ጥቅምት ፲፮(አስራ ሥድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በጋምቤላና በደቡብ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች በሚኖሩ በመዠንገርና በመንግስት ታጣቂ ሃይሎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ፣ ቁጥራቸው 50 የሚጠጋ የፌደራል ፖሊስ፣ የመከላከያና የአካባቢው ሚሊሺያዎች ከተገደሉ በሁዋላ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመከላከያ ሰራዊት አሁንም በአካባቢው እንቅስቃሴ እያደረገ ነው።
ወኪላችን እንደሚለው ጦርነት ይነሳል በሚል ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ ከፍተኛ ስጋት የነበረ ሲሆን፣ ትምህርት ቤቶች ለአንድ ቀን ተዘግተው መዋላቸውንም ገልጿል። የጦርነት ወሬዎች መናፈሳቸው በአካባቢው ነዋሪ ላይ አለመረጋጋት ቢፈጥርም እስካሁን ይህ ነው የሚባል ነገር አለመከሰቱንና የወሬው ምንጭም በአካባቢው የሚታየው የሰራዊት እንቅስቃሴ ሊሆን ይችላል ብሎአል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ በአበቦና በጋምቤላ ከተማ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ የተገመገሙ በርካታ ቁጥር ያላቸው የልዩ ሃይል አባላት እስከነመሳሪያቸው መጥፋታቸውን ምንጮች ገልጸዋል። በርካታ ቁጥር እንዳላቸው የተነገረው እነዚህ አባላት፣ የአኝዋክ፣ ኑዌርና መዠንገር ተወላጆች ናቸው። ኢሳት የጠፉትን ወታደሮች ለማነጋገር ካለፉት ሶስት ቀናት ጀምሮ ሲያደርገው የነበረው ሙከራ በስልክ ኔትወርክ ችግር ምክንያት ሊሳካለት አልቻለም።
ከዚሁ አካባቢ ሳንወጣ ካለፉት አራት ቀናት ጀምሮ በአራት ዞኖች የታየው የመብራት መጥፋት የአካባቢውን ነዋሪዎች ለችግር ዳርጎአቸዋል። በጅማ፣ ከፋ፣ ማሻ ና ቤንች ማጂ ዞኖች የታየው የመብራት መጥፋት መንስኤ ምን እንደሆነ ለማወቅ አልተቻለም። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የውሃ እጥረትም ተከስቷል። በጉዳዩ ዙሪያ የአካባቢውን ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። http://ethsat.com/amharic/
No comments:
Post a Comment