sourse reporter
በአዲስ አበባ ከተማ የአልሸባብን የሽብር ተልዕኮ ለመፈጸም ሲዘጋጅ ነበር የተባለ ግለሰብ መያዙን፣ የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ ግብረ ኃይል ማክሰኞ ምሽት አስታወቀ፡፡
ግብረ ኃይሉ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ተያዘ የተባለው ግለሰብ በአዲስ አበባ ከተማ የሽብር ጥቃት ለማድረስ የሚያስችል ዝግጅት ሲያደርግ እጅ ከፍንጅ ተይዟል፡፡ ኅብረተሰቡ የተለዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያስተውል ለሚመለከተው አካል በፍጥነት እንዲያሳውቅ የጠየቀው ግብረ ኃይሉ፣ ስለግለሰቡ ዝርዝር መግለጫ አልሰጠም፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ አልሸባብ በኢትዮጵያ ላይ በተደጋጋሚ ከሚያደርገው ዛቻ የዘለለ ጥቃት በኢትዮጵያ ላይ ሊፈጽም እንደማይችልና የሚያሰጉ ሁኔታዎች በኢትዮጵያ አለመኖራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የአሜሪካ መንግሥት በአዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲው አማካይነት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩና ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙ አሜሪካውያን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ አስታውቋል፡፡
አልሸባብ በኢትዮጵያ ጥቃት ለመፈጸም እንደሚችል የሚያስረዱ ታማኝ መረጃዎች እንደደረሱት በመጠቀስ ነው የጥንቃቄ ማሳሰቢያውን ኤምባሲው በድረ ገጹ ላይ ይፋ ያደረገው፡፡
ጉዳዮችን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ምንም ዓይነት የፀጥታ ሥጋት እንደሌለበት አስታውቀዋል፡፡
አልሸባብ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ ላይ እንደሚዝት የጠቆሙት ቃል አቀባዩ፣ የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ምንጊዜም ዝግጁና ጥንቁቅ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ያወጣው የጥንቃቄ ማሳሰቢያን በተመለከተ፣ በራሳቸው መንገድ የተለመደ አሠራር ነው ብለዋል፡፡
‹‹በኢትዮጵያውያና በምዕራባውያን ማዘውተሪያዎች ላይ አልሸባብ የፈጠረው ሥጋት›› በሚል የወጣው ይኼው የአሜሪካ መንግሥት የጉዞ ማስጠንቀቂያ፣ ‹‹ኤምባሲው አልሸባብ በኢትዮጵያ ኢትዮጵያውያንንና ምዕራባውያንን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ለመፈጸም መዘጋጀቱን ታማኝ የሥጋት ማስጠንቀቂያ ሪፖርቶች ደርሰውታል፤›› ይላል፡፡
ኤምባሲው በደረሰው መረጃ መሠረት የአልሸባብ አባላት በቅርብ ሳምንታት ውስጥ፣ በኢትዮ ሶማሊያ ድንበር አካባቢ ወደ ኢትዮጵያ ሰርገው መግባታቸው ታውቋል፡፡
ኤምባሲው ጥቃቱ የሚፈጸምበትን ጊዜና ቦታ በግልጽ ባይጠቅስም፣ በኢትዮጵያ አሜሪካውያንና ሌሎች ምዕራባውያን በብዛት ተሰባስበው የሚገኙባቸው ሆቴሎች፣ መጠጥ ቤቶች፣ የገበያ ማዕከላትና የእምነት ቦታዎች ላይ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል በማመላከት፣ በእነዚህ ሥፍራዎች የሚንቀሳቀሱ አሜሪካውያን ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስጠንቅቋል፡፡ ማስጠንቀቂያው በኢትዮጵያ የሚኖሩና ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙ ዜጐች፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጉዞ ማስጠንቀቂያ ፕሮግራምን በተጠንቀቅ እንዲከታተሉ አሳስቧል፡፡
የአፍሪካና የአሜሪካ ኢነርጂ ሚኒስትሮች በአዲስ አበባ ስብሰባቸውን እያካሄዱ ሲሆን፣ በመዲናው እንግዶች ሲበዙ በሆቴሎች ከአባባቢ ጠበቅ ያለ ፍተሻና ጥበቃ ማድረግ የተለመደ ቢሆንም ሪፖርተር ተዘዋውሮ ማረጋገጥ እንደቻለው፣ በበርካታ ሆቴሎችና ሥፍራዎች የአሜሪካ መንግሥት የጉዞ ማስጠንቀቂያ መውጣትን ተከትሎ እጅግ የተጠናከረ ፍተሻ እየተደረገ ይገኛል፡፡
አልሸባብ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ስታዲየም በእግር ኳስ ተመልካቾች ላይ ለማፈንዳት ያዘጋጀው ቦምብ ድንገት ፈንድቶ ሽብር ሊፈጽሙ የተዘጋጁ አባላቱ መሞታቸው የሚታወስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወታደሮች በቅርቡ በሶማሊያ የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) ከተቀላቀሉ ጊዜ ጀምሮ፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ በርካታ የአገሪቱ ከተሞች ከአልሸባብ ነፃ መውጣታቸው በስፋት እየተዘገበ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አልሸባብ በኢትዮጵያ ላይ ሲዝት ቆይቷል፡፡ ሰሞኑን የኢትዮጵያና የሶማሊያ ወታደሮች በከፈቱት ጥቃትም 74 የአልሸባብ ታጣቂዎች መገደላቸውን ከሶማሊያ የወጡ ዘገባዎች ያስረዳሉ፡፡
No comments:
Post a Comment