመንገድ ሞተዋል። ዛሬ በደቡብ
ሱዳን፤ በሶሪያ፤ በኢራክ፤ በአፍጋኒስታን፤ በሶማሊያ፤ በዛየር፤ በመካከለኛው አፍሪካ ወዘተ የምናየው የእርስ በርስ ጦርነት ያለፈው
የአገርና የማእከላዊ መንግሥት ዓመሰራረት አሁንም እንደቀጠለ ያሳያል። የቅኝ ገዥነት፤ የአገር አመሰራረት፤ የዘመናዊነት ግንባታ ወዘተ
አወንታዊነት የተለያዩ መልኮች ወስዷል። ይህ በሰላም ቢካሄድ ኑሮ ሁሉም ይደሰታል። ሃቁ አገሮችና ዘመናዊነት የተገነቡት በሰላም
አይደለም። በአብዛኛው የሚታየው ሃቅ በጦርነት፤ በእርስ በርስ ግጭት፤ በአብዮት ወዘተ ነው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነትና
ዘመናዊነት ምስረታ (የአሁኑን ስርዓት ጨምሮ) “አለንጋው” ያልነካው የሕብረተሰብ ክፍል የለም። ቁም ነገሩ ከአለንጋው ላይ ላይ ብቻ
አተኩሮና ለይቶ አንዱን ጥፋተኛ ሌላውን “መልዓክ” ከማድረጉ ላይ አይደለም። ካለፈው ስህተቶች ተምሮ፤ ስህተቶችን እንደ አስፈላጊ
የታሪክ ሂደት አይቶ፤ ተወያይቶና ተቀብሎ እንዳይደገሙና ተከታታይ ትውልድን እንዳይበክል መጣር ነው። ሌሎች አገሮች ያደረጉት
ይኼን ነው። እኛ ወደን ለመጨራረስ ከፈለግን መሳሪያ የሚነግድ ሞልቷል። የዛሬውና የነገው ትውልድ መተላለቅን እንደማይፈልግ
አምናለሁ። የሚፈልገው ፍትሃዊ ስርዓት ነው።
ከውጭ ጠላት ጋርና በውስጥ የተካሄዱ የእርስ በርስ ውጊያዎች ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲጣመር፤ አንዲሰራጭ አድርገዋል።
ይኼንም የሚክዱ አሉ። ልክ ጀርመኖች፤ ጣሊያኖች፤ ቻይኒሶች፤ ናይጀሪያኖች፤ አሜሪካኖች ወዘተ እንዳደረጉት የኢትዮጵያ ብሄራዊ
አንድነትና ዘመናዊነት ግንባታ ሂደት (formation of a multiethnic state into one) በሰላም፤ ያለ ሰው እልቂት ወዘተ
አልተካሄደም። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ዓለም ያላደረገውን ማድረግ ነበረባቸው የሚል የአስተሳሰብ ሕግ አላገኘሁም። ለምሳሌ፤ አገር
ወዳድና ደፋር የነበሩት አጼ ቲዎድሮስ ከዝቅተኛ ቤተሰብ ተነስተው መሳፍንት የበታተኗትን፤ ቀሳውስት የተሳለቁባትን፤ የውጭ አገር
የኃይማኖት ተከታዮች የራሳቸውን ኃይማኖት ሊተኩባት የፈለጓትን፤ ቅኝ ገዢዎች ዓባይን ለመቆጣጠር አሰፍስፈው አይናቸውን
የጣሉባትን፤ በቴክኖሎጅ ኋላ ቀር የነበረችውን፤ ዘመናዊ የወታደር ኃይል ያልነበራትን ኢትዮጱያ አንድና ዘመናዊ ለማድረግ ሞክረዋል።
ይህ ማንንም ኢትዮጵያዊ ያኮራል። እኒህ የኢትዮጵያ ዘመናዊነት አባት የተመሩት በጎንደሬነታቸው ነው የሚል ሰው ካለ ተሳስቷል።
የታላቅነታቸው መለኪያ ኢትዮጵያዊነታቸውና የኢትዮጵያ መሪ መሆናቸው ነው። በጎንደሬነት ክልል መወሰን መለኪያ ከሆነ ሌሎች
አገራቸውን ያስተባበሩ መሪዎች ሁሉ መንደረኛ መሆናቸው ነው። የዘማኒዊዋ ተርኪ አባት ተብሎ የሚጠራው ከማል አታተርክ፤
አንዳንድ ግለሰቦች ልከ አፄ ቴዎድሮስን እንደሰደቧቸው “እብድ ነበር” ብለው የሚዘልፉት የተወለደበት ቴሶሎንኪ ግሪስ አገር ነው።
በአሁን የኢትዮጵያ አገዛዝ ባስቀምጠው “ከሌላ ክልል የተወለደና በማያገባው የገባ” ማለት ነው። አገሩን ዘመናዊ ለማድረግ የተመራበት
ርዮት በተወለደበት መንደር የተወሰነ አይደለም። ታላቁ ማኦ ሲቱንግ የተወለደበትና ያደገበት ጠቅላይ ግዛት ሁናን ነው። ዓመራሩና
“ጨፈጨፈ” የሚባለው ብዙ ሚሊዮን ሕዝብ ተመሳሳይነቱ ከስታሊን ጋር ነው። ሂትለርን ይመስላል ያለ ወዳጅም ሆነ ጠላት
አላገኘሁም። ስምምነት ያለው ማኦ አገሩን ከነበረችበት መከፋፈልና ኋላ ቀርነት አውጥቶ ከዓለም ታላቅ አገሮች አንዷ ለማድረግ ታግሏል
የሚል ነው። ዛሬ ሃውልቱ በቻይና የተከበረ ነው። ቲቤቶችና ሞንጎሎች ወገኖቻችን ጨፍጭፏል ብለው እሱን የሚነቅፍ ሃውልት
በግዛታቸው አልገነቡም። ብዙ ሚሊዮን ቻይኒሶች ስላስገደለ “ጠላት ነው” ብሎ የከሰሰው ዜጋ አላገኘሁም። ማኦ የታገለው ለአካባቢው
(ለመንድሩ) እውቅናና ታላቅነት አልነበረም። ቲቤቶች፤ ሞንጎሎች፤ ካንቶኒሴች፤ ኡጉሮች ወዘተ ሚዛናዊ የሆነ መብትና የኢኮኖሚ ተሳትፎ
ያስፈልጋቸዋል። የቻይና ሕዝባዊ አብዮት ለሁሉም ማገልገል አለበት በሚል ርዮት ነው።
በአገር ወዳዶች የሚመራ ለውጥ መስፈርቱ በመጀመሪያ ህብረተሰቡ የሚያስፈልገውን የኑሮ ችግር ያስወግዳል፡፡ ብዙ የሕዝብ እልቂት
የተካሄደባት ቻይና ቀደምትነት የሰጠችው ረሃብን ከማስወገድ ላይ ነው። ይህ ርእዮት የፕሮፖጋንዳ ብቻ አልነበረም። ሚዛናዊ የሆነ 6
የትምኅርት፤ የመሰረታዊ ኢንዱስትሪ፤ የእርሻና የምግብ ዋስትና ወዘተ ልማት ተካሂዷል። ማኦ ቻይና አንድ ናት። መበታተኗ ደካማ፤
ረሃብተኛና ጥገኛ አድርጓታል የሚል እምነት እንደነበረው ሁሉም ሊቃውንት ይስማማሉ። የዛሬዋ ቻይና ታላቅነት መሰረት የተጀመረው
በድንገት አይደለም። በአገር ወዳድነት፤ ለተጎዳው ሕዝብ ተቆርቋሪነት በማሳየትና ታላቋን ቻይና ለመመመስረት በተደረገ ጥረት ነው።
የወደፊቱ እንዲሻሻል፤ ከዓላማ አንድነት ላይ የሚያተኩር አገር ወዳድና ሁሉን አስተናጋጅና ዲሞክራሳዌ ዓመራር ወሳኝ መሆኑን
በተደጋጋሚ ያሳያል። ለጀርመን፤ ለጣልያን፤ ለቻይና፤ ለናይጀሪያ፤ ለአሜሪካ ወዘተ ብሄራዊ አንድነት፤ የአገርና የማህበረሰብ ታላቅነትና
የኑሮ መሻሻል ወሳኝ ሚና የተጫወቱ መሪዎች ሁሉ የተመሩበት ርእዮት የተለያየ ቢሆንም መድረሻቸውን ያውቁ ነበር። በኢትዮጵያም
ለማህበረሰብ ህይዎት መሻሻል የሚረዳ ራእይና ሁሉን አሳታፊ የሆነ ዓመራር ለብሄራዊ አንድነትና ማንነት ይረዳል የሚል አስተሳሰብና
ለዚህ አስተዋፆ ያደረጉ መሪዎች ነበሩ የሚል እምነት አለኝ። የገሰኛነት ራእይና ዓመራር ከዚህ ይለያል። ጠባብ ነው። ግጭቶች ፈጣሪ
ነው። በሰብአዊ መብት አያምንም። እስካሁን ያለውን እድገት ስናይ፤ የእድገቱ ውጤት ተጠቃሚ ጠባብ ቡድን ነው። አስገደ
ገብረሥላሴ “የህወሓት መሪዎች ፋሺስታዊ ተፈጥሮ ሲጋለጥ” በሚል አርእስት በዚህ ሳምንት ያቀረበው ትንተና በተደጋጋሚ
ያቀረብኩትን፤ በተለይ በ”ድርጅታዊ ምዝበራ” የተነትንኩትን መሰረተ ሃሳብ ያጠናክረዋል። እኛ በሩቅ ሆነን ያላየነውን እርሱ ፊት ለፊት
ባየው ምስክርነት አቅርቦታል። “የሃገራችን ሃብትም በሙስና ተመዝብሮ ውጭ አገር ሰፍሯል…..የኢትዮጵያ ገበሬ የመሬት ባለቤትነት
አጥቷል…የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚደፍር፤ የባህር በር የሌላት ያደረገ ሕገመንግሥት መስርቷል…ትግራይን እንደመደበቂያ ዋሻ
ይጠቀምባታል…ተቃዋሚዎች አማራጭ ሃሳብ እንዳይሰጡ በጠላትነት” ወንጅሏቸዋል፤ “ሃሳቤን ያልተቀበለውን ሁሉ ጥይት አጉርሰው”
በሚል ፈሊጥ ሲገዛ ቆይቷል ወዘተ። የሚያሳዝነው ህወሓት የትግራይ ሕዝብ ባላደረገው ጥፋት፤ በሌሎች ኢትዮጱያውያን ስሌት
“እንዲጠላ” ለማድረግ መሞከሩ ነው። የዚህ ደፋር ኢትዮጵያዊ ትንተና ያስተማረኝ ህወሓት የትግራይን ሕዝብ የማታለሉ እድሜ
እያከተመ መሄዱን ነው። ቀስ በቀስ፤ የትግራይ ሕዝብ “የህወሓት መሪዎችን በእኛ ስም አትነግዱ” እያለ መሆኑን አስገደ ከመቀሌ ሁኖ
የሚይስተላልፋቸው ዘገባዎች ያመለክታሉ። ይህ ክስተተ ኢትዮጵያን በመተባበር ለማዳንና ዲምክራሳዊ ስርዓት ለመተካት ለሚደረገው
ለማይቀር የሕብ ዓመጽ አመልካች ነው።
የኢኮኖሚው ትንተና እንከን የለውም። በ2013 የወጣው የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት ሁለ-አቀፍ የድህነት መለኪያ
ያቀረበው ዘገባ ኢትዮጵያና ኒጀር ድሃ ከተባሉ አስር የአፍሪካ አገሮች የመጀመሪያውን ደረጃ እንደያዙ ያሳያል። ገዢው ፓርቲ ተራው
ኢትዮጵያዊ ሊዳስሰው የማይችል እጥፍ እድገት አለ ይላል። መሰረተ ልማት በሰፊው እንደዘርጋ አያከራክርም። ዋናው መለኪያ ግን
የአብዛኛው ሕዝብ ኑሮ መሻሻል ነው። ዘጠና በመቶ የሚገመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ በኑሮ ውድነት፤ በጠለላ እጥረት ወዘተ ሲማረር
ይታያል። አዳማጭ ግን የለውም። የእድገቱ ውጤት ኪሱን የሚሞላለት ክፍል የገዢው ፓርቲ የበላዮችን፤ ቤተሰቦችንና ወዳጆችን ነው።
የዓባይን ግድብ ጥቅም ከማህበረሰቡ ህይዎት ጋር እንየው የምለው ለዚህ ጭምር ነው።
ከላይ የጠቀስኳቸው አገሮች በውጣ ውረድ የተገኘ ብሄራዊ አንድነት በኢትዮጵያም ተከስቷል። ሆኖም፤ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ብሄራዊ
አንድነት ፍትሃዊ ከሆነ የዘመናዊነት እቅድ ጋር አብረው አልተጓዙም። የማይካደው ሃቅ ግን የአገር ብሄራዊ አንድነትና ደህንነት ከሌለ
ዘላቂነትና ፍትሃዊነት ያለው ልማት መሰረት ለመጣል ያስቸግራል። የኢትዮጵያን ብሄራዊ ግንባታ ለየት የሚያደርገው የአገሪቱ የሕዝብ
ስርጭት በፍትህና በእውነተኛ እኩልነት አለመመስረቱ፤ ተቀናቃኝ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ልዩነቶችን ለፖለቲካ ጥቅም ማዋላቸው
ጭምር ነው። ላወቀበት የሕብ ስርጭት ጥንካሬ እንጅ ድክመት አይደለም። ስርጭቱን ወደ ማህበረሰባዊ አቅም ለመለወጥ ሁሉን
አሳታፊ አመራርና መንግሥት መመስረት ያስፈልጋል። የተማረው ክፍል ሃላፊነት የጎሳ ልዩነቶችን ከማካረር ይልቅ፤ በጋራ እሴቶች ላይ
መረባረብ ነበር። ይሕ በኢትዮጵያ አልሆነም። በሌሎች አገሮች እንደታየው (ናይጀሪያ፤ ጋና) የሕዝብ ስርጭት መሰረታዊ ማነቆ
አልሆነም። እነዚህ አገሮች ብዙ ችግሮች አሉባቸው (ሙስና ለምሳሌ)። ሆኖም ከጎሳ በላይ የዘረጉት የማህበረሰብ መቀራረብ መሰረት
የወደፊቱን ትውልድ እንደሚያገለግለው አልጠራጠርም። በጋና የቮልታ ግድብ ለመላው የጋና ሕዝብ አገልግሎት ውሏል። በኢትዮጵያ
ታሪክ ሂደትም በቀና ለተመለከተው የሕዝብ ስርጭት በቀውጢ ቀን ለህብረት ማነቆ አልነበረም። ለሃገሩ የሚቆረቆር መሪ ሲነሳ ሁሉም
ተባብሮ ኢትዮጵያን ከውጭ ጠላቶች አድኗታል።
ለዚህ ዋና ምሳሌ በብዙ ማስረጃ የተደገፈው በትግራይ ክፍለ ሃገር የተካሄደው የአድዋ ጦርነት ድል ነው። አጼ ምኒልክ የኢትዮጵያ
ብሄራዊ አንድነትና ከዚህ የሚገኝ ጥንካሬ ወሳኝ መሆኑን የተገነዘቡ አስተዋይና በኢትዮጵያ ዘመናዊነት (ቴሌፎን፤ ፖስታና የሃዲድ
መንገድ መገናኛ ፤ ዘመናዊ ትምህርት) ወዘተ የሚያምኑ መሪ ናቸው ለማለት እደፍራለሁ። ከ1857-1879 (ሃያ ሁለት ዓመታት) ባለው
ጊዜ ኢትዮጵያን ለመገንባት ባደረጉት ጥረት በተለያዩ በጥንት ጊዜዎች የነበሩትን ክፍለ ሃገሮች ወደ አንድነት ለመሰብሰብ ሞክረዋል።
ጥረታቸው ስኬታማ የሆነው የኃገሪቱን ባህል በማወቃቸውና አብረዋቸው ሊሰልፉ የሚችሉ ኃይሎችን በውይይትና በድርድር
ማቀራረባቸው ነው። ይህ ሂደት ቀላል እንዳልነበረ አምናለሁ። በሌሎች አገሮች ግንባታ የተከሰተ ሂደት በተመሳሳይ ባይባልም በቅርበት
በአርሲ፤ በሓዲያ፤ በጉራጌ፤ በሊሙ፤ በጅማ፤ በወለጋ፤ በሲዳሞ፤ በቦረና፤ በሃረርጌ፤ በኦጋዴን፤ በኦሞ ሸለቆና ሌሎች ክፍለ ሃገሮች
ከብሄራው ምስረታ ጋር የተያያዘ መተባበርም፤ እልቂትም ነበር። አገር ግንባታ እንዲሁ በምኞትና በሰላም የተካሄደበት አገር በሻማ
መብራት ፈልጎ ለማግኘት የማይቻል መሆኑን አመልክቻለሁ። በየትኛውም አገር ብሄራዊ አንድነት የሠው ህይዎት ዋጋ እንደሚከፈልበት
ሊካድ አይችልም። አሜሪካኖች አገራችውን ሲመሰርቱ ህንዶች ተብለው የሚጠሩትን ነዋሪዎች መጨፍጨፋቸው እስካሁን ያነጋግራል።
ብራዚል፤ ቢያንስ ከአገሪቱ ሕዝብ አርባ በመቶ የሚገመተውን ከአፍሪካ በንግድ “የተሸመተ” የጥቁር ሕዝብ እንደ ባሪያ ቀጥቅጣ ገዝታ
መብታቸውን መቀበል የጀመረችው በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን፤ በተለይ በፕሬዝደንት ሉላ መንግሥት ነው። የአሜሪካ ጥቁሮች
የጥቁር ፐሬዝደንት ቢመረጥም፤ አሁንም ሙሉ መብታቸው ስኬታማ አልሆነም። ዘረኛነት በገቢ ልዩነት፤ በአመለካከት፤ በእስር ቤት
በሚገኘው የጥቁር ወንድ ሕዝብ ብዛት፤ በትምኅርት፤ በቤት ባለቤትነት፤ ወዘተ በግልፅ ልዩነትና አድልዎ ይታያል። ጥቁሮች 7
ከማንኛውም የአሜሪካ ሕዝብ በበለጠ ደረጃ የበታችነት እርከን ይዘው ይገኛሉ። እውነተኛ እርቅና ሰላም የተካሄደባት ደቡብ አፍሪካ
ሁሉን አቀፍ መንግሥት ብታቋቁምም፤ በገቢ፤ በሃብት፤ በተፈጥሮ ሃብት የበላይነት ወዘተ አንጋፋውን የያዙት ነጮች ናቸው። ኢትዮጵያ
ተመሳሳይ የሰላምና የእርቅ ድርድር ማካሄድ እንዳለባት አምናለሁ። ያለፉ ችግሮችን እንደሌሉ ደብቆ ጠንካራ አገርና ጠንካራ
ሕብረተሰብ ለመገንባት አይቻልም። ሆኖም ፍትህ-ርትእ በአጭር ጊዜ ስኬታማ አይሆንም። በኢትዮጵያ አደጋና ግጭት ፈጣሪ የሆነ
የገቢ፤ የሃብትና የኑሮ ልዩነቶች እንድሌሉ አድርጎ መቀበል ለህሊና ይቀፋል። ድሃና ኋላ ቀር ለሆኑ አገሮች ዘላቂነትና ፍትሃዊነት ያለው
እድገት ወሳኝ መሆኑን በተደጋጋሚ በጥናት በተደገፉ ትንተናዎች አሳይቻለሁ። ይህ የኑሮና የእድገት ልዩነት በሚዘገንን ደረጃ
በኢትዮጵያ ይታያል። ያለመሰረታዊ ለውጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ መዋቅራዊ ችግሮች ሊፈቱ አይችሉም። ገዢው ፓርቲ ማንም
በማያምነው ደረጃ አስደናቂ እድገት አለ። ረሃብ የለም። የነፍስ ወከፍ ገቢ በማደግ ላይ ነው። የዛሬ አንድ ዓመት ኢትዮጵያ አብዛኛዎቹን
የተባበሩት መንግሥታት የተስማማባቸውን የሚሊኒየም እድገት ግቦች ትቀዳጃለች ወዘተ ይላል። ቢሆን ሁላችንም ደስ ይለናል።
አብዛኛዎቹ፤ ለምሳሌ፤ የሴቶች እኩልነት፤ የንፁህ ውሃ አቅርቦት፤ የረሃብ መወገድ፤ የፍጹም ድህነት ቅነሳ ስኬታማ አይሆኑም።
መሰረታዊ የስርዓት ለውጥ በይደር ከታየ ሁኔታው ይባባሳል። የገቢ፤ የሃብትና የኑሮ ልዩነት መዋቅራዊ ከሆነ ልክ እንደ ብራዚል፤
አሜሪካ፤ ደቡብ አፍሪካ ወዘተ በቀላሉ አይቀየርም። ቱኒሺያና ሌሎች አገሮች እንደሆነው የሕዝብ አብዮት ያስፈልገዋል።
የአጼ ምኒልክ የአገር ግንባታና የማአህበረሰብ ማቆራኘት ተቀዳሚነት የውጭ ጠላትን ለመከላከል ረድቷል። የአድዋ ጦርነት ድል
የተሳካው በአጼ ምኒሊክ ጥበባዊ ዓመራር፤ በኢትዮጵያ ስብጥር ሕዝብ ጥረት ህብረትና መስዋእት ነው። ጥበባዊ ዓመራር ያልኩበት
ምክንያት፤ አፄ ምኒልክ አግባብ ካላቸው የአገሪቱ ታዋቂዎች ጋር የመመካከርና የመግባባት እውቀት ስላሳዩ ነው። የቸክ ተወላጅ
የነበረው ኢትዮጵያዊ አዶልፍ ፓርለሳክ “የሃበሻ ጀብዱ” በተባለው መፅሃፉ አመራራቸውን እንዲህ ሲል ጠቅሶታል። “በአምባላጌ ተራራ
ወገብ ላይ ጉብ ካለችው ዋርካ ስር ራስ ካሳና በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል አሉ የሚባሉ ከፍተኛ ሹሞች ዙሪያውን ገጥመው
ተቀምጠዋል። በዚችው ዋርካ ስር ከዛሬ አርባ ዓመት በፊት ታላቁ የጦር ሰው እምዪ ሚኒልክም ተቀምጠው ከሹማምንቱ ጋር እንዴት
ወደ አድዋ መዝለቅ እንዳለባቸው ለድል ያበቃቸውን የጦር እቅድ መክረውና ነድፈው አውጥተዋል።” አስቀድሞ መመካከርና እቅዱን
ሰፋ ያለ ባለቤትነት መስጠት የዓመራር ጥበበኛነትን የሚያሳይና ወሳኝ የዓመራር ዘዴ መሆኑን ተረድተው ኢትዮጵያ በጥቁር ሕዝቦች
ታይቶ የማይታወቅ ፀረ-ቅኝ ገዢዎች ድል ለመጎናፀፍ ችላለች። ዓመራሩ ብሄር/ብሄረሰብ/ኃይማኖት/ጾታ/እድሜ/ሃብታምና ድሃ ብሎ
ቢለይ ኑሮ፤ የአድዋ ድል አይታሰብም ነበር። አዝማቾቹ አጼ ምኒልክና ጀግናይቱ እቴጌ ጣይቱ ቢሆኑም፤ የጦር መሪዎቹና ሰራዊቱ
ከሁሉም ብሄር/ብሄረሰብና ኃይማኖቶች የተወጣጡ ናቸው። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ፤ ራስ ወሌ ብጡል፤ ልዑል ራስ መኮነን፤ ራስ መንገሻ
ጉግሳ፤ ራስ መንገሻ፤ ዋግ ስዮም ጓንጉል፤ ንጉስ ተከለኃይማኖት፤ ወዘተ (ደራሲ ተክለ ፃድቅ መኩሪያ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ-- ከአፄ
ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ)። እነዚህ የጦር መሪዎች በሚኖሩበትና በሚመሩት ክፍለ ሃገር ያለውን ሕዝብ ስሜት ቀስቅሰው
ለሃገሩ እንዲዋጋና ጠላቱን እንዲያሸንፍ አድርገዋል። የአድዋ ድል የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድል መሆኑን በማያሻማ ደረጃ
አስመስክረዋል። ለዛሬው ውጥረት ዋና ትምኅርት ነው የሚል ግምት አለኝ። ግብጾች ከሁሉም በላይ የሚፈሩት የኢትዮጵያን ሕዝብ
ብሄራዊ አንድነት እንደሆነ ተረድቻለሁ። ፍትሃዊ ስርዓት ከተመሰረተ ግብጾች ኢትዮጵያን ለማጥቃት አይችሉም። ደጋግመው ሞክረው
አልተሳካላቸውም። ኢትዮጵያን የሚያስጠቃት አምባገነናዊ ፀረ-ሕዝብ፤ ፀረ-ዲሞክራሲ አገዛዝና በብሄር/ብሄረሰብ/ኃይማኖት መከፋፈል
እንደሚሆን አልጠራጠርም። ህወሓት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ ከጠላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር
ለመወያየት ወደ አዲስ አበባ ከመሄዱ በፊት ስድስት የድህረገጽና ሌሎች ጋዜጠኞችን፤ መላውን የሰማያዊ ፓርቲ ዓመራር ሰብስቦ
ሲያስር በራሱ ዓመራር እምነት እንደሌለውና የመለስ ዜናዊይን አምባገነናዊ አመራር እንደሚከተል ያሳያል።
የአድዋ ድል ከአባይ ወንዝ የኢትዮጵያ ይገባኛልነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው
ቁም ነገሩ ከአድዋ በፊትና ከአድዋ በኋላ የታዩ ድሎች የኢትዮጵያውያን ሁሉ ድሎች መሆናቸው ነው። የታሪክ ክህደት ይጎዳል የምለው
ለዚህ ነው። ብንወድም ባንወድም፤ ጦርነት ለስብጥሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግንኙነት፤ መተባበር፤ መተማመን፤ እርስ በርስ መጋባት፤
ብሄራዊ አንድነትን ማጠንከር ወዘተ ከፍተኛ አስተዋዖ አድርጓል። በክፉ ጊዜ አብሮና ተደጋግፎ የቆመ ሕዝብ እትብት በቀላሉ ሊፈርስ
አይችልም። በተመሳሳይ፤ በሰላም ጊዜ የእድገት ተጠቃሚ የሆነ ሕብረተሰብ ለክፉ ጊዜ ምሰሶ ነው። አደጋው ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ
የእድገቱ ተጠቃሚ አለመሆኑ ነው። ጊዜ ይወስዳል እንጅ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚጣጣሩ ኃይሎች የፈጠሩት አዲስ የሕዝብ ከፋፋይ
ታሪክ ራሳቸውን ያጋልጣቸዋል። አሰገደ ያቀረበው ትንትና ይኼን ያመለክታል። ዶር ኃይሌ ወልደ ሚካኤል “የኢትዮጵያ ሕዝብ
መስተጋብር” በሚል አርእስት በ1993 ዓም ያበረከተው ትንተና የኢትዮጵያ ሕዝብ ግንኙነት ጠንካራና የቆየ መሆኑን ያመለክታል።
“የአክሱም መንግሥታት በዮዲትና በቤጃዎች ሲደመሰስ፤ አክሱማውያን ወደ ሰመኔንና መሃል ኢትዮጵያ እንደፈለሱና ኑሮ እንደመሰረቱ
ግልፅ ነው። የዛጉዪ መንግሥት ሮሃ ላይ ከተመሰረተ በኋላ፤ የአክሱማውያን እደ ጥበበኛነትና ሌሎች አገልግሎት ሰጭ ሰዎችን ወደ ሮሃ
ሰዷል። የሸዋ መንግሥት በጀመረው የመስፋፋት ፕሮግራም ምክንያት ቋሚ የጦር ሠፈሮችና የአካባቢ ጋሻ ጃግሬዎች በሃረር፤ በሶማሌ፤
በአፋር፤ በዳዋሮ፤ በባሌ፤ በሃዲያ፤ በከምባታ፤ በወላይታ፤ በጋሙጎፋ፤ በሸዋ፤ በሲዳሞ፤ በዳሞት፤ በእናርያ፤ በጉራጌ፤ ወዘተ
እንደነበሩትና በዚህም ምክንያት የሕዝብ መስተጋብር እንደተከናወነ ግልፅ ነው።” የኦሮሞ መሪዎች በጎንደር ከፍተኛ ሚና
እንደተጫወቱ፤ ከአካባቢው ሕዝብ ጋር እንደተዋለሁ የአንደኛ ክፍል ተማሪ ሆኘ ተመሪያለሁ። የህወሓት/ኢህአዴግ ዓመራር ይኼን
መስተጋብር ክዷል፤ አፍርሷል። ብናውቅበት ከላይ የጠቀስኩት የታሪክ አመሠራረት ሂደት የታላቅነት ምልክቶ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ስርጭት ምን ቁም ነገር አለው? ለአሁኑ የጎሳ ክልል ውጥ እንቅጥ (“የአክሱም ኃውልት ለወላይታው ምኑ ነው”)
ለሚለው የልብ ወለድ አባባል መልስ የሚሰጥ ይመስለኛል። “ዛሬ ድረስ ወላይታ ውስጥ ትግሮ (ትግሬ)፤ ቡልጎ (ቡልጋ)፤ መንዞ 8
(መንዝ)፤ ቄሶ (ቄስ)፤ መራቤት (መርሃ ቤቴ)፤ ወዘተ የሚባሉ ጎሳዎች እንደሚገኙ አቶ ኃይለጊዮርጊስ አጀቦ ገልጸውልኛል። በአጼ
ምኒልክ የተሸነፈው የወላይታ ሥርው መንግሥት የትግሬ ዳይናስቲ በመባል ይታወቃል። …..ሃዲያ ውስጥ ጋስ አማራ (የጥንት አማራ)
የሚባል ጎሳ እንደነበር ይታወቃል። የጉራጌ ሕዝብም በአመዛኙ የአማራ፤ የትግሬ፤ የእናርያ፤ የሲዳማ፤ የሃረሬ፤ የኦሮሞና የሃድያ ሕዝቦች
መስተጋብር ውጤት እንደሆነ አናውቃለን። ባሌ ውስጥ የነበረው የሸዋ መንግሥት ሰራዊት በግራኝ መሐመድ ጦር ከተመታ በኋላ፤
እዚያው ተቆርጦ እንደቀረና የፋሲል ዘሮች በሚባል የሚታወቁ ጎሳዎች እንደመሰረተ ታውቋል” ወዘተ ወዘተ። እንደዚህ ለብዙ
ትውልዶች የተሳሰረን ሕብረተሰብ ለፖለቲካ የበላይነት መለያየት ክህደትና ወንጀል ነው። በአብዛኛው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጦርነት፤
በንግድ፤ በስራ፤ በተፈጥሮ ሃብት፤ በተለይ ለም መሬት ፍለጋ፤ በኃይማኖት ስርጭት ወዘተ ተደባልቋል። ተጋብቷል፤ ተዋልዷል።
የትግራይ ሕዝብ የአክሱም መንግሥታት ከወደቁ በኋላ በመላው ኢትዮጵያ ተሰራጭቷል። ጎንደር ወጣት ሆኘ በትምኅርት ገበታ ላይ
ሳለሁ፤ የዘመናዊ ኢኮኖሚው የበላዮች ኤርትራውያንና የትግራይ ተወላጆች ነበሩ። የእነሱን ስርጭት ያገበ ወይንም ይህ ተገቢ አይደለም
ያለ ግልሰብ ሰምቸ አላውቅም። በሌሎችም ክፍለ ሃገሮች የነበረው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አለመሆኑን ዶር ኃይሌ ወልደሚካኤል
ያቀረበው ሰፊ ጥናት ያሳያል። ልክ እንደ ትግሬው፤ አማራው በአጼ ምኒልክና ከዚያ በፊት በነበሩ ነግስታት በየቦታው ተሰራጭቷል።
ኦሮሞው ከደቡብ መጥቆ መሃል አገሩንና ሰሜኑን ተዋግቶ ሌላውን ሕዝብ ገዝቷል፤ ከሌላው ጋር ተቀላቅሏል። ኢትዮጵያና
ኢትዮጵያዊነት የሁሉም መታወቂያና የሁሉም መኩሪያ ሊሆኑ ይገባቸዋል ማለት ነው። ኢትዮጵያዊ ማነው የሚለው በተማሪ እንቅስቃሴ
የተጀመረው ክርክር ታሪክን እንደ ማስረጃ ለተቀበለ ሁሉ መልስ አለው። የባህል፤ የቋንቋ፤ የልምድ ወዘተ ልዩነቶች መኖራቸው
አይካደም። እነዚህ በሕግ መከበር አለባቸው። አከራካሪው የማይታረቀው የብሄር/ብሄረሰብ ልዩነት ከየት ላይ እንደሆነ አመርቂ መረጃ
አለመኖሩ ነው። የማይታረቁ ልዩነቶች የተባለው ሆነ ተብሎ በጎሰኞች ለፖለቲካና ለኢኮኖሚ የበላይነት የተፈጠሩ የሚመስሉት በዚህ
ምክንያት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ ውህደት እንደነበረው የታሪክ ባለሞያዎች፤ ለምሳሌ፤ አንጋፋው የታሪክ ሊቅ አቶ
ተክለፃድቅ መኩሪያ----የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፂ ልብነድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ፤ አፄ ቴዎድሮስና የኢትዮጵያ አንድነት፤ ዶር ላጲሶ ጌ.
ደሌቦ፤ የኢትዮጵያ ረጅም የሕዝብና የመንግሥታት ታሪክ ወዘተ በሚገባ አቅርብውታል።
ታሪካዊ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተደረገ ስልታዊ ውሳኔ
የአባይ ረጅም ታሪክ ከኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ጋር የተያያዘና ብዙ ደም የፈሰሰበት፤ ብዙ ሃብት የባከነበት ነው። በጽሁፎች ከታወቀበት
ጀምሮ እስከ ዘመነ ክልል ድረስ የዚህ የወንዞች ወንዝ የጅዖግራፊ ወይንም ግዛታዊ አቀመማጥ አላሻማም ነበር። እንግሊዞች፤ ጣልያኖች፤
አሜሪካኖች፤ ግብፆችና ሌሎች ታላቁ ዓባይ፤ ዛሬ የተሃድሶ ግድብ የሚሰራበትን ሸለቆ ጨምሮ በጎጃም ክፍለ ሃገር እንደሚገኝ
ደጋግመው ያስታውሱናል። ሃጋይ ኤርሊች እንዲህ ብሏል። “አፄ ዮሃነስ ለማእከላዊ መንግሥት ብዙም ደንታ አልነበራቸው። ሆኖም
በኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት፤ ሏአላዊነትና ነጻነት ሙሉ በሙሉ ያምናሉ። የኢስማኤልን ጦር ተዋግተው ድል አድርገዋል። ለኢትዮጵያ
አንድነት ተዋግተው ሞተዋል። የክፍለ ኃገሮችን የራስ አስተዳደር….የወቅቱ የጎጃም ንጉስ የዓባይ (Blue Nile) የበላይ መሆናቸውን”
ወዘተ ተቀብለዋል። በ1933 ዓባይን ለመሻገር የሚያስችል ዘመናዊ ድልድይ ከመሰራቱ በፊት፤ በተለይ በክረምት፤ “ዓባይ የሚገኝበት
ጎጃም ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ክፍለ ሃገሮች በተፈጥሮ አጥር የተከለለ፤ ራሱን የቻለ ነበር።” ለነዋሪዎቹ ያለውን ጠቃሚነትና ምንነት
ሲገልጽ፤ እንዲህ ብሏል። “The people of Gojjam considered the Abbai a protector and a sysmbol of their local
autonmy. They often called themselves the river’s children and sang about its bounty…As long as Abbai is our
river whoever rules is not our concern. Yohannes legitimized Gojjam’s autonomy by recognizing the head of the
leading local Amhara family as Negus, or King… ዓባይ ተጠቫቫቂያችን ነው። እኛ የዓባይ ልጆች ነን። ዓባይ የእኛ መሆኑ
እስከተረጋገጠ ድረስ ማንም ቢገዛ ግደ የለንም።” ይኼን በማጤን “አፄ ዮሃንስ በአካባቢው የሚገኙትን ተቀባይነት ያላቸው ኣንድ
የታወቀ የአማራ ሕዝብ ዘርፍ ወይንም ክፍል መሪ ንጉስ አድርገው ሾሟቸው” ይላል። ህወሓት/ኢህአዴግ ይኼን ታሪክ ያውቃል።
አዲሱን የክልል አወቃቀር ሲቀይስ ይህን በብዙ ማስረጃ የተገፈ የዓባይ ግዛታዊ አቀማመጥ ሆነ ብሎ ለውጦ ዛሬ ግድቡ በሚሰራበት
ክልል በቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ ሆኗል። የቤኒ ሻንጉል ጉሙዝና የጎጃም/ጎንደር ሕዝብ የተቆራኘ የመደጋገፍ ታሪክ አለው። በጀርባው ሌላ
አጀንዳ ከሌለ በስተቀር የዓባይ ግድብ ለእነዚህ አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም መዋል አለበት።
የአካባቢዎቹን ወንድማማች/እትምማች ሕዝቦች የሚያጋጭ መሆን የለበትም። ይኼን ሊታደግ የሚችለው ሕዝቡ ነው።
ህወሓት የአባይን ባለቤትነት ካመነ የኢትዮጵያን ታሪክና ብሄራዊ አንድነት፤ የሕዝቧን ሉአላዊነትና ትሥስር መቀበለ ግዴታ
ይሆንበታል። የስርዓት አቀራረፁ ከዚህ የተለየ ነው። መለስ ዜናዊ የድርጅቱን አቋም ጸንሶ የመራውና ከስልጣን ያደረሰው ህወሓት
የተቀበለው የኢትዮጵያ አመሰራረትና ግዛታዊን አንድነት ታሪክ ሂደት እንደሌሎች ጥንታዊ አገሮች (ቻይና ጥሩ ምሳሌ ናት) ውጣ
ውረድ ያለበት ሆኖ፤ ተከታታይነቱ የማያሻማ መሆኑን ፈጽሞ ያልተቀበለ ድርጅት ነው። ሌላው ቀርቶ የአረብ ሊቃውንትና ታዛቢዎች
የተቀበሉትን ክዷል። ለምሳሌ፤ “The Beautiful Daimonds in the History of Ethiopians, Cairo, 1902-1903,” አህመድ አል
ሂፍኒ አል ኪናይ የዓረብ ምሁራንና ጥቂት የአውሮፓ ምሁራን ስለ ኢትዮጵያ ጥንታዊነት የጻፉትን ዘርዝሯል። ዋናው ነጥቡ ኢትዮጵያ
ታላቅ የክርስቲያን አገርና የእስልምና ተከታዮችን ተቀብላ ያስተናገደች ወዳጅ አገር መሆኗን አስምሮበታል። “የእስልምና ኃይማኖት
ተከታዮች የኢትዮጵያ ባለውለታ ናቸው። የኢትዮጵያን ታሪካዊ ሚና፤ ግዛታዊ አንድነትና ሉዓላዊይነት መቀበል የተቀደሰ ተግባር ነው”
ይላል። ለማጥበቅ፤ “ሃበሻዎች እናንተን እስካላስቸገሩ ድረስ በነጻነታቸው እንዲኖሩ ተዋቸው። May God let it be that Ethiopia
will stay well as long as this book (a Quaran he is said to have hidden from his people) stays with them).”
የህወሓትን የታሪክ ክህደት በግልፅ የሚያሳይ ሌላ ነጥብ አቅርቧል። “In fact, if you look at the history of the nations,
especially those situated in close proximity to the Center of the Islamic Religion, you will not find any state that 9
has kept its internal independence and its freedom from foreign control but Ethiopia, from the beginning of Islam
to the present. የአገሮችን ታሪክ ስናይ፤ በተለይ የእስልምና ኃይማኖት መዲና ወደ ሆነው ማእከል፤ ኢትዮጵያ ራሷን ከውጭ ወረራ
የተከላከለች ብቸኛ ነጻ አገር ናት።” የእስልምና ኃይማኖት ተከታይ የሆኑ አገሮች ተመሳሳይ የነጻነት ታሪክ የላቸውም ማለቱ ነው። ይህ
የኢትዮጵያውያን አኩሪና በራስ የመተማመን ታሪክ የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች እንዲሰደዱ ሲገደዱ “አይዟችሁ፤ ኑ፤
እናስተናግዳችኋለን፤ እናንተም ወንደሞቻችን ናችሁ” ብላ የተቀበለቻቸው አገር ኢትዮጵያ መሆኑን ያሳያል። የህወሓትና ለሌች ጎሰኞች
ለዚህ ከፍተኛ ዋጋ አልሰጡትም።
ይኼም ሆኖ የፖለቲካ ኢስላም መሪዎችና መንግሥታት ለኢትዮጵያ ሰላም ሰጥተዋት አያውቁም። በፍጥነት እንደ ጃፓን ለማደግ
የምትችል አገር ያላደገችበት ዋና ምክንያት የውጭ ከበባው ተከታታይ ስለሆነ ነው። በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን የዚህ ዋና
ተጠቃሚዎች ሻቢያ፤ ህወሓትና ዛሬ ለመገንጠል ወይንም የቀረችውን ኢትዮጵያ ሰላም ለመንሳት የሚጣጣሩ ኃይሎች ናቸው። የዓረብ
መንግሥታትና ሌሎች ኃያላን ለሻቢያና ጉልምስና ለሰጠው፤ ወሳኝነት ሚና ለተጫወተው ተባባሪ ለህወሓት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ
ከፍተኛ የቁሳቁስ፤ የዲፖላማሲ፤ የመረጃ፤ የሰብአዊ እርዳታ፤ የስለላ፤ የመጠጊያና ሌላ ድጋፍ ባይሰጡ ኖሮ ኢትዮጵያ ተበታትና የባህር
በሯ አይዘጋም ነበር። የህወሓት ዓመራር የሻቢያን ምኞት ስኬታማ ለማድረግና ጎሳዊ ስርዓትን ለመመስረት አመቻች ለሆኑ እቅዶች
ቅድመት ሰጥቷል። ከዚህ ዋናው የስነ ልቦና ጦርነት ማካሄድ ነበር። ታሪክን እንዳልነበረ ማድረግ የስነልቦና ጦርነት አካል ነው። ይኼን
ጦርነት ከላይ ከተጠቀሰው ከአል ኪናይ መጽሃፍ አንጻር ብቻ ብናየው (ፍትህ የሚከተል የዓረብ ምሁር ስለሆነ) በታሪክ በራዢዎችና
በኢትዮጵያ የታሪክ ሂደት ላይ ያለውን ከፍተኛ ልዩነት እናያለን። ይህ ሆነ ተበሎ የተፈጠረ በሕዝብ መካከል የማይታረቅ ልዩነት
ለኢትዮጵያ የወደፊት ታላቅነት ብቻ ሳይሆን ህልውና በጣም አደገኛ እየሆነ ሂዷል። ጸሃፊው የአድዋን ድል ለተጎናፀፉት ለአፄ ምኒልክ
ያለውን አድናቆት፤ ማለትም፤ ጎሰኞች አሉንታዊ ትርጉም የሰጡትን፤ በሰፊው ይገልጻል። “ይህ ድል በአውሮፓውያን አእምሮ በማይረሳ
ደረጃ ተቀርጿል። ለአፄ ምኒልክና ለኢትዮጵያ ከፍተኛ አድናቆት ተክሏል።” ጎሰኞች እንወክለዋለን የሚሉት ሕዝብ ያስገኘውን ድል
አልተቀበሉም። በተመሣሳይ፤ የሶሪያዊው ሳዲክ አል ሙአያድ አል አዝም “The Voyage to Ethiopia,” በተባለው መጽሃፉ ወደ ሃረር
ተጉዞ በዚያ ጊዜ የክፍለ ሃገሩ የበላይ የሆኑትን ራስ መኮነንን አነጋግሮ የእስልምና ተከታዮች በሰላምና በክብር ከክርስቲያን ወገኖቻቸው
ጋር መኖራቸውን መዝግቧል። “ኢትዮጵያ የክርስቲያን ኃይማኖት አገር ናት። ፍትሃዊነት ያላት ናት። የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮቿን
እንደሌሎቹ ታስተናግዳለች” ወዘተ ብሏል። “አፄ ምኒልክን ባነጋገርኩበት ወቅት፤ በኢትዮጵያና በእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ዓለም
መካከል ያለው ግንኙነት ጥሩ” መሆኑን፤ “የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ሲሰደዱ ኢትዮጵያ መጠጊያ የሰጠች” መሆኑን ነገርኳቸው
ይላል። ይኼን ሲሰሙ አፄ ምኒልክ ደስ እንዳላቸውና “እኔ የእስልምና ተከታዮችን እንደሌሎች ኢትዮጵያውያን ነው የምቆጥራቸው።
እንደሌሎቹ አፈቅራቸዋለሁ” ካሉ በኋላ “በኢትዮጵያና በእስልምና ኃይማኖት አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት በመከባበር እንዲቀጥል”
ያላቸውን መንግሥታዊ አቋም ገልጸዋል። ጸሃፊው ወደ አገሩ ተመልሶ ለሳቸው ያለውን አድናቆትና የኢትዮጵያን የመልካም ጉርብትና
አቋም አስራጭቷል።
ቁም ነገሩ ሶስት ነው። አንድ፤ ጥቂቶችም ቢሆኑ መልካም ዓመለካከት ያላችው የዓረብ ምሁራን የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት፤
ሉዓላዊነትና ረጂም ታሪክ ተቀብለዋል። ሁለት፤ ኢትዮጵያ ለእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች መጠለያ እንደሰጠችና በፍትህ
እንደምታስተናግድ አረጋግጠዋል። ሶስት፤ የዓረብ አገሮች የኢትዮጵያን ነጻነት፤ ዘላቂ ጥቅምና ሏአላዊይነት እንዲቀበሉ የሚል መልእክት
አስተላልፈዋል። የዓረቡ ዓለም ስለ ኢትዮጵያ ማንነት እንዲያውቅ ያደረጉት ጥረት ከፍ ያለ ነው። የመጨረሻው ነጥብ የተከታታይ
ኢትዮጵያ መንግሥታት አቋም መሆኑና ቢያንስ የእስልምና ኃይማኖት ከተመሰረተበት በኋላ እውቅና ማግኘቱ ከፍተኛ በረከት ነው። አፄ
ቴዎድሮስና አፄ ዮሃንስ ተዋግተው መስዋእት የሆኑበት እሴት ተመሳሳይ መሆኑን አምናለሁ። ህወሓትና ሌሎች ጎሰኞች ይኼን
አልተቀበሉም። የታሪክ ብረዛ መመሪያ የተሰጠው በህወሓት “አባት መስራቾችና መሪዎች” ነው። ጥያቄው ዓረቦች የኢትዮጵያን
ተከታታይ ታሪክና ጥቅም እውቅና ሲሰጡ ህወሓት ለምን ካደ? የህወሓትና የሌሎች ጎሳዊ ፓርቲ መሪዎች፤ በተለይ አገሪቱን ከሃያ
ዓመታት በላይ በበላይነት የመራው መለስ ዜናዊ ስለ ኢትዮጵያ ታላቅነት ለመጻፍ ያልቻለውና በጥላቻ ግንዛቤ ላይ የተመሰረተ የጎሳዎች
ክልል ያቋቋመበት ዋና ምክንያት ምንንድን ነው? የህወሓት “አባት መስራቾች በመገንጠል” የሚያምኑ ከሆነ ለሁሉም ብሄራዊ ክልሎች
ይኼን መብት መስጠት የተሳናቸው ለምን ይሖን? የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ በግልፅ ሳይወያይበትና ድምጹን ሳይሰጥበት ኤርትራ
የመገንጠል መብት አላት፤ ኢትዮጵያ የባህር በር መብት የላትም ብሎ ሲወስን የምን መስፈርት ተጠቅሞ ነው?
መለስ ዜናዊ “የኤርትራ ህዝብ ትግል ከየት ወዴት” በተባለው የአቋም መጽሃፉ እንዲህ ሲል አዎንታዊነት ሰጥቶታል። “የዛሬይቱን
ኢትዮጵያ ከ3000 ዓመታት ዕድሜ ያለው የጋራ ታሪክ የነበራትና ያላት አገር አይደለችም። የኢትዮጵያ ታሪክ በአንድ ማእከላይ
መንግስት በመተዳደር በሃገር ደረጃ መቆም ከጀመረችበት ከዳግማዊ ሚኒሊክ የንግስና ዘመን ወዲህ የመቶ ዓመት እድሚ አይሞላም።”
የኤርትራና የሌሎች ክልሎች ጥያቄ የቅኝ አገዛዝ ጥያቄ ነው በሚል አቋም ተወሰደ ማለት ነው። ይኼ አቋም ህወሓት ስልጣን ከያዘ
በኋላ የሚወስደውን ውሳኔ አስቀድሞ አመቻችቷል። “የኤርትራ ጥያቄ በታሪካዊ፤ ህጋዊና ፖለቲካ-ኢኮኖሚ ትንታኔ አኳያ ሲታይ ይህን
የቅኝ ግዛት ጥያቄ ለመሆኑ አያጠያይቅም። ሆኖም፤ ይህን የቅኝ አገዛዝ ቀንበር መደምሰስ እንደ ዋነኛው ዓላማው አድርጎ የተነሳና
የሚካሄድ ትግልም ፍትሓዊና ሊደገፍ የሚገባውም ይሆናል። ….ይህ ትግል ምንም እንኳን ሌላ ተጨማሪ ጠቀሜታን ባያስገኝም ቅሉ
በኤርትራ ጭቁን ሕዝብ ጫንቃ ላይ ተጭነው ከሚገኙት የተለያዩ ጭቆናዎች መካከል አንደኛውንና ከፍተኛውን በማስወገድ የኤርትራን
ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽልና መብቱን የሚያስከብር በመሆኑ ፍትሃዊና የሚደገፍ ይሆናል።” ከሶስት ሽህ ዓመታት በላይ እውቅና
የነበራት፤ ብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የሞቱላት ኢትዮጵያ አሉታዊ በሆነ መንገድ የመቶ ዓመታት ግዛታዊ አንድነትና ሏአላዊይነት 10
እውቅና ብቻ እንዲኖራት ተፈረደባት። ህወሓት በኤርትራና በሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ሲወርድ ሲዋረድ የነበረውን ግንኙነት
እንዳልነበረ አድርጎ ኤርትራን ከኢትጵያ አስገነጠለ። የዚህ ጎጅ ውሳኔ ቢያንስ የሚከተሉትን ጉዳቶች አስከትሏል፤
አንድ፤ መለሰ የሽግግሩ መንግሥት ፕሬዝደንት ሆኖ ሲመራ የመጀመሪያ ስራው አድርጎ የወሰደው ቃል የገባበትን የኤርትራን
መገንጥለ ከስራ ላይ ማዋል ነበር። በDecember 13, 1991, ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሃፊ ሃቪየ ፔሬዝ ዴ ኹያ “ሰላሳ
ዓመታት የወሰደው የእርስ በርስ ጦርነት በሰላም እንዲያልቅ ስለተወሰነ፤ የተባበሩት መንግሥታት የኤርትራን መገንጠል
ለማመቻቸት አግባብ ያለውን እርዳታና ድጋፍ እንዲሰጥ” የሽግግሩ መንግሥት እንደተስማማ ገለፀ። “ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ”
እንደሚካሄድ አስታወቀ። በቅድሚያ የተስማማበትንና የወሰነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይወያይበትና ድምፅ ሳይሰጥበት
ስኬታማ አደረገ። የኢትዮጵያ የባህር በር ይገባኛልነት (Legitmacy and primacy) ከዓባይ ይገባኛልነት የበለጠ እንጅ ያነሰ
አይደለም። ለዚህ ከኔ የበለጠ ለመናገር የሚችሉት የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት ሲታደጉ ያለፉ አገር ወዳዶች ናቸው። “አይ
ምፅዋ/ሞት የተፈረደባቸው አስራ ሰባት ሺህ የኢትዮጵያ ሠራዊት” በሚል አርእስት የብእር ስሙ ታደሰ ቴሌ ስልቫኖ የተባለ
በውጊያው የተሳተፈ ደራሲ የካቲት 9, 1982 ዓም የስድስተኛው ጦር አዛዥ ጀኔራል ተሾመ ተሰማ ጦራቸውን ሰብስበው
የተናገሩትን ተከታታይ ትውልድ ሊያውቀው ይገባል። የሻአቢያን አዲስ ጉልበት ካሰሱ በኋላ እንዲህ አሉ። “እኔ
የሚፈለግብኝን አደራ ተወጥቻለሁ። ከጥር 30 ቀን 1982 እስከ ዛሬ የካቲት 9, 1982 ሞት ሽረት ትግል አድርጌአለሁ።
የሻእቢያን የጥፋት ዓላማ ለመግታት ያላደረግኩት ጥረት የለም። ከዚህ በኋላ ግን የራሴን ህይዎት በክብር ከማጥፋትና
ለኢትዮጵያ ጀግኖችና ታሪክ ፀሃፊዎች ታላቅ ተምሳሌት ከመሆን ሌላ አማራጭ የለኝም።” ይህን ጀግንነት ተናግረው
አላቆሙም። ዋናው ለዚህ ያደረሳቸው ተልእኮ ሆኖ አገኘዋለሁ። “በዚች የኢትዮጵያ ሕዝብ የባህር በርና ዓለም ዓቀፍ ወደብ
በሆነችው በምፅዋ ከተማና በቀይ ባህር ጠረፍ ላይ ቆሜ ሽጉጤን ለመጠጣት ዝግጁ ሆኜአለሁ። በእውነት እኔ ዛሬ በሞት
ብሸነፍም በታሪክና በመጭው የኢትዮጵያ ትውልድ ፊት አልሸነፍም። የኢትዮጵያ ሕዝብ እጁን አይሰጥም። ይህ ከሆነማ የአፄ
ዮሃንስ የቀይ ባህር ተጋድሎ እና የጀግናው ራስ አሉላ አባነጋ አጥንት ይፈርዳል። ኢትዮጵያ ሃገሬ የጀግኖች መፍለቂያና ገናና
ታሪክ ሃገር ናት። ሻቢያ ምፅዋን እንደያዘ ለዘላለም አይኖርም ብለው እንደ አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ገድለው አልፈዋል።
ከጌታቸው ረዳ፤ “ይድረስ ለጎጠኛው መምህር” የተጨመቀ ጥቅስ።
ህወሓት የዚህ አመቻች ቡድን ነው። ስለሆነም፤ የኢትዮጵያን የባህር በር ዘጋ፤ የሃገሪቱን ደህንነት ለአደጋ አመቻቸ። በተጨማሪም፤
ሁለት፤ የኢትዮጵያ ጠላት መንግሥታት የፈለጉትን የቀይ ባህር የበላይነት ሳይዋጉ አስረከበ፤
ሶስት፤ የኤርትራንና የኢትዮጵያን ወንድማማች/እትምማች ሕዝብ ጥንታዊ ግንኙነት አፈራረሰ/ለማፈራረስ ሞከረ፤
አራት፤ በሁለቱ ህብረተሰቦች መካከል ያለውን ተደጋጋፊ የኢኮኖሚ፤ የንግድ፤ የማህበረሰብ፤ የኃይማኖት ግንኙነት በከለ፤
አምስት፤ በኤርትራና በኢትዮጵያ አምባገነናዊ ስርዓቶች እንዲመሰረቱ አደረገ፤
ስድስት፤ በመገንጠል የሚገኝ “የኤርትራ ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ መሻሻል” አለ ብሎ የኤርትራን ወጣት ትውልድ በባሰ ሁኔታ
ከኤርትራ እንዲሰደድ፤ የኤርትራ ኢኮኖሚ ከኢትዮጵያ ጋር እንዳይቆራኝ በረከት አቀረበ፤
ሰባት፤ ህወሓት ተወዳዳሪ ስለማይፈልግ ሁለቱን ሕብረተሰቦች ለከፋ ጦርነት ዳረገ፤ የብዙ ሽህ ህይዎት እንዲጠፋ አደረገ፤
ስምንት፤ ሰላም፤ እርጋታና እርቅ እንዳይኖር የውክልና አመፅ እንዲካሄድ አመቻቸ፤
ዘጠኝ፤ የኢትዮጵያን የባህር በር ኤርትራንም ኢትዮጵያንም በሚጠቅም መንገድ ተደራድሮ በማስተካከል ፋንታ የደረቅ
ወደብ፤ ማራገፊያና መጫኛ (Dry Docck) ገነባ፤ በሌሎች አገሮች ወደቦች አማራጭ ለማግኘት ሞከረ፤ አሁንም ወደፊትም
ይሞክራል፤
አስር፤ የኤርትራን ፈለግ ተከትሎ በኢኮኖሚ፤ በባህልና በሌሎች መስፈርቶች ያልተደገፈ፤ በቋንቋና በመሬት ይዞታ በተደገፈ
ሚዛን ኢትዮጱያን በክልል አስተዳደር መሰረተ፤ የፈለገ ለመገንጠል እንደሚችል በአንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ ደነገገ። ዛሬ እነዚህ
ክልልሎች “የተለያዩ አገሮች” በመሆን ላይ ናቸው። በመካከላቸው ያለውን አገሪቱንና ሕብረተሰቡን ታላቅ የሚያደርግ
ግንኙነት ተበክሏል። ሚዛናዊ የሆነ ልማት የለም።
የኤርትራ መገንጠል የሚያመለክተው ህወሓት ሲፈልግ ኢትዮጵያዊ፤ ሳይፈልግ ጎሰኛ ሊሆን እንደማይችል ነው። አለበለዚያ ባለፈው
እንዳደረገው ኢትዮጵያ እንድትደክምና እንድትፈራረስ ከሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች የሚለየው መስፈርት አይኖርም። ይኼን ህወሓት
አሉንታዊ የሰጠው የሚያኮራ ታሪክ እንዳይታወቅ ጥረት ያደረጉና አሁንም የሚያደርጉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች አሉ። የአሁኑ የአገዛዝ
ስርአት ስልት ታሪክን በማኮላሸትና ሕዝብን በመከፋፈል ጥንክርናውን ያስተጋባል። ዓባይን በሚመለከት በውጭ ያለው ኃይል ልክ
እንደ ቀይ ባህር የኢትዮጵያን ይገባኛልነት የማይቀበል (ግብፅ መሪ ናት) ነው። የኢትዮጵያን ከግብፅና ከሌሎች ጋር ተወዳዳሪ ታሪክ
አይቀበልም። ህወሓትም አልተቀበለም። ግብጾችና ሌሎች ኢትዮጵያ ደካማ፤ ኋላ ቀርና ለመከፋፈል አመች አገር ናት የሚል ዘዴ
ይጠቀማሉ። የአድዋን ድል በሚመለከት ከላይ የተጠቀሱት መልካም አመለካከት ያላቸው የዓረብ ምሁራን ትንተና እንዳለ ሆኖ፤ 11
በወቅቱ የነበሩ የግብፅ ደራሲዎችና ጋዜጦች ኢትዮጵያ ጣልያንን እንዳሸነፈች፤ ከዚያ በፊት አፄ ዮሃንስ በ 1876 ኢትዮጵያን ሊያንበረክክ
የመጣውን የግጾችን የጦር ኃይል ጉራ በተባለ ቦታ በማያሻማ ሁኔታ ማሸነፋቸውን፤ ወራሪዎችን መማርካቸውን ምንም አያወሱም።
አሚር አሌ ኢስማኤል ሳርሃንክ የተባለ ግብፃዊ “The Truthful News about the Countries of the Seas,” በተባለው መጽሃፉ
ግብፅ ኢትዮጵያን እንደ መሪ ጠላት ስለምታይ ኢትዮጱያ የተጎናፀፈችው ድል ሁሉ እንዳልነበረ ይናገራል። አፄ ዮሃንስ የተቀዳጁት ድል
እንዳልተካሄደ አድርጎ ጽፏል። አድዋ የሚባል ነገር ፈጽሞ አልተነሳም። ሙሃመድ ሪፋት የተባለው የጦር መኮንን የአፄ ዮሃንስ ምርኮኛ
ሆኖ የደረሰበትን ችግር ለግብፅ ሕዝብ “Overcoming the Calamity in Release from Captivity” በተባለ መፅሃፍ አቅርቦታል።
ከአሚር ለየት የሚለው ይህ ደራሲ የኢትዮጵያ ወታደሮች ጠንካራና ቆራጥ መሆናቸውን ይቀበላል። ሆኖም፤ ለኢትዮጵያውያን ያለውን
“ንቀት” ያሳያል። “ኢትዮጵያውያን ኋላ ቀር፤ ያልሰለጠኑ፤ ንፅህና የሌላቸው፤ ስጋ ሳይበስል የሚበሉ” ወዘተ እያለ ንቀቱን ይናገራል።
ግብጾች የደረሰባቸውን ጥቃት እንደማይረሱና ኢትዮጵያ እንደ ጃፓን ሃብታምና ዘመናዊ ከሆነች ግብፅ በዓባይ ላይ ያላትን የበላይነት
እንደምታጣ ይጠቁማል። ይህ ፀረ-ኢትዮጵያ ስሜት ጥልቀትና ስፋት ባለው ሁኔታ የተከሰተው በግብፅ የመከላከያና የስለላ ተቋሞች
መሆኑን አስምሮበታል። ህወሓት የኢትዮጵያን የሰለጠነ የጦር ኃይል ሲያጠፋ አብሮ ያጠፋው የኢትዮጵያን ተቋማዊ የመከላከያ
ጥንክርና ነው። በተመሳሳይ የደርግ መንግሥት ስድሳዎቹንና ጀኔራሎቹን ሲገድል አብሮ የገደለው የኢትዮጵያን የሰለጠነ፤ የአገር አንድነት
አስተባባሪና አገር ወዳድ ኃይል ነው። ሁለቱም አምባገነናዊ መንግሥታት ለአገሪቱ ድክመት ተጠያቂዎች ናቸው።
ሚዛናዊ ለመሆን ህወሓት ደፍሮ የማይቀበለውንም ያመለከቱ ሃቀኛ ግብፃውያን ደራዊዎችም አሉ። ደጋግሜ በመጻህፍት
ያቀረብኳቸውን መሰረታዊ ሃሳቦች ይደግፋሉ። ይኼን የምልበት ዋና ምክንያት ሁሉም ግብፃውያን የኢትዮጵያ ጠላቶች ናቸው ከሚል
የተሳሳተ ድምዳሜ እንዳንደርስ ለማሳሰብ ነው። አል ማንሱር የተባለው የግብፅ መጽሄት በ1897--የኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት
እየጠነከረና የዘመናዊነት ጮራ እየታየ በነበረበት ወቅት-- እንዲህ ሲል ጽፏል። “በአስራ ዘጠንኛው መቶ ዓመት አማካይ ወቅት ጎራዴ
የተባለ መሳሪያ ሁለት ታላላቅ ግዛቶችን መሰረተ። አንዱ የጀርመኖች፤ ሌላው የኢትዮጵያውያን ነው። ጀርመኖች ፈረናሳዮችን አሸነፉና
የተባበረችውን ጀርመኒን ኃይል ተጠቅመው፤ የራሳቸውን ወገኖች ጨፍጭፈው ታላቋን ጀርመኒን መሰረቱ። የጀርመኖች ግዛታዊ
አንድነት በጦርነት የመጣ ነው። የኢትዮጵያውያን ግዛታዊ አንድነት የተገኘው ደግሞ በአፄ ምኒሊክ ዓመራር በአድዋ ድል ነው።
ኢትዮጵያውያን ከምስራቅ አገሮች ጋር የተያያዘ ታሪክ አላችው። ኢትዮፕያውያን የነቁት የጣሊያን መድፍ ሮምታ ለአገራቸው ህልውና
አደጋ መሆኑን ሲያዩ ነው። ይህ ሮምታ ኢትዮጵያ በአፋጣኝ ዘመናዊ እንድትሆን ቀሰቀሰ። በእኛ ግምት ኢትዮጵያ ዘመናዊ እሆናለሁ
ብላ ከወሰነችና አደጋ ካላጋጠማት አምሳ ዓመታት በኋላ እንደ ጃፓን መሆኗ አይቀርም። ይክ ሲሆን አገሪቱ የረጋችና ሃብታም
ትሆናለች” ብሎ ነበር። የህወሓት መስራቾችና መሪዎች ለኢትዮጵያ የዚህ አይነት ራእይ አልነበራቸውም። ቢኖራቸው ኢትዮጵያ
በመበታተን፤ የባህር በሯን ፈልገውና ፈቅደው በማዘጋት ፋንታ ሁሉን አሳታፊ ዲሞክራሳዊ መንግሥት ለመመስረት ሁኒታዎችን
ያመቻቹ ነበር። አልሆነም።
አሚር የግብፅን የአስራ ዘጥንኛ መቶ ዓመት የውጭ ጉዳይ አመራር በጠራ መልክ አቅርቧል። የዓባይ ጉዳይ ለግብፅ ወሳኝ ስለሆነ፤
ግብፆች ገና ነጻነታቸውን ከመቀዳጀታቸው በፊት የግብፁ መሪ ከዲቭ ኢስማኤል እንግሊዞችን በስለላና በጉልበት እየረዳ፤ በአገር ውስጥ
ሰላዮችና ተባባሪዎች እየተደገፈ የእንግሊዝ ወራሪዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ያልተቆጠበ “ድጋፍ ሰጥቷል” ብሎ በመፎከር ይናገራል።
የዓባይ ጉድ አያልቅም። ኢስማኤል የፈለገውና ያደረገው፤ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ፤ ጦሯን ዘመናዊ አድርገው ግዛቷና የተፈጥሮ
ሃብቷ እንዳይደፈር ጥረት ያደረጉትን አፄ ቴዎድሮስን እንግሊዞች ከበው እንዲሸነፉ፤ ራሳቸውን አልሰጥም ብለው ለሃገራቸው ክብር
መስዋእት እንዲሆኑ ለቅኝ ገዢዎችና ለውስጥ ተባባሪዎች በረከት መስጠቱን በማስረጃ አቅርቦልናል። ኮፕቲክ ክርስቲያኑ ቡትሮስ
ቡትሮስ ጋሊ የኤርትራን ነጻ መውጣት በቀጥታ የተቀበለውና የደገፈው በዚህ ተከታታይነት ባለው ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም ነው። ቡትሮስ
ቡትሮስ ጋሊ ያሳየን ከኃይማኖቱ በላይ ግብፅን እንደሚወድ ነው። ሻቢያ የዓረብ ድጋፍ ባይኖረው የትም አይደርስም ነበር የምለው
ለዚህ ነው። ይህን ስል፤ ለመለየት የምፈልገው ከውስጡ የእርስ በርስ የስልጣን ሽሚያና የኋላ ቀር የሆነው ንግሳዊው ስርዓት የአፄ ኃይለ
ሥላሴ መንግሥትና ደርግ ለኤርትራ መገንጠል አስተዋጾ አላደረጉም ማለቴ አይደለም። አገር ወዳድ መንግሥታት መሆናቸው በምንም
አያከራክርም። የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ኤርትራን የኢንዱስትሪ፤ የዘመናዊ እርሻና ትምሕርት መዲና አድርጓል። ነጋዴዎች ከማህል
አገር የእርሻ ውጤት ይዘው አስመራ ይመላለሱ ነበር፡፡ ከአስመራ የእኒዱስትሪ ውጤት እቃዎች ወደ ማህል አገር ያመጡ ነበር። ይህ
የማይካድ የኢኮኖሚ መተሳሰር ለሁለቱም ሕብረተሰቦች ጠቅሟል። ዛሬ የኤርትራ አናቶች ቡና ሲፈልጉ የኢትዮጵያን ቡና ከአሜሪካ
የሚያስመጡ ብዙ ናቸው። ኢትዮጵያንና ኤርትራን የጎዳው ውሳኔ ፌደሬሽኑን ማፍረሳቸው ነው። የታሪክ ተጠያቂ አድርጓቸዋል። ደርግ
የኤርትራን ጥያቄ ዲሞክራሳዊ በሆነ፤ ለምሳሌ የፌደሬሽን አይነት የፖለቲካ ትብብር እንዲኖር ጥረት በማድረግ ፋንታ ሁሉን ነገር
በጦርነት እወጣዋለሁ ማለቱ የዓመራር ጉድለት ነው። በተከታታይ ስርአቶቹ ዲሞክራሳዊና ፍትሃዊ ስላልነበሩ የኢትዮጵያን ጥንክርና
አዳክመዋል። የውጭና የውስጥ ኃይሎች ተባብረው ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ወደኋላ እንደማይሉ ቢገነዘቡም፤ ፍትህ ከሚፈልጉ ኃይሎች
ጋር ያደረጉት ድርድር አጥጋቢ ሆኖ አላገኘሁትም።
ሆኖም፤ ይህ ድክመት ወደ ባሰ “የጠላቴ ጠላት ወዳጀ ነው” ወደሚል ስህተት በተደጋጋሚ ማሸጋገር የለበትም። መቀበል የምንገደደው
የግብፆች መሰረታዊ ዓላማ በምንም አይለወጥም። በመሰረቱ የሱዳኖችም የሚለወጥ አይመስለኝም። ለዚህ ነው፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ
የሚያስተባብረው መሰረት ለሆነው ፍትህ ትኩረት መስጠት ወሳኝ የሚሆነው። ህወሓት/ኢህአዴግ በጣም ስለደለበ ራሱን ለመለወጥ
አይችልም። ሁል ጊዜ የማመካኘው በወደቀው በደርግ ላይ ነው። የደለበ ከሆነ አማራጩ የሕዝብ ለመብቱ መቆምና ሰላማዊ ዓመፅ
ማዘውተር ብቻ ነው። ደጋፊ የሆነው ብንያም ከበደ በFebruary 8, 2014, “ኢህአዴግ ክብደት ካልቀነሰ ለህይወቱ ያሰጋዋል” ያለው
አግባብ አለው። ችግሩ ክብደት ያላቸው ሰዎች የበሽታቸውን መንስኤ አያውቁም። ቢያውቁም አይቀበሉም። ኢህአዴግ የራሱን በሽታ 12
(ክብደት) ሳይቀበል ችግሮችን የሚከምረው በተቃዋሚው ላይ ነው። በፈጠራ መረጃ ሰውን ከሶ፤ “እንድፈታህ ከፈለግህ ይቅርታ
ጠይቅ”) የሚል መንግሥት ራሱን ሊለውጥ አይችልም። መድለቡን ሳይሆን፤ የሚመለከተው ስልጣኑና ተጨማሪ ሃብት ለራሱ፤
ለቤተሰቡና ለወዳጀቱ ማካበቱን ነው። ወጣቱ ትውልድ ይኼን ሸክም እንዳያውቅ በጎሳ ፖለቲካ ተበክሏል። ሆነ ብሎ የትምህርቱን
ይዘት ራስ ወዳድ፤ አጎብዳጅ፤ ፈሪና የውጭ ባህል ተቀባይ አድርጎታል።
የትምኅርት ዓመራር ማህበራዊ ጥቅም ጉድለት
የኢትዮጵያ የትምኅርት አቀራረጽና አቀራረብ የኢትዮጵያን የታሪክ፤ “መስተጋብር”፤ ውህደትና ፈተና አላስተማረንም። ከሁሉም
ብሄር/ብሄረሰቦች የተዋጣጡን የሚያኮሩ ጀግኖች ከማወቅ ይልቅ የነ ሆመርን፤ የነሃኒባልን፤ የነናፖሊዮንን፤ የነቸርችልን፤ የነ ጆርጅ
ዋሽንግቶንን ወዘተ ታሪክ እንድንማር ተገደናል። የራሳችን ብሄረሰቦች ልዩ ልዩ ባህሎች፤ ቋንቋዎች፤ ወግና ማእረጎች፤ የቆዩ ግንኙነቶች
በማወቅ ፋንታ የምእራባውያንን ተምረናል። ራሳችን ዝቅ በማድረግ አንርፃፅረናል። ይህ የትምሕርት ሂደት ልዩነቶችን አጋኖብናል።
የግራው ክንፍ ለለውጥ የነበረው ጥንካሬና ድፍረት ያኮራኝ ነበር። ሰለ አገሩ ያለው እውቀት ማነስም ያስደነግጠኝ ነበር። ለምሳሌ፤
ለሰው ህይዎት የነበረው ዝቅተኛ አመለካከት። እኔም በዝቅተኛ ደረጃ ተባባሪ ነበርኩ። ማርክስ፤ ሌኒን፤ ስታሊን፤ ማኦ፤ ቸ፤ ሆ ችሚን፤
ሆሳ ወዘተ እያልን ፎከርን ከኢትዮጵያ ታሪክና ልምድ ጋር ለማገናኝት አልቻልነም። ለአገሩ ዘመናዊይነት ለመሞት የተዘጋጀውን ወጣት
ትውልድ በጥበብ መራነው ለማለት አንችልም። አብዮታዊ ለውጥ ያካሄዱትን አገሮችና የራሳችን ታሪክና ልምድ በጥልቀት አናውቅም
ነበር። “ፋኖ ተሰማራ” እስከ ተወሰነ ደረጃ ድረስ ወጣቱን ያንቀሳቅሳል። በጥበብ ካልተመራ ወጣቱ ትውልድ የእሳት እራት ይሆናል
የሚል ጥናትና ግንዛቤ አልነበረም። የሚያስከትለውን የአገር መዳከም ሂደት አይተነዋል። ዘላቂነት ያለው መሰረታዊ ለውጥ ከአገር
ባህል፤ ከአገር ልምድ፤ ከአገር ጀግኖች፤ ከአገር ሽማግሌዎች ወዘተ ጋር ካልተቆራኘና እንደ ሃገሪቱ ሁኔታ ካልተመራ መጨረሻው አዘቅት
እንደሚሆን አነጋጋሪ መሆን ነበረበት። ረጋ ባለ አእምሮ ይኼ ለአገሬና ለማግገል ለምፈልገው ድሃ ሕዝብ ይረዳል ወይንስ አይረዳም
የሚል ጥያቄ አልሰማም ነበር። በኔ ትውልድ ሌላው ቀርቶ ለኢትዮጵያ ሆነ ተብሎ የተፈጠረላትን ስም የተቀበልን ብዙ ነን። “አቢሲኒያ”
የተባለው የአረቦች ስያሜ የመጣው ከንቀትና ቁጥጥር ስልት ነው። አቢሲኒያ የሚለው ቃል ኢትዮጵያውያን ጥቁሮች ከነጮች (ነጭ
አረቦች) ጋር ቅልቅል መሆናቸውን፤ ለብቻቸው ለመፍጠር፤ እድገትን ለመጎናፀፍ እንደማይችሉ የሚገልፅ ነው። It should be clear
that the name “Abyssinia was used precisely to avoid ‘Ethiopia,’ with its indelible association with
blackness (Africanness).” ኢትዮጵያ የምትባል፤ ተከታታይነትና የጥንት እውቅና ያላት አገር የለችም ለማለት ሆነ ተብሎ የተፈጠረ
ስም ነው።
ሌላው ችግር እንዳለ ሆኖ፤ የስድሳ ስድስቱ የሕዝብ አብዮት ጥንክርና ነበረው። ወጣቱ ትውልድ ለሃገሩ በጋራ ወደኋላ ሳይል መነሳቱና
መስዋእት ዋናው ነው። ከዚህ ጋር አብሮ የሚሄደው ልንክደው የማንችል ራስን ያለማውቅና በራስ ባህል አለመተማመንን ይታይ ነበር።
በሃገር ልምድ፤ በስልትና በሕግ የበላይነት ቢመራ፤ የግራው ክንፍ ለኤርትራ ነጻ አውጭ ግንባሮች ሰለባና የስለላ ወንፊት አይሆንም
ነበር። ይህ ክንፍ ከሁሉም በላይ አገሩን ቢያስቀድም፤ እርስ በርሱ ቢነጋገር፤ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት ቢችል ወዘተ እልቂት
የሚያስከትለውን ጠንቅ ይረዳ ነበር የሚል ግምት አለኝ። ባቋራጭ፤ ሕዝቡ ለመብቱ ሳይደራጅ፤ ለስልጣን እርስ በርሱ ባይጨፋጨፍ
ወዘተ ወዘተ ኑሮ ኢትዮጵያ አስደናቂ የሆነ ለውጥና ዘመናዊነት ታሳይ ነበር። ወታደራዊ ክፍል ይኼን ክፍተት ለራሱ ስልጣን
እንደተጠቀመበት አውቃለሁ። በብዙ መስዋእት የተገኘው አብዮት ባከነ። የኢትዮጵያን ታሪክ፤ የስብጥር ሕዝቧን ባህልና ልምድ ወዘተ
በሚገባ ሳናውቅ የማርክስ፤ ሌኒን፤ ማዖ፤ ስታሊን፤ ቸ ጉቤራ ወዘተ ርእዮት የችግር መፍቻ እንደሆነ አድርገን ለለውጥ ለተዘጋጀው
የኢትዮጵያ ሕዝብ አቀረብነው። የሚከተለውን ያልታሰበ አደጋ (unintended consequences) ስሌት ሲደረግ አላየሁም። የግራ ክንፉ
ሆነ የወታደራዊው አመራር ያላደረገው የእርስ በርስ እልቂቱና የስልጣን ሺሚያው ለሃገሪቱና ለሕብረተሰቡ አደጋ እንደሚኖረው
አስቀድሞ በጥናትና በረካ ውይይት አለማየቱ ነው።
ያለፈው ተደጋጋሚ ልምድ የሚያሳየው የለውጥ ሃይሎች ነን የምንለው ስብስቦችና ግለሰቦች አሁንም በብሄር፤ ብሄረሰብ፤ ኃይማኖት፤
ጥቅም፤ ጾታ፤ ሞያና ገቢ ሳንገደብ አበይት በሆኑ ጥያቄዎች ላይ የረባ የጋራ ሰብሳቢና አስታራቂ ውይይት ለማካሄድ አለመቻላችንን
ነው። በአበይት ጉዳዮች ላይ በተናጠል ውሳኔ ወስደን “ተቀበሉኝ፤ ካልተቀበላችሁ የዚህ የዚያ ደጋፊዎች ናችሁ” የሚለው ባህል
በዓባይም ላይ ይታያል። ሁሉም “ከኔ በላይ” እውቀት ያለው የለም የሚል ይመስላል። ልክ እንዳለፈው አንዱ ከሌላው የመማር፤
የመቻቻል ባህል አይታይም። በአብዛኛው የሚታየው ኢትዮጵያ በጣም የተለያዩ ማህበረሰቦችንና አገሮችን በመመስረት ሂደት ላይ
የምትገኝ አገር መሆኗን ነው። የተለያዩ አገሮች እየተመሰረቱ ከሆነ ህወሓት/ኢህአዴግ “የዓባይን የተሃድሶ ግድብ” የሚሰራው ለማን
ነው? ብለን የመወያየት ሃላፊነት አለብን።
መደምደሚያ
የኢትዮጱያ ሕዝብ መንታ መንገድ በኢትዮጵያ የዓባይ ባለቤትነት አግባብነትና በህወሓት/ኢህአዴግ የስርዓት አፋኝነት መካከል
የሚሽከረከር አስኳል ጉዳይ ነው። በሕግም ሆነ በተፈጥሮ የኢትዮጵያ የዓባይ ባለቤትነት አያጠያይቅም። የህወሓት/ኢህአዴግ ስርዓት
ከማጠያየቅ አልፎ የአገሪቱን ህልውና ከጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል። ለዚህ መልሱ እንዳለፈው የፖለቲካ ሂደት መከፋፈል፤ መጠላለፍ፤
መካሰስ፤ መገዳደል፤ የስልጣን ሽሚያ ወዘተ አይደለም። የዓላማ አንድነት ነው። 13
ዛሬ በዓባይ ግድብ ዙሪያ በጥናት፤ በእውቀትና በመወያየት የተወሰደአቋም አላየሁም። ሁሉም እንደመሰለው ሃሳቡን ያበረክታል።
ኢትዮጵያዊይነት አጥፍቶ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው፤ በቀጥታም ሆነ በተወካዮች አማካይነት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ያጠፋው
ህወሓት ዓባይን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም እገድባለሁ ሲል መጠንቀቅ አለብን። ይህ የጥናት ዘገባ ያሳየውና በተከታታይ የሚያሳየው፤
ኢትዮጵያ ፈተና ሲገጥማት ያዳኗት ብሄር፤ ብሄረሰብ ፤ ኃይማኖት ፤ ጾታና እድሜ ሳይለዩ በአንድነት የቆሙ አገር ወዳዶች ናቸው። ይኼን
መሰረተ ሃሳብ የሚጋራው (በአፄ ኃይለ ሥላሴና በደርግ ዘመን) በአንድነትና በዲሞክራሳዊ ለውጥ ሜዳ ተሰልፎ የነበረውና በህወሓት ዘመን
ህይዎት እንደሌለው ድምጥማጡ የጠፋው ተቆርቋሪ ኃይል ከእንቅልፉ የሚነሳበት ወቅት አሁን ይመስለኛል። ድምጥማጡ ስለጠፋ
የፖለቲካና የዲሞክራሲ ለውጡን ድርጅታዊና ማህበረሰባዊ ክፍተትና አደጋ አይቶ ባለፈው ጥፋት ሳይወጠር ህወሓትና የግብፅ መንግሥት
በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያጠመዱትን “ቦምብ” ሕዝብን በሚወክል ስርዓት ለመተካት ተባብሮ መነሳት የወቅቱ ጥያቄ ነው።
ይቀጥላል
sourse abugda
No comments:
Post a Comment