P.O.Box 9929 Alexandria, VA 22304 Tel: 1-206-203-3375 Tel: +44-7958-487-420 Email: contact@etntc.org Website: www.etntc.org January 6, 2014 January 6, 2014 January 6, 2014 ለውድ ሀገርወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ብሄራዊ ውርደት አጥልቶባታል። ህዝባችን በሀገር ውስጥና በስደት ለአሰቃቂ ግፍና በደል ተዳርጓል። በአሁኑ ሰዓት ለኢትዮጵያ የቆመ መንግስት የለም። ይህን ሁኔታ ለመቀየር ጸረኢትዮጵያ የሆነውን የወያኔ-ኢህአዴግ ስርዓትን አስወግዶ ሁሉንአቀፍ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ብቸኛ መፍትሄ እንደሆነ የኢትዮጵያ የሽግግር ምክርቤት ያምናል። የሽግግር ምክር ቤቱ ከተነሳበት አላማ ጋር ተያይዞ የአምባገነናዊነት አዙሪት በአገራችን ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይሰበር ዘንድ ስርዓቱ ተወገዶ የሽግግር መንግስት የሚቋቋምበት ሂደት ላይ እየሰራ ይገኛል። ይዋል ይደር እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ ማሸነፉና የወያኔ ጸረ-ኢትዮጵያ ስርዓት መገርሰሱ አይቀሬ ነው። በተደጋጋሚ በታሪካችን እንዳየነው ይሄኛው ሄዶ በሌላ አምባገነን የሚተካበት ዘመን እንዲያቆም ነው ጥረታችን! ከላይ የተዘረዘረውን ለመተግበር ከተደረጉት ጥረቶች አንዱ ባለፈው ጁላይ 2013 ዓ/ም (እኤአ) የመጀመሪያውን ዙር የምክክር ጉባኤ በማዘጋጀት በርካታ የድርጅት ተወካዮች፥ ምሁራንና ታዋቂ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አስከፊ ስርአት በማስወገድና ከተወገደ በኋላ በምን ሊተካ እንደሚችል በቀረቡ አማራጮች ላይ ለ2 ተከታታይ ቀናት ውይይትና ምክክር በማድረግ፤ በተባበረ ሃይልና በተቀናጀ ህዝባዊ ትግል ስርዓቱን አስወግዶ ወደዴሞክራሲ መንገድ የሚወስድ ሁሉን አቀፍ ህዝባዊ የሽግግር መንግስት የማቋቋም አስፈላጊነትና ለዛም የሚደረገው ዝግጅት ከአሁኑ መጀመር እንዳለበት ስምምነት ላይ መደረሱ በወቅቱ በተለያዩ ዜና ማሰራጫዎች ተገልጿል። በዚህም መሰረት ከጸደቁት የተግባር መርሐግብሮች መካከል በሽግግሩ ወቅት በሚኖረው ህገመንግስት (ቻርተር) የማርቀቅ ስራን ለመጀመር ነበር። የሽግግር ወቅት ወሳኝ ጊዜ ነው። ካሁኑ ዝግጅት ካልተደረገ በሌሎች ሀገሮች እንደታየው ለውጥ ቢመጣም የመጣውን ለውጥ እንደወያኔ ባሉ መሳሪያ ያነገቱ አምባገነኖች የስልጣን መወጣጫ እንደሚያደርጉት አያጠራጥርም። ሀገራችን ወደ መልካምም ይሁን መጥፎ አቅጣጫ ልትጓዝ የምትችለው በዚህ ወሳኝ የሽግግር ወቅት በሚፈጠሩ ክስተቶች ይሆናል። በመሆኑም በሽግግር ወቅት የሽግግር መንግስት ሊመራበት የሚገባውን ህገመንግስት (ቻርተር) ህዝብ ተወያይቶበትና መክሮበት ሊያጸድቀው ይገባል። ከአሁኑ ተወያይተንበትና ተማምነንበት ያጸደቅነው ሰነድ ወያኔ በፈጠራቸው የዘር፤ የሃይማኖትና የኢኮኖሚ ልዩነቶች ሊደርሱ የሚችሉ አለመግባባቶችን ያስወግዳሉ። ይህንን የሽግግር መንግስት ቻርተር ረቂቅ (draft) ለህዝዊ ውይይት ከማቅረባቸን በፊት ለበርካታ ምሁራን ለተለያዩ ድርጅቶች ማሰራጨት ጀምረን ሰንዱ ከደረሳቸው ከብዙዎቹ አስተያየት በመቀበል ላይ እንገኛለን። ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ደግሞ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እና ሌሎችም ዘዴዎች ተጠቅመን የሽግግር ህገመንግስቱ ረቂቅ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲደርስ በማድረግ ላይ እንገኛለን። ከዚህ በተጨማሪ በዚህ ረቂቅ ዙርያና ስለወደፊቱ የመንግስት ቅርድ፥ እንዲሁም ስርዓቱን በተባበረ ሃይል አስወገዶ በሽግግር መንግስት በመተካት ዙርያ ባሉ ፍሬ ሀሳቦች ላይ ለመምከርና የጋራ አቋምና የስራ እቅድ ለማውጣት የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክርቤት ሁለተኛውን ሁሉን አቀፍ የምክክር ጉባኤ የፊታችን ጥር 17 ቀን 2006 ዓ/ም (January 25, 2014) በዋሽንግተን ዲሲ አዘጋጅቷል። ከዚህ በተጨማሪ በጥር 18 ቀን 2006 (January 26, 2014) የምክክር ጉባኤውን ውጤት ለማሳወቅና ውይይት ለማድረግ ህዝባዊ ስብሰባ በዋሽንግተን ዲሲ ይደረጋል። ይህ ረቂቅ በእጃችሁ እንደገባ ለሌሎች ሀገርወዳድ ኢትዮጵያን በማሰተላለፍና በጽሞና በማንበብ አስተያየታችሁንም ከታች በተጠቀሰው የኢሜይል አድራሻ በመላክ የሽግግር ሂደቱ ተሳታፊ እንድትሆኑ ሀገራዊ ጥሪ እናቀርባለን። የቻርተሩ ረቂቅ በሀገር ውስጥ እና በዓለም ዙሪያ ባሉ ኢትዮጵያውያን ሰፊ ውይይት ከተደረገበት እና የሚቀርቡትን ሃሳቦች ካሰባሰብን በኋላ የህዝብ ተወካዮች ለሚሳተፉበት የህገመንግስት አርቃቂ ጉባኤ ለውሳኔ ይቀርባል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሽግግር ምክር ቤት የኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ህገመንግስትከኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት ለውይይት የቀረበ ረቂቅ December 2013 * ማስታወሻ፤ ይህ ሰነድ ረቂቅ ሲሆን የሚጸድቀው በህገመንግስት ጉባኤ ነው መግቢያ እኛ የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች በአንድነት እና በነፃነት ለመኖር እንዲቻለን፣ የጎጠኝነት ጠባሳዎቻችንን፣ ከጎሳ ፖሊሲና ስርዓት ጋር ለማጥፋት፣ በሥልጣን ላይ ባለው ኣምባገነናዊ መንግሥት የተነጠቅነውን ነፃነታችንን ለማስመለስ፣ መከፋፈልንና አክራሪነትን በመጣል በልዩነቶቻችን ላይ የተመሠረተ ጠንካራ አንድነት ለመገንባት፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተጣሉትን ጅምላ የሰው ልጆች መብት ረገጣዎች እየተገነዘብን ዴሞክራሲን፣ የሀግ የበላይነትን፣ ፍትህን እና ሌሎች የዲሞክራቲክ ተቋማትን በኢትዮጵያ መልሶ የማቋቋምን እና የማምጣትን አስፈላጊነት በማመን፣ ብሄራዊ እርቅን፣ አንድነትን እና መልካም አስተዳደርን ለማምጣት በቁርጠኝነት በመነሳት፣ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት መሥራች እንደ መሆንዋ የኢትዮጵያን ዓለማቀፍ ህግ አክባሪነት በማረጋገጥ፣ አዲስ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ይህን የሽግግር ወቅት ህገመንግስት አፅድቀን ለኢትዮጵያ ህዝብ አስረክበናል። ይህ የሽግግር ወቅት ህገ-መንግስት የተቀረጸው በህዝብ ዕውቅና የተሠጠውንና ሙሉ ዴሞክራሲን የሚያጎናጽፈውን ቋሚ ህገ-መንግሥት የሚያከብር፣ በህግና በነፃ ምርጫ የተመረጠ መንግሥት እስከሚመሠረት ድረስ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ነው። ምዕራፍ 1 - መሠረታዊ መርሆዎች አንቀጽ 1 ሀ) ይህ ህገመንግስት (ቻርተር) “የኢትዮጵያ መንግሥት የሽግግር ጊዜ ህገመንግስት” ተብሎ ይጠቀሳል፣ ይህም ቃል (ሃረግ) “ይህ ቻርተር” በተጠቀሰበት ቦታ ሁሉ “የኢትዮጵያ መንግሥት የሽግግር ጊዜ ቻርተር” ተብሎ ትርጉዋሜ ይሰጠዋል። ለ) ፆታ የተገለጸበት የቋንቋ አጠቃቀም ሲያጋጥም በወንድ ፆታ የተደነገገው ለሴትም ፆታ በእኩልነት ያገለግላል። አንቀጽ 2 ሀ) ይህ ቃል “የሽግግር ጊዜ” የሚገልጸው ከ ________ ጀምሮ ቋሚ ቻርተሩን ተከትሎ የሚመረጠው ህዝባዊ መንግሥት እስከ ተመሠረተበት ድረስ ያለውን ጊዜ ይሆናል፣ በዚህ የሽግግር ወቅት ህገመንግስት ውስጥ እንደተጠቀሰውም በምዕራፍ 9 የተቀመጠው ደንብ እስካልተፈጸመ፤ የሽግግር ጊዜው ከ _______በፊት ይጠናቀቃል። ለ) የሽግግሩ ጊዜ በሁለት ክፍሎች ይከፈላል 1) የመጀመሪያው ክፍል የሚጀምረው ሉዓላዊ የሆነ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት አስተዳደርን በ _______ቀን _________ዓ/ም በመመሥረት ነው። ይህ የሽግግር መንግሥት አስተዳደር የሚመሠረተውም የኢትዮጵያ ህዝብን ተሳትፎ በማካተት በሚደረጉ ውይይቶችና ስምምነቶች መሠረት ይሆናል። ይህም የሽግግር መንግሥት በዚህ ቻርተር መሠረት ሥልጣኑን በተግባር ያረጋግጣል፣ በቻርተሩ ውስጥ የተጠቀሱትንም መሠረታዊ መርሆዎችን እና መብቶችን ያስከብራል፣ የሽግግሩ ጊዜ ከመጀመሩ በፊት በተደረጉ ውይይቶች እና ስምምነቶች መሠረት የፀደቁ ዕዝሎችም የዚህ ቻርተር ኣካል ሆነው እንዲያገለግሉ ያደርጋል። 2) የሁለተኛው ክፍል የሚጀምረው የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት አስተዳደር ከተመሠረት በኋላ ሲሆን ይህም የሚሆነው በዚህ ቻርተር ውስጥ እንደተጠቀሰውም ከብሄራዊ ሸንጎ ምርጫ በኋላ ሲሆን፣ ይህም ምርጫ በተቻለ ከ _________ በላይ ሳይዘገይ ይደረጋል። የሁለተኛው ክፍል የሚያበቃውም ቋሚ ህገ መንግሥት መውጣቱን ተከትሎ የሚመሠረተው የኢትዮጵያ መንግሥት አስተዳደር ከሽግግሩ መንግሥት ሥልጣንን በሚረከብበት ጊዜ ነው። አንቀጽ 3 ሀ) ይህ ቻርተር የሃገሪቱ የበላይ ህግ ሆኖ በማንኛውም የሃገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ተፈጻሚ ይሆናል። በዚህ ቻርተር ላይ ምንም ዓይነት ማሻሻያን ለማድረግ የብሄራዊ ሸንጎ ኣባሎችን ሶስት-አራተኛ አብላጫ ድምፅ ድምፅ ማግኘት ያስፈልጋል። በተመሳሳይም፣ በዚህ ውስጥ የተቀመጡትን የኢትዮጵያን ህዝብ መብቶች ለመቀንስ ወይም ለመሸራረፍ ምንም ዓይነት ማሻሻያዎችን ማድረግ ኣይቻልም። ለ) ከዚህ ቻርተር ጋር የሚፃረሩ ህጎች ሁሉ ተሽረዋል ተፈፃሚነትም አይኖራቸውም። ሐ) ቋሚ ህገ መንግሥት መውጣቱን ተከትሎ በምርጫ የሚመሠረተው የኢትዮጵያ መንግሥት አስተዳደር ሥራውን ሲጀምር የዚህ ቻርተር ተፈፃሚነትም ያቆማል። አንቀጽ 4 በኢትዮጵያ የሚመሠረተው የመንግሥት ስርዓት ዲሞክራሲያዊ እና ብዙሃኑን ያካተተ የአስተዳደር ስርዓት ሆኖ የአስተዳደር ሥልጣንንም በማዕከላዊ፣ በክፍለ ግዛት፣ በከተሞች፥ በወረዳዎች፥ እና በቀበሌዎች አስተዳደር መሃል በማካፋፈል ነው። የሚመሠረተውም የአስተዳደር ስርዓት ጂኦግራፊና እና ታሪካዊ እውነታዎችን በማገናዘብ ሥልጣን ጎሳን፣ ወይም ሃይማኖትን መሠረት ሳያደርግ ነው። አንቀጽ 5 የኢትዮጵያ የጦር ሃይሎች ተጠሪነታቸው ለሽግግር መንግሥቱ የሲቪል አስተዳደር ሆኖ የሚተዳደሩትም በቻርተር ምዕራፍ 3 እና 5 ውስጥ በተቀመጡት አንቀጾች መሠረት ይሆናል። አንቀጽ 6 የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ባለፈው ኣገዛዝ ያላግባብ የተፈጸሙ የህዝብ መፈናቀልዎች፣ የዜግነት መብት ገፈፋዎች፣ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የተወሠደ ገንዘብና ንብረት፣ ከመንግስት ሥራቸው በፖለቲካ እምነታቸው፣ በጎሣቸው ወይም በሃይማኖት ምክኒያት በተሰናበቱት የኢትዮጵያ ዜጎች ላይ የደረሱትን በደሎች ለመካስና ፍትህ ለማግኘት ወሳኝ እርምጃዎችን ይወስዳል። አንቀጽ 7 ኢትዮጵያ የሁሉም ብሄረሰቦች አገር ናት፣ ይህም ቻርተር ለሁሉም ብሄረሰቦች በእኩልነት ያገለግላል። አንቀጽ 8 የኢትዮጵያ ህዝብ ብሔራዊ መዝሙር እና ብሔራዊ አርማ በሕግ ይወሰናል። አንቀጽ 9 የኢትዮጵያ ዋና ይፋ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ሲሆን ኦሮምኛ፥ ትግሪኛ፥ ሶማሌኛ እና እንግሊዘኛ ተደራቢ የስራ ቋንቋዎች ናቸው። የ “የሥራ ቋንቋዎች” አሰያየም፣ ዓላማና እና አፈጻፀሙም ብሄራዊ ሸንጎ በሚያወጣቸው ህጎች ይወሰናል። ምዕራፍ 2 - መሠረታዊ መብቶች አንቀጽ 10 የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት የኢትዮጵያን ህዝብ መብት እና በዚህ ቻርተር ውስጥ የተጠቀሱትንም ጨምረው ያከብራሉ ያስከብራሉም። አንቀጽ 11 ሀ) ማንም የኢትዮጵያ ብሄራዊነቱን የሚያረጋግጥ ሁሉ የኢትዮጵያ ዜጋ ሆኖ ይወሰዳል። በዜግነቱም በዚህ ቻርተር ውስጥ የሠፈሩት መብቶች እና ግዴታዎች ይከበሩለታል፣ ከትውልድ ቀዬውና ከሃገሪቱም ጋር የመተሣሠሪያው መሠረቶች ይሆናሉ። ለ) በስጦታ የተገኘ የዜግነት መብት ኖሮት የዜግነትን ጥያቄ ባቀረበ ጊዜ የሃሰት ማስረጃ መጠቀሙ እና ዜግነትም የተሠጠው በተጭበረበረ ማስረጃ መሆኑ በፍርድ ቤት ከልተረጋገጠበት በስተቀረ ማንም ኢትዮጵያዊ የሆነ ዜጋ ዜግነቱን አይገፈፍም ወይም ኣይሰደድም። ሐ) እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጥምር ዜግነት የመያዝ መብቱ የተረጋገጠ ነው። የሌላ ሃገር ዜግነት በመቀበሉ ምክንያት ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን ያጣ ማንም ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱ ይከበርለታል። መ) የብሄራዊ ሸንጎም በዚህ ቻርተር መሠረት ዜግነትን እና በስጦታ የሚገኝ ዜግነትን አስመልክቶ ህጎችን ያወጣል። ሠ) ፍርድ ቤቶችም በዜግነት ህጎችና ደንቦች አፈጻጸም ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችንና ክርክሮችን ይመለከታሉ። አንቀጽ 12 በኢትዮጵያዊ ዜጋ ላይ በፆታ፣ በሃይማኖት ወይም በዘር ሐረጉ ምክኒያት ልዩነት ማድረግ የተከለከለ ነው። ማንም ሰው በሰብአዊነቱ የማይደፈር የመኖር፣ የነፃነት እና የአካል ደህንነት መብት አለው። ማንም የማንንም የመኖር እና የነፃነት መብት በህግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጪ መግፈፍ አይችልም፣ በህግ ፊት ሁሉም እኩል ናቸው። አንቀጽ 13 ሀ) የግለሰብ እና የማህበረሰብ መብቶችና ነፃነቶች ጥበቃ ይደረግላቸዋል። ለ) ማንኛውም የመንግስት አካላት የፕሬስ እና ሀሳብን የመግለጽ መብቶችን የሚገድቡ ህጎችንና መመሪያዎችን ማውጣት አይችሉም። ሐ) በሠላም የመሰብሰብ፣ በማህበር የመደራጀት፣ ማህበራትን እና ፖለቲካ ፓርቲ የመመሥረትና የመቀላቀል መብቶች ይረጋገጣሉ። መ) እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በሃገሪቱ ማንኛውም ክፍሎች በነፃ የመንቀሳቀስ እና ከሃገር ውጭም ተጉዞ የመመለስ መብት አለው። ሠ) እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በነፃ የማሰብ፣ የህሊናና የሃይማኖት ነፃነት አለው። ረ) እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የግል ህይወቱ የተከበረ መብቱ ነው። አንቀጽ 14 የሞት ቅጣት የተከለከለ ነው። አንቀጽ 15 ሀ) ወንጀል በተፈጸመበት ጊዜ በወንጀሉ የሚያስጠይቅ ህግ ከሌለ በስተቀር ወንጀልም ሆነ ቅጣት ሊኖርም አይችልም። ለ) ፖሊስ፣ መርማሪዎች ወይም ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት የግል መኖሪያ ቤትን መድፈር አይችሉም፣ እነዚህ ባለሥልጣናት የሃሰት መረጃ መስጠት በህግ እንደሚያስጠይቅና እንደሚያስቀጣ ባወቀ ግለሰብ በቃለ መሃላ በተሰጠ መረጃ መሠረት ዳኛ የፍርድ ቤት ማዘዣ ካልሰጣቸው በስተቀረ የግል መኖሪያ ቤትን መድፈር አይችሉም። ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ ፍተሻ ቢደረግ፣ የተያዘው ማስረጃ እና ሌሎች በዚሁ ፍተሻ ወቅት የተገኙ መረጃዎች በወንጀሉ ክስ ቢመሠረት ተቀባይነት አይኖራቸውም። ሐ) ማንም ሰው በህገ ወጥ መንገድ መያዝ ወይም ማሠር አይቻልም፣ ማንንም ሰው በፖለቲካ ኣመለካከቱና በሃይማኖት እምነቱ በተያያዘ ምክንያት ማሠር አይቻልም። መ) ሁሉም ሰዎች በፍትሃብሔር ወይም በወንጀል ነክ ጉዳዮች ላይ በነፃ ፍርድ ቤቶች የመዳኘት መብት ኣላቸው። ለተከሳሹም የፍርድ ቤት መጥሪያና የክሱ ህጋዊ መሠረቶች ዝርዝር በአስቸኳይ እንዲደርሱት ይደረጋል። ሠ) ተከሣሽ በህጉ መሠረት ጥፋተኛ መሆኑ እስከሚረጋገጥ ድረስ ንጹህ ነው፣ በተጨማሪም ገለልተኛና ብቁ የሆነ ጠበቃ የመያዝ፣ ዝም የማለትና ለሚጠየቀውም ጥያቄ መልስ ያለመስጠት፣ በመከላክል ዝግጅት ላይ የመሳተፍ፣ ምስክሩን የመጥራትና የመጠየቅ፣ ወይም ዳኛውን እንዲያስፈጽምለት የመጠየቅ መብቶቹ የተጠበቁ ናቸው። አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር በሚውልበት ሰዓት እነዚህ መብቶቹ ይገለጹለታል። ረ) በነፃ ፍርድ ቤት ፍትህን በአፋጣኝ የማግኘት መብት የተከበረ ነው። ሰ) ማንኛውም ሰው ነፃነቱን በእሥራት ወይም በቁጥጥር ሥር በመሆኑ ምክኒያት ቢያጣ፣ በአስቸኳይ በእሥር ወይም በቁጥጥር ሥር የመሆኑን ህጋዊነት ፍርድ ቤት እንዲወስንለት፣ ህገ ወጥ በሆነ መንገድም ከሆነ በእሥር ወይም በቁጥጥር ሥር የዋለው የመጠየቅ መብት አለው:: ሸ) ማንኛውም ሰው በተከሰሰበት ወንጀል ነፃ መሆኑ ከተረጋገጠ፣ ተከሳሽ በተመሳሳይ ወንጀል ተመልሶ እንደገና ሊጠየቅ አይችልም። ቀ) ሠላማዊ ሰዎች በወታደራዊ ፍርድ ቤት አይዳኙም። በ) በማስገደድ፣ በማሰቃየት ወይም በማስፈራራት የተገኘ ቃል አመኔታ አይኖረውም፣ በወንጀልም ሆነ በማንኛውም የፍርድ ሂደት ውስጥ ማስረጃም ሆኖ ሊቀርብ አይችልም። አንቀጽ 16 ሀ) የህዝብ ሃብት የተከበረና የማይደፈር ነው፣ እያንዳንዱም ዜጋ የህዝብ የሆነን ሃብት የመጠበቅ ሃላፊነት አለበት። ለ) የግል ንብረት የማፍራትና ባለቤት የመሆን መብት የተከበረ ነው፣ በህጉም መሠረት እስከተፈፀመ ድረስ የግል ንብረት ወደ ሌላ ማስተላለፍ አይከለከልም። ለህዝብ ጠቀሜታ በሚውል አገልግሎት ሳቢያ ማንም ሰው ከንብረቱ ላይ ህጉ በሚፈቅደው መሠረት መነሳት ከአለበት ለንብረቱ ፍትሃዊ የሆነ ካሣ በወቅቱ የማግኘት መብቱ የተጠበቀ ነው። ሐ) ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ የሆነ ሁሉ በየትኛውም የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ቤትና ንብረት መሬትን ጨምሮ ያለምንም ገደብ ባለቤት የመሆን መብት አለው። መ) ያለፍርድቤት ፈቃድ የመንግስት ባለስልጣናትና መንግስታዊ አካላት የዜጎች የግል መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ያለባለቤቶቹ ፈቃድ መግባት፣ የዜጎችን የግል ስልክና ኢንተርኔት መስመሮች መጥለፍ፣ እና የባንክ ሂሳብ ከፍቶ ማየት የተከለከለ ነው። አንቀጽ 17 ዜጎች ለራስ ጥበቃና ለአደን የሚጠቀሙባቸው ሽጉጦችና ጠመንጃዎች ባለቤት የመሆን፤ የመግዛት እና የመሸጥ መብት አላቸው። አንቀጽ 18 ከንብረት ልውውጥ ቀረጥ ውጪ መንግስት ከግለሰቦች ደሞዝ ላይ ግብር መውሰድ አይችልም። የቀረጥ መጠን በብሄራዊ ሸንጎ ይወሰናል። አንቀጽ 19 ህጉ በሚፈቅደው መሠረት የፖለቲካ ጥገኝነት የተሰጠውን ሰው ሸሽቶ ለመጣበት ሃገር ኣሳልፎ መስጠት ወይም አስገድዶ መመለስ የተከለከለ ነው። አንቀጽ 20 ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ የሆነ በብሄራዊ ምርጫ ህግ የተቀመጡትን ሁኔታዎች እስከአሟላ ድረስ ነፃ፣ ግልጽ፣ አፎካካሪ በሆኑና በየጊዜው በሚደረጉ ምርጫዎች ላይ የመምረጥም ሆነ ድምጹን በሚስጥር የመስጠት መብቱ የተጠበቀ ነው። ማንኛውም ዜጋ በጾታ፣ በሃይማኖት፣ በእምነቱ፣ በጎሳው፣ በቋንቋው፣ በሃብቱና በትምህርት ደረጃው ልዩነት አይደረግበትም። አንቀጽ 21 የመንግሥትን ሥራ በማስፈጸም ተግባር ላይ የተሠማራ የማዕከላዊ መንግሥት፣ የክፍለ ግዛትና የከተምች ወይም የቀበሌዎች አስተዳደር ባለሥልጣን የተሠጠውን የሥራ ሃላፊነት በሚወጣበት ጊዜ በዚህ ቻርተርም ሆነ በሌላ የኢትዮጵያ ህግ የተከበሩትን የግለሰብ መብቶች ቢነፍግ፣ ተበዳይ ግለሰቦች በባለሥልጣኑ ላይ ክስ መመስረትና ለደረሰባቸውም መብት ረገጣ ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ የመጠየቅ፣ መብታቸውን የማስከበር ወይም ሌላ ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ መብት አላቸው። አንቀጽ 22 ቀደም ብለው በዝርዝር የቀረቡት መብቶች ለኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ የተቀመጡ መብቶች ሆነው መተርጎምና መወሰድ የለባቸውም። በኢትዮጵያ የሚኖሩና ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ዜጎች በዝርዝር የቀረቡት የሰው ልጅ መብቶች ተጠቃሚዎች ይሆናሉ። ምዕራፍ 3 - የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት አንቀጽ 23 የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት በዚህ ቻርተር ውስጥ “የማዕከላዊ መንግሥት” ተብሎ የሚጠቀሰው ብሄራዊ ሸንጎ፣ ፕሬዝዳንት እና የፍርድቤት አካሎችን ያካትታል። ሦስቱ የሥልጣን አካላትም ህግ አውጪ፣ ህግ አስፈጻሚ እና ህግ ተርጓሚ ናቸው። እነዚህም የመንግሥት አካላት የተለያዩና አንዱ በሌላው ላይ ተጽእኖ አያደርግም። አንቀጽ 24 የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት በሚከተሉት ከፍተኛ የሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ የተለየ ሥልጣንና ሃላፊነቶች ይኖሩታል፦ ሀ) የሃገሪቱን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲና የዲፕሎማቲክ ግንኙነቶችን ወስኖ ማውጣት፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችንና ውሎችን መደራደር፣ መፈረምና ማጽደቅ እና የውጪ ኢኮኖሚና ንግድ ፖሊሲንና የሃገሪቱን የውጪ ብድር ፖሊሲ ያዘጋጃል። ለ) የሃገሪቱን ብሄራዊ የፀጥታና የደህንነት ፖሊሲዎች ማዘጋጀትና ማስፈጸም፣ የሃገሪቱን የመከላከያ ሃይል ማዘጋጀትና ማደራጀት እና የሃገሪቱን ዳር ድንበር ማስከበርንና ከውጪ ጠላት መከላከልን ይጨምራል። ሐ) የሃገሪቱን የገንዘብ አያያዝና አስተዳደር ፖሊሲ ማውጣት፣ ገንዘብ ማተምና ማሰራጨት፣ ግብርን ማስተዳደርና መቆጣጠር፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት ክፍላተ ግዛቶች መሃከል ያለውን የንግድ ፖሊሲ መቆጣጠር፣ የሃገሪቱን ብሄራዊ በጀት ማዘጋጀት፣ የሃገሪቱን ገንዘብ ነክ ፖሊሲ ማዘጋጀትና ብሄራዊ ባንኩን ማስተዳደር። መ) የሃገሪቱን ደረጃዎች ምደባ ይቆጣጠራል፣ አጠቃላይ የደመወዝ ፖሊሲም ያዘጋጃል። ሠ) የሃገሪቱን የተፈጥሮ ሃብት ያስተዳድራል። ከየክፍለ ግዛቱ አስተዳዳሪዎች ጋር በመነጋገርም ከዚሁ ሃብት የሚገኘውን ፈሰስ ለየአስተዳደሮቹ እንደ አላቸው የህዝብ ብዛት ተነጻጻሪ በሆነ መልኩ የበጀት ድልድል ይደረግላቸዋል። ይህም ሲደረግ ባለፈው አስተዳደር ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ከዚህ ሃብት ገቢ ፈሰስ ሊደርሳቸው ላልቻሉ አካባቢዎች ልዩ ትኩረት ይሰጣቸዋል። ረ) የኢትዮጵያ ዜግነትን፣ የስደተኞችንና የፖለቲካ ጥገኝነት ጉዳዮችን ይቆጣጠራል። አንቀጽ 25 ሀ) በዚህ ቻርተር ካልተካተተ በስተቀር ወይም የኢትዮጵያ ሽግግር መንግስት እስካልሻረው ወይም እስካላሻሻለው ድረስ፤ በኢትዮጵያ _______ ቀን _______ ዓ/ም ሥራ ላይ የዋለው ህግ ተፈጻሚ ይሆናል። ለ) በሌላ ማንኛውም የህግ አውጪ አካል የወጡ ህጎች በማዕከላዊው የህግ አውጪ አካል ከወጡት ማናቸውም ህጎች ጋር የሚቃረኑ ከሆኑ በአንቀጽ 54(ለ) ከተጠቀሱት በስተቀረ በማዕከላዊው የህግ አውጪ አካል በወጡት ህጎች ተተክተዋል። አንቀጽ 26 ሀ) የኢትዮጵያ የጦር ሃይሎች የሚወጣጡት ከመደበኛና ከተጠባባቂው ክፍሎች እና ከመሳሰሉት ነው፣ የነዚህም ሃይሎች ዋና ዓላማ ኢትዮጵያን መከላከል ነው። ለ) በማዕከላዊው ህግ ካልታቀፉ በስተቀረ በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ሥር ያልሆኑ የታጠቁ ሀይላትና የሚሊሽያ ቡድኖች የተከለከሉ ናቸው። ሐ) የኢትዮጵያ የጦር ሃይልና ኣባሎቹ በመከላከያ ሚንስትር ወይም በሥሩ በሚተዳደሩ ማናቸውም መሥርያ ቤቶች ውስጥ የሚሠሩትን የጦር ሃይል አባሎች ጨምሮ ለፖለቲካ ሥልጣን አይወዳደሩም፣ ለሚደግፉዋቸው ተፎካካሪዎችም የምረጡልኝ ዘመቻ ማካሄድ አይችሉም፣ ወይም በመከላከያ ሚንስትሩ በተከለከሉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ መካፈል አይችሉም። ይህ እገዳ ከላይ የተጠቀሱት አባሎች በግላቸውም ሆነ በመደበኛ ሥራቸው የሚያደርጉትን ሁሉ ያካትታል። በዚህ አንቀጽ ውስጥ እነዚህ አባሎች በምርጫ ጊዜ ለመምረጥ ያላቸውን መብት የሚጥስ ምንም ነገር አይኖርም። መ) የኢትዮጵያ የደህንነት ጥበቃ አገልግሎት መረጃዎችን ይሰበስባል፣ በብሄራዊ ደህንነቶች ላይ የተፈጠሩትን ሥጋቶች ያጠናል ይመረምራል፣ የኢትዮጵያን የሽግግር መንግሥት ያማክራል። ይህ አገልግሎት በህግ አውጪው ተቆጣጣሪነት በሲቪል ሠራተኞች አስተዳደር ሥር ሆኖ በህግና በሰው ልጆች የመብት መርሆዎች መሠረት ይሠራል። አንቀጽ 27 የብሄራዊ ሸንጎ አባሎች፣ ፕሬዘዳንቱ፣ የፍርድ ቤት ዳኞችና የፍትህ አካላት አባል የሆኑ በሌላ ሥራ ላይ በመንግሥት ውስጥም ሆነ ከመንግስት ውጭ መመደብ አይችሉም። አንቀጽ 28 በማንኛው ሁኔታ የጦር ሃይል አባል የሆነ ሰው የብሄራዊ ሸንጎ አባል፣ ፕሬዘዳንት፣ ሚንስትር ወይም የፕሬዘዳንቱ ምክር ቤት አባል መሆን አይችልም፣ መሆንም ከፈለገ በጦር ሃይሉ ውስጥ ያለውን ሥልጣንና ማዕረግ መልቀቅ ወይም በጡረታም ተገልሎ ከሆነ ከነዚህ ሥልጣናት ለአንዱ ከመብቃቱ በፊት ቢያንስ ከ 24 ወራት በላይ በጡረታ ላይ መቆየት ይኖርበታል። ምዕራፍ 4 - የሽግግሩ ህግ አውጪ አካል ሥልጣንና ተግባር አንቀጽ 29 ሀ) በሽግግሩ ጊዜ ኢትዮጵያ “ብሄራዊ ሸንጎ” ተብሎ የሚጠራ የህግ አውጪ አካል ባለሥልጣን ይኖራታል። የሸንጎው ዋና ዋና ተግባራት የሽግግር ወቅት ፕሬዝደንት መምረጥ፥ ቋሚ ህገመንግስት ማርቀቅና ለህዝበ-ውሳኔ ማቅረብ፥ የሃገሪቱን ህጎች ማውጣትና የህግ አስፈፃሚውን (የፕሬዚዳንቱን) ሥልጣን መከታተልና መቆጣጠር ነው። ለ) ህጎች በኢትዮጵያ ህዝቦች ሥም ይወጣሉ። በተያያዘም ህጎች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ይወጣሉ፣ የሚወጡትም ህጎች አጥብቆ የሚከለክል ሁኔታ እስከሌለ ድረስ ከታተሙበት ቀን ጀምሮ ተፈፃሚ ይሆናሉ። ሐ) የሽግግር መንግስቱ ብሄራዊ ሸንጎ አባላት ምርጫ ወይም ምደባ በፖለቲካ ፓርቲዎችና ባለድርሻዎች መካከል በሚደረጉ ውይይቶችና ስምምነቶች ይጠናቀቃል። መ) የሽግግር መንግስቱ የብሄራዊ ሸንጎ አባላት ምርጫና ምደባ ከ ___________ ቀን ________ ዓ/ም ይከናወናል። አንቀጽ 30 ሀ) የብሄራዊ ሸንጎ አባላት ብዛት 525 ይሆናል። ሸንጎውም አሠራሩን አስመልክቶ አባሎች በፈቃዳቸው ከብሄራዊ ሸንጎ ወንበራቸው ቢለቁ፣ ቢነሱ ወይም በሞት ቢለዩ ስለሚተኩበት ሁኔታ ህግ ያወጣል። ለ) የብሄራዊ ሸንጎ አባሎች ቢያንስ የሚከተሉትን መስፈርቶች የግድ ማሟላት አለባቸው:: 1) ኢትዮጵያዊ የሆነና ዕድሜው ከ21 ዓመት ማነስ የለበትም:: 2) ዜጎችን በማሰቃየት ሥራ ውስጥ ያልተሣተፈ። 3) ያገሪቱን ሃብት በመመዝበርና የመንግሥት ገንዘብ በማካበት ራሱን ህገ ወጥ በሆነ መንገድ በሃብት ያላከበረ። አንቀጽ 31 ሀ) ብሄራዊ ሸንጎ የራሱን የውስጥ የአሠራር ደንቦች ያወጣል፣ ሁኔታዎች ካላስገደዱ በስተቀረ እና የውስጥ አሠራር ደንቡ እስከፈቀደ ድረስ ስብሰባዎቹን ለህዝብ ክፍት ያደርጋል። ለ) የብሄራዊ ሸንጎ ምክር ቤት ከአባሎቹ ውስጥ የሸንጎውን አፈ ጉባኤና ምክትል አፈ ጉባኤ መርጦ ይሠይማል። አፈ ጉባኤ ሆኖ የሚመረጠው ሰው ለወንበሩ ከተሰጠው ድምፅ ውስጥ አብላጫውን ያስቆጠረው ነው፣ ምክትል አፈ ጉባኤም የሚሆነው በሁለተኛ ደረጃ አብላጫውን ያስቆጠረው አባል ነው። የሸንጎው አፈ ጉባኤ ከፈለገ ድምፅ መስጠት ይችላል፣ ነገር ግን በክርክር ወቅት የክርክሩ ተካፋይ ሊሆን አይችልም። ይሁንና አፈ ጉባኤው የክርክሩ ተካፋይ ለመሆን በወሰነ ጊዜ ወንበሩን በጊዜያዊነት ለቆ በሚካሄደው ክርክር ላይ እንደማንኛውም የሸንጎ አባል መሳተፍ ይችላል። አንቀጽ 32 ብሄራዊ ሸንጎ ማንኛውንም የህግ ማሻሻያ ለማፅደቅ ድምፅ ከመስጠቱ በፊት በሸንጎው መደበኛ ስብሰባ ላይ የህግ ማሻሻያው ረቂቅ ሁለት ጊዜ በንባብ መሰማት አለበት። አንቀጽ 33 ሀ) የብሄራዊ ሸንጎ ምክር ቤት ስብሰባዎች ለህዝቡ ክፍት ናቸው፣ ለየስበሳባዎቹም የጽሁፍ ጥንቅሮች ይዘጋጃሉ ታትመውም ይወጣሉ። እንዳንዱ የብሄራዊ ሸንጎ ምክር ቤት አባል ድምፅ የሠጠባቸው መረጃዎች ተመዝግበው ህዝብ እንዲያውቀው ይደረጋል። በዚህ ቻርተር እስካልተጠቀሰ ድረስ የብሄራዊ ሸንጎ ምክር ቤት ውሳኔዎች ቀላል የአብላጫ ድምፅ በማስቆጠር ብቻ ይወሰናሉ። ለ) የብሄራዊ ሸንጎ ምክር ቤት በፕሬዘደንቱ የሚቀርቡለትን የህግ ማሻሻያዎችንና የበጀት ማሻሻያዎችን ጨምር ይመረምራል። ሐ) የሃገሪቱ ብሄራዊ በጀት የሚዘጋጀው በብሄራዊ ሸንጎና ፕሬዘዳን ባቀረበው የበጅት ጥያቄ መሰረት ይሆናል ነው። ብሄራዊ ሸንጎው የበጀት ምደባን የማዛወር ወይም ከጠቅላላው በጀት የመቀነስ ሥልጣን አለው፣ በተጨማሪም ሸንጎው አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው በአጠቃላይ በጀቱን ከፍ አድርጎ ወደ ፕሬዘዳንቱ ቢሮ ይመልሰዋል። መ) የብሄራዊ ሸንጎ አባሎች ሸንጎው ባለው የውስጥ አሠራር ደንብ መሠረት ኣዳዲስ የህግ ማሻሻያዎችን አዘጋጅተው ያቀርባሉ። ሠ) የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ሃገሪቱን ከውጭ ወራሪ ለመከላከልም ቢሆን በፕሬዘዳንቱ ጠያቂነት በብሄራዊ ሸንጎ ምክር ቤት ካልፀደቀ በስተቀረ ከኢትዮጵያ ውጭ ሊዘምት አይችልም። ረ) ዓለም ዓቀፍ ውሎችንና ስምምነቶችን የማፅደቅ ሙሉ ሥልጣን ያለው የብሄራዊ ሸንጎ ምክር ቤት ብቻ ነው። ሰ) የብሄራዊ ሸንጎ ምክር ቤትና ኮሚቴዎቹ ባላቸው የመቆጣጠር የሥራ ድርሻ መሠረት የመንግሥት ሥራ አስፈፃሚ ባለሥጣኖችን፣ ፕሬዘዳንቱንና ሌሎች ዝቅተኛ የመንግሥት ባለሥጣኖችን ጨምረው ይቆጣጠራሉ። ሸ) የብሄራዊ ሸንጎ ምክር ቤትና ኮሚቴዎቹ ባላቸው የመቆጣጠር የሥራ ድርሻ መሠረት ምርመራ ማድረግ፣ መረጃ መሰብሰብና ማናቸውንም ባለስልጣናትና ዜጎችን ወደ ምክር ቤቱ ለጥያቄ እንዲቀርቡ መጥሪያ የመስጠት ሥልጣን አላቸው። አንቀጽ 34 እያንዳንዱ የብሄራዊ ሸንጎ ምክር ቤት አባል በሸንጎው ስብሰባ ላይ በሚያነሳቸው ጉዳዮች አይከሰስም። የብሄራዊ ሸንጎ ምክር ቤት በሥራ ላይ እያለ የምክር ቤት አባሉን ማሠር አይቻልም፣ አባሉ በወንጀል ተከሶ ምክር ቤቱ አባሉ ያለውን ያለመከሰስ መብት ካልገፈፈው ወይም እጅግ ከፍተኛ የሆነ የማጭበርበር ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካለተያዘ በስተቀር ሊታሰር አይችልም። ምዕራፍ 5 - የሽግግሩ የሥራ አስፈጻሚው አካል ሥልጣንና ተግባር አንቀጽ 35 የሥራ አስፈጻሚው አካል ሥልጣን በሽግግሩ የሥራ ዘመን ወቅት በፕሬዘደንቱ ዕዝና እጅ ሥር ይሆናል። አንቀጽ 36 ሀ) የፕሬዚዳንቱን የሚኒስትሮች ምክርቤት አባላትን ሹመት ያጸድቃል። የፕሬዚዳንቱና የሚኒስትሮች ምክርቤት ዋና ሥራቸውም የሚሆነው የኢትዮጵያን ልዑዋላዊነትና ልዕልናን ማስጠበቅና፣ የሃገሪቱን ዋና ዋና ጉዳዮች በበላይነት መቆጣጠር ነው። ለ) ማንም ሰው የሚኒስትሮች ምክርቤት አባል ሁኖ ከመመረጡ በፊት ማሟላት ያለበት ግዴታዎች ለብሄራዊ ሸንጎ ምክር ቤት አባልነት ለመመረጥ ከሚያስፈልጉት ግዴታዎች ጋር ከዚህ በታች ከተጠቀሱት በስተቀር ተመሳሳይ ናቸው፦ 1. ቢያንስ የሠላሳ ዓመት የሞላው 2. የወንጀል ሬከርድ የሌለው አንቀጽ 37 ፕሬዘደንቱ ብሄራዊ ሸንጎ ያሳለፈውን ህግ ውድቅ ማድረግ አይችልም። አንቀጽ 38 ሀ) ፕሬዘደንቱ ጠቅላይ ሚንስትሩን ይሾማል፣ በጠቅላይ ሚንስትሩም አቅራቢነት የሚንስትሮች ምክር ቤት አባሎችን ይሰይማል። ጠቅላይ ሚንስትሩና የሚንስትሮች ምክር ቤት አባሎች እንደ መንግሥት ሆነው ሥራ ከመጀመራቸው በፊት የብሄራዊ ሸንጎ ምክር ቤትን ይሁንታ በአብላጫ ድምፅ ማግኘት አለባቸው። ተመራጩ ጠቅላይ ሚንስትርም በአንድ ወር ጌዜ ውስጥ የሚንስትሮች ምክር ቤቱን ማቋቋም ካልቻለ ፕሬዘደንቱ ሌላ ጠቅላይ ሚንስትር ይሾማል። ለ) ጠቅላይ ሚንስትር የሚሆነው ግለሰብ የሚጠበቅበት የብቃት ደረጃ ፕሬዘደንቱ ማሟላት ካለባቸው የብቃት ደረጃ ተመሳሳይ ሆኖ በተጨማሪ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ወንበር ተረክቦ ሥራ በሚጀምርበት ጊዜ ዕድሜው ከ25 ማነስ የለበትም። አንቀጽ 39 ሀ) የሚንስትሮች ምክር ቤት ዓለም ዓቀፍ ውሎችንና ስምምነቶችን ተደራድረው እንዲያስፈጽሙ ተወካዮችን መርጦ በመሾም በፕሬዘደንቱ ያፀድቃል። ፕሬዘደንቱ እነዚህን ዓለም ዓቀፍ ውሎችንና ስምምነቶችን ህግ ሆነው እንዲወጡ ለብሄራዊ ሸንጎ አቅርቦ ያፀድቃል። ለ) ፕሬዘደንቱ የሃገሪቱን ጠቅላይ ጦር አዛዥነት ሥራዎች ያከናውናል። በአሠራሩም የሃገሪቱ ጠቅላይ የጦር ሃይል የትዕዛዝ ተዋረድ ፕሬዘደንቱ ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ መከላከያ ሚንስትር፣ ከመከላከያ ሚንስትር፣ ወደ ሀገሪቱ የጦር ሃይል አዛዦች ይሆናል። ሐ) ፕሬዘደንቱ በይበልጥ በምዕራፍ 6 እንደተቀመጠው ሁሉ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባኤ አቅራቢነት ሰብሳቢ ዳኛንና የማዕከላዊውን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞችን ይሾማል፣ መሻርም ይችላል። መ) ፕሬዘደንቱ የሃገሪቱን ብሄራዊ ደህንነትና ፀጥታ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም ጄኔራልና ከዛ በላይ ላሉ መኮንኖች፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል የሃላፊነት ሥልጣን ይሰጣል፤ እነዚሀ የሥልጣን ወንበሮች በብሄራዊ ሸንጎ በአብላጫ ድምጽ ይጽድቃሉ። አንቀጽ 40 ጠቅላይ ሚንስትሩና ሚንስትሮቹ ተጠሪነታቸው ለፕሬዘደንቱ ነው። ፕሬዚዳንቱ ተጠሪንቱ ለብሄራዊ ሸንጎ ነው። አንቀጽ 41 ፕሬዘደንቱ የመንግሥቱን የዕለት-ተዕለት ተግባራት የማከናወን ከፍተኛ ሃላፊነት አለበት፣ አስፈላጊም ሆኖ ሲያገኘው ሚኒስትሮቹን ከሥልጣን ሊያነሳ ወይም ሊያሰናብት ይችላል። አንቀጽ 42 የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥራዎቹን ለማስፈፀም የሚያስፈልጉትን የሥራ ስርዓተ ደንቦች በማውጣት ህጎችን ለማስፈፀም የሚያስችሉትን ደንቦችና መመሪያዎች እነደ አስፈላጊነታቸው ያወጣል። ተጨማሪም የህግ ማሻሸያዎችን አዘጋጅቶ ለብሄራዊ ሸንጎ በማቅረብ ያፅድቃል። እያንዳንዱ የሚንስትር መሥሪያ ቤትም በሥልጣኑ ሥር ምክትል ሚንስትሮችን፣ አምባሰደሮችን እና ልዩ ደረጃ የሚሰጣቸውን አባሎች ለሥልጣን ማጨት ይችላል። የሚንስትሮች ምክር ቤትም እጩዎቹን ከተቀበለ ለፕሬዘደንቱ አቅርቦ ሹመቱን ያፀድቃል። ሁሉም የምክር ቤት ውሳኔዎች የሚወሰኑት የአባሎቹን አብላጫ ድምፅ በማስቆጠር ነው። ምዕራፍ 6 - የማዕከላዊ ዳኝነት ሥልጣንና ተግባር አንቀጽ 43 ሀ) ዳኞችና ፍርድ ቤቶች ፍፁም ነፃ ናቸው፣ በምንም ዐይነት መንገድ ቢሆን የፍርድ ሚንስትሩን ጨምሮ ከማንኛውም የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ ባለሥልጣን ተጽዕኖ ነፃ ናቸው። ዳኞች ላቅ ያለ ብቃት ኖሯቸው ተከሳሾች በህጉ መሠረት ነፃ ወይም ወንጀለኛ መሆናቸውን ሲወስኑ ከህግ አውጪም ሆነ ከህግ አስፈጻሚው አካላት የሚደርስባቸው ምንም አይነት ተፅዕኖ አይኖርም:: ለ) በየፍርድ ቤቱ የሚመደቡ ዳኞች ከ _______________ ቀን ________________ ዓ ም ጀምሮ ከሥራቸው ላይ በዚህ ቻርተር መሠረት ካልተነሱ በስተቀረ በዳኝነት ሥራቸው ላይ ይቆያሉ። ሐ) የብሄራዊ ሸንጎ ምክር ቤት ለፍርድ ቤቶችና ለዳኝነት ሥራ ነፃና በቂ የሆነ በጀት ይመድባል። መ) የማዕከላዊ ፍርድ ቤትች የማዕከላዊ ህጎችን ከማስፈጸም አኳያ በሚነሱ ጉዳዮች ላይ ብያኔ ይሰጣሉ። እነዚህን ፍርድ ቤቶች የመመሥረት ሙሉ ስልጣን ያለው የማዕከላዊው መንግሥት ነው። የእነዚህ ፍርድ ቤቶች በየክፍላተ ግዛቱ መመሥረት የሚረጋገጠው ከየክፍላተ ግዛቱ የዳኞች ጉባኤ ፕሬዘዳንቶች ጋር በመነጋገር ይሆናል። አንቀጽ 44 ሀ) የማዕከላዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በህግ በኢትዮጵያ ይቋቋማል። ለ) የማዕከላዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሥልጣንም እንደሚከተሉት ይሆናል። 1. ልዩና ዋና የህግ የስልጣን ሂደት በኢትዮጵያ ጊዜያዊ መንግሥት እና በክፍለ ግዛት መንግሥታት፣ በከተማና ቀበሌ መስተዳድሮች ይገለፃል። 2. ባለው ልዩና ዋና የህግ ስልጣን ከተበዳይ በቀረበ አቤቱታ ወይም ከሌላ ፍርድ ቤት በተመራ ጉዳይ ላይ የማዕከላዊ፣ የክፍለ ግዛት መንግሥታት፣ የከተማ እና የቀበሌ አስተዳደራት የሚከተሉት የህግ ሂደት፣ ህግ፣ መመሪያ ወይም ትዕዛዝ ከዚህ ቻርተር ጋር የሚጻረር መሆኑን ይገመግማል። 3. የማዕከላዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝን አስመልክቶ የሚኖረው የህግ ስልጣን ወደፊት በህግ ይወሰናል። ሐ) የማዕከላዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጥያቄ ውስጥ የገባው ህግ፣ ደንብ፣ መመሪያ ወይም እርምጃ በዚህ ቻርተር የተቀመጠውን የሚቃረን ነው ብሎ ከወሰነ እንደተረ ተደርጎ ይወሰዳል። መ) የማዕከላዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክስ አመሠራረት ስርዓቶችንና ጠበቆች የጥብቅና ግዴታቸውን እንዴት እንደሚወጡ መመሪያና ደንቦችን አዘጋጅቶ ያሳትማል። በዚህ ቻርተር ውስጥ በአንቀጽ 44 (ለ) (1) በተያያዘ ከሚወሰኑት በስተቀረ ውሳኔ የሚሰጠውም ሁለት-ሦስተኛ ድምፅ በማስቆጠር ነው። ፍርድ ቤቱም ውሳኔውን የማስከበር፣ ፍርድ ቤቱንም ለሚዳፈሩ መጥሪያ የመስጠትና በክሱም ላይ እርምጃን የመውሰድ ሙሉ ሃይልና ሥልጣን አለው። ሠ) የማዕከላዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አባሎች ጠቅላላ ብዛት 11 ይሆናል:: ከፍተኛ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የክፍለ ግዛት ዳኞች ጉባኤን በማማከር በመጀመሪያ ከ10 ያላነሱና ከ25 የማይበልጡ ዳኞች መርጦ ከላይ ለተጠቀሱት መዋቅራት ያሉትን ክፍት ቦታዎች ለመሙላት በእጩነት ይመርጣል። ከዚህም በኋላ ክፍት ቦታ በሞት፣ በፈቃደኝነት ዳኞች ከስልጣን በመልቀቃቸው ወይም ከስልጣናቸው በመነሳታቸው ምክኒያት ሲፈጠር ተመሳሳይ ስርዓት በመከተል ሦስት ዳኞችን መርጦ ለሹመት ያቀርባል። ፕሬዘደንቱ የዚህን ፍርድ ቤት አባሎች ይሾማል ከመሃላቸውም አንዱን መርጦ ስብሳቢ ዳኛ አድርጎ ይሰይማል። የፕሬዚዳንቱን ሹመት ብሄራዊ ሸንጎ ያጸድቃል ወይም ይሽራል። አንቀጽ 45 ከፍተኛ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ተመስርቶ ጉባኤውን ያስተዳድራል። ከፍተኛ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የማዕከላዊውን የዳኝነት ሥራዎች ይቆጣጠራል በጀቱንም ያስተዳድራል። ይህ ጉባኤም የሚውጣጣው የማዕከላዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስብሳቢ ዳኛ፣ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች ሰብሳቢ ዳኛ፣ የየክፍለ ግዛቱ ሰብሳቢ ዳኞችና ሃያ ምክትል ስብሳቢ ዳኞች በማካተት ነው። የማዕከላዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስብሳቢ ዳኛ የከፍተኛ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤን ይመራል። ይህ ስያሜ ተቀባይነት ካላገኘ የከፍተኛ ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ በድጋሚ ሶስት ግለሰቦችን መርጦ በእጩነት ያቀርባል። አንቀጽ 46 ሀ) የማዕከላዊው የዳኝነት አካሎች የሚያጠቃልሉት ያሉትን ፍርድ ቤቶች የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ፣ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ የወንጀል ፍርድ ቤት፣ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች እና ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ሲሆን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም በዚህ ቻርተር በአንቀጽ 44 ከተጠቀሰው በስተቀር የበላይና የመጨረሻ የዳኝነት ሥልጣን ይኖረዋል። እንደ አስፈላጊነታቸውም ተጨማሪ የማዕከላዊ ፍርድ ቤቶች በህግ ይቋቋማሉ። የነዚህን ፍርድ ቤት ዳኞች ፕሬዝደንቱ ይሾማል። ለ) የክፍለ ግዛቶችና ያካባቢ ፍርድ ቤቶች የሚወስኑት ውሳኔዎች የመጨረሻ ይሆናሉ። ነገር ግን ውሳኔዎቹ ከዚህ ቻርተርና ከማዕከላዊው መንግስት ህግ ጋር የሚጣረሱ ከሆነ የማዕከላዊ ፍርድ ቤት ጉዳዩን አስቀርቦ የማየት ሥልጣን አለው። በማዕከላዊ ፍርድ ቤትም ተመልሰው ሲለሚታዩ ጉዳዮች ወደ ፊት በህግ ይቀመጣል። አንቀጽ 47 ማንኛውም ዳኛ ወይም ከፍተኛ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አባል የሆነ ሰው ከፍተኛ የሆናና ሞራልን በሚነካ ወንጀል፤ የእምነት ማጉደል ወንጀል ወይም በሙስና ወንጀል ወንጀለኛ ሆኖ ካልተገኘ ወይም በቋሚነት የአካል ብቃቱን ካላጣ በስተቀረ ከፈቃዱ ውጭ በሆነ መንግድ ከዳኝነት ሥራው ላይ ሊነሳ አይችልም። ማንኛውንም ዳኛ ከሥልጣን ማንሳት የሚቻለው የማዕከላዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወስኖ ውሳኔውን ፕሬዝደንቱ ሲያፀድቀው ብቻ ነው። የይነሳ ውሳኔ ከተላለፈ ወዲያውኑ ተፈጻሚ ይሆናል። ከላይ በተጠቀሱት ወንጀሎች የተወነጀለ ዳኛ በዚህ አንቀጽ በተቀመጠው መሠረት ጉዳዩ ውሳኔ እስኪሰጠው ድረስ ከዳኝነት ሥራው ሊታገድ ይችላል። ምዕራፍ 7 - የልዩ ፍርድ ቤትና ብሄራዊ ኮሚሽኖች መቋቋም አንቀጽ 48 በዘር ማጥፋትና በኢሰብአዊነት ወንጀሎች የሚጠረጠሩ ግለሰቦች የሚጠየቁበትና የሚዳኙበት ልዩ ፍርድ ቤት ይቋቋማል። አንቀጽ 49 ሀ) በዚህ ቻርተር የሚቋቋሙት ኮሚሽኖች ሥራ ላይ ሲውሉ፤ የብሄራዊ ኮሚሽኑ ምሥረታ ይረጋገጣል። የዚህ ብሄራዊ ኮሚሽን አባላት በአንቀጽ 51 መሠረት ህገ ደንቡ ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ ማገልገል ይጀምራሉ። ለ) የብሄራዊ ኮሚሽን አባሎች አመዳደብ በህግ መሠረት ይሆናል። አንቀጽ 50 የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት በዚህ ቻርተር ውስጥ በተነጻጻሪ የተቀመጡት መብቶች መተግበራቸውንና ከሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመመርመር የሚችል ኮሚሽን ያቋቋማል። የኮሚሽኑ ጽህፈት ቤትም በራሱ ተነሳሽነት ወይም በሚቀርብለት አቤቱታ መነሻነት በመንግሥት ባለሥልጣኖች ላይ ህግን በማዛባትና ወይም ባለአግባቡ በመጠቀም በሚነሱ ውንጀላዎች ላይ ምርመራ የማካሄድ ሥልጣን ይኖረዋል። አንቀጽ 51 ማንም የኢትዮጵያ ልዩ ፍርድ ቤት ወይም በማናቸውም በማዕከላዊ መንግሥት በሚቋቋሙት ኮሚሽንኖች ውስጥ አባል የሆነ ሰው በማንኛውም ዓይነት የሥልጣን ደረጃ በመንግሥትም ውስጥም ሆነ ውጭ ተቀጥሮም ሆነ በነፃ መሥራት አይችልም። ይህ እገዳ በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት የሥራ አስፈፃሚ፣ የህግ አውጭ እና የህግ ተርጓሚ ዘርፎችን ይጨምራል። ሆኖም ግን የልዩ ፍርድ ቤት አባል ሆኖ የተመረጠ ሰው በፍርድ ቤቱ ሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ ቀድሞ ይዞት የነበረውን ሥራና የሥራ መደብ በይደር ማቆየት ይችላል። ምዕራፍ 8 - የክፍለ ግዛቶችና የማዘጋጃ ቤቶች አስተዳደር አንቀጽ 52 በኢትዮጵያ የሚመሠረተው የማዕከላዊ መንግሥታዊ ሥርዓት ሥልጣንን በማዕከላዊ መንግሥታዊ መዋቅራት ሥር እንዳያሰባስብ ተደርጎ የሚዋቀር ነው። የምንመሠርተውም የማዕከላዊ መንግሥታዊ ሥርዓት በሥሩ በሚቋቋሙት የየክፍለ ግዛቱና የየአካባቢ አስተዳደር ሥልጣናትና ባለሥልጣኖች ዋና የመንግሥት ሥራ አስፈፃሚነት የምናስተዳድራትና የምንተዳደርባት አንድ ኢትዮጵያ መሥርተን ከተጽዕኖ ነፃ የሆነችና እያንዳንዱ ዜጋ በመንግሥት ጉዳይ ያገባኛል የሚልባትና መብቱን የሚያስከብርባት ሃገር እናደርጋታለን። አንቀጽ 53 የወቅቱ የኢትዮጵያ ክፍለ ግዛቶች ወሰን በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት የሥራ ጊዜ ገደብ ውስጥ ያለምንም ለውጥ እንዳለ ሆኖ እንዲቆይ ይደረጋል። አንቀጽ 54 አሁን ያሉት የኢትዮጵያ ክፍለ ግዛት አስተዳደሮች በሽግግሩ ጊዜ በዚህ ቻርተር መሠረት ለማዕከላዊ መንግሥቱ ከተተውት ሥልጣኖችና ሥራዎች በስተቀረ በፊት ይሠሩዋቸው የነበሩትን የአስተዳደር ሃላፊነቶችንና ሥራዎችን እየሠሩ ይቆያሉ። ለክፍለ ግዛት አስተዳደር ሥራዎች አስፈላጊ የሆነው በጀት በማዕከላዊ መንግሥቱ ይመደባል፣ የበጀት ምደባውም በተለመደው አሠራርና በዚህ ቻርተር አንቀጽ 25 (ሠ) መሠረት ይሆናል። አንቀጽ 55 ሀ) ማናቸውም የኢትዮጵያ ክፍለ ግዛት አስተዳደሮች፣ የከተማም ሆነ የቀበሌ አስተዳደር አባል የሆነ በማዕከላዊ መንግሥቱ ወይም በማንኛውም ባለስልጣን በመደበኛ ፍርድ ቤት ተከሰው በህጉ መሠረት ወንጀለኛ ሆነው እስካልተገኙ ድረስ ከሥራቸው አይሰናበቱም። ለ) እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ክፍለ ግዛት አስተዳዳሪ ሥልጣን ከያዘበት ከ _____ ______ ቀን ___ ___ ዓ/ም ጀምሮ ስለ ክፍለ ግዛት አስተዳደር ሥልጣንና ሃላፊነት በሚወጣው ህግ መሠረት የሚሰየመው አስተዳደር በህጉ መሠረት ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ተደርጎ ቋሚ አስተዳደር እስኪመሠረት ድረስ በሥራው ላይ ሊቆይ ይችላል። የክፍለ ግዛት አስተዳዳሪ፣ የከተማ ከንቲባ ወይም የክፍለ ግዛት ጉባኤ አባል የሆነ ከሥልጣኑ ከተነሳ ወይም በፈቃዱ ከለቀቀ ጉዳዩ የሚመለከተው ጉባኤ በግዛቱ ነዋሪ ከሆኑና ለሥልጣኑ ለመወዳደር ፍላጎት ካላቸው ሰዎች ጥያቄ ይቀበላል። በነዚህ ሃላፊነቶች ውስጥ ለመሥራት የሚያስፈልጉት ቅድመ ዝግጅቶችም በአንቀጽ 31 ለብሄራዊ ሸንጎ አባልነት ለመመረጥ የሚያስፈልጉት ቅድመ ዝግጅቶች ይሆናሉ። አንድ እጩ ተወዳዳሪ ወንበሩን ለመውሰድ ቢያንስ የምክር ቤቱን አባሎች አብላጫ ድምፅ ማስቆጠር መቻል አለበት። አንቀጽ 56 ሀ) የክፍለ ግዛት አስተዳደር ጉባኤዎች የሚኒስትር መሥርያ ቤቶች በየአስተዳደሩ ያላቸውን ሥራዎች እንዲያስፈጽሙ በማስተባበርና በሚንስትሩ መሥሪያ ቤት በአስተዳደሩ ሥር ለሚሠሩ ሥራዎች የተያዘውን የሥራ ዕቅድና በጀት በመገምገም የማዕከላዊ መንግሥትን ይረዳሉ። የማዕከላዊ መንግሥት ካለው ጠቅላላ በጀት በመነሳት ለክፍለ ግዛት አስተዳደር ጉባኤዎች በጀት መድቦ ይሰጣል። የክፍለ ግዛት አስተዳደር ጉባኤዎች በክፍለ ግዛታቸው አስተዳደር ሥር ታክስ የመጣልና ሌሎች ክፍያዎችን የመመደብ ስልጣን አላቸው፣ የክፍለ ግዛታቸውን አስተዳደር የሥራ ዕቅድ አፈፃፀም ያደራጃሉ፣ ፕሮጀክቶችን በግላቸው ወይም መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ያዘጋጃሉ፣ በሥራም ላይ ያውላሉ። ለ) የወረዳ አስተዳደር ጉባኤዎች ወይም ሌሎች ጉባኤዎች የማዕከላዊውን ሥራዎች ለማስፈጸም እና የመንግሥት አገልግሎቶችን ለህዝብ ለማቅረብ ከላይ የተጠቀሱትን የሚኒስትር መሥርያ ቤቶችን ዕቅዶችን መርምረው በማስፈጸም ይተባበራሉ፣ የታቀዱት ሥራዎችም በአካባቢያቸው ቅድሚያ የሚሰጣቸው መሆኑን ያረጋግጣሉ፣ በብሄራዊ የበጀት የአሠራር ደንብ መሠረትም የሚያስፈልጋቸውን በጀት ያዘጋጃሉ፣ ግብር ታክስና ሌሎች ገቢዎችን ሰብስበው ያስገባሉ፣ ፕሮጀክቶችን በግላቸው ወይም መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ያዘጋጃሉ በሥራም ላይ ያውላሉ። ሐ) የማዕከላዊው መንግሥት ተጨማሪ የሥልጣን ድርሻን ለመቀበል ብቃት ላላቸው የክፍለ ግዛት አስተዳደሮች ተጨማሪ ሥልጣን ስልታዊ በሆነ መንገድ ያስተላልፋል። የክፍለ ግዛት አስተዳደሮች ሥልጣን በተዋረድ ለአካባቢ መንግሥታትና ለማዘጋጃ ቤቶች አስተዳደር በመስጠት ይደራጃሉ። አንቀጽ 57 ሀ) ለኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት ብቻ ተብለው ካልተተዉት ሥልጣኖች በስተቀረ፣ ሌሎቹን የሽግግሩ መንግሥቱ እንደተመሠረተ የሚቋቋሙት የክፍለ ግዛት አስተዳደር ምክር ቤቶች እንዲያስፈጽሙዋቸው ይደረጋል። ለ) የክፍለ ግዛት የአስተዳደር ጉባኤ አባሎች ምርጫ የሚከናወነው የብሄራዊ ሸንጎ አባሎች ምርጫ በሚደረግበት ጊዜ ነው። አንቀጽ 58 ከቦታቸው ተፈናቅለው የተባረሩትን ወይም የተሰደዱትን ዜጎቻችንን በተመለከተ በኢትዮጵያ የንብረት ካሣ ኮሚሽንና በሌሎችም በህጉ መሠረት በሚወሰዱ እርምጃዎች በመጠቀም ተቀባይነት ባለው የጊዜ ገደብ ውስጥ ግለሰቦቹ ወደ መኖሪያቸውና ንብረታቸው እንዲመለሱ ይደረጋል፣ መመለሳቸውም በተጨባጭ ተግባራው ሊሆን ካልቻለ ፍትሃዊ የሆነ የካሣ ክፍያ እንዲደርሳቸው ይደረጋል። ምዕራፍ 9 - የሽግግሩ ጊዜ አንቀጽ 59 ሀ) የሚመሠረተው ቋሚ ህገ መንግሥት የኢትዮጵያ የጦር ሃይሎች የኢትዮጵያን ህዝቦችን የመጨቆኛና የማሸበሪያ መሣሪያ ሆነው ማገልገል የማይችሉ መሆኑን ማረጋገጫ ይሰጣል። ለ) የኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት የማስተዳደር ሥልጣንን እንደተቀበለ የኢትዮጵያን የልዑዋላዊነት ክብር በሚያስጠብቅ መልኩ ኢትዮጵያ የምታከብራቸውን ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ይፈርማል። አንቀጽ 60 የብሄራዊ ሸንጎ የኢትዮጵያን ቋሚ ህገ መንግሥት ረቂቅ ያዘጋጃል። የብሄራዊ ሸንጎ ይህንን ሃላፊነቱን ለመወጣት ሲል መደበኛ የሆኑ ህዝባዊ ውይይቶችን በመላው የኢትዮጵያ ግዛቶች ውስጥ ያካሂዳል:: ውይይቱን በይበልጥ ለማዳረስም የብዙሃን መገናኛ አገልግሎቶችን በስፋት ይጠቀማል። ከኢትዮጵያውያንም ረቂቅ ህገ መንግሥቱ በሚያዘጋጅበት ጊዜም አስተያየቶችን ይቀበላል። አንቀጽ 61 ሀ) የብሄራዊ ሸንጎ የኢትዮጵያን ቋሚ ህገ መንግሥት ረቂቅ ከ _________ ቀን _______ ዓ ም በፊት ጽፎ ማጠናቀቅ አለበት። ለ) የተዘጋጀው ረቂቅ ቋሚ ህገ መንግሥት ለኢትዮጵያ ህዝብ ቀርቦለት በ _______________ ቀን ______________ ዓ ም በሚያደርገው ሕዝበ ውሳኔ እንዲያፀድቀው ይደረጋል። ረቂቁ ህገ መንግሥት ለሕዝበ ውሳኔ እስከሚቀርብበት ጊዜ ድረስ ታትሞ ለህዝቡ በሰፊው እንዲሰራጭና ህዝቡ ህዝባዊ ውይይቶችና ክርክሮች እንዲያደርግበትና ሃሳብ እንዲሰጥበት ይደረጋል። ሐ) ረቂቁ ቋሚ ህገ መንግሥት አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በሕዝበ-ውሳኔው ከደገፈውና ካፀደቀው የኢትዮጵያ ቋሚ ህገ መንግሥት ይሆናል። መ) የቀረበው ቋሚ ህገ መንግሥት በሕዝበ ውሳኔ ከፀደቀ የቋሚ መንግሥት ምርጫ ከ ________ ቀን __________ ዓ ም በፊት ይካሄዳል፣ አዲሱም መንግሥት ከ ______ ቀን ________ ዓ ም በፊት ሥልጣኑን ከሽግግር መንግሥቱ ተረክቦ ሥራውን ይጀምራል። ሠ) የኢትዮጵያ ህዝብ በሕዝበ-ውሳኔው ረቂቁን ቋሚ ህገ መንግሥት ካልተቀበለውና ካላፀደቀው ብሄራዊ ሸንጎ አዲስ የህገመንግስት አርቃቂ ጉባኤ ጠርቶ የህዝቡን ፍሎጎቶች የሚያንጸባርቁ ማሻሻያዎች ካደረገ በኋላ የተሻሻለው ረቂቅ ለህዝበ-ውሳኔ ይቀርባል። ረ) አስፈላጊ ከሆነም የብሄራዊ ሸንጎ አፈ ጉባኤ ከምክር ቤቱ አብላጫ ቁጥር ካላቸው አባሎች ጋር በመስማማት ረቂቅ ቋሚ ህገ መንግሥቱን አዘጋጅቶ ለህዝበ ውሳኔ ለማቅረብ ተጨማሪ ጊዜ ማስፈለጉን አስረግጦ ለፕሬዝዳንቱ ከ _________ ቀን ______ ዓ/ም በፊት ለውሳኔ ያቀርባል። ፕሬዘዳንቱ የመጨረሻው ቋሚ ህገ መንግሥት ተረቆ ለህዝበ ውሳኔ የሚቀርብበትን ቀን ለ12 ወራት ብቻ ያራዝማል። አንቀጽ 62 ይህ ቻርተር ቋሚ ህገ መንግሥት ወጥቶ በህገ መንግሥቱ መሠረት አዲስ የኢትዮጵያ መንግሥት እስከ ሚመሠረትበት ጊዜድረስ ያገለግላል:: /
No comments:
Post a Comment