ሚያዚያ ፲፬ (አስራ አራት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፈው መጋቢት ወር በሃረር የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ ተከትሎ እቃ ሰርቀሃል በሚል የ21 ዓመቱ ወጣት ዳንኤል ጎሳ በእስር ቤት ውስጥ ለብቻው እንዲታሰር ተደርጎ ከፍተኛ ደብደባ ተፈጽሞበት መሞቱን ኢሳት የእስር ቤት ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ከዘገበ በሁዋላ ወላጅ አባቱ አቶ ጎሳ አበበ ፣ የልጃቸውን አሟሟት ትክክለኛ መንስኤ ለማጣራት ጥረት ቢያደርጉም እስካሁን እንዳልተሳካለቸው ገልጸዋል።
አቶ ጎሳ ያለ እናት ያሳደጉት ልጃቸው በቃጠሎው ወቅት በከተማው ያልነበረ መሆኑን ተናግረዋል። በፖሊሶች መንገድ ላይ ተይዞ እስር ቤት ከገባ በሁዋላ ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመበትና ” እኔ ምንም አይነት እቃ አልወሰድኩም እያለ ጮክ ብሎ ሲናገር ሌሎች እስረኞችና ከእርሱ ክፍል ራቅ ብሎ እንድትታሰር የተደረገችው ባለቤቱም መስማቱዋን “ተናግረዋል።
ፖሊስ ወጣቱ ራሱን አንቆ ገድሏል ብሎ አስከሬኑን ካስረከባቸው በሁዋላ፣ ለአስከሬን ምርምራ ወደ አዲስ መውሰዳቸውን፣ ምርምራው በ5 ደቂቃ ቢጠናቀቅም ሪፖርቱን ለማግኘት አለመቻላቸውን ገልጸዋል።
ልጃቸው ትዳር ከመሰረተ ገና ሁለተኛ ወሩ በመሆኑ ህይወትን በማጣጣም ላይ ይገኝ እንደነበር የገለጹት ወላጅ አባቱ፣ ራሱን የሚያጠፋበት ምንም ምክንያት እንደሌለና በድብደባ ብዛት ተገድሏል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የፖሊስን አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ኢሳት በሃረር እስር ቤት ውስጥ ስለተፈጸመው ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ዘገባ ሲያቀርብ ቆይቷል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር በቅርቡ ወደ ሃረር ተጉዘው የተለያዩ ሰዎችን ማነጋገራቸው ታውቋል።
No comments:
Post a Comment