Wednesday, June 19, 2013

በኢትዮጵያዊያ የመሳፍንት ዘመን አጭር ታሪክ

በኢትዮጵያዊያ የመሳፍንት ዘመን አጭር ታሪክ

June 16, 2013

መምህር ገብረኪዳን ደስታ “ለVOA” ለሰጡት መልስ የግል አስተያየት

በተክሎ አባተ
ከኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ሳንገባ ለዚህ ጽሁፍ መነሻ እንዲያመች ትንሽ ቀንጨብ ማድረግ አስፈላጊ ነው። በ1529 – 1543 ዓ.ም ኢማም አህመድ የተባለው የአፋር ተወላጅ በሐረር አካባቢ የሚገኙ ደጋፊዎቹን በማስተባበር በመላው ኢትዮጵያ የእስላም መንግሥት ለመመስረት ከፍተኛ ጦርነት አድርጓል። በጦርነቱ ምክንያት በእሰልሞናዊ ገዥዎችና በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ላይ ብዙ እልቂት ደረሰ። በዚህ የተነሳ የያሬድ መንፈሳዊ ኪነት እድገት ሳያሳይ በቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ብቻ ተወስኖ ቀረ።
ነገ ርግን ከኢማም መሃመድ ጥፋት በኋላ የሰለሞናዊ ሥርወ-መንግሥት የቀድሞ ግዛቶቹን አስመለሰ። ቢሆንም በተደረጉ የእርስ በርስ ጦርነቶች የኃይል ክፍተት የተነሳ ከደቡብ እስከ ምስራቅ ድረሰ የኦሮሞዎች ወረራ ተስፋፋ። የኦሮሞ ወራሪዎች ገዳ በሚባል ስርዓት ሉባ በሚባሉ የጦር አበጋዞች አማካኝነት ጋሻና ጦር ይዘው የአዳልን የአካባቢ ነገሥታት እየወጉ፤ ነዋሪውን እያስለቀቁ በራሳቸው ቋንቋና ባሕል ለማዋሃድ ከፍተኛ ጦርነት አካሂደዋል።
እሮሞዎች ያደርጉት ጦርነት ራሳቸውን ችለው መንግሥት አይመስርቱ እንጂ በደቡብ መሀል አገር የሚገኙ እሮሞዎች፤ ገራጌዎች፤ ከምባታዎች፤ ሃዲያዎች፤ ሲዳማና ሌሎችም ብሄር-ብሄረስቦች ተቀላቅለው ግዛታቸውን ለማስፋት ሞክረው ነበር።
በጦርነቶች ምክንያት በአንድ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች እየፈለሱ ከሌሎች ጋር በመቀያየጥ አዲስ የአኗኗል ዘቤዎችን በመለማመድ በአሸናፊዎች ተጽኖ ሥር የመውደቅ እጣ ደርሶባቸዋል። በተለይ በምስራቅ አፋር፤ ሱማሌና እሮሞዎች ጐልቶ ይታይ ነበር።
በዘመነ መሳፍንት በኦሮሞ መሪዎች አማካኝነት ይደረጉ የነበሩ ጦርነቶች ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች ብቻ የተወሰነ አልነበረም። በሽዋ ከነበሩ መንግሥታት ጋር በመመሳሰል አጼ ሱሰንዮስ የተባሉ እሮሞዎችን ይዘው ከጐንደር ነገሥታት ጋር ተዋግተው ጐንደር መንግሥት መስርተው ነበር። በየጊዜው የሚደረጉ የሥልጣን ፉክክሮች የኃይል ሚዛናቸው እያየለ ሲመጣ ዛጉዌዎች የሃይማኖትንና የአገር አመራርን ለሰለሞናዊ ሰርወ-መንግሥት አስተላፉ። በዚህ ጊዜ በሰሜን በኩል አማራና ትግሬ የበላይነት እንዳላቸው በሌሎች ዘንድ ጥርጣሬን እንዳስከተለ ይገመታል።
ከላይ የተጠቀሰውን አጋጣሚ በመጠቀም ቱርክ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ የአካባቢ የጐሳ መሪዎችን በጥቅማጥቅም እየደለለች በ1557 ምጽዋን ተቆጣጠረች። እንዲሁ ግብጽ የሱዳን ወደብ የነበረውን ዘይላን ያዘች። ከዛም እስከ ቀይ ባሕር ድረስ ለመስፋፋት ሞክራለች። በ19ኛው ከፍለ ዘመን ጣሊንና እንግሊዝም ቅኝ ግዛታቸውን ለማስፋፋት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ስላደረጉ አገሪቱ በውጭና በእርስ በርስ ጦርነት ተወጠረች።
በዘመነ መሳፍንት የግዛት ዘመን የአገሪቱ ማዕከላዊ መንግሥት እየተዳከመ ሲመጣ የትግራይ ገዥ የነበሩ ራስ ሚካኤል ስሁል የተባሉ ኢዮአስ 1ኛን በ1769 ከሥልጣን አውርደው አስገደሏቸው። እንዲሁ አጼ ዮሃንስ 2ኛ አጼ ተክለሃይማኖት 2ኛን ሲሾሙ ለዘመነ መሳፍንት የመጀመሪያው ክስተት ሆነ።
የተካሄደው የእርስ በርስ የሥልጣን ሽኩቻ በተራዘመ ቁጥር ግብጽ አጋጣሚውን በመጠቀም 1874 ዓ.ም ሀረርን ተቆጣጥራ ነበር። በ1875 ዓ.ም በሰሜን በኩል ጣሊያኖች ከፍተኛ የመስፋፋት ወረራ አደረጉ። ይሁን እንጂ በአጼ ዮሃንስ አራተኛ የግዛት ዘመን ሥመ ጥሩው አሉላ አባ ነጋ ባደረጉት የተቀነባበረ ጦርነት በ1887 ዓ.ም ዶጋሌ ላይ ጣሊያን መሸነፏ አልቀረም። በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲሁ ጉራአ አካባቢ ግብጽ የላከቸው ጦር በኢትዮጵያ አልበገር ባይነት ድባቅ ተመታች።
በኢትዮጵያ የተማከለ መንግሥት ለመመስረትም ሆነ የበላይነትን ለማሳየት ብዙ ጊዜ የእርስ በርስ ጦርነቶች መካሄዳቸውን ከፍ ሲል አውስተናል። ይህ ሁኔታ ባለበት አጼ ቴዎድሮስ 2ኛ በጐንደር በኩል ሥማቸውና ኃይላቸው ጐልቶ ወጣ። ነገር ግን በአገሪቱ የተማከለ መንግሥት ለመመስረት ከፍተኛ ተጋድሎ በሚያደርጉበት ወቅት የቤተክርስቲያን ሹማምትም ሆኑ አንዳንዶች ሥልጣናቸውን ላለማስነጠቅ ውስጥ ውስጡን በአጼ ቴዎድሮስ ላይ መዶለት ጀመሩ። ከዚህ አድማ ባልተናነሰ ሁኔታ የየጁ ኦሮሞ የሽዋ፤ የጐጃም መሳፍንቶች በጐንደር በኩል የሥልጣን ተፎካካሪ የሆኑ አጼ ቴድሮስን ለመውጋት ተነሱባቸው።
የሰሜኑ የትግሬው በዝብዝ ካሣ (አጼ ዮሃንስ 4ኛ) ሥጣል ከቴዎድሮስ እጅ ነጥቀው ብቸኛ ንጉሥ ለመሆን ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው የመሣሪያ እርዳታ አገኛለሁ በሚል ከኢንግሊዝ ጋር ተስማሙ። ይሁን እንጅ አጼ ቴዎድሮስ የውጭ ባዕድ ወራሪ ኃይል አገሪቱን እንዳይደፍራት ኃይላቸውን በማጠናከር ብዙ ጊዜ ተዋግተዋል።
ነገር ግን አገር በቀል ባንዳዎች ለእንግዝሊዝ ጦር መረጃ እያቀበሉ የአጼ ቴዎድሮስ ኃይል እንዲሳሳ ማድረጋቸው አልቀረም። ለዚህ ማስረጃ አጼ ዮሃንስ አራተኛን ከእንግሊዝ ጋር ባደረጉት ውል የናፒየርን ጦር ወደ መቅደላ መምራታቸው ነው። በመጨረሻም አጼ ቴዎድሮስ የሚደርስባቸውን ተቃውሞ እየተጋፈጡ ከ1855 1868 በንግሥና ቆይተው መቅደላ ላይ ከኢንግሊዞች ጋር በተከፈተው ጦርነት ለጠላት እጅ መስጠትን እንደነውር ቆጥረው የራሳቸውን ሽጉጥ ጠጥተው ለአገራቸውና ለሕዝባቸው መስዋዕት መሆናቸውን ታሪክ መዝግቦታል።
ከአጼ ቴዎድሮስ በኋላ አጼ ዮሃንስ 4ኛ ኃይላቸው በማጠናከር ከተቀናቃኞቻቸው ጋር ከፍተኛ ውጊያ አድርገዋል። በእንግሊዝ መንግሥት ተባባሪነት የአጼ ዮሃንስ አራተኛ ኃይል ጐልቶ ሊወጣ ቻለ። ይሁን እንጂ የአካባቢ ገዥዎችን ከማስተባበር ባለፈ አገሪቱን በተማከለ መልክ ማስተዳደር አለመቻላቸውን ከታሪክ መረዳት አያዳግትም። በሰሜን ጀግናው አሉላ አባ ነጋ የጣሊያንን ወረራ እየተጋፈጡ ባለበት የአጼ ዮሃንስ ኃይል እምብዛም እንዳልታከለበት የብዙዎች ግምት ነው።
አጼ ዮሃንስ አገራቸውን ለባዕድ ወራሪ አሳልፈው ላለመስጠት መተማ ላይ ከድርቡሾች ጋር ሲዋጉ ሕይወታቸው ልፏል። አንገታቸው ተቆርጦ ካርቱም መሄዱ እውነት ነው። በዚህ ሁኔታ አጼ ዮሃንስ አራተኛ 1872–1889 ድረሰ ሥልጣን ላይ መቆየታቸው የማይታበል የታሪክ ሃቅ ነው።
አጼ ዮሃንስ አራተኛ ኢትዮጵያን በተማከለ መልክ ለማስተዳድር ጥረት በማድረጋቸው ለኢትዮጵያ ባለውለታ ናቸው። ነገር ግን በግዛት ዘመናቸው ሕዝብ አብሯቸው ተሰልፎ እያለ በእስልምና ተከታዮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደር ጀመሩ። አጼ ዮሃንስ አራተኛ የአስተዳደር ጉድለት ወይም ብቃት ስላልነበራቸው በእስልምና ተከታይ ሕዝብ በኩል ሊያገኙ ይችሉ የነበረው ድጋፍ አጡ። ጠቅለል ባለ መልኩ አጼ ዮሃንስ አራተኛ በታሪክ መልካም ሥም ቢኖራቸውም አጼ ቴውድሮስ በባዕድ ወራሪ እንዲጠቁ ማድረግ ባልተገባቸው ነበር። በዚህ የተነሳ ይመስላል ብዙ ጊዜ የአጼ ዮሃንስ መንግሥት በባዕዳን የተገነባ እንደነበር የተለያዩ የታሪክ ፀኃፊዎች ዘግበውታል።
በልማት በኩል ያደረጉት አስተዋጽዖ ጐልቶ አልታየም። የእስልምናን ሃይማኖት ጠቅለው ወደ ክርስትና ሃይማኖት ለማስፋፋት ከፍተኛ ሥራ ሰርተዋል። ቢሆንም ከጥቅሙ ጉዳቱ እያመዘነ የሃይማኖት ልዩነት በፈጠረው ክፍተት የሰው ሕይወትና ንብረት ከማለቁም ባሻገር የእስላምና የክርስቲያን አንድነት እንዳይጠነክር የአጼ ዮሃንስ አራተኛ አስተዳደር ምክንያት ሆኗል።
ባጠቃላይ በዛ ዓለም ባልሰለጠነት፤ አገሪቱ በእርስ በርስ የሥልጣን ሽኩቻ እየታመሰች ባለበት አገራቸውን ለድርቡሽ አሳልሆፎ ላለመስጠት ያደረጉት ጀግንነት ለመላ ኢትዮጵያ ዋስትና ነበር ማለት ይቻላል።
ከዝርዝር ጉዳዩ ከመግባቴ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ መምህር ገብረ ኪዳን ደስታ ጊዜያቸውን ወስደው የአገር ታሪክ በመፃፋቸው ላንደቃቸው እወዳለሁ። ከዚህ በፊት የተፃፉም ሆነ ያልተፃፉ በታሪክነት እንዲቀመጡ ችሎታ ያላቸው የመፃፍ አገራዊ አደራ አለባቸው። እርግጥ ነው ሰው የማይገሰስ ሰብአዊ መብቱን በመጠቀም መፃፍና መናገር እንደሚችል አምናለሁ። ነገር ግን የአገርና የሕዝብ ታሪክ በዘፈቀደና ክልልን ያማከለ ከሆነ ለትውልዱም ሆነ ለአገር ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ከመምህር ገብረ ኪዳን አንደበት ማድመጥ እንደተቻለው ችግራቸው ከአጼ ምኒሊክ ጋር የተያያዘ ነው። ይህን ካልኩ ዘንዳ ወደ መነሻየ ላምራ።
መምህር ገብረኪዳን ደስታ በቅርቡ ስለአጼ ዮሃንስ አራተኛ ገድል የሚያሳይ መጽሕፍ መፃፋቸው ይታወሳል። ይህን መነሻ በማድረግ የአሜሪካ ሬዲዮ አማርኛ ዝግጅት የትግራይ ቃላቀባይ አቶ ገብራይ ገብሩ የአጼ ዮሃንስን ገድል የሚያወሳ መጽሕፍ መፃፍ ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው ማዳመጥ ችያለሁ።
የመምህር ገብረ ኪዳን ደስታ መልስ፟፦ሌሎች ስለአካባቢያቸው ሲጽፉ እኔም ስለአካባቢየ እጽፋለሁ፤ አጼ ዮሃንስ ለኢትዮጵያ ጥሩ ሰርተዋል፤ ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ ታሪክ የተባለው ለአንድ ውስን ሰርዓ-ተማኅበር ብቻ በማጠንጠን አንድ አቅጣጫ ይዟል፤ ለማቃናት የሚተጋ ሰው አላጋጠመኝም፤ በአጼ ዮሃንስ ላይ የተሳሳተውን ዘገባ ለማስተካከል ነው አሉ። ጋዜጠኛው ገብራይ ገብሩ አክሎ ለዚህ ምን ማሰረጃ አለዎች የሚል ጥያቄ አቀረበላቸው።
የደራሲ ገብረ ኪዳን መልስ ፦ ስለመረጃ ከትግራይ ሕዝብ በላይ ምንጭ የሚሆነኝ ሌላ ሕዝብ የለም የሚል ነበር።
መምህር ገብረ ኪዳን ማብራሪያቸውን ሰፋ በማድረግ አጼ ምኒሊክ የሽዋ ሰው ብቻ ስለነበሩ ሰሜኑን ክፍል እንደ ኢትዮጵያ አይመለከቱትም፤ ለኮሎኒያሊዝም ምክንያት ናቸው ወዘተ በማለት ደጋግመው ነግረውናል።
አዎ አጼ ምኒሊክ የሸዋ ሰው መሆናቸው አይካድም፤ በዚህ ሁላችን ልዩነት ያለን አይመስለኝም፤ እሽ እንስማማ። ችግሩ ግን የሽዋ ሰው ብቻ ስለነበሩ ሰሜኑን ክፍል እንደ ኢትዮጵያ አይመለከቱትም የሚለውን አምኖ ለመቀበል ህሊናየ አልደፈረም። አባቶቻችና የታሪክ መዛግብት እንደሚያስረዱን ከሆነ አጼ ምኒሊክ የመላ ኢትዮጵያ አካል መሆናቸውን ነው ታሪክ የነገረን።
በዘመኑ መሳፍንታት ሲነሱ መጀመሪያ የአካባቢያቸውን ሕዝብ ይሁንታ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ነው። የአጼ ዮሃንስን፤ የአጼ ቴዎድሮስም የኃይል አደረጃጀት እንዲሁ በአካባቢ ላይ የተገነባ ነበር። የአጼ ምኒሊክም አደረጃጀት ከዚህ የተለይ አይደለም። በዚህ ዓይነት መነሻቸውን አውቀው እያሰፉ ሌላውን አካባቢ ማስተዳደር ችለዋል።
አጼ ምኒሊክ ከአጼ ዮሃንስ ለየት የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር አጼ ምኒሊክ አንድ ነገር ከማድረጋቸው በፍፊት አቅምና ችሎታቸውን የማመዛዝን ችሎታ ነበራቸው። በወቅቱ አጼ ዮሃንስ ከእንግሊዝ ባገኙት መሣሪያ የተጠናከሩ ስለነበር ለብቻ ከመዋጋት ይልቅ ኃይል ካለው ጋር በመሆኑ አገሪቱን ማስተዳደር ይቻላል በሚል አጼ ምኒሊክ ከትግሬ ከተወለዱት ከአጼ ዮሃንስ ጋር ወዳጅነት መፍጠር ብቻ ሳይሆ እስከ መጋባት ደርሰዋል። ታዲያ ከሸዋ እስከ ትግራይ ድርሰ ዘር ሳይለዩ በጋብቻ ከተሳሰሩ የሽዋ ብቻ ነበሩ ለማለት አያስደፍርም። ታሪኩ እንደታሪክ ይቀመጥ ከተባለ የጠባብነት ስሜት ያልነበራቸው ምኒሊክ ብቻ ነበሩ ማለት ይቻላል።
የኢትዮጵያን ሉዓዊነት ለማስከበር የተማከለ መንግሥት ለመፍጠር የተለያዩ አካባቢዎችን አንድ እያደረጉ እቅዳቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ እየተንቀሳቀሱ እያለ ከመሳፍንቶች የእርስ በርስ ጦርነት በከፋ መልኩ የጣሊያን መንግሥት ኢትዮጵያን ለመቀራመት ወረራ ጀመረ። ይሁን እንጅ በአጼ ምኒሊክ ድፍረትና በእትጌ ጣይቱ ብልህነት በ1896 የአድዋን ድል ተጐናጸፉ። ነገር ግን የአገሪቱ ማዕከላዊ መንግሥት በመላላቱ የተነሳ ቀረጥ ወይም ታክስ የሚከፍለው የሰው ቁጥር ቀነሰ። የገቢ ምንጭ በቀነሰበት ሁኔታ እስከ መጨረሻው ከጣሊያን ጋር ጦርነት ቢገጥሙ ውድቀት ሊደርስባቸው እንደሚችል በመገመት ለጊዜው ኤርትራን ከጣሊያን እጅ ማስወጣት አልቻሉም።
ለዚህ ዋናው ምክንያት የኢኮኖሚ አቅም ማነስና በሰሜ ኢትዮጵያ አገር በቀሎች ከጠላት ጋር በመወገናቸው ወደ ፊት ቢገሰግሱ ድል ሳይሆን የያዙትን እንደሚያጡ ከግምት በመሳገባት ነው።
የዚህ አይነት የጦርነት እስትራቴጅ በዚህ በ21 ክፍለ ዘመንም ቢሆን አንድ መንግሥት ለውጊያ ሲነሳ መጀመሪያ የጦር ኃይሉን የኢኮኖሚ አቅሙ በማገናዘብ ነው ። ታዲያ የአጼ ምኒሊክ ጥፋት ተምኑ ላይ ነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ይሁን እንጅ አጼ ምኒሊክ ቀስ በቀስ የመሳፍንት ገዥዎችን ወደ አንድ በማምጣት ለማዋሀድና አገሪቱ ከውጭ ወራሪ ጦርነት ተላቃ የቴክኖሎጅ እድገት እንድታሳይ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። የተለያዩ የእምነት ተከታዮች የእርስ በርስ ውጊያን አስቀርተው ወደ አንድ እንዲመጡ አድርገዋል።
አጼ ምኒሊክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የዛሬው ምሁር ያላሳየውን የተራማጅነት ባሕሪ እንደነበራቸው አሳተው አልፈዋል። በአገሪቱ ሰላም የሰፈነ በአጼ ዮሃንስ ዘመን ሳይሆን በአጼ ምኒሊክ የግዛት ዘመን ስለመሆኑ ታሪክ ነጋሪ አያስፈልግም። ድሃው ሰርቶ የመኖር መብቱ ተከብሮ፤ ግብር እንኳን መክፈል ያልቻሉ እርዳታ እየተሰጣቸው በሰላም የኖሩበትን ዘመን ፈጠረዋል። የአግሪቱን የሥልጣኔ ጉዳና ለማፋጠን ገጠሬውን ከከቴሜው፤ የውጩን ከኢትዮጵያ ጋር ለማገናኘት የባቡር መስመር፤ የስልክ አገልግሎት እንዲስፋፋ የመጀመሪያ የእድገት በር ከፋች አጼ ምኒሊክ ናቸው።
በአጼ ዮሃንስ ዘመን ጣሊያን በቀይ ባሕር ሲስፋፋ ነበር። አጼ ምኒሊክ ግን የባድ ወራሪን መስፋፋት ዘመቻ ለመደምሰስ ባደረጉት ጦርነት አድዋ ላይ ድል መቀዳጀታቸው ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌ አጼ ምኒልክ ብቻ ናቸው። የአገሪቱን የእርስ በርስ ጦርነት አስወግደው አዲስ አበባን ቆርቁረው ዛሬ ለአፍሪካ አንድነት ጽሕፈት ቤት በር የከፈቱ ምኒሊክ ብቻ ናቸው።
ኢትዮጵያን በሕግ የሚተዳደር ሕዝብ ፈጥረዋል። ዓለም ባልሰለጠነበት በእርስ በርስ ጦርነት ወቅት አጼ ምኒሊክ ሥልጣ ከአንዱ ወሌላው በሰላም እንዲሸጋገር ለመጀመሪያ ጊዜ የዴምክራርሲን ይትባህል አሳይተው አልፈዋል።
ደራሲው ከአንደበታቸው ሲናገሩ እንደተደመጠው ከሆነ በጐጥ ዙሪያ የተሸበቡ መሆናቸውን አሳይቷል።
በጣም አዛዛኝ ሆኖ ያገኘሁት ደግሞ መላውን ኢትዮጵያ በማግለል ምስክሬና የታሪኩ ምንጭ የትግራይ ሕዝብ ብቻ ነው ማለታቸው የደራሲነታቸውን ማንነት በሚገባ አሳይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የህወሐትን የድል ቀን ትግራይ ውስጥ ሲያከብሩ እንኳ ከወርቅ ሕዝብ ተወለድኩ ያሉትን ቃል ያጠናከረ መጽሕፍ መስሎ ታይቶኛል።
ኢትዮጵያ ከመሳፍንት እስከ አሁን ድረሰ ሕዝቦች ተዋደው ተፋቅረው ዘር ሳይለዩ ተጋብተው ተዋልደው አገራችን አቆይተው አስረክበውናል። በመሆኑም ይህ ትውልድም ሆነ ቀጣዩ ትውልድ አንድ በሆነች አገሩ እንዲኮራ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠነክር የታሪክ መጽሀፍ እንደሚፈልግ አያጠያይቅም።
በመጨረሻ፦መምህር ገብረኪዳን ደስታ በቃለመጥይቁ ላይ የተሳሳትኩት ካለ እታረማለሁ ማለታቸው ኢትዮጵያዊነትን ያሳያል። በመሆኑም መምህር ገብረኪዳን በታሪክነት ያቀረቡትን መጽሀፍ ለአገርና ለሕዝብ አፍራሽ መሆኑን ልብ እንዲሉት ተመልሰው እንዲያነቡትና የሚስተካከለውን በእርምት መልክ ቢያወጡት በሕዝብ ዘንድ ሊኖረዎት የሚገባው ተቀባይነት ቦታ ይኖረዋል። ነገር ግን ወግቶ ይማርህ ከሆነ በታሪክ ማስወቀሱ አይቀርም።
አንባቢያን በዚህ ዙሪያ የተሳሳትኩት ወይም የጐደለ ካለ ለመታረም ዝግጁ ነኝ።
ሁሉም ቀናውን እንዲያሰብ የእግዚአብርሄር ረዴት ይደርብን።

No comments: