Wednesday, October 29, 2014

አዳማጭ እና አክባሪ ያሌለበት ትግል ዋጋ የለውም። ለህዝባዊ ድል የጋራ ጉዞ ውጤት አለው። ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ ሳይሆን ተደማመጡ ተከባበሩ ተቀናጁ የኛ ምክር ነው። Minilik Salsawi እንደማመጥ !!! እንከባበር !!!



October 28th, 2014
ባሳለፍናቸው አመታቶች የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሃገር አቀፍ በብሄር አቀፍ እና ቤተሰብ አቀፍነት ተመስርተው ከስመዋል። ሲንደባለሉ ለአሁኑም ወቅታዊ ጡዘት የደረሱም እያዛጉ እና እያፋሸኩ በፖለቲካ አንጎበር እየተናጡ በገሺው አምባገነን ፓርቲ እየተደቆሱ ላለመሞት በወንዳታነት እየተፈራገጡ ይገኛል።
የተቃዋሚ ሃይሎች እና የለውጥ ፈላጊ ሃይሎች አንድነት የሚያስፈልግበት ወቅታዊ እና ወሳኝ ትግል ላይ መድረሳችን ለሕዝብ ያለንን አክብሮት ለማሳየት እና ግባችንን በመምታት ለህዝባዊ ድል መብቃት የምንችለው የጋራ ጉዞ በማድርግ ትግሉን እጅ ለእጅ ተያይዘን በመደማመጥ እና በመከባበር ያሰብነውን ግብ መምታት የምንችል ሲሆን እኔን ብቻ ስሙ እና ከኛ በላይ ላሳር የሚሉ ቡድኖች ከነገው ውርደታቸው ራሳቸውን እንዲያድኑ እየመከርን ነው።
ህዝብን ለጊዜው ማታለል እንደሚቻል እና ሕዝብም በአሁን ጊዜ ንቃተህሊናው የሰፋ በመሆኑ ትግሉን በምን መልኩ እናሯሩጠው ብቻ ሳይሆን ጎን ለጎን የህዝብ እና የለውጥ ሃይሎችን በጋራ ሃገራዊ አጀንዳ ማሰለፍ ስንችል ግቡን መምታት እንደሚቻል ግልጽ የሆነ ጉዳይ ነው። ከአሁን ቀደም የተቃዋሚ ሃይሎች ተባበሩ አሊያም ተሰባበሩ እየተባለ ሲወረወር የነበረው ታሪክ በማብቃቱ አሁን ህዝቡ ለሚሻው ለውጥ መደማመጥ እና መከባበር ዋናው ስራችን ሊሆን ይገባል። መፈራረጅ መጠላለፍ አንዱን አጥፍቶ በአንዱ ላይ መረማመድ ወዘተ የፖለቲካ ሴራ እና ደባ ወንዝ እንደማያሻግለን ማወቅ ይኖርብናል።
ይህንን በመጻፌ ምናልባት ካለኛ ምንም የለም የሚሉ ሃይሎች የመናቅ እና የማጓጠጥ የማጥላላት ሙጥመጣ ቢያደርጉም ደግሜ ልነግራቸው የሚገባው ነገር ማንኛውም ቡድን ብቻውን ተጉዞ ምንም ማምጣት እንደማይችል እና በመደማመጥ እና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ውጤት እንዳለው ላስውጣቸው እፈልጋለው። በፖለቲካ ሴራ አንዱ ከአንዱ ሌላው ከተባባሪው ሆኖ አንዱን አሊያም ትንንሹን ለመዋጥ የሚያደርገው ጥረት ለጊዜው ስኬታማ ቢመስልም እንደማያዋጣ ለመናገር እደፍራለሁ።
ወያኔን ለመጣል በሚደረገው ትግል ውስጥ አንድ ወጥ ፓርቲ በመመስረት አሊያም በመዋሃድ የቶሎ ቶሎ ፖለቲካ በማራመድ የሚመጣ ለውጥ ስለሌለ መጀመሪያ በመቻቻል እና በመተባበር መንፈስ ሀገራዊ አጀንዳን በመያዝ ከፓርቲ ጥገኝነት በመላቀቅ በብሄራዊ ጥቅም ላይ ያተኮረ ስራ በመስራት መጓዝ ሲቻል ካለመደማመጥ እና ካለመከባበር የሚደረጉ የበላይነት ስሜትን ያቀፉ ሂደቶች የትም ስለማያደርሱ ባለን ሃይል የለውጥ ሃይሎችን በማስተባበር በመተቃቅፍ በሃዝባዊ ጥቅሞች እና በአገራዊ ውነቶች ላይ ተመርኩዘን ያለውን አምባገነን ስራት መጣል የምንችል መሆኑን ለመግለጽ እየሞከርኩ አዳማጭ እና አክባሪ ያሌለበት ትግል ዋጋ የለውም። ለህዝባዊ ድል የጋራ ጉዞ ውጤት አለው።እላለሁ። እንደማመጥ !!! እንከባበር !!! ይህ የዜግነት ግዴታችን ሊሆን ይገባል።      http://www.abugidainfo.com/amharic      sourse 

No comments: