ሚያዝያ ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰሞኑን ከፍተኛ የደህንነት ሃላፊዎች ያስተላለፉትን ድንገተኛ ትእዛዝ ተከትሎ በፌደራል ፖሊስ አባላት የእጅ ስልኮችና የኢሜል አካውንቶች ላይ በተደረገ ፍተሻ፣ የተቃዋሚ መሪ ፎቶዎችን፣ አገራዊ ሙዚቃዎችንና ማንኛውም ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ከኢንተርኔት አውርደው በስልካቸው ላይ ያስቀመጡ ፖሊሶች ተይዘው የተወሰኑት ማእከላዊ ሲገቡ፣ የተወሰኑት ደግሞ ጃንሜዳ አካባቢ በሚገኝ እስር ቤት መታሰራቸውን የፖሊስ ምንጮች ገልጸዋል።
በድንገት የተደረገውን ፍተሻ ተከትሎ በአጠቃላይ ከ120 ያላነሱ ፌደራል ፖሊስ አባላት ሲታሰሩ፣ በፍተሻው በቀጥታ የተቃዋሚ መሪዎች ፎቶዎች ወይም ፖለቲካ ነክ የያዙ ጽሁፎች የተገኙባቸው 37 የሚሆኑ ፖሊሶች ማእከላዊ ተወስደው ታስረዋል።
ከ80 በላይ የሚሆኑት ደግሞ አጠራጣሪ የሆኑ ጉዳዮች አሉ በሚል ለተጨማሪ ምርመራ ጃን ሜዳ አካባቢ በሚገኝ ማቆያ እንዲታሰሩ ተደርጓል።
የፌደራል ፖሊስ አዛዦች የሚሰጡትን ትእዛዝ ላለመቀበል ያንገራግራሉ ተብለው አስቀድመው በተለዩ ፖሊሶች ላይ ደግሞ ክትትሉ መጨመሩን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በዚህም መሰረት በአርማጭሆና ሰሜን ጎንደር የጸረ ሽብር ግብረሃይል ሃላፊዎች የሆኑት ኢንስፔክተር ስንታየሁ፣ ሳጅን አበበ እና ም/ል ሳጅን ብርሃኑ ተይዘው ወደ ማእከላዊ ተወስደዋል።
በእስር ላይ የሚገኙት የግንቦት7 ዋና ጻሃፊ የአቶ አንዳርጋቸውን ፎቶ ግራፍ በብዙ ወታደሮች ሞባይል ስልኮች ላይ መገኘቱን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
ከድምጻውያን ደግሞ የቴዲ አፍሮ፣ የብርሃኑ ተዘራና የፋሲል ደሞዝ ሙዚቃዎችን ከኢንተርኔት አውርዶ ማዳመጥ ኢህአዴግን እንደመክዳት እያስቆጠረ ነው ተብሏል።
በተመሳሳይ ዜና ድሬዳዋ ውስጥ በበረራ አስተማሪነት ይሰሩ የነበሩ ሁለት መኮንኖች ሰሞኑን ተይዘው ማእከላዊ መታሰራቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። ስማቸውን እስካሁን ለማወቅ ባይቻልም፣ አብራሪዎቹ ቀድም ብሎ ከታሰሩት 4 አብራሪዎች ጋር ግንኙነት ነበራችሁ ተብለው መታሰራቸው ታውቋል።
የኤም 35 ተዋጊ ሄሊኮፕተር የበረራ አስተማሪ የነበረው የሻለቃ አክሊሉ መዘነ ወንድም ሰይፉ መዘነም ማእከላዊ ታስሮ በመሰቃየት ላይ ነው። የቀድሞው አንድነት ፓርቲ የአመራር አባል የነበረው መሳይ ትኩም ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰበት ነው።
ገዢው ፓርቲ በደህንት ተቋማት ላይ ያለው ጥርጣሬ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍ እያለ መምጣቱን የሚናገሩት ምንጮች፣ ተጨማሪ ፍተሻዎች፣ ድንገተኛ ግምገማዎችና እስሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገልጻሉ።
የጥርጣሬው መነሻ ምን እንደሆነ በውል ለማወቅ አልተቻለም። ይሁን እንጅ ስራቸውን እየለቀቁ የሚጠፉ የፌደራል ፖሊሶች ቁጥር መጨመር ስርአቱን ስጋት ላይ ሳይጥለው እንደማይቀር ምንጮች ይገልጻሉ።
No comments:
Post a Comment