Monday, December 8, 2014

በዘጠኙ ፓርቲዎች ሰልፍ ላይ የተወሰደውን ህገወጥ እርምጃ እናወግዛለን! (አንድነት ፓርቲ)


  • 101
     
    Share
አምባገነኑ የኢህአዴግ መንግስት ሰላማዊ ታጋዮችና በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማሳደዱን አሁንም ቀጥሎበታል። የዘጠኙ ፓርቲዎች ትብብር ለህዳር 27 ጠርተውት በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በመንግስት ኃይሎች የተወሰደውን እጅግ አረመኔያዊ የሆነ ህገ ወጥ እርምጃ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ በጥብቅ ያወግዛል።
እነዚህ ፓርቲዎች የሀገሪቱ ህገ መንግስት፣ የስብሰባና ሰልፍ አዋጁ በሚፈቅደው መሰረት ለአዲስ አበባ መስተዳድር ሰልፍ እንደሚያደርጉ ቀኑንና ቦታውን ጠቅሰው አሳውቀዋል፤ በአዋጁ መሰረት ደግሞ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ እንጂ ፍቃድ መጠየቅ ግድ የሚል አይደለም። ነገር ግን ህገ ወጥ በሆነ ሁኔታ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ከሰማያዊ ፓርቲ ፅህፈት ቤት እየወጡ የነበሩትን ሰልፈኞች በመንግስት ኃይሎች ከፍተኛ የሆነ ድብደባ እንዲፈፀምባቸው ተደርጓል። ከዚህም ባሻገር የትብብሩ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት አፍሶ በመውሰድ በጨለማ ክፍል ውስጥ አስሯቸው ይገኛል። ወዳጅና ዘመድ እንዳይጠይቃቸው መደረጉም የአንድነት ከፍተኛ አመራሮች ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ በትናንትናው ዕለት በአካል ተገኝተው አረጋግጠዋል። የአዲስ አበባ አስተዳደር ይሄ ጉዳይ በአግባቡና ህጉ በሚፈቅደው መንገድ መፍታት ሲችል፤ በሚዲያ እርምጃ እወስዳለሁ ብሎ ማወጁና በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ግፍ እዲፈፀም በማድረጉ ሀላፊነቱን መውሰድ አለበት። በተለይ ኢህአዴግ የ2007 ምርጫ እየቀረበ ባለበት ሁኔታ እንዲህ ዓይነቱ አፈናና ህገወጥ እርምጃ መውሰዱ ምርጫውን ችግር ውስጥ የሚከት ጉዳይ መሆኑ ሊገነዘብ ይገባል። አንድነት ፓርቲ ይሄ ጉዳይ በዝምታ የሚያየው ነገር አይሆንም፤ በቅርቡም አስፈላጊውን መረጃዎች ሁሉ አሰባስቦ ጋዜጣዊ ይሰጥበታል።
የዘጠኙ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን ሰላማዊ ሰልፍ የማድርግ መብት ከመጠቀም ውጪ ያጠፉት ምንም ዓይነት ነገር ስለሌለ በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል። ገዥው መንግስት ከህግና ከስርዓት ውጪ በሰላማዊያን ዜጎች፣ በፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ላይ እየወሰደ ያለውን አፈና፣ ድብደባና እስር እንዲያቆም፤ የህግ የበላይነትን፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እንዲያከብር አለም አቀፉ ማህበረሰብ ተገቢውን ጫና እንዲያሳድሩ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ ጥሪውን ያቀርባል። በተለይ ደግሞ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህ ህገወጥና አረመኔያዊ ድርጊት በዝምታ ሊያልፈው አይገባም፤ ኢህአዴግ በቃህ ሊለው ይግባል።
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ      
ህዳር 29 /03 /2007
አዲስ አበባ          sourse ze habsha
UDJ

No comments: