‹‹መመርያው የወጣው ክልሎች ተገቢውን ዕርምትና ጥበቃ ሊያደርጉ ስለማይችሉ ነው››
የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር
የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የሕግ ታራሚዎች ዝውውርን በሚመለከት ያወጣውና ከሰኔ 12 ቀን 2006 ዓ.ም. ተግባራዊ መደረጉ የተገለጸው የአፈጻጸም መመርያ ቁጥር 2/2006 ተቃውሞ ገጠመው፡፡
ተግባራዊ መደረግ የጀመረውን የማረሚያ ቤቱን የአፈጻጸም መመርያ የተቃወሙት፣ በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ታራሚዎች ናቸው፡፡ ታራሚዎች በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የሕግ ታራሚዎችን በሚመለከት በአንቀጽ 21 (2) ሥር ባሰፈራቸው ድንጋጌዎች፣ በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከሃይማኖት አባቶቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸውና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር የመገናኘትና እንዲጎበኟቸው ዕድል የማግኘት መብት እንዳላቸው ስለተደነገገ ደንብ መውጣቱን አስታውቀዋል፡፡
የሕገ መንግሥቱን የመብት ድንጋጌ ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 138/99 አንቀጽ 19 ላይ የሕግ ታራሚዎችን የዝውውር ጥያቄ በሚመለከት እንደገለጸው፣ ማንኛውም ታራሚ የመጨረሻ ውሳኔ ተሰጥቶት በሌላ ክስ የማይፈለግ ከሆነ፣ ቤተሰቦቹ በሚኖሩበት አካባቢ ወደሚገኝ ማረሚያ ቤት እንዲዛወር ካመለከተ፣ ሊፈቀድለት እንደሚችልና ቤተሰቦቹም እንዲያውቁ እንደሚደረግ የተደነገገውን ደንብ መመርያው እንደሚጥስና ታራሚዎቹንም መብት እንደሚያሳጣ አስረድተዋል፡፡
መመርያ ደንብን ሊጥስ ወይም ሊያርም እንደማይችል የሚናገሩት ታራሚዎቹ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣውን ደንብ ማረሚያ ቤቱ ምንም ሳይሸራረፍ ተፈጻሚ ማድረግ ሲገባው፣ አስተዳደሩ መመርያ እያወጣ መሠረታዊ መርሆዎችን መጣስ እንደማይችልና ተገቢም አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማረሚያ ቤቱ ተግባራዊ ባደረገው ደንብ የሚጥስ የአፈጻጸም መመርያው ‹‹የሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 138/1999 አንቀጽ 19 ስለታራሚዎች ዝውውር የተደነገገ ቢሆንም›› ካለ በኋላ፣ ዝውውር የማይፈቀድባቸውን የወንጀል ዓይነቶች በዝርዝር ማስቀመጡን ታራሚዎቹ ተናግረዋል፡፡ በሰው ዘር ማጥፋት ወንጀል፣ በሽብርተኝነት፣ በሃይማኖት አክራሪነት፣ በአገር ክህደት፣ የአገሪቱን ሚስጥር አሳልፎ መስጠት፣ በከባድ ውንብድና፣ በጦር መሣሪያ ንግድ፣ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በሙስና፣ ገንዘብ ማሳተምና ዝውውር፣ በሴቶች፣ በሕፃናትና በአካል ጉዳተኞች ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎችና ሌሎች በርካታ የወንጀል ዓይነቶችን አስተዳደሩ በመመርያው በመዘርዘር፣ በእነዚህ ወንጀሎች የተፈረደባቸው ታራሚዎች ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ወደ ክልሎች ማረሚያ ቤቶች መዘዋወር እንደማይችሉ ማስታወቁን ታራሚዎቹ ጠቁመዋል፡፡ አስተዳደሩ የወንጀል ዓይነቶቹ አዲስና ውስብስብ እንደሆኑ የገለጸ ቢሆንም ለዘመናት የነበሩና አዲስ አለመሆናቸውን ገልጸው፣ በአሁኑ ጊዜ ለዚያውም ደንብ ጥሶ ለመከልከል የፈለገበት መንገድ አሳማኝ አለመሆኑን ተቃውመዋል፡፡
ማረሚያ ቤቱ ያወጣው አዲስ የአፈጻጸም መመርያ በታራሚዎች ላይ ከፍተኛ ችግር የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ፣ ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚጋፋና በመታሰራቸው ምክንያት ንብረታቸው እንዲወድም፣ ቤተሰቦቻቸውን እንዳያገኙና እንዳይጠይቋቸው፣ በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድርባቸው ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
አንድ ታራሚ በመሠረታዊ መርህ ደረጃ በሕግ የተጠበቀ መብቱ ሊገደብ የሚችለው፣ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ በሚያሳየው ያልተገባ ባህሪና የማረሚያ ቤቱን ሕግና ደንብ ንዶ ሲገኝ እንጂ፣ ከዓመታት በፊት በተቀጣበት ወንጀል መሆን እንደሌለበት ታራሚዎቹ ተናግረዋል፡፡ የክልል መንግሥታት የፌዴራል መንግሥቱ ያወጣቸውን ሕጐች የማስፈጸም ሕገ መንግሥታዊ መብት እንደተሰጣቸው የጠቆሙት ታራሚዎቹ፣ በመመርያው የዝውውር ዕገዳ የተጣለባቸው የወንጀል ዓይነቶች 90 በመቶ የሚሆኑት በክልሎች ፍርድ ቤትም የሚታዩና ውሳኔ የሚሰጥባቸው መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ያወጣው የታራሚዎች የዝውውር መመርያ፣ ባጠፉት ጥፋት ተፀፅተው በመታረም ብቁ ዜጋ በመሆን ላይ ለሚገኙ ታራሚዎች በሕግ የተሰጣቸውን መብት የሚገድብ ከመሆኑም በላይ፣ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 138/1999ን የሚቃረን በመሆኑ እንዲስተካከልላቸው ጠይቀዋል፡፡
ታራሚዎቹ የተቃወሙትን የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ያወጣውን የአፈጻጸም መመርያ በሚመለከት ማብራሪያ እንዲሰጡ የማረሚያ ቤቱን የሕዝብ ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ረዳት ኃላፊ አቶ አዲሱ ጴጥሮስን ሪፖርተር አነጋግሯቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አቶ አዲሱ በሰጡት ምላሽ፣ እንደገለጹት ‹‹የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስለፌዴራል ታራሚዎች አያያዝ ባወጣው ደንብ ቁጥር 138/1999 ማንኛውም ታራሚ የመጨረሻ ውሳኔ ካገኘና በሌላ ክስ የማይፈለግ ከሆነ፣ ቤተሰቦቹ በሚኖሩበት አካባቢ ወደሚገኘው ማረሚያ ቤት እንዲዛወር ካመለከተ ሊፈቀድለት ይችላል፤›› ሲል ‹‹ላይፈቀድለትም ይችላል ማለቱ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ማረሚያ ቤቱ በመመርያው ላይ ዘርዝሮ ዝውውር የከለከላቸው የወንጀል ድርጊቶች ፈጻሚ ታራሚዎች ወደ ክልል ማረሚያ ቤቶች ቢላኩ፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን ያህል ጥበቃ ሊደረግላቸውና ሊታረሙ ይችላሉ የሚል እምነት ባለመኖሩም ጭምር መሆኑን አቶ አዲሱ አስረድተዋል፡፡
በዚህ ጊዜ የታራሚዎች ዝውውር ዕግድ እንዲጣልበት የተደረገበትን ምክንያት እንዲያስረዱ የተጠየቁት አቶ አዲሱ፣ ምክንያቱ የሽብርተኝነት ወንጀል እየተስፋፋ በመምጣቱና ከሃይማኖት አክራሪነት ጋር የተያያዘ ወንጀል እየተስፋፋ መምጣቱና ሌሎችም ምክንያቶች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ ደንቡ ሲወጣ ደግሞ በመመርያ የሚወጣውን ዝርዝር ጉዳይ ታሳቢ በማድረግ በመሆኑ፣ የወጣው መመርያ ሊነቀፍ እንደማይገባው የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊው አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ምሁራን ግን በወንጀል ሕጉም ሆነ በሌሎች የወንጀል ኃላፊነት የሚያስከትሉ ሕጎች ውስጥ የሃይማኖት አክራሪነት የሚባል ወንጀል እንደሌለ በመግለጽ፣ መመርያው ምን ለማት እንደፈለገ ግልጽ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡
No comments:
Post a Comment