Saturday, June 21, 2014

ድርብ አኃዝ ዕድገት ወይስ ድርብ ድህነት?


poor1
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የዓለምአቀፍ ልማት ትምህርት ክፍል ሥር የኢኮኖሚ ጥናት የሚያካሂደው የኦክስፎርድ የድህነትና የሰብዕ ልማት ማዕከል (The Oxford Poverty and Human Development Initiative (OPHI)) ሰሞኑን ባወጣው የ2014 የጥናት መረጃ ደሃ ከሚባሉት አገራት ዝርዝር ኢትዮጵያ ከመጨረሻው ሁለተኛ መሆኗን ገለጸ፡፡ የጥናቱ ዘገባ ኢህአዴግ በየጊዜው ከሚያቀርበው የዕድገት ስሌት ጋር በግልጽ የሚጋጭ መሆኑ ተነገረ፡፡
በዓለማችን በሚገኙ 108 በማደግ ላይ ባሉ አገራት በየጊዜው ጥናት የሚያካሂደው ማዕከል ጥናቱን በሚያካሂድበት ጊዜ 10 መለኪያዎችን እንደ ግብዓት እንደሚጠቀም ይናገራል፡፡ እነዚህም በሦስት ዘርፎች የተጠቃለሉ ናቸው – ትምህርት፣ ጤና እና የኑሮ ሁኔታ፡፡ በተለይ በኑሮ ሁኔታ ሥር ኤሌክትሪክ፣ ጽዳት፣ የሚጠጣ ውሃ፣ የንብረት ባለቤትነት፣ ወዘተ በግብዓትነት ተወስደዋል፡፡
በዚህ ዓይነት እኤአ ከ2002 እስከ 2011 ድረስ ያለውን መረጃ በማጠናቀር በወጣው ዘገባ መሠረት በኢትዮጵያ ውስጥ ከ100 ሰዎች መካከል 87ቱ ድሃ ተብለው የሚጠሩ ሲሆን 58ቱ ሰዎች ግን መናጢ ደሃ ተብለው የሚጠሩ መሆናቸውን ይናገራል፡፡ ድህነቱ በገጠር እጅግ የከፋ እንደሆነ በመጠቆም ከ100 ሰዎች ውስጥ 96ቱ ደሃዎች እንደሆኑ፤ በከተሞች አካባቢ ግን ከ100 ሰዎች መካከል 46ቱ ደሃ ተብለው የሚጠሩ መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአጠቃላይ የአገሪቷ ክፍሎች ከ100 ሰዎች መካከል 31ዱ በቀን ከ20ብር በታች በሚገኝ ገቢ እንደሚኖሩ ጠቁሟል፡፡
ድህነቱ የከፋባቸው “ክልሎች” ብዙም ልዩነት እንደሌላቸው የሚያሳየው የጥናቱ ዘገባ ከሁሉም ግን ሶማሊ በደሃነት ቀዳሚ ነው፡፡ በጥቂት ነጥብ ልዩነት ኦሮሚያ፣ አፋር፣ አማራ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል፡፡ በእነዚህ አምስት ክልሎች ከ100 ሰዎች ውስጥ 90 እና ከዚያ በላይ የሚሆኑት ደሆች መሆናቸው በጥናቱ ተዘርዝሯል፡፡
የ108 በማደግ ላይ ያሉ አገራት የድህነት መለኪያ ዝርዝር የያዘው ዘገባ በግልጽ እንደሚያሳየው የመጨረሻዋ ደሃ አገር ኒጀር ስትሆን ከዚያ ቀጥላ ኢትዮጵያ ነች፡፡ እስከ 10 ባሉት የመጨረሻ አገራት ውስጥ ማሊ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ላይቤሪያ፣ ጊኒ፣ ሶማሊያ፣ ቡሩንዲ፣ መካከለኛው አፍሪካ እና ጊኒ ቢሳው ከ3 – 10 ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡
በየጊዜው የኢትዮጵያ ዕድገት “ድርብ አኻዝ” እንደሆነ ለሚናገረው ኢህአዴግ ይህ ዓይነቱ ዓለምአቀፋዊ ዘገባ የከፋ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር በአስተያየት ሰጪዎች ዘንድ ይነገራል፡፡ በተለይ “ምርጫ” እየቀረበ ባለበት ወቅት ይህ ዓይነቱ በታዋቂ ዩኒቨርሲቲ የሚመራ ማዕከል የወጣ የጥናት ዘገባ የሚያመጣው ተጽዕኖ ከፍባለ ሁኔታ ለመጠቀም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በቂውን ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባቸው እነዚሁ ወገኖች ይናገራሉ፡፡ ኢህአዴግ የማይስማማውን ማንኛውንም ዓይነት ዘገባ “የልማት ጸሮች” ያወጡት፣ “የአሸባሪዎች እጅ ያለበት”፣ “የኒዎ ሊበራል አቀንቃኞች ዘገባ”፣ “የኪራይ ሰብሳቢዎች ምኞት”፣ ወዘተ እያለ እንደሚያጥላላውና እንደሁኔታው የተለመደውን “ማጣፊያ” በኢቲቪ ወይም ሌሎች ድቃይ “የሚዲያ” ክፍሎች ላይ እንደሚያቀርብ ጎልጉል አስተያየት የጠየቃቸው በኢትዮጵያ የከፍተኛ ተቋም ምሁር ገልጸዋል፡፡
ይህ የኦክስፎርድ ማዕከል ይህንን ጨምሮ በየጊዜው የሚያቀርባቸው የጥናትና ምርምር ውጤቶች በበርካታ ዓለምአቀፋዊ ድርጅቶች፣ በፖሊሲ አውጪዎች እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) እና ሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት ጥቅም ላይ እንደሚያውሉት በድረገጹ ላይ አስታውቋል፡፡
የጥናቱን ዘገባ በPDF ለማግኘት እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡ በቀጥታ ከማዕከሉ ድረገጽ ላይ ለማግኘት እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

No comments: