* “ወደ አገራቸው መመለስ ለሚፈልጉት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን” ቴድሮስ አድሃኖም
በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ አፍሪካውያን ላይ የተጀመረው ጥቃት ያስቆጣቸው የናይጄሪያ እንደራሴዎች በደቡብ አፍሪካ የሚገኙት አምባሳደር ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ውሳኔ አስተላለፉ፡፡ የሩዋንዳውን ፕሬዚዳንት በማስተናገድ የተጠመዱት ጠ/ሚ/ር ሃይለማርያም ደሳለኝ በደቡብ አፍሪካ “የተፈጠረው ጊዜያዊ ችግር ነው ብለን እናምናለን” በማለት አስተያየት ሰጡ፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚ/ር ቴድሮስ ከየቦታው ሃሳብ እየሰበሰብኩ ነው፤ “ወደ አገራቸው መመለስ ለሚፈልጉ ድጋፍ እናደርጋለን” አሉ፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ግን የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡
ሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ የተነሳው አሰቃቂ ግድያና ዘረፋ ብዙዎችን እኤአ በ2008 የተከሰተውን እንዲያስታውሱ አድርጓቸዋል፡፡በወቅቱ ከስድሳ በላይ አፍሪካውያን የተገደሉና የበርካታዎች ንብረት የተዘረፈ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ሰሞኑን በተነሳው ሁከት ሶስት ኢትዮጵያውያን መሞታቸውንና አስከሬናቸውን ወደ ኢትዮጵያ መላኩን ከዚያው የወጡ መረጃዎች ቢጠቁሙም የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ግን የሞተው አንድ ብቻ ነው ማለታቸውን ኢቲቪ ዘግቧል፡፡
ከኢትዮጵያውያኑ ሌላ ዜጎቿ እንደሞቱባት የምትጠቀሰው ናይጄሪያ በድርጊቱ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅቶች እያደረገች መሆኑ ተሰምቷል፡፡ የናይጄሪያ እንደራሴዎች በደቡብ አፍሪካ ላይ የከረረ እርምጃ እንዲወሰድ እየሞገቱ ነው፡፡ የናይጄሪያ ተወካዮች ምክርቤት በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ካደረገ በኋላ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙት የናይጄሪያ አምባሳደር ወደ አገራቸው እንዲመጡ አጽድቋል፡፡
በኢትዮጵያ ጉብኝት የሚያደርጉትን የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት እያስተናገዱ ያሉት ሃይለማርያም ደሳለኝ በደቡብ አፍሪካ የደረሰውን በተመለከተ በእንግሊዝኛ ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡ ጠ/ሚ/ሩ ታሪክን የዘነጋ በሚመስል ለስላሳ አነጋገር “ደቡብ አፍሪካ ከቅኝ አገዛዝም ሆነ ከአፓርታይድ አገዛዝ ነጻ እንድትወጣ ድጋፍ መስጠታችን ይሰማናል” በማለት አጭሩን ንግግራቸውን አሰምተዋል፡፡ ሲቀጥሉም “አፍሪካውያን በፈለጉበት መኖር” እንደሚችሉ ከገለጹ በኋላ “አሁን የተፈጠረው ጊዜያዊ ክስተት ነው ብለን እናምናለን፤ የደቡብ አፍሪካ መንግሥትና ፓርቲ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ እንጠብቃለን” በማለት ወደ ግብዣቸው ተመልሰዋል፡፡
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት አራተኛዋ ባለሥልጣን የሆኑትን የበታች ጸሃፊ ዌንዲ ሸርማንን በማስተናገድ የተጠመዱት ቴድሮስ አድሃኖም በፌስቡክ በለቀቁት አጭር መልዕክት “በደቡብ አፍሪቃ ከሚገኙ አንዳንድ ወገኖች” ጋር በስልክ እየተነጋገሩ መሆናቸውን እና ምን መደረግ እንዳለበት ከየቦታው እስካሁን ሃሳብ በመሰብሰብ ሥራ ላይ መጠመዳቸውን
የሚገልጽ እንደምታ ያለው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ “ወደ አገራቸው መመለስ የሚፈልጉትን” ለመደገፍ መዘጋጀታቸውን በዚሁ መልዕክት ገልጸዋል፡፡
ነዋሪዎችን ከየመኖሪያቸው በማፈናቀል፤ መኖሪያ በማሳጣት እና በግዳጅ ባልፈለጉበት ቦታ በማስፈር የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙ በተለያዩ ዘገባዎች በማስረጃ የሚነገርለት ኢህአዴግ ወደ አገር ለመመለስ ለሚፈልጉ ዝግጅቱ ማድረጉን ቢገልጽም በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ግን ሁኔታው አስፈሪ ቢሆንም ወደ አገራቸው መመለስ እንደማይፈልጉ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ አንዳንዶችም “ከአገራችን የወጣነው የኢኮኖሚ ጥገኝነት አስገድዶን ብቻ አይደለም፤ የመኖር ኅልውናችን አደጋ ላይ በመውደቁም ጭምር ነው” ሲሉ ተሰምተዋል፡፡
ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ እንዳሉት “ደቡብ አፍሪካውያን ኢትዮጵያዊ ስለተባልን አገር ያለን መስሏቸው ከአገራቸው እንድንወጣ ይነግሩናል፤ በህይወት እያለን ወደ ኢትዮጵያ ሄደን በደኅንነት መኖር ስለማንችል እኮ ነው ስንሞት አስከሬን የምንልከው፤ ይህንን ግን የተረዱት አይመስለኝም” በማለት ሃሳባቸውን ተናግረዋል፡፡
“ደቡብ አፍሪካውያን አንድ ነጭ በህይወት እያለ በጥፊ ለመምታት ሙከራ እንኳን ስለማያደርጉ (ስለሚፈሩ) ነጭ ሲሞት ሃውልቱን ይደበድባሉ፤ ነገር ግን አንድ ጥቁር የሌላ አገር ዜጋ በመሆኑ ብቻ በድንጋይ ወግረው ይገድላሉ፡፡”
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
No comments:
Post a Comment