Tuesday, August 26, 2014

ሥርዓቱን ለ 20ዓመት አይተነዋል መቀየር አለበት! የተማሪዎች ተቃውሞ

 | 
  • 407
     
    Share
የኢትዮጵያ የባህር በር ለኤርትራ መሰጠቱ ስህተት ነው
የኢኮኖሚ እደገቱ እውነት አይደለም
የትምህርት ስርዓቱ ወድቋል
የተማረ ሰው ክብር አይሰጠውም
Ethiopian_Student_Protest_2001_02አዲስ አበባ ውስጥ ሳውዝ ካምፓስ (ልደታ)፣ አቃቂ (AASTU)፣ ፍቼ የግብርና ኮሌጅ፣ ስድስት ኪሎ፣ አምስት ኪሎ፣ አራት ኪሎ፣ የአዲስ አበባ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስት ትምህርት ክፍልና ሌሎችም አካባቢዎች ከነሃሴ 15 ጀምሮ ስልጠና ላይ የሚገኙ የመጀመሪያ ዙር ሰልጣኞች ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን እንደቀጠሉ የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገለጹ፡፡ ተማሪዎቹ ገዥው ፓርቲ አለ በሚለው እድገት፣ የባህር በር፣ የተማረው የማህበረሰብ በሚደርስበት በደል፣ የትምህርት ጥራት፣ የመምህራን የእውቀት ደረጃ ማነስ፣ ድህነትና አጠቃላይ ኢኮኖሚ ውድቀት ላይ ጠንከር ያለ አስተያየትና ተቃውሞ መሰንዘራቸውን ተገልጾአል፡፡
የኢኮኖሚ እድገት
ተቃውሞ ከገጠማቸው ጉዳዮች መካከል የኢኮኖሚ እድገት አለ የለም የሚለው ሲሆን ተማሪዎቹ ‹‹በአክሱም ዘመን ገናና የነበረችው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚው መስክ ጭራ›› መሆኗን በመግለጽ እድገቱ አለ መባሉ ስህተት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎቹ ጨምረውም “በቀን አንድ ጊዜ እንኳን መመገብ የማይችል ማህበረሰብ ይዘን አድገናል ማለት አንችልም” በሚል እድገት አለመኖሩን ተከራክረዋል፡፡ “ሀገራችን ውስጥ የምግብ፣ የቤት፣ የትምህርት፣ የኔትወርክና ሌሎች ችግሮች አሉ፡፡ ስኳርና ዘይት ለመግዛት ህዝብ ቀበሌ ተሰልፎ ነው የሚውለው፡፡ በ400 ብር ደምወዝ ቤተሰብ የሚያስተዳድር ህዝብ ያለባት ሀገር የሌሎችን እድገት ፈዛ እያየች ያለችን ሀገር አድጋለች ልንል አይገባም” ማለታቸው ተገልጾአል፡፡
በተመሳሳይም “2 በመቶ የሚሆነው የአሜሪካ አርሶ አደር ዓለምን በሚመግብበት በአሁኑ ወቅት 85 በመቶ አርሶ አደር ይዘን ለምን እንራባለን?” የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውንም የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡ ተማሪዎቹ “አድገናል ብለን ራሳችን ማወዳደር ያለብን ከ40 አመት ከነበረ ስርዓት ጋር መሆን የለበትም፡፡ እድገታችን መለካት ካለበት ከሌሎች አገራት ጋር ነው፡፡ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት በ2020 እንመደባለን ከተባለ መንግስት መቀየር ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ይህን ስርዓት ለ20 አመት አይተነዋል፡፡ ባለፉት አመታት ለውጥ ሊያመጣ አልቻለምና በ2020ም ለውጥ ያመጣል ብለን አንጠብቅም” የሚል ጠንካር ያለ ሀሳብም አቅርበዋል፡፡
እድገት ላይ ነው የሚባለው የኮንስትራክሽን ዘርፍ የጥራት ደረጃው ዝቅተኛ መሆኑን በተለይ በዘርፉ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ተማሪዎች አንስተዋል፡፡ ተማሪዎቹ “እድገት የምንለው የህንጻዎችን ወደላይ ማደግ ወይንም መብዛት ሳይሆን የማህበረሰቡን አስተሳሰብና አኗኗር ዘይቤ መቀየር ነው” ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ በስልጠናው ወቅት ገዥው ፓርቲ የቻይናን ፈለግ ተከትሎ እድገት ማስመዝገቡን በመቃወም “ቻይና ከ2.3 እስከ 2.7 በመቶ እያደገች እንደሆነ ይነገራል፡፡ የእሷን ፈለግ ተከተለች የተባለችው ኢትዮጵያ ከ11.2 በመቶ በላይ አደገች ነው የሚባለው ከየት አምጥተነው ነው? ወይስ እንደ ቀን አቆጣጠራችን እድገታችንም ይለያያል?” ሲሉም አሰልጣኖቹን ጠይቀዋል፡፡
የባህር በር
ተማሪዎቹ ለኤርትራ መሰጠቱ አግባብ እንዳልሆነ፣ የባህር በርና ወደቡ ለኢትዮጵያ ቀጣይ እድገት፣ ደህንነትና ታሪክ አንጻር አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ ገዥው ፓርቲ በባህር በር ላይ ያለውን አቋምና ፈጸመ ያሉትን ስህተት ተችተዋል፡፡ ወደብ አልባ በመሆናችን ኢኮኖሚያችን ወደኋላ መቅረቱንም አንስተዋል፡፡ በሌላ በኩል “በአገራችን የሚመረቱ ሰብሎችና ፍራፍሬዎች ለአገር ውስጥ ገበያ የሚቀርቡት ከውጭ ከተላከው ሲተርፍ ነው” በማለት በኤክስፖርት ዘርፍ ያለውን ችግር፣ አገር ውስጥ እየተፈጠረ ያለውን የኑሮ ውድነት ከዚሁ ችግር መመንጨቱን ጠቅሰዋል፡፡
የትምህርት ጥራት
ተማሪዎቹ የራሳቸውን ተሞክሮ በመጥቀስ የትምህርት ስርዓቱ ችግር ያለበት መሆኑን በመከራከሪያነት አቅርበዋል፡፡ “ለተማረ ሰው ክብር እየተሰጠ አይደለም” በሚል የእነሱም እጣ ፈንታ ተመሳሳይ መሆኑን ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም “የሚያስተምሩን አስተማሪዎች የእውቀት ደረጃ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ነው፡፡ በየ ዩኒቨርሲቲው በአመራር ላይ የሚገኙ ግለሰቦች እውቀት የላቸውም” በማለት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የተደቀነውን አደጋ አንስተዋል፡፡
ዲግሪ ይዘው በስራ ፈጠራ ስም በጥቃቅንና አነስተኛ እንዲደራጁ የሚደረገውን የተቃወሙት ተማሪዎቹ “የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተደራጅተው ካፌ ከፈቱ፣ ኮብልስቶን አነጠፉ ሲባል ነው የምንሰማው፡፡ ለዚህ ስራ ደግሞ ዩኒቨርሲቲ መማር አያስፈልገውም፡፡ ይህን ስራ ለመስራት የሶስት ወር ስልጠና በቂ ሆኖ እያለ ዩኒቨርሲቲ መማር ባላስፈለ” ሲሉ የትምህርት ስርዓቱ ውድቀት እንደገጠመው መግለጻቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
(ምንጭ: ነገረ ኢትዮጵያ ፌስቡክ – ፎቶ ከፋይል ማህደር)
-- Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of various information and content providers. The Website neither represents nor endorses the accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors.--

No comments: