Friday, October 24, 2014

በአዲስ አበባ በሚካሄደው የፖለቲካ ስልጠና ላይ ሰልጣኞች ለምናነሳቸው ጥያቄዎች መልስ አላገኘንም አሉ




ጥቅምት ፲፫(አስራ ሦስትቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-በአዲስ አበባ ለ3ኛ ጊዜ በተዘጋጀው የፖለቲካ ስልጠና መድረክ ከወረዳ ጽ/ቤት እስከ ማዕከል ቢሮዎች የሚገኙ ሰራተኞች እና የፌደራል መ/ቤት ሰራተኞች ከማክሰኞ ጥቅምት 3 ቀን እስከ ቅዳሜ ጥቅምት 14/2007 ዓ.ም ለተከታታይ 11 ቀን የፖለቲካ ስልጠና የተሰጠ ሲሆን፣  በዚህ መድረክ እስካሁን ከታዩት በላይ በሰልጣኖችና በኢህአዴግ አመራሮች መካከል ፍጥጫ ታይቷል። ጠንካራ ጥያቄ በማቅረብ ሰልጣኙን አነሳስቷል የተባለ አንድ ሰልጣኝ ከስራው እንዲባረር መደረጉን ዘጋቢያችን ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ብሎ በነበሩት የስልጠና መድረኮች የነበሩ ሰልጣኞች በተለይ የድርጅት አባሎቹ በስልጠና ላይ ሳሉ ከአበል በተጨማሪ በእረፍት ሰዓት እሽግ ውሃ፣ ሻይ ቡና እና በቂ የእረፍት ጊዜ እንዲሁም የፌደራል መ/ቤት ሰራተኞች ደግሞ በአዲስ አበባ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ገብተው የተሟላ  የምግብና መኝታ አገልግሎት በማግኘት ሰልጥነው ሲወጡ በአንፃሩ ደግሞ የ2ኛና 3ኛ ዙር ሰልጣኞች ለእኛ ለምን የተሟላ አገልግሎት አይሰጠንም በማለት ተቃውሞ አሰምተዋል።
ሰልጣኞቹ ከመንግስት የስራ ሰዓት ውጪ በእረፍት ቀን ቅዳሜ ጭምር በጫና ተገደን ለምን እንድንሰለጥን ይደረጋል ሲሉም ተደምጠዋል።
ሰልጣኞቹ ላነሱዋቸው ጥያቄዎች ተገቢ መልስ ሳይሰጥ ወደ ስልጠና እንዲገቡ የታዘዙ ሲሆን በዚህም ሁኔታ ላይ እንዳሉ በከተማው ሁሉም የስልጠና ቦታዎች በአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽ/ቤት ተዘጋጅቶ ለመጀመሪያ ዙር ሰልጣኞች የተከፋፈለው ተመሳሳይ ቪዲዮ  በድጋሚ በፕሮጀክተር ስክሪን በመታገዝ በተመሳሳይ የጊዜ ሰሌዳ በከተማው በተዘጋጁ ሁሉም የስልጠና አዳራሾች አንድ ጊዜ ገለጻ አንድ ጊዜ የጥያቄና መልስ ውይይት እየተደረገ ሰልጣኝ ሰራተኞችም በ1ለ5 በቡድን እንዲከፋፈሉ ተደርጎ በገለጻው ላይ ውይይት እንዲያደርጉ ተደርጓል።
ሰልጣኝ የመንግስት ሰራተኞች ጥያቄ ማንሳት ሲጀምሩ በአንዳንድ መድረክ የሚገኙ አወያዮች የተሳታፊ ጠያቂዎችን ስምና የመጡበትን መ/ቤት በመጠየቅ ማስታወሻ ሲይዙ ተስተውሏል።  ይህንንም ተከትሎ ሰራተኛው ለምን ትጠይቁናላችሁ በማለት ተቃውሞ ሲያነሱ አወያዮች ደግሞ ለመግባባትና ለመተዋወቅ ያክል ነው በማለት ሲመልሱ በተቃራኒው ሰራተኛው እናንተ የምታመጡት አይታወቅም! አናምናችሁም! በማለት ተቃውሞ አሰምቷል።
በተከታታይ በተደረጉት የስልጠና ቀናት የአዲስ አበባ መስተዳድር የተለያዩ የካቢኔ አባላት ቅሰቀሳ አድርገዋል። አቶ ተወልደ ገ/ፃድቅ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊና የከንቲባው ዋና አማካሪ “የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግልና አገራዊ ህዳሴያችን” የሚል ሰነድ፤ አቶ አባተ ስጦታው /የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ “የተሃድሶው መስመርና የኢትዮጵያ ህዳሴ” የሚል ሰነድ፤ አቶ ይስሐቅ ግርማይ /የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቅም ግንባታ ዋና ቢሮ ኃላፊ “የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ትግላችንና ፈተናዎቹ” የሚል ሰነድ፤ ዶ/ር ታቦር ገ/መድህን /የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ “የኢ.ፌ.ዴ.ሪ.ህገ መንግስትና የፌደራል ሥርዓቱ ዓላማዎች፣ መርሆዎች፣ዕሴቶች፣ባህሪያትና ውጤቶች” የሚል ሰነድ፤ እንዲሁም ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ /የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቅም ግንባታ ም/ቢሮ ኃላፊ “ልማታዊ ሲቪል ሰርቪስ የመገንባት ፋይዳና አገራዊ ሕዳሴውን በማሣካት ሂደት የሲቪል ሰርቪሱ ሚና” በሚሉ ሰነዶች ላይ በንባብ ብቻ የተመሰረተ አሰልቺ የቪዲዮ ገለጻ እስከ ስልጠናው መጨረሻ በቅደም ተከተል ሰጥተዋል፡፡
ሆኖም ሁሉም የካቢኔ አባላት በተቀረጹት ቪዲዮ ላይ ከሰነዱ ወጪ በራሳቸው ሃሳብ የታቃኘ ገለጻ ሲያደርጉ ወይም ከሰነዱ ወጪ አንድም ሃሳብ ሲያብራሩ አልታዩም።
ከዚህ በተመሳሳይ ደግሞ ቀድሞ ብሎ ነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ ስልጠና ገብተው ለነበረው የድርጅት አባላት ሰልጣኞች በየመድረኩ አንስተውት በነበረው ጥያቄ ላይ የተመለሰውን በቪዲዮ የተቀረጸ የቪሲዲ መልስ በተመሳሳይ ሁኔታ ለአሁኖቹ ሰልጣኞች ሲከፍትላቸው እንደነበር ሰልጣኞች ገልጸዋል።
“የተሃድሶው መስመርና የኢትዮጵያ ህዳሴ” የሚለው ሰነድ በ2003 ዓ.ም የታተመ ሲሆን የተቀሩት ሁሉም ሰነዶች ግን ነሐሴ 2006 ዓ.ም የታተሙ ናቸው፡፡
በሰነዶቹ ላይ ኢህአዴግ ለሃገራችን ኢትዮጵያ ፍጹም ትክክለኛ ተመራጭ ፓርቲ፣ የህዝብ ሁለንተናዊ ጥያቄ መፍትሔ አምጪ ፤በኢትዮጵያ ከነበሩ ነገስታት ሁሉ በማንኛውም ሁኔታ የተለየ  መንግስት ተደርጎ ተወድሷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሰልጣኞች ሰነዶቹ የሃገሪቱን ብሎም የዓለምን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያላስገቡ፤ ኢትዮጵያ በታሪክ የነበሯትን የስልጣኔ በር የከፈቱና ለአፍሪካ ነፃነትን አስተምረው ያለፉ መንግስታትን ታሪክ በቁንጽል አቅርባችሁ፣እንዲሁም አዛብታችሁ የቀድሞ ስርዓቶችን በጅምላ አጣጥላችሁና ኮንናችሁ በተፃፃራሪው ደግሞ የራሳችሁን ብቻ ያሞካሻችሁበት ነው በማለት ሲሞግታቸው ሰንብተዋል፡፡
በተለይም ባለፉት 12 ዓመታት አገራችን በዓለም ፈጣን እድገት አላቸው ከሚባሉት አገሮች ቀዳሚነት ተጠቃሽ መሆኑዋ፣ በዚህም በ1994/95 ከ83 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ያላመረተችው አገራችን በአሁኑ ጊዜ 254 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ያመረተችበት ደረጃ ላይ እንድንደርስ አስችሏል ተብሎ ሲገለጽ እንዲሁም “በአለም ባንክ ጥናት መሰረት የኢትዮጵያዊያን የነፍስ ወከፍ አማካይ የህይወት ዘመን (life expectancy) ከ23 ዓመታት በፊት ከነበረበት 49 ዓመት ወደ 64 ዓመት ከፍ ብሏል ተብሎ ሲነገር ተሳታፊዎች አዳራሾችን በሳቅ ሞልተዋቸው እንደነበር ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
እስካሁን በሰልጣኝ የመንግስት ሰራተኞች ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል፣  የትምህርት ጥራት ችግርና የፕሬስ አፈና ይገኙበታል።
ኢህአዴግ ለውጥ አላመጣም በሚል ትችት ሲቀርብበት ራሱን ከነበሩት መንግስታት ማነፃጸሩ ተገቢ ነወይ?  በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የተሰገሰጉት 1ለ5፣ የልማት ቡድን፣ የለውጥ ቡድን፤ ህዋስ፣ ብሄራዊ ድርጅት ወ.ዘ.ተ የሚባሉት  አደረጃጀቶች ከብዛታቸው አንፃር ለሁሉም ጊዜ ሲመደብላቸው ለስራ ማነቆ አይሆኑሞይ? በአለም ገበያ ብዙ አለም አቀፍ ተወዳዳሪ የንግድ ድርጅቶች እያሉ መንግስት ለሚገነባቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች የግባአት አቅርቦት ለመከላከያ ኢንጅነሪንግ ያለጨረታ መስጠቱ ተገቢ ነወይ? ፓርቲዎቸን ኪራይ ሰብሳቢ፣የድሮ ስርዓት ናፋቂ፣የኋልዮሽ ጉዞ፣ብጥብጥ ናፋቂ ብሎ በማጣጣል የዳበረ ዴሞክራሲ ማምጣት ይቻላል? የልማታዊ ዴሞክራሲ አማራጪን ተግባራዊ የምናደርገው ለስንት አመት ነው? በተቃራኒው ደግሞ የኒዮሊበራሊዝም አስተሳሰብን ለአገራችን ጭራሽ አይጠቅምም ትላላችሁ? በቻይና ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች ሰብዓዊ መብታቸው ሲጣስ ይታያል፤ በአገራችን ሁለተኛ ዜጋ ልንሆን ነወይ? የክህሎትና የአመለካከት ለውጥ ተቀራራቢነት በሌለበት ሁኔታ ልማታዊ ሲቪል ሰርቪሱ እንዴት ሊሳካ ይችላል? የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል።
እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት ከድርጅት ወገንተኝነት ነፃ ነው ብሎ መናገር ይቻላል? ብዙህነትን የማስተናገድ ችግር ጎልቶ የወጣው በኢህአዴግ ወይስ በድሮ የአገራችን ገዥዎች ነው በግልጽ ብታብራሩት? በአዲስ አበባ የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥና አፈጻጸም መመሪያ መሰረት ቦታ ተረክበው ከ6 ወር በላይ የግንባታ እንቅስቃሴ ካልተደረገ አስፈላጊው ርምጃ እንደሚወሰድ ቢታወቅም የመንግስት የቅርብ ወዳጆች የሆኑት ግን ለረጅም ዓመት ሰፊ ሄክታር መሬት አጥረው ሲቀመጡ ጠያቂ የለም ይሄን እንዴት ታዩታላችሁ? ህገ መንግስቱ በተለያዩ አዋጆች የሚሸራረፍ ከሆነ የዜጎችን ህገ መንግስታዊ መብቶች እንዴት ማስጠበቅ ይቻላል? ይህን ስልጠና በዚህ ወቅት ለመንግስት ሰራተኛው ለምን መስጠት አስፈለገ? ዓላማውስ ምንድን ነው? በዴሞክራሲ ስርዓት ትግበራ ትችት ሲቀርብባችሁ ዴሞክራሲያችን ገና በጅምር ላይ ነው ትላላችሁ፤ መቼ ነው በተግባር ሲውል የሚታየው? በኢህአዴግ ውስጥ የተማሩ ሰዎች የሉበትም ብሎ ለመናገር ባያሰደፍርም በፖለቲካ ታማኝነታቸው ብቻ አቅም የሌላቸው ሰዎች አይሾሙም ወይ፤ ይህ ከሆነ ቀጣይነት ያለው ለውጥ እንዴት ሊመጣ ይችላል? ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነት አለ እየተባለ፤ፓርቲዎች ሰልፍ ሲያዘጋጁ በመርፌ ቀዳዳ የማለፍ ያክል ምክንያትና ሰበብ በመደርደር በግልጽ ታደናቅፋላችሁ ለምን የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል።
ሰልጣኞች ባለፉት ሶስት ቀናት ውስጥ ካነሱዋቸው ጥያቄዎች መካከል ደግሞ በድሮ መንግስታት የኢትዮጵያ የብር ምንዛሬ ከሌሎች አገራት ገንዘብ ጋር ሲነፃጸር ተቀራራቢ ነበር፣ የአሁንስ ምንዛሬ እንዴት ትገመግሙታላችሁ? በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ በሚገኙ ሠራተኞች የድርጅት አባል ባልሆኑት ላይ በደረጃ እድገትና በሌሎች ጥቅማጥቅሞች ላይ ግልጽ አድሎ ታደርጋላችሁ፤ አሁን አሁን ደግሞ እየባሰ መጥቷል እንዴት ታዩታላችሁ? የአጼ ሚኒሊክ ወታደር ነፍጠኛ ከተባለ የኢህአዴግ ወታደርስ ምን ይባላል? ጋዜጠኛችና ጦማሪዎችን በዘመቻ ታስራላችሁ፤ራሳችሁ ቪዛና ፓስፖርት አዘጋጅታችሁ ከአገር እንዲሰደዱ ምቹ ሁኔታ እየፈጠራችሁ አይደለሞይ? በአሸባሪነት ሰበብ ህዝብ ከአደጋ ለማዳን ነው ይሄን ያደረግነው እያላችሁ ከፍ/ቤት የመያዣና የብርበራ ትዕዛዝ ሳይወጣ ዜጎችን በድንገት ታፍናላችሁ፤ ይሄ ድርጊት ህገ መንግስቱን መጣስ አይሆንሞይ? በኢህአዴግ የመተካካት መርህን ተግባራዊ እያደረገ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል ወይ? የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በአውራ ፓርቲ ሲመራ አምባገነንነትን አያመጣም ወይ? የኢትዮጵያና የኤርትራ ወቅታዊ ግንኙነት ሰላምም ጦርነትም የለም ሆኖ እስከመቼ ይቀጥላል? በህግ መንግስቱ ችግሮች ላይ ሃገራዊ መግባባት ያልተቻለው ለምንድን ነው? የትምህርት ጥራት የሚመጣው በሂደት ነው እየተባለ ነው ታዲያ ለየትኛው ትውልድ ይደርሳል? አንድ ሰው በቁጥጥር ስር ውሎ ከታሰረ በኋላ በ48 ሰዓት ፍ/ቤት መቅረብ እንዳለበት ህጉ ያስቀምጣል፤ ነገር ግን ተግባራዊ ሲደረግ አይታይም፤ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህጉ ሲከበር አይታይም፣ ጠባብነትና ብሔርተኝነት ከእናንተ ወጪ በማን ይገለጻል? የአገራችንን ፖሊስና ስትራቴጅ የፃፈው መለስ ነው ብላችሁ ነበር መለስ ከሞተ ወዲህ አዲስ አስተሳሰብ ማውጣት አልቻላችሁም ወይ? መንግስት በየአቅጣጫው የአፈጻጸም ችግር አሉብን ይላል ነገር ግን ችግሮች ከታወቁ መፍትሔ ሲወሰድና ለውጥ ሲመጣ አይታይም፤ በየዓመቱ የሚታዩ ያልተፈቱ ችግሮች ማለቂያቸው መቼ ነው? የሚሉት ይጠቀሳሉ።
በአንደኛው ስልጠና ላይ ያወያዩት አቶ ይስሃቅ ግርማይ በሲቪል ስርአቱ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ የትምክት ሃይሎች አሁንም በህዝብና በመንግስት መካከል ልዩነት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል። ይህ ሃይል ለማጥፋት እንዳልተቻለም ገልጸዋል
መንግስት ስልጠናው ያስፈልገበት ምክንያት ከዜጎች ጋር አገራዊ መግባባት ለመፍጠርና ህዝቡ ስለሚካሄደው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዲያውቅ ነው ይላል። ሌሎች ወገኖች በበኩላቸው ስልጠናውን የምርጫ ቅስቀሳ አንዱ አካል አድርገው ይመለከቱታል።                    sourse  esat radio

No comments: