Wednesday, December 17, 2014

በሃረር ከ10 ሺ በላይ ህገወጥ ቤቶች ይፈርሳሉ


ታኀሳስ (ስምንትቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-የክልሉ መንግስት የሃማኖት፣ የእድር፣ የአፎቻ መሪዎችን፣ የአገር ሽማግሌዎችንና ታዋቂ ግለሰቦችን በራስ መኮንን የህዝብ አዳራሽ ታህሳስ 5 ቀን 2007 ዓም ሰብስቦ ባወያየበት ወቅት ፣ ከ1990-2004 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ የተሰሩ ቤቶች በሰነድ አልባ ቤትነት የተመዘገቡ እና ከከተማው ማስተር ፕላን ጋር የማይጋጩ ከሆነ ህጋዊ ይደረጋሉ፣ ከ2004 ዓም እስካሁን ካርታና ፕላን ለሌላቸው ከሊዝ ውጪ የተገነቡት ግን በሙሉ ይፈርሳሉ ብሎአል።
ስብሰባውን የመሩት የክልሉ ፍትህና ጸጥታ ጉዳይ ቢሮ ም/ል ሃላፊ አቶ ሳላሃዲን ቶፊቅ ፣  የከተማ ፕላንና ኮንስትራክሽን ሃላፊ አቶ ካሊድ አብዱረህማንና የኦህዴድ ተወካይ አቶ አብዲ ናቸው።
ባለስልጣናቱ ለውይይት ያነሱት መነሻ “ሐረር ከተማ ከሌላ አካባቢ በመጡ ሰዎች ተወራለች፤ መሬት በመወረሩ እና ህገወጥ ግንባታ በመስፋፋት ስርአት አልበኝነት ነግሷል፣ የክልሉ የቆዳ ስፋት እጅግ ጠባብ በመሆኑ መጪው ትውልድ መሬት የማግኘት መብቱን ያሳጣል፣ በአሁኑ ወቅት ከ10-30 ሺ ቤቶች ተገንብተዋል ” የሚሉት ይገኙበታል።
ህገ-ወጥ ግንባታ ተስፋፍቶባቸዋል ከተባሉት የከተማና ገጠር ወረዳዎች መካከል በዋነኝነት ከሶፊ ወረዳ ደከር፣ ከሐኪም ወረዳ ሐኪም ጋራ አካባቢ ገልመሺራ ቀበሌ፣ ከአቦከር ወረዳ ጊዮርጊስ አካባቢ፣ ከድሬጥያራ ወረዳ ፣ ወንዝ ማዶና መቆራን ተብለው የሚጠሩት አካባቢዎች ናቸው።
በስብሰባዎች ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎች በበኩላቸው ” ህገ-ወጥ የተባሉት ቤቶች ሲገነቡ መንግስት እያየ ዝም ብሎ አሁን ዜጎችን ማፈናቀልና በቢሊዮኖች የሚገመት ሃብትና ንብረት ማውደም ተገቢ ነውን? አብዛኛው ህገ-ወጥ ግንባታ የተፈፀመው በባለሥልጣናትና በቤተሰዎቻቸው ስለሆነ እነርሱ ምሳሌ ሆነው እንዲያፈርሱ ለምን አይደረግም ? ህገ ወጥ የተባሉት ቤቶች ሲገነቡ የማዘጋጃ ቤትና የከተማ ልማት ኃላፊዎች ከፍተኛ ብር እየወሰዱ የተፈፀመ ድርጊት በመሆኑ መንግስት ለምን ራሱን አይፈትሽም? ሙስና በፈፀሙት ላይስ እርምጃ ለምን አይወሰድም? ዜጎች መሬት ሲጠይቁ ዘርና ሃይማኖት እየተለየ ስለሚሰጥ ለህገ-ወጥነት መስፋፋት ምክንያት ሆነኗል፡፡ ለባለሥልጣናትና ለቤተ ሰዎቻቸው ከከተማ ማሰተር ፕላን ጋር የሚጋጭ ቦታ እየተሰጣቸው ካርታና ፕላን እንዲወስዱ በማድረግ ህጋዊ ይደረጋሉ፣ ይህ ለምን ይሆናል? ” የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል።
ባለስልጣናቱ ለተነሱት ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ሳይሰጡ ቀርተዋል። መንግስት ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው አፍራሽ ግብረሃይልና በፖሊስ ልዩ ሃይል አማካኝነት ከህዳር 25 ቀን 2007 ዓ/ም ጀምሮ የማፍረስ ዕርምጃ እየወሰደ ሲሆን ህብረተሰቡም በድርጊቱ ከፍተኛ ተቃውሞ እየገጠመው ነው፡፡                          sourse        esat radio

No comments: