Monday, August 12, 2013

የሚሊዮኖች ለነጻነት ግብረ ኃይል በዳያስፖራ አስተባባሪ ኮሚቴ በሰሜን አሜሪካ


Monday, August 12,

አገርን የሚመሩና የሚያስተዳድሩ ሰዎች የሚወስኗቸው ዉሳኔዎች፣  አገርን በማልማትም ሆነ በማጥፋት ረገድ ትልቅ አስተዋጾ አላቸው። ብዙዎች በአፋቸው «ፖለቲካን አንፈልግም። ፖለቲካ ውስጥ የለንበትም» ቢሉም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ግን፣ የፖለቲካዉ አካል ናቸው። ፖለቲካዉ የማይነካዉ ማንም ዜጋ የለም። የፖለቲካ ስልጣን የያዙ በሙስና ከተጨማለቁ፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንደ ዜጋ ሊያገኝ የሚገባዉን አገልግሎት በሚገባ አያገኝም። ፖለቲካዉ ዜጎችን  በዘር ከፋፍሎ ፣ «የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ ነህ» በሚል የሥራ እድል የሚነፍገው፣ እንዲፈናቀልና እንዲባረር የሚደረገዉ «ፖለቲከኛ» ያልሆነው ዜጋ ነዉ። የፖለቲካ ዉሳኔ ያመጣዉ የኑሮ ወድነት ቀንበር እየከበደው ያለ፣ «ፖለቲከኛ» ያልሆነዉ ዜጋ ነዉ።
ለሃያ አመታት፣  ብዙዎቻችን፣  ፖለቲካ ወለዶቹ፣ የሰብአዊ መብት ረገጣን፣ የኑሮ ዉድነትን፣ የዘር መከፋፈልን ፣ በመንግስት ባለስልጣናት የሚደርሱትን እንግለትና ወከባን ስናማርር ቆይተናል።  ነገር ግን ለችግሩ መፍትሄ ማምጣቱ ላይ ብዙ ሳናተኩር፣ ባይመቸንም ያለዉን ሁኔታ አሜን ብለን መኖሩን መርጠናል። ነገር ግን ይሄ መቀየር ይኖርበታል። የፖለቲክዉ ችግር የሚፈታዉ በፖለቲካ ትግል ነዉ። ወደድንም ጠላንም፣  ፖለቲካዉ በእያንዳንዳችን ላይ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተጽእኖ ማሳደሩ ካልቀረ፣ ፖለቲካዉ ህዝብን የሚጎዳ ሳይሆን ህዝብን የሚጠቅም እንዲሆን ማቅናቱ፣ ብቸኛ የተሻለ አማራጭ ነዉ። ፖለቲካዉ እንዲቀየርም የሰለጠነ፣ ሁሉንም የሚያሰባስብ፣ በጥላቻ ላይ ያልተመስረተ፣ ከዚህ በፊት ከተሰሩ ስህተቶች የተማረ፣  የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ፖለቲካን ማራመድ ያስፈልጋል። የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት በሚል፣ የአንድነት ፓርቲ ላለፉት በርካታ ሳምንታት ያደረጋቸውን እንቅስቃሴዎች ተመልክተናል። ገዢው ፓርቲ እንቅስቃሴዉን የነፍጠኞች ወይንም የሙስሊም አክራሪዎች እንቅስቃሴ እንደሆነ አደርጎ ለማጥላላት እየሞከረ ነዉ። በደሴ በርካታ ሙስሊሞች እንደመኖራቸው ፣ እንደ ኢትዮጵያዉያን ከሌሎች አምነት ተከታዮች ጋር ሙስሊሞች የአንድነትን ጥሪ ተቀብለው የነጻነት ድምጽ አሰምተዋል። በጂንካና በአርባ ምንጭ ብዛት ያላቸው ፕሮቴስታንቶች፣ በባህር ዳርና ጎንደር ብዛት ያላቸው ኦሮቶዶክሶች፣  ከሌሎች እምነቶች ጋር በመሆን ተመሳሳይ ድምጽ አሰምተዋል። የሚሊዮኖች ድምጽ ንቅናቄ፣  ኦሮቶዶኮሱን፣ ፕሮቴስታንቱን፣ ሙስሊሙን፣ ካቶሊኩን እንዲሁም ሌሎች እምነቶች የሚከተሉትን ኢትዮጵያውያኖችን ሁሉ ያቀፈ ነዉ። «አንድነት የነፍጠኞች ቡድን ነው» የሚል ያረጀበት ፕሮፖጋንዳ አገዛዙ ቢረጭም፣ አንድነት በጂንካ፣ በመቀሌ (ሰልፉ በመጨረሻ ሰዓት እንዲራዘም ቢደረግም) ፣ በአርባ ምንጭ በወላይታ፣ በደሴ፣ በጎንደርና በባህር ዳር እንዳሳየው፣ በኢትዮጵያ ባሉ ግዛቶች ያሉ ብሄረሰቦችን ሁሉ ያቀፈ ፣ አገራዊና  ሰላማዊ እንቅስቃሴ መሆኑንም በግልጽ እያሳየ ነዉ። ይህ የሰለጠነና ሁሉንም ያቀፈ ፖለቲካ ለአገራችን የሚጠቅም ፖለቲካ ነዉ። ጥሩና መልካም ጅማሬ ነዉ። ይሄ እንቅስቃሴ በአጭሩ ከተቀጨ፣  ነገ ተመሳሳይ እንቅስቅሴ እስኪመጣ አመታት ሊፈጁ ይችላሉ። በመሆኑም ይሄ እንቅስቃሴ በሃሳብም በሰው ኃይል በገንዘብ እንዲጠናከር ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነዉ። ይሄ የፖለቲካ ፓርቲ ጉዳይ አይደለም። ይሄ አገርን የማዳን፣ አገርን ወደፊት የማስኬድ ጉዳይ ነዉ። ይህ የሰባአዊ መብት ጉዳይ ነዉ። ሰላማዊ ሰልፎችና ህዝባዊ እንቅስቅሴዎች በጋምቤላ፣ በአዳማ፣ በፍቼ፣ በወሊሶ፣ በባሌ፣ በአዲስ አበባ ይኖራሉ። የተላለፈው የመቀሌዉ ሰልፍ በተጠናከረ ሁኔታ ይደረጋል። ለዚህ ሁሉ፣  ብዙ ወጭ ያስፈልጋል። በሚከተለው ድህረ ገጽ በመሄድ፣ የገንዘብ እርዳታ እናድርግ። ከሚሊዮኖች አንዱ እንሁን ! በመላዉ የኢትዮጵያ ግዛቶች ድምጻቸውን እያሰሙ ካሉ ወገኖቻችን ጋር እንቁም !
  1. በኦንላይን እርዳታ ለማድረግ ለምትፈልጉ በፔይፓል (pay pal secure payment) ከሚከተሉት አንዱ ድህረ ገጾችን ይጎብኙ
http://www.fnotenetsanet.com/?p=5337

No comments: