Friday, February 19, 2016

እኔንም ታዘብኩት (ሀገሬ)

እኔንም ታዘብኩት (ሀገሬ)

ሀገሬ
ሰሞኑን በኃይሌ ገብረሥላሴ ላይ በስጨትጨት ብለው ከተናገሩት መሀል አንዱ ነኝ። በ”ይቻላል” አባባሉና ተግባሩ የምናውቀውና ጥሩ አርአያ ይሆናል የምንለው ጀግናችን አፍሪካ ውስጥ ዲሞክራሲን መመኘትን በ”ትለበሰው የላት ትከናነበው አማራት” ፈሊጥ አይነት ማስቀመጡ በእርግጥም አስከፍቶኛል። የሕዝባችን ሰብአዊ ክብርና የዜግነት መብት መጠበቅ በይደር የሚተው አይደለም። ከዘላለም ባርነት ያንድ ቀን ነጻነት ይባል የል! እንዴት ነው 25 አመት ሙሉ ከአንድ መንደር በመጡ ወያኔዎች መረገጥን ቻሉት የሚባለው? ኃይሌ የሚሳተፍባቸውን ውድድሮች በአሸናፊነት መወጣቱን እንደራሳችን ድል በመቁጠር ውድድሩ ተጀምሮ እስኪያልቅ እንጨነቅ የነበርን፣ ሲያሸንፍ የምንቦርቅ፣ ሲሸነፍ ወይንም ውድድር ማቋረጥ ሲገደድ ከልብ የምናዝን በርካታ ነበርን። ተፎካካሪው ቀነኒሳም እንኳን ቀድሞ መግባት አላስችል ብሎት ወደኋላ መለስ እያለ በማየት ሲጠብቀው አልነበር? ታዲያ በዚህ ደረጃ የኛ ነው ያልነው አትሌት ዛሬ ስንት መስዋእትነት የሚከፈልበትን የዲሞክራሲ ህልም “ቅንጦት” እያለ ሲያጣጥል እንዴት አልዘን?
ኃይሌ ፖለቲካ ውስጥ መግባት መከጀሉን ሲጠቁመንም አመታት ቆጥረናል። ለቢቢሲው ጋዜጠኛ ሲመልስልትም “አሁን ተዉኝ ንግዱንም፣ እርሻውንም፣ ሆቴሉንም፣ ወርቅ ማእድኑንም ላትርፍባቸውና ከዛ በኋላ ፊቴን ወደ ፖለቲካ እመልሳለሁ” ያለ መሰለኝ። የዚህ ስሌት መሰረቱ አሁን ብፈልግም እነአቦይ ስብሀት አይሰጡኝም የሚል ፍርሀት ይሁን ወይንም አሁን በሀብት ማካበቱ ላይ ልትጋና ፖለቲካው ላይ ወደኋላ እደርስበታለሁ ማለቱ እርግጠኛ አይደለሁም። ፖለቲካውን የሚፈልገው ሕዝብን ለማገልገል ከሆነ የሀገራችን ሰው “እኔ የምሞተው ዛሬ ማታ እህል የሚደርሰው ለፍልሰታ” የሚለውን አይዘንጋ። አንዱ የፈረንጆቹ የምጣኔሀብት ባለሙያም “በረጅም ጊዜ ውስጥ ሁላችንም እንሞታለን” (In the long-run we are all dead) ብሏል አሉ። ሁለቱም አባባሎች ዛሬ መወሰድ ያለበትን እርመጃ ለነገ ተነጎዲያ እየተባለ ማጓተት ችግር ሊያስከትል እንደሚችል የሚያሳስቡ ናቸው። ይህን ስል በጭራሽ ኃይሌ ዛሬውኑ ፖለቲካ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ይኑረው ለማለት አይደለም። ያውሳኔ የኃይሌና የቤተሰቦቹ ብቻ ነው። ደግሞም ፍላጎቱ በስልጣን ማገልገል ሳይሆን መገልገልና ዝና ማትረፍ ከሆነ አለምግባቱ ይመረጣል። ግን ዛሬ ዳቦን ብቻ እናስብ ዲሞክራሲ ቅንጦት ነውና እሱ ሆድ ከሞላ በኋላ ይደረስበታል አይነት አባባሉን አይድገመው ነው ምኞቴ። ምክንያቱም ይህ ሀሳብ እራስን ከትግል ከማሸሽ ባሻገር ሌላውንም ትጥቅ አስፈቺ ነው።
አሁንም ኃይሌን እየወቀስክ ይመስላል። ታዲያ እራስህን የምትታዘብበት ምክንያት ምንድን ነው ትሉኝ ይሆናል። እራሴን የታዘብኩት በሁለት ነገር ነው። መጀመሪያ ትኩረቴ “ዲሞክራሲ ቅንጦት ነው” የሚለው አባባሉ ላይ ሆነና የተናገረውን ጥሩ ጥሩ ነገር ዘለልኩት። ለምሳሌ “መልካም አስተዳደር ቢኖረን አፍሪካ የት በደረሰች” ሲል የክፍለአለማችንና የሀገራችን የእድገት ማንቆ የመልካም አስተዳደር እጦት ነው ማለት ነው። በተጨማሪም “አንድ ሰው ወይንም አንድ ወገን ህልጊዜ እኔ ብቻ መሪ ልሁን ማለቱ ትክክል አይደለም” ብሏል። የዚህም ፍሬ ሀሳብ ዘላለም እንምራ ከሚሉት ወያኔዎች ባሻገር የላቅ ብቃት ያለቸው መሪዎች አሉንና እነሱም እድል ይሰጣቸው ከማለት የተለየ አይደለም። ሀገርን ከእናት ጋር በማነጻጸር “እናትህ መጥፎ ባህሪይ ስላሳየችህ እናትነቷን አትክድም” ያለውም ልብ የሚነካ አባባል ነው። ይህም በግልጽ የሚጠቁመው ሀገራችን አሁን ባለችበት ሁኔታ ብዙ ችግር ያለባት ቢሆንም ከነቢሮክራሲው የመልካም አስተዳደር እጦት ሀገሬ እናቴ ናት ማለቱን ነው። ይህም የነቢዩ መኮንንን  “ሀገርህ ናት በቃ” ጽሁፍ አስታወሰኝ። https://www.youtube.com/watch?v=D0G5qs7wPvk
እናም ጨካኝ ወያኔዎች በሞሉበት ምድር ሀብቱን ለመዝረፍ ያሰፈሰፉ ጆፌ አሞራዎች በሞሉበት ምድር ላይ ሁኖ ኃይሌ ዲሞክራሲ ቅንጦት ነው ስላለ ቅሬታዬን ያለማመንታት የገለጽኩት ሰው እንዴት ነው ለሃያአምስት አመታት ህዝባቸን አሳሩን ሲበላ ትንፍሽ የማይሉትን ከወያኔ በጣም ርቀው አሜሪካና አውሮፓ የሚኖሩ “ምሁራንን” ምነው ዝምታችሁ ምነው ወያኔን መደገፋችሁ ብዬ አለመጠየቄ ነው ሌላው እራሴን ታዘብኩት ያሰኘኝ።
እነኃይሌ ሲያሸንፉ እንደምንደሰተው ኢትዮጵያዊ ምሁር በሙያው እውቅናና ሽልማት ሲያገኝ እንፈነድቃለን። ዶክተር እከሌና ዶክተር እከሊት ታላቅ ሳይንቲስት ተባሉ፣ እነእከሌ ለአለም አቀፍ ድርጅት በመሪነት ተሾሙ፣ እከሊት ታላቅ ሰአሊ ተባለች፣ እከሌ ታላቅ ሼፍ ተባለ፣ እከሊት ታላቅ ሞዴል ተባለች እረ ስንቱ አንቱ በተባለ ቁጥር ፈንጥዘናል። ይሀው ዛሬም መሰረት ደፋርና ገንዘቤ ዲባባ የሩጫ ባለድል ሆኑ መባሉንና የካናዳው አቤል ተስፋዬ ግራሚ ሽልማት አገኘ የሚለውን ዜና በየአምዱ እያነበብን እየተደስትን ነው። የወገን ድል የኛም ድል ነው በሚል ስሜት።
ሕዝባችን ለነጻነትና እኩልነት የሚያደርገውን ትግል በተመለከት ደካማ አስተያየት የምንሰማው አንዱ ጸሀፊ እንዳለው “ታዋቂነት አዋቂነት ከሚመስላቸው” ብቻ አይደለም። በሙያቸው አንቱ የተባሉ በኢትዮጵያ የከበሩና የተከበሩ የቢሮዋቸው ግድግዳና መደርደሪያ በዲግሪና በተለያዩ ሽልማቶች የተጨናነቀባቸው “አዋቂዎች” ናቸው ዛሬ የወገንን መከራና ሰቆቃ “በፖለቲካና ኮረንቲ በሩቅ” አይነት ተልካሻ ምክንያት በዝምታ የሚያልፉት። በቅርብ አንዱ አርቲስትም ቃለ ምልልስ ላይ “ፖለቲካንና ሙያን ማደባለቅ ፍጹም ስህተት ነው” ሲል ሰምቼው ነበር። ሙያ የሚተገበረው ህብረተሰቡ ውስጥ ነው። ህብረተሰብ ላይ በጎና ክፉ ተፅእኖ የሚያደርገውን በሙሉ አይመለከተኝም እያሉ ሸቃጭ እንጂ እንዴት ባለሙያ እንደሚኮን አይገባኝም።
ታዲያ እኛ ስኬታችሁ ስኬታችን ነው የምንላቸው በተለይም ደሀው የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍሎ አስተምሮ ለከፍተኛ ማእረግ ካበቃቸው ምሁራን መሀከል በጣት የሚቆጠሩት ብቻ የህዝቤ ህመም የኔም ህመም ነው ማለታቸው ለምንድን ነው? እነሱ ሲሳካላቸው እኛ በደስታ እንዘፍንላቸዋለን፣ አክብረን መቀመጫችንንም እንለቅላቸዋለን፣ ወደድ ያለ ውስኪም ይዘን “እንኳን ደስ አለን!” ለማለት ከቤታቸው ጎራ እንላለን። እኛ ስናለቅስ እነሱ የታሉ ነው የኔ ጥያቄ። ክፍል ውስጥ ስለነጻነት አስፈላጊነት ስለህግ የበላይነት ስለመልካም አስተዳደር ግድ ማለት ፈላስፋ እያጣቀሱ በስሜት ያስተምራሉ። ነገርግን ህዝባቸው ከግፍ ሰንሰለት እንዲፈታ ቅንጣት ታክል አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ አይታዩም። ሌላው ለመብቱ ለነጻነቱ መታገል መብቱ ብቻ ሳይሆን ሰብአዊ ግዴታውም ጭምር እንደሆነ ክፍል ውስጥ ይሰበካል ወደራስ ዘንድ ሲመጣ ግን “ጎመን በጤና” ይመረጣል። አጋዚን የሀገራችን ሕዝብ “የቤት አንበሳ የውጪ እሬሳ” እንደሚለው መሆኑ ነው።
እነኚህ ምሁሮችም ወይ ሀገርቤት ለመጦሪያ የቀለሷት ቤት እንዳትወሰድባቸውና ኢትዮጵያ ተዝናንተው መምጣት ወያኔ እንዳያግዳቸው በመፍራት ዝምታን መርጠዋል። ከዚህ የከፉም አሉ። በርካታ አመታት ትምህርትቤት አሳልፈው የዕውቀት ጠርዝ ላይ ደርሰናል የሚሉ ግን “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይበቀል” አለች ከምትባለው እንስሳ ባነሰ አስተሳሰብ ወገናቸውን ለሚያሰቃየው ወያኔ ገንዘብ ለማሰባሰብ ቶምቦላ የሚያሻሽጡ ማፈሪያ ዶክተሮች አሉን አሉ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ፡፡ ወያኔም እንዲህ በኮንዶሚኒየምና መዋእለንዋይ እንቁልጭለጭ “ማኖ” እያስነካ ትልልቁን ዳቦ ሊጥ ያደርገዋል።
ዶክተር ብርሀኑ በቅርብ አሜሪካ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያውያን ልሂቆች ከተደበቁበት ወጥተው የሀገሬና የህዝቤ ጉዳይ ያገባኛል ብለው መነሳት እንዳለባቸው አሳስበዋል። ሌላው ሞቶ ነጻ ባወጣት ምድር ላይ ከበርቴ ሁኖና አንቱ ተብሎ መኖርን ማለም ብልህነት ሳይሆን ሌላውን ገድሎ መኖር የሚከጅል ደም መጣጭ መዥገርና ፓራሳይት መሆን ነው። እርግጥ ነው በታሪካችን ለሀገር የቆሰለውና የሞተው ተረስቶ ከሀዲ ባንዳ የተሾመበት ጊዜ ብዙ ነው። ዛሬም ቢሆን ኢትዮጵያችን ውስጥ ለአንድነቷ ሲዋጉ የነበሩት ለማኝ ሁነው ሀገሪቱን ለማፍረስ ያሴሩ ባንዳ የባንዳ ልጆች ተሹመው ይፈነጩባታል። ለዚህም ነው “ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” የሚለው አባባል ዛሬም ወቅታዊ የሆነው። ነገርግን ህሊና ላለው ሰው ከሀዲ ባንዳ ተብሎ ሆድን ከመሙላት ሀቀኛ ጀግና ተብሎ በገንዘብ ችግር መኖር ይመረጣል። ለዚህም ኩሩው የሚሊሺያ አሊ በርኬ ታሪክ ታላቅ ምስክር ነው። ለጊዜያዊ ጥቅም ሲል ክብሩንና ሀገሩን ያዋረድ ሆዳም መባልን እንፍራ እንጥላ።
(It takes to Tango) ታንጎ ለመደነስ ሁለት ሰው ያስፈልጋል እንደሚባለው ምሁሮቻችንን የኛ እንድንላቸው እንሱም እኛን የኛ ይበሉን። እንድናከብራቸው እንድንወዳቸው እንድናወድሳቸው የኛን ችግር እንደ ባዕድ ከርቀት ሁነው ስራችሁ ያውጣችሁ ማለቱን ትተው መፍትሄ ፍለጋው ላይ አብረው ይስሩ።

1 comment: