መስከረም ፳፫(ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ለተቃውሞ ወደ ኢትዮጵያ ኤምባሲ በተጓዙት ኢትዮጵያውያን ላይ ጥይት የተኮሰው የኢምባሲ ሰራተኛ በ48 ሰአታት ውስጥ አገር ለቆ እንዲወጣ መደረጉን ኢሳት በሰበር ዜና መዘገቡን ካስታወቀ ከአንድ
ቀን በሁዋላ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግለሰቡ ከአገር መባረሩን አረጋግጧል።
የኢትዮጵያ መንግስት በቅጽል ስሙ ወዲ አይኑ የተባለውን የደህንነት ሰራተኛ የዲፕሎማቲክ ከለላ እንዲያነሳ ቢጠየቅም፣ ፈቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ ከአገር ለቆ እንዲወጣ መደረጉን የስቴት ዲፓርትመንት ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ ገልጸዋል።
አሜሪካ ለወሰደችው ጠንካራ እርምጃ የኢህአዴግ መንግስት እስካሁን የሰጠው መልስ የለም።
አሜሪካ “የዲፕሎማቲክ ኮንሱላር ከለላን “በተመለከተ የምትጠቀምበት የአሰራር መመሪያ እንደሚያመለክተው አንድ የዲፕሎማቲክ ከለላ ያለው ሰው ከፍተኛ የሆነ ወንጀል እስካልሰራ ደርስ የዲፕሎማቲክ ከለላውን አይነጠቅም።
መመሪያው አሜሪካ አንድን የዲፕሎማቲክ ከለላ ያለውን ሰው ከአገሯ ከማባረሩዋ በፊት ፖሊስ ትክክለኛ ማስረጃ መያዙን ማረጋገጥ እንዳለበት ያዛል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የዲፕሎማቲክ ከለላ ያለው ሰው ከፍተኛ ወንጀል መፈጸሙን ከጸጥታ ሰራተኞች አስተማማኝ መረጃ ካገኘ በሁዋላ፣ ዲፕሎማቱን የላከቸው አገር ወንጀል የሰራውን ሰው የዲፕሎማቲክ ከለላ እንዲያነሳ ከጠየቀ በሁዋላ፣
ዲፕሎማቱን የላከው አገር ወንጀል የሰራውን ዲፕሎማት ከለላ ለማንሳት ፈቃደኛ አለመሆኑን ካረጋገጠች በሁዋላ በ48 ሰአታት ውስጥ ከአገር እንደምታባርር በአሰራር መመሪያው ላይ ሰፍሯል። sourse ecdef
No comments:
Post a Comment