Tuesday, June 3, 2014

ሰኔ 1 ቀን ትኩረቱ አዳማና ደብረ ማርቆስ ላይ ነው -አማኑኤል ዘሰላም



የአሥራ ስድስት አመት ወጣት ነበረች። ይሄን ጊዜ ከኮሌጅ ተመርቃ፣ ሥራ ይዛ ምናልባትም ተድራ፣ የልጆች እናት ትሆን ነበር። አሁን ግን የለችም። ኮተቤ አካባቢ ነበር፤ ከአጋዚ ጦር አንዱ በተተኮስ ጥይት ተመታ ወደቀች። ሰኔ አንድ ቀን 1997 ዓ.ም።
shibere
የአሥራ ስድስት አመት ወጣት ነው። በእጆቹ ድንጋይ አልያዘም። ተማሪ ነበር። ወደቤቱ ሲመለስ፣ በአካባቢዉ ግርግር ተፈጠሮ ስለነበረ፣ ሰላምና መረጋጋት እናመጣለን ባሉ ታጣቂዎች ተገደለ። ከጥቂት ሳምንታት በፊት በጊምቢ ወለጋ። ያኔ ደም ፈሰሰ። አሁንም ደም እየፈሰሰ ነው። ያኔም ድብደባ ነበር አሁን ድብደባ ነው።፡ያኔ መታሰር፣ መታፈስ ነበር፣ አሁንም መታሰር፣ መታፈስ ነው። ያኔም አንገት ደፍቶ አቀርቆ ባርያ ሆኖ መኖር ነበር። አሁን አንገት ደፍቶ መኖር ነው። ያኔም ዜጎች ከቅያቸው ይፈናቀሉ ነበር። አሁንም ዜጎች እየተፈናቀሉ ነው። አይበቃም እንዴ ወገን ? ?
አንድ ነገር መርሳት የሌለብን ነገር አለ። ይሄ ሁሉ በአገራችን እና በሕዝባችን ላይ እንዲኖር የፈቀድነው እኛዉ እራሳችን ነን። አምባገነኖችን ማማረርና መራገም ማቆም አለብን። እነርሱ አሁን እያደረጉት ያለውን እንዲያደርጉ የፈቀድንላቸው እኛው ነው።
አንዳንዶቻችን ትችት እንወዳለን። «ይሄ ለምን አልተሰራም፣ ተቃዋሚዎች እንደዚህ ናቸው….» ማለት እንወዳለን። አገር ቤት ያሉ ታጋዮች ትንሽ ስህተት ከሰሩ ፣ ስህተታቸውን አጋነን እናወራለን። የተሰሩ መልካም ስራዎችን ላይ አናተኩርም። ነጻነትን እንፈልጋለን። ግን ሌሎች ታግለው ነጻነትን እንዲያመጡልን ነው የምንጠብቀው። ይሄ አይሆንም !!! ይሄ አይሰራም። ዳር ቆም ትችት ያለፈበት ፖለቲካ ነው።
ለዉጥ ከፈለግን ፣ ሌሎች ለምን ይሄን አያደርጉም ማለት አቁመን፣ እኛ ምን እያደረግን ነው ብለን መጠየቅ አለብን። ያልተሰራ ነገር ካለ፣ ሰብሰብ ብለን፣ ጓደኞቻችን ይዘን እኛው እንስራው። በአገራችን ጉዳይ ላይ ነጋሪና ጎትጓች ሊኖረን አይገባም። ትግሉን ለመርዳት ተሯሩጠን መምጣት አለብን እንጂ መለመን የለብንም። በአገራችን ሰለምና ደሞክራሲ ኒኖር እኮ፣ እስክንደር ነጋ ወይንም አንዱዋለም ወይንም አገር ቤት እየተጋሉ ያሉቱ ብቻ አይዴልም የሚጠቀሙት። እያንዳንዳችን ነው የምንጠቀመው። ኢትዮጵያ ስትመነጠቅ፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ነው የሚመነጠቀው። ስለዚህ የምንታገለው ፣ ባናስተዉለው ነው እንጂ፣ ለራሳችን ነው።
ለበርካታ አመታት የአንድነት ፓርቲ ላይ ከፍተኛ ትችት ይቀርብ ነበር። «ምን እየሰሩ ነው ? ለምን አያታግሉንም ? ..» እያሉ የሚጮሁ ጥቂት አልነበሩም። እነሲህ ሰዎች ያኔ ትክክል ነበሩ። አዎን አንድነት ተኝቶ ነበር። ግን ያለፈው አመት የተለየ ሁኔታ እያየን ነው። ባህር ዳር፣ ደሴ፣ ጊዶሌ አዲስ አበባ ….ይመስክሩ። አንድነት አስደሳች በሆነ ሁኔታ የተጨበጡ ስራዎችን እየሰራ ነው። ታዲያ ትላንት አንድነትን ለምን አልሰራም ብለን ስንተች የነበረን፣ ዛሬ ድምጻችን ለምን ጠፋ ? ታዲያ የኛንስ ድርሻ ለመወጣት ለምን ዘገየን ?
እንግዲህ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከራሱ ጋር እንዲነጋገር እጠይቃለሁ። የፊታችን እሁድ ሰኔ 1 ቀን በአዳማና በደብረ ማርቆስ ታልቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተጠርቷል። ባለስልጣናት ለሰልፉ እውቅና ሰጥተዋል። እንግዲህ በአዳማ እና በደብረ ማርቆስ ያለን በነቂስ እንወጣ። ድምጻችንን እናሰማ። «ነጻነት ፣ ነጻነት፣ ቢሊሱማ ! ቢሊሱማ» እያለን እንጩህ። በራሳችን እንተማመን። እነርሱ ምንም ማድረግ እንደማንችል ነው ደጋግመው ሊነግሩን የሚፈልጉት። ያንን ከማለትና ልቦናችንን ለመስለብ ከመሞከር ዉጭ ሌላ አማራጮች የላቸውም። እኛ ግን ልባሞች እንሁን። አንፍራ። በደብረ ማርቆስና በአዳማ የነጻነት ደዉል ይሰማ።
በተቀረው የኢትዮጵያ ግዛት እንዲሁም በዉጭ አገር ያለን፣ በመንፈስ ሰልፉን እንቀላቀል። በሶሻል ሜዲያዎች ዘምቻዉ ፣ ቅስቀሳው ይጧጧፍ። በስካይፕ፣ ቫይበር፣ ኢሜል ወዳጅ ዘመዶቻችንን ወደ ሰልፉ እንዲወጡ እናበረታታ። እንነቃነቅ!!!!!!
በዉጭ አገር ላለን በተለየ ሁኔታ ሌላ ትልቅ ሃላፊነት አለብን። ገዢው ፓርቲ እንዳለ ኢኮኖሚዉን ተቆጣጥሯል። የአገሪቷ ካዝና በ እጃቸው ነው። የህዝብን ጥያቄ አንግቦ የሚንቀሳቀሰው የሚሊዮነሞች ንቅናቄ፣ የጀርባ አጥንቱ ህዝብ ነው። እኛ ነን። በዚህ ጊዜ አገር ቤት ያለው ሕዝባችን ፈታኝ ትግል እያደረገ ባለበት ወቅት፣ በዉጭ ካለን ብዙ ይጠበቃል። ለሌሎች ፣ ሌሎች ጉዳዮች ብዙ ገንዘብ እየተሰበሰበ ባለበት ሁኔታ፣ ወሳኝ ለሆነው ነገር ዝምታዉና መቀዝቀዙ ትክክል አይደለም። ዳያስፖራው ፕራዮሪቲዉን ማስተካከል አለበት።

No comments: