(ዘ-ሐበሻ) ISIL ወይም ISIS በሚል የሚታወቀው ቡድን በሊቢያ 30 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን ግማሹን በማረድ ግማሹን በጥይት መግደሉን በለቀቀ ቪዲዮ አስታወቀ::
ISIL በለቀቀው የ29 ደቂቃ ቪዲዮ በሊቢያ ሁለት ግዛቶች ውስጥ ማለትም ባርካ እና ፋዛን ከተሞች ውስጥ እነዚህን ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በጥይት እንዲሁም ሌሎቹን ሲያርዷቸው አሳይቷል::
ማስክ ያጠለቁት እነዚሁ የISIL አባለት ኢትዮጵያውያኑን የያዟቸውና ከላይ በተጠቀሱት ከተሞች ሕይወታቸውን ያጠፉት ከምስራቅ እና ደቡብ ሊቢያ እንደተያዙ ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ ይጠቁማል:: ክርስቲያኖቹ ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ አልያም የተለየ ታክስ እንዲከፍሉ ከመታረዳቸውና ከመገደላቸው በፊት እንደተጠየቁ የዘገበው አሶሺየትድ ፕሬስ ኢትዮጵያዊያኑ በባህር ዳርቻ አካባቢ ሕይወታቸው ተቀጥፏል ብሏል::
በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሰሃራ በረሃን በማቋረጥ ሊቢያ በሚገቡበት ወቅት ለበርካታ ችግሮች በተለይም ለተገዶ መደፈር; ለኩላሊት መሰረቅ እንዲሁም ለመገደልና ለመታሰር ሲበቁ ቆይተዋል::
ISIL የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ በርካታ አስተያየቶች እየተሰጡ ሲሆን ጋዜጠኛና አክቲቭስት አበበ ገላው በፌስቡክ እጹ የሚከተለውን አስፍሯል::
ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ወያኔ ነው!
በየመንና በደቡብ አፍሪካ የተከሰተው ሰቆቃ ሳያንሰን ዛሬ ደግሞ በሊቢያ ISIS ኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖችን ሰብስቦ ማረዱን አረዳን። ኢትዮጵያዊው በአገሩ ክብርና መብት ተነፍጎ፣ በአስከፊ ድህነት ይሰቃያል፣ ከመሬቱ፣ ከቤቱ ከቀዬው ይፈናቀላል፣ ታፍኖ በየእስር ቤቱ ይታጎራል፣ ይገደላል፣ በሃሰት ይከሰሳል፣ ሰቆቃ ይፈጸምበታል። የተሰማኝ ሃዘን ጥልቅ ነው። ቸሩ አምላክ የነዚህን ምስኪን ሰማእታት ነፍስ ይታደግልን፣ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ይስጥልን።
በስደትና በሽሽት ምድር ተዋርዶ መኖር ሳይበቃው በቁሙ ይቃጠላል፣ እንደ በግ ይታረዳል። የዚህ ሁሉ ችግር ዋነኛ መንስኤ ወያኔዎች ኢትዮጵያን ለጥቂቶች ምድራዊ ገነት ለብዙሃኑ ደግሞ ምድራዊ ሲኦል በማድረጋቸው ምክንያት መሆኑ ህሊና ላለው ሁሉ ግልጽ ነው። ለአንድ ህዝብ ከዚህ የከፋ የቁም ሞት የለም። ኢትዮጵያዊ ሁሉ በያለበት በቃ ብሎ የሚነሳበት ግዜ አሁን ነው። አገሩን ያላስከበረ ትውልድ ከዚህም የከፋ ይገጥመዋል። ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ወያኔ ነው። በቃ ብለን በአንድነት የምንነሳበት ግዜ አሁን ነው። ሊነጋ ሲል ይጨልማል!
No comments:
Post a Comment