Thursday, August 1, 2013

በቦረናዎች እና በመንግስት መካከል ያለው ፍጥጫ እንደቀጠለ ነው

ሐምሌ ፳፬(ሃያ አራት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የዞኑ ነዋሪዎች ከመንግስት ጋር ምንም አይነት ትብብር እንደማያደርጉ መግለጻቸውን ተከትሎ፣ ከጠቅላይ ሚ/ሩ ጀምሮ ያሉ ባለስልጣናት ከቦረና ሽማግሌዎች ጋር ውይይት ቢያደርጉም ችግሩ አልተፈታም።
ውዝግቡ የተጀመረው መንግስት ገሪ እየተባሉ የሚጠሩትን የሶማሊ ጎሳ አባላት በቦረና ዞን ለማስፈር እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ ነው። በቅርቡ የ50 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ግጭት ከመከሰቱ በፊት መንግስት ” የገሪ ጎሳ አባላትን” በቦረና ዞን የማስፈር እቅድ እንዳለው በአንድ ጉበኤ ላይ ለህዝቡ ያስታውቃል። ስበሰባውን የመሩት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ካኑ ጂሎ የመንግስትን ውሳኔ እያሳወቁ ባሉበት ወቅት ህዝቡ ተቃውሞውን ማሰማት ይጀምራል። አንዳንዶች ” መንግስት በእኛ ላይ ምን አለው? ለምን አይተወንም?” በማለት ቁጣቸውን መግለጽ ጀመሩ። አስተዳዳሪው አቶ ካኑም ” እኔ ምን ላድርግ ትእዛዝ ስለሆነብኝ ነው እንጅ እኔም እንደናንተው  ውሳኔውን አላምንበትም፣ አቋማችሁን ለመንግስት በቀጥታ አስተላልፋለሁ” በማለት በመድረኩ ላይ ይናገራሉ።
የፌደራል ጉዳዮ ሚኒስቴር የህዝቡን ተቃውሞ ወደ ጎን በማለት እና በአቋሙ በመጽናት ሰዎቹን ለማስፈር እንቅስቃሴ ይጀምራል። በአካባቢውም በቦረና ዞን ፖሊስ ፋንታ የኦሮሚያ ክልል የፖሊስ ሀይል እንዲሰፍር አደረገ። የቦረና ዞን የፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ናታ ዳባ በዞናቸው የክልሉ ፖሊስ መስፈሩን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸው ብቻ ሳይሆን መሬቱን አናስረክብም የሚል አቋም ያዙ ። ፍጥጫው አይሎ ወደ ግጭት ደረጃ አደገ። ኮማንደር ናታ እና አስተዳዳሪው አቶ ካኑን ተይዘው ታሰሩ። አቶ አበረ አየለ የተባሉ ሰውም ቦረና ዞን አስተዳዳሪ ተብለው ተሾሙ።፡ ህዝቡ ግን አዲሱን ሹመት ሊቀበለው አልፈቀደም። የፌደራል ጉዳዮችም መሬቱን የመስጠቱን እንቅስቃሴ አቆመ። ይሁን እንጅ ህዝቡ በመንግስት ላይ የጀመረውን አመጽ ሊያቆም ፈቃደኛ አልሆነም። ቦረናዎች ከመንግስት ጋር ላለመተባበር ቃል በገቡ ማግስት ከገሪ ሶማሊዎች ጋር እርቅ አወረዱ። ” መጀመሪያውኑም መንግስት በመካከላችን ገብቶ ባያጣላን ኖሮ የራሳችንን ችግር ራሳችን እንፈታው ነበር” የሚሉ አስተያየቶች ከሁለቱም ወገኖች ቀረቡ።
በሁኔታው የተደሰተ ያልመሰለው መንግስት ጎሳ ግጭት እንዲፈጠረው አድርገዋል በማለት የዞኑን አስተዳዳሪና  የፖሊስ አዛዡን ጨምሮ በ18 ሰዎች ላይ ክስ ተመሰረተ። እስረኞቹም ወደ ቃሊቲ ተዛወሩ።
ከሁለት ወራት በፊት የኦሮሞያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አለማየሁ አቶምሳ ህዝቡን ለማነጋገር ወደ ያቤሎ ሲያቀኑ ህዝቡና አባገዳው ” ለቦረና ችግር የተሰጠው መፍትሄ መሬታችንን አሳልፎ መስጠት፣ መሪዎቻችንን ማሰር ነው።” የሚል ምላሽ ሰጡ። አንዳንዶች ” አንተ የኦሮምያ መሪ ነህ ብለን እውቅና አንሰጥህም፣ በከተማው ለሚደርስብህ ችግርም ሀላፊነት አንወሰድም” በማለት ሲናገሩ ተሰሙ።
ከአንድ ወር በፊት በያቤሎ ፣ ሀራሮ፣ ሜጋ እና ሞያሌ ወረዳዎች የሚኖሩ ቦረናዎች ለ3 ቀናት ጉባኤ አካሂደው ” ከእንግዲህ በምንም አይነት ሁኔታ አንዱ ሌላውን አሳልፎ ላለመስጠት ፣ አንድነታቸውን ለመጠበቅ፣ ከታሰሩት ጎን እስከመጨረሻው ” ለመቆም ውሳኔ አሳለፉ። አዲሱ አስተዳዳሪ ወደ ጉባኤው ለመምጣት ቢያስቡም ‘ ከህዝቡ በተሰነዘረባቸው ዛቻ ሳይሳካለቸው ቀረ። ኦነግም አጋጣሚውን ተጠቅሞ በአካባቢው ላይ በስፋት መንቀሳቀስ ቻለ። ጥቃት መፈጸሙን ቀጠለ። ዞኑ በግጭት ታመሰ።
በመሀሉ የቦረና አባ ገዳ ጉየ ጎባ እና አቶ ኑራ ዲዳ የተባሉ አገር ሽማግሌ 10 ታዋቂ ሰዎችን ያቀፈ የሽምግልና ቡድን አዘጋጅተው ባለፈው አርብ ከኦሮምያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አለማየሁ ጋር ከተወያዩ በሁዋላ በማግስቱ ከጠቅላይ ሚ/ር ሀይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተወያዩ። ተመሳሳይ ውይይቶችም ከአቶ አባዱላና ከወ/ሮ አስቴር ማሞ ጋር ተደረገ። ሽማግሌዎች የታሰሩት ካልተፈቱ ምንም እንደማይደረግ በመግለጻቸው መንግስት አቋሙን ማለሳለስ ጀመረ።
የመንግስት ባለስልጣናት ” ሀምሌ 25 በመጀመሪያ ደረጃ ብይን ዋናዎቹን እስረኞች ማለትም የዞኑን አስተዳዳሪ፣ የፖሊስ አዛዡንና ሌሎች የካቢኔ አባላትን እንደሚለቅ፣ ሌሎችን ደግሞ በፍርድ ቤት ውሳኔ ካሰጠ በሁዋላ በ14 ቀናት ውስጥ በይቅርታ እንደሚፈታ ” ለሽማግሌዎች አስታወቀ።
የአገር ሽማግሊዎች ወደ መጡበት ተመልሰው ውሳኔውን ለህዝቡ ሲያስታውቁ  ህዝቡ ” ግማሽ ጸጉር ተላጭቶ ግማሽ ማስቀረት የለም” የሚል ምላሽ በመስጠት የመንግስትን የመደራደሪያ ነጥብ ውድቅ አደረገ። ሽማግሊዎችም ተመልሰው ከፍትህ ሚ/ር ባለስልጣናት ጋር ሀምሌ 22 ውይይት አደረጉ። የውይይቱ ውጤት ገና አልታወቀም። ህዝቡ  ሁሉንም እስረኞች አስተፈትታችሁ ካልመጣችሁ፣ ወደዚህ እንዳትመጡብን በዚያው ቅሩ የሚል መልስ በመስጠቱ ፍጥጫው አሁንም እንደቀጠለ ነው።
18ቱ ሰዎች በወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 240 ክስ እንደተመሰረተባቸው ታውቋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የዞኑን አስተዳዳሪ አስተያየት ለማግኘት ሙከራ ብናደርግም ሳይሳካልን ቀርቷል። የመንግስት አስተያየት ከደረሰን የምናቀርብ መሆኑን እንገልጻልን።

No comments: