Thursday, May 15, 2014

አዲስ አበባ ውስጥ ከእንግዲህ መኖሪያ ቤቶችን በሕግና እኲልነት ለማስተላለፍ የሚያስችል ‘ምች’ በምርጫ ዋዜማ መቶኛል ይላል ዋሾው ሕወሃት! በከፍያለው ገብረመድኅን

እንደተለመደው ዘወትር በየቀኑ እንደማደርገው ሁሉ – ማክሰኞ ምሽት አካባቢ (ግንቦት 5፣ 2006) የኢትዮጵያን ጠረንና ሙቀት በመሻት፡ የሃገር ቤት ወቅታዊ ዜናዎች ገጾችን ሳፈላልግ/ሳገላብጥ – በቤት ማስተላለፍ ሂደት የሚታየውን የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር ለማስወገድ እርምጃ እየተወሰደ ነው የሚለው በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የተጻፈው አርዕስት ላይ ዐይኔ በድንገት አረፈ።
አገራችን ምርጫ ዋዜማ ላይ ስለሆነች፡ በየመሥሪያ ቤቱ ባለሥልጣኖች ያልሆነውን ሆነ፡ አገሪቱ ያለችበት ተጨባጭ የፖለቲካና ኤኮኖሚ ሁኔታ እንደሌለና እንዳልነበር ተደርጎ፡ በዕድገትዋ ወደ ህዋዕ መተኮሷ የሚፈበረኩበት ወቅት በመሆኑ፡ ተናዳፊ እባብ ያየሁ ይመስል፡ ከኔ ትዕዛዝ ውጭ ሰውነቴ ክስክስ ብሎ፡ ዜናውን ማንበብ ጀመርኩ።
አርዕስቱ እንደሚያመለክተው፤ ዜናው ስለመከረኛውና እየተባባስ በመሄድ ላይ ስላለው፡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎቿ ቁጥር በዓመት በ96,000 – ወይንም በዓመት 3.3 በመቶ – የሚያድገው ሕዝብ ብዛትና በነበረውና ባለፈው የከተማዋ ዝቅተኛ የአገልግሎቶች ሁኔታ (የውሃ፡ የመብራት፡ የመንገዶች፡ የትምህርት ቤቶች፡ ሕክምና አገልግሎቶች፡ የመጸዳጃ ሥፍራዎች ወዘተ…) የመኖሪያ የቤቶች ዕጥረትን ተንተርሶ ጉበኝነትና ሙስና እየተባባሱ መምጣታቸውን ነው።
የቤት ዕጥረት ወሬ ከተነሳ ዘንዳ፡ ሁሉም ፍሬዎች መራራ አለመሆናቸው፡ ወይንም አንዱ ነጻ አውጭዬ ብሎ የሚደግፈው ለሌው ጠላት መሆኑ፡ ኢትዮጵያ ውስጥም በአባባል ደረጃ ሲነገር ይሰማል። የአዲስ አበባ መሬት ይዞታ ሁኔታና የከተማዋ የቤቶች ዕጥረት ያስከተሉት ችግሮችም እንዲሁ። አንዳንዶቹን እስከዛሬ መናና በባዶ ተስፋ የማስቀረቱን ያህል፡ የሕወሃትን ሰዎች (ሲቪልና ወታደራዊ) እና አጋፋሪዎቻቸውን – ማለትም አዳዲሶቹ ባለጸጋዎች (nouveau riche) አድርጓቸዋል – የ’ባለሰማይ ጠቀስ’ ፎቆችና ቪላዎች ባለቤቶች።
እንደትክክለኛው ሥነ ምግባር ከሆነ፡ ተምሮ፡ ሠርቶ፡ ለፍቶ ጥሮ ግሮ የከበረ ይከበራል! የኛማ ወንበዴዎች ከግድያ በስተቀር በቂ ትምህርትም ስለሌላቸው፡ ትዝብቱ ምን ያህል እንደሆነ፡ ለተባበሩት መንግሥታት ወታደራዊ አገልግሎት የተጠሩት የሕወሃት ጄኔራሎቻች እንግሊዝኝ/ፈረንሣይኛ ወይንም ምንም ዐይነት የውጭ ቋንቋ አለመቻላቸው፡ ለድርጅቱ የውርደትና የወጭ ምንጭ መሆናቸው ሊታሰብ ይገባል! ሰለሆነም፡ በሥርቆትና በቁማር የከበረውን ግለስብ ኅብረተስብ አያከብረውም። ዘመናዊ የሶሲኦሎጂ ጥናቶችም፡ የነዚህ ዐየነት ባላሃብቶችን የጎሪጥ በመመልከት Deviant behavior category ውስጥ ያስልፏቸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ፡ ሌሎች ዜጎች በትውልድ ወይንም በውርስ ያገኟቸውንም ሆነ ሌት ተቀን ለፍተው ያፈሯቸውን መሬቶችና ንብረቶች እነዚሁ የሕወሃት ባለሥልጣኖችና ትክሎቻቸው መንግሥታዊ ሥልጣን፡ ክፋትንና ብልግናን ተገን በማድረግ፡ በዝርያዎቻቸው ስም ሳይቀር ዋና ዋና የክተማ መሬቶችን – ተገቢውን ካሣ እንኳ ሳይከፍሉ – ማግበስበሳቸውን ማስታወሱ፡ ከዚህ በታች ስላለው ስላስገረመኝና ስለምተርክለት የዛሬው የኢዜአና የፋና የጋርዮሽ ዜና አስገራሚ ይዘት ጥሩ መንደርደሪያ ይሆናል ብዬ አምናለሁ።
አገራችን በሕወሃት ምርጫ ዋዜማ
በመነሻነት፡ የአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ አሊማ ባድገባ የኤጀንሲውን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃፀም አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለማይገባቸው ግለሰቦች በሕገ-ወጥ መንገድ በሚያስተላልፉ ሠራተኞች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው በማለት እርግጠኛ ሆነው የሰጡትን ምስክርነት ኢዜአ ይጠቁማል።
ባለሥልጣኗ እንደሌሎቹ አቻዎቻችው ሁሉ፡ አድርጉ ተብሎ በሙሉ ለፓርቲና መንግሥት ተወካዮች ‘ከበላይ አካል’ የተሠጠውን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ መሞከራቸው ቢሆንም፡ የሚሉትን ነገር ግን ጠለቅ አድርገው እንዳላስቡበት ለአንባቢ ግልጽ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ “የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች በማስተላለፍ ረገድ የሚስተዋሉ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባርን ለማስወገድ” የተወሰደ ሆኖ፡ ዋና መነሻው ይህ አገር አጥፊ “አመልካከትና ተግባር” ነባር መሆኑን ጭምር ወይዘሮ አሊማ ይጠቁማሉ!
ታዲያ በቅርብም ሆነ በሩቅ ሆኖ ስለሃገር ጉዳይ የሚከታተል ሰው አዕምሮ ውስጥ ከሚከሰቱት የመጀመሪያዎቹ ጥያቄዎች መካከል – ለምን እስከዛሬ ድረስ እርምጃ ሳይወሰድ ተከርሞ አሁን ምን ትልቅ ወይንም ጎጂ ወንጅል ተፈጸመ እርምጃ እንዲወሰድ የሚያስገድድ? ይህንን ብልሹ አሠራር ለማሰወገድ ለሕወሃትሰ መነቃቃት የሰጠው ምክንያት ምንድነው? ይህ ቁርጠኝነት ግንባሩንና አጋፋሪዎቹን ሕጋዊ የመሆን ‘ምች’ መቷቸው ሊሆን ይችላል ብለን ልናስብ እንችላለን።
ከዚያም አልፈው ለተአማኒነት ያህል፡፡ ኃላፊዋ ጥናት ተደርጎ “እርምጃ እየተወስደ” መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
ጥያቄው፡ እርምጃ ተወስደ ካሉ – ስንት ኃላፊዎች ክያዙት ኃላፊነት ተነሱ/በሕግስ ተቀጡ? ቅጣቱስ ምንድነው? ተቀባዮቹ በወንጀል ተባባሪ ስለሆኑ: ከእነርሱስ ምን ያህሉ የዚህ ብልሹ አሠራር ራሳቸውን ሰለባ አደረጉ? ስንቶቹ ያላግባብ ያገኟቸውን ቤቶች ተነጠቁ? ዜናው ላይ መመልከት እንደሚቻለው፡ መልሱ ዜሮ ነው! እንዲያውም፡ ወንጀሉንና እነርሱ እንቅፋት የሚሉት ችግር ለመፍታት የሄዱበታ አቅጣጫ በገሃድ ከሚካሄደው የሕወሃት ዘረፋ በተቃራኒው መንገድ ነው።
ለነገሩ እኔም ለእነዚህ ጥያቄዎች ወይዘሮ አሊማ ትክለለኛ መልስ ይኖራቸውል የሚል እምነት አልነበረኝም።
ይህንንም የምልበት ምክንያት፡ በጉቦ፡ ዘርና የሕወሃትና የአንዳንድ ጋሻ ጃግሬዎቻቸው መንደርተኝነትና በኔፖቲዝም በበሰበሰ ሥርዓት ውስጥ: ለቅጣት የሚዳረጉት አጥፊዎቹ ሳይሆኑ፡ በአርከበ እቁባይ ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ እንደታየው: ትዕዛዝ ተቀባዮቹና ፈጻሚዎቹ ላይ ነው።
አቶ ዮሃንስ ታደስ አካ፡ በመሬት ጉዳይ በአዲስ አበባ አስተዳደር በሃላፊነት ላይ የሠሩ የቀድሞ ባለሥልጣን፡ ይህንን የሕወሃት ራሱ ተጠቃሚ ሆኖ ስህተቶችና ለፈጸማቸው ወንጀሎች፡ ሌሎቹን የማሰርና የማሰቃየት ተግባር፡ ከእሥረኞች ያገኙትን በማስታወስ: አንድ እስረኛ የነገራቸውን እንደሚከተለው አስፍረውታል፡ “ያዘዘን አርከበ እቁባይ፣ መሬቱን የወሰዱት ዘመዶቹ እና ሴቶቹ፤ አኛን ምን ፍጠሩ ነው የሚሉን?”
ከላይ ወይዘሮ አሊማ ባድገባ ሲጀምሩ እርምጃ ተወስዷል የሚሉት – ኢዜአ እንደዘገበው – በየክፍለ ከተማው በስም መመሳሰልና በሕገ-ወጥ መንገድ በተዘጋጁ የመታወቂያ ደብተሮች በሚያዋውሉ አስፈፃሚዎች ላይ መሆኑን አመልክተዋል። ለዚህም በምሳሌነት የጠቀሱት፡ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ በየካ፣ በአዲስ ከተማና በጉለሌ ክፍለ ከተሞች በሕገ-ወጥ መታወቂያ ውል ለማዋዋል ሲሞክሩ የተገኙ ፈፃሚ አካላት ላይ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ነው ብለዋል።
እርምጃው ምን እንደሆነ እንኳ ጥቆም አይሰጡም።
ዋና ዋና የመሬት ዘራፊዎችና ቸርቻሪ የሆኑት የሕወሃት ባለሥልጣኖች (ሲቪልና ወታደራዊ) ቢሆኑም፡ እነርሱ የነኩት ወንጀል ግን በተአምር ወደሕጋዊነት ተለውጦ እነርሱ በአንድ በኩል ወደ መዝናናቱ: በሌላ በኩል ደግሞ የያዙትን መልካም ሕይወት እንዳያጡ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ የሚያካሄዱትን አፈና፡ ግድያና የስብአዊ መብቶች ጥሰቶች ጥልቀት ወደ መሰጥት ተሸጋግረዋል!
መለስ ዜናዊ እስከ መጨረሻው እስከተሰናበተ ድረስ፡ የመሬት ቅርምት አደገኛነትን አስመልክቶ ሲሰጥ የነበረውን የይስሙላ ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ ላስታወሰ ማናኝውም ኢትዮጵያዊ፡ አሁንም የሕወሃት የፖለቲካ ጨዋታ ያተኮረው ሕዝቡን ክግንቦት 2007 ምርጫ በፊት ሆን ተብሎ ለማደናገር ክዚያው ከመለስ ገጽ የተወስደ ስትራቴጂ ነው።
የቀድሞ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ደኤታ አቶ ኤርምያስ ለገሠ ለኢሳት ስሞኑን የሰጡትን ቃለ መጠይቅ ልብ ብሎ ላዳመጠና ላስተዋለ ሰው፡ መለስ ዜናዊ እራሱ መሬት እየዘረፈና እያዘረፈ፡ ማን መክሰርና፡ ማን መክበር፡ መርዘምና ማጠር እንዳለበት ሁኔታዎችን ሲያመቻች፡ “የኛ የመንግሥት ሌቦችና፡ በየቦታው ከተማ ውስጥ የተሰገስጉት ሌቦች” በሃገራችን ዕድገትና ልማት ላይ አደጋ ሊያደርሱ ነው እያለ ነበር። ፓርላማ ውስጥ ቁጭ ብሎ አንዳንዴ እንደማግሳት እያለው: በአገራችንና ሕዝባችን ላይ ሲያሾፍ – የዘረፋው አቀነባባሪ እራሱ እንደነበር ቀድም ብሎ ግንዛቤው ቢኖረንም – በየቀኑ በመረጃ መደገፉ ምን ያህል ልብን እንደሚያደብን ያሰበበትና ያጤነው ሁሉ ይገነዘበዋል።
ይህም በመሆኑ፣ ስሞኑን ትዊተር ላይ ያየሁት (አድራሻውን የረሳሁት) መልዕክት በዛሬይቷ ኢትዮጵያ ውስጥ፡ ትልቁን ቤት በእግዚአብሔርና ሌሎቹን ቤቶች በሙሉ ወደ ገብረእግዚአብሔር የሚያደላድለው ፖለቲካዊ ጠረባ ከእውነትና ክተጨባጭ ሁኔታው የራቀ አይደለም! የአሁኑም የመኖሪያን ቤቶችን በሕግ ሥነ ሥርዐት የማስተላለፋ ቅብጠራ፡ የዚያ የመለስ ዜናዊ ትያትር ተከታይ አካል ነው። የሕወሃት ሰዎች አባሎቻቸውን፡ ዝርያዎቻቸውን በግንባር ቀደምትነት፡ ቀጥሎም አሽቃባጮቻቸውን በኢትዮጵያ ዘላለማዊ በትረ መንግሥትና ሥልጣን ለማቆናጠጥ የታለመ ደባ ነው።
ስለሆነም፡ የአቶ ኤርምያስንና ቀደም ሲል ደግሞ አቶ ዮሃንስ ታደሰ አካ – የቀድሞው መሬት አስተዳደር ባለስልጣንና የተስፋው ነጸብራቅ – (2013) ደራሲን ጨምሮ – በቅርብ ያዩዋቸውንና ያወቁዋቸውን በጽሁፍም በቃለ መጠይቆችም ለሕዝብ ይፋ ማድረጋቸው፡ ሃገራችን ከየት ወዴት ለሚለው ጥያቄ ተገቢውን መልስ በበቂነት የሚያስጨብጡ በመሆናቸው፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሠፊው እንዲሰራጩ ማድረጉ እጅግ ጠቃሚ ነው።
ለምሳሌ፡ አቶ ዮሃንስ ታደሰ አካ በተስፋው ነጸብራቅ ውስጥ፡ የችግሩን ምንነት ሲተርኩ እንዲህ ይላሉ-
“እርግጥም ‘የህዝብና የመንግስት’ የተባለው መሬት ተወሯል። የቀበሌ ቤቶች እና የኪቤአድ [ኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት] ቤቶች ተወርሰዋል። ከመወረሳቸው ባሻገር የቀበሌ እና የኪቤአድ” በእርግጥም ‘የህዝብና የመንግስት’ የተባለው መሬት ተወሯል። ከመወረሳቸው ባሻገር የቀበሌ እና የኪቤአድ የነበሩ የህዝብ ቤቶች ያለአንዳች መሰረት ወደ ምርጦቹ የግል ባለቤትነት ተቀይረው የባለቤትነት ስም ዞሮ ከባንክ ብዙ ሚሊዮኖች እንዲበደሩ ተደርገዋል! ባዶ መሬት ዋስትና ‘collateral’ ተይዞ ከሁለት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ያገኙ ምርጦች ብዙ ናቸው።”
የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን በተጠናወተው የታዛዥነት ስሜት ነገ የከፋ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ተገንዝቦ፡ ዛሬ ነው አንድነቱን አጥናክሮ እነዚህን የሃገር ጠላቶች መዋጋትና ለፍርድ ማቅረብ ያለበት!
የሕወሃት ሰዎች ዓላማ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን በማዋረድ ራሳቸውን ለመካብ ነው
የሕወሃት ሰዎች ዓላማ አዲስ አበባን ዘላለማዊ “ከተማቸው” (ኢትዮጵያን’የቅኝ ግዛታቸው ማዕከል’) ማድረግ ነው፡፡ የአዲስ አበባን ዙሪያ መሬት የአካባቢውን የኦሮሞ ገበሬዎችን በማሰወገድ – ካሳ እንኳ ሳይከፍሉ – ነው መቀራመት የጀመሩት። ሕወሃቶች ቅኝ ግዛታቸውን ለማስፋፋት ለዓመታት ያደረጓቸው ጥረቶች አሁን መደምደሚያ ላይ በመድረሳቸው፡ ቁጥራቸው ብዙ የሆነ – አምቦ፡ ወለጋ፡ ባሌና ሃሮማያ ላይ የወደቁት – የመብትና ሰብዓዊ ክብር ተፋላሚ ኦሮሞ ኢትዮጵያውያን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሕወሃት የተጨፈጨፉት የግንባሩ ዓላማ ወደስኬት እየተቃረበ መምጣቱን በመገንዘቡ ነው።
እነዚህ በሕወሃት ጭካኔ የረገፉት ኦሮሞ ኢትዮጵያውያን የመጀመሪያዎቹ ያለመሆናቸውን ያህል፡ የመጨረሻዎችም አይሆኑም። የሕወሃት ዓላማ ኦሮሞችንና አማሮችን ረግጦ መያዝ፡ ለኢትዮጵያ ይዞት የመጣው የክፋት አጀንዳ አካል ነው። ይህ ማለት ጥፋቱ በእነዚህ የሃገራችን ትላልቅ ብሄረስቦች ተወስኖ ይቀራል አለመሆኑን፡ ጋንቤላ፡ አፋር፡ ኦጋዴን፡ ወዘተ ውስጥ የተፈጸሙት የጥፋት ዘመቻዎች ማስረጃዎች ናቸው።
ወደኋላ መልስ ብለን ለማስታወስ ያህል፡ ዶር ባርናባስ ገብረአብ በግጭቱ ጊዜ ጋንቤላ ውስጥ የፌዴራል ሚኒስቲር ዋና ተወካይ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ 1,200 የጋምቤላ ተወካዮችን ካስገደሉ በኋላ The McGill Report ለተሰኘ የካናዳ ጋዜጣ ሲናገሩ፡
“If I died tomorrow, I would die with a clear conscience … I have made mistakes. I am not a perfect man. But I know that I have always done my best in life.”
ይህን ያህል የሰው ሕይወት አጥፍተው “ንጹህ ነኝ” የሚል ግለስብ የግድ የሕወሃት አባል መሆን አለበት! ነገሩ ያስገረመው ጋዜጠኛ Doug McGill እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥታችሁ ይህን ሁሉ ሕዝብ በአንድ ጊዜ ሲፈጅ ምን ለማግኘት ነው ብዬ ደጋግሜ ጠይቄአለሁ ይላል። መልሱን ራሱ ሲመልስ እንዲህ ይላል፦
“There are several possible answers. One is that Gambella state, the Anuak’s ancestral homeland, is geographically remote but is agriculturally fertile and contains gold and oil reserves. This makes it attractive for economic development and population resettlement programs by the central government.”
የዶ/ር ባርናባስ ወንጀል ጥንስስ በትክክል ከላይ የተገለጸው ነው። በዚህ ብቻ አያከትምም። እርሳቸው በራሳቸው አንደበት ሐምሌ 1 2004 ዓ.ም. ለአሜሪካ የሕዝብ ራዲዮ (NPR) የሚክተለውን ነበር የተናዘዙት፡
“Gambela is potentially very rich; it is probably the richest place in Ethiopia. If it uses those rivers and the fertile soil, Gambela can be a miracle economically tomorrow. It is a question of investing and the whole Gambela will become the breadbasket for the country.”
ወዲያውኑ ሕወሃት ጋምቤላ ውስጥ ወደ መሬት ነጠቃ አምርቶ፡ የመሬቱ ባለሃብቶች መና ሲቀሩ፡ የውጭ ባለሃብቶችና የሕወሃት አባሎች ከነባለሟሎቻቸው ኢንቬስተሮች ሆነው ቁጭ አሉ። በዚያ የግድያ ማግሥት የማሌዥያ ዘይትና ነዳጅ ቆፋሪ ድርጅት ምቹ ኮንትራት ተሰጥቶት ጋንቤላ ውስጥ ቁፋሮውን ጀመረ!
ይህም የሚያሳየን፡ ሕወሃት በአቋራጭ ለመክበር፡ የሃገሪቱን ሃብት እያሳደደ፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋምቤላ ላይ፡ በኦሮሚያ ብዙ አካባቢዎች፡ አፋር፡ አማራ ውስጥ፡ ሲዳሞ፡ ወዘተ … የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ተዛማጅነታቸውን በመገንዘብ፡ ‘በሕግ ደረጃ’ እነዚህ ሃገረ ቢስ ወንበዴዎች – የኢትዮጵያ ሲሰል ሮድሶች (Cecil Rhodes – founder of white minority regime in Rhodesia) እና ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የባርነት ሥርዓት ዘመናዊ ቅርጽ የሰጠውን ሄንድሪክ ቬርዎርድ (Architect of Apartheid Hendirk Verword – በኢትዮጵያ የመለስ ዜናዊ አቻ) እንዳደረጉት ሁሉ – በሕዝባችን ላይ የሁለተኛና ሶስተኛ ዜግነት ውርደት ለመጫን መዘጋጀታቸውን ነው።
ሲስል ሮድስም አፍሪካ መጥቶ ያለው የሚከተለውን ነበር – ልክ እንደ ሕወሃት ሁሉ የተናገረውና የተመኘው።
“We must find new lands from which we can easily obtain raw materials and at the same time exploit the cheap slave labor that is available from the natives of the colonies. The colonies would also provide a dumping ground for the surplus goods produced in our factories.
ከኛዎቹ ጠባብ ወንበዴዎች ጋር ሲነጻጸር እርሱ እንኳ ሃገር ነው ያሰበው!
በተባበሩት መንግሥታትም በኩል በመሬት መቀራመት ዙሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸሙ ያሉት ወንጀሎች ልዩ ልዩ አሻራቸው እየተመዘገበና ቅርጻቸው ለዓለም እነደሚክተለው ፍንጭ እየሰጠ በመሆኑ፡ THE STATE OF AFRICAN CITIES 2014: Re-imagining sustainable urban transit: መንግሥት ለሕዝቡ ተገቢውን አገልግሎት ከማቅረብ ይልቅ፡ ማን ትልቋን ዘመናዊ ሜትሮፖሊስ በማስተዳደር ላይ እንዳተኮረ ለመዋዕለ ንዋይ ፍሰት በአፍሪካ ያለውን ፉክክር እንደ ምክንያትነት እንደሚከተለው ይጠቅሳል፦
“The mega-urban region of Gauteng with its aggregate population of well over 12 million is, therefore, a de facto megacity. Likewise, the EMRs [Extended Metropolitan regions] of Addis Ababa, Alexandria, Dar es Salaam, Kenitra-El Jadid and Tangier, as well as the transboundary urban system of Kinshasa-Brazzaville, could soon qualify as de facto “megacities” if a wider concept than that dictated by somewhat artificial administrative municipal boundaries is taken into account.”
ድህነት የተንሰራፋባት አዲስ አበባ፡ የነዋሪዎቿ የተራቆተ ሕልውና በዘመናዊ ኤኮኖሚክስ ዕይታ ከአጠቃላይ የሃገሪቱ ሕዝብ የገቢ ሁኔታ (City gini coefficient) እና (Country gini coefficient) አዲስ አበባ ጋር ሲወዳደር አስፈሪ ድህነት እንዳዣበባት የተባበሩት መንግሥታትም ጥናት በተደጋጋሚ አመልክቷል።
ለምሳሌ የካቲት 2014 ይፋ የተደረገው ይህ ከላይ የተጠቀሰው የከተሞች ጥናት ሲዘጋጅ፡ አጥኝዎቹን ያስገረማቸው ነገር ቢኖር፡ በመሬት ቅርምቱና ባለፉት 23 ዓመታት በስፈነው በዘር ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ምክንያት፡ አዲስ አበባ ከድሮዋ በተለየ አደገኛ ደረጃ በመቀያየር ላይ መሆኗ ነው። ይህንኑ አስመልክትቶ፡ ጥናቱ ስለአዲስ አበባ የሚከተለውን አስፍሯል፦
“Even in cities that were once praised for diversity and pluralism, such as Addis Ababa, the emergence of gated communities and sprawl threatens to eradicate any memory of tolerant coexistence.”
ማሳረጊያ
የሃገራችንና የዋና ከተማችን ዕጣ ፈንታ የሚወሰንበት አቃጣጫ የተቀየሰው በፋሽስታዊው ፀረ-ኢትዮጵያዊ መለስ ዜናዊና በሕወሃት ሲሆን፡ በአሽቃባጭነትም የተሠለፉት ከሃዲዎች በሃገራቸው ላይ ክህደትና እየፈጸሙ ያሉት ደባ: ከፋሽት ኢጣልያ ጋር ካበሩት ባንዳዎች ጋር ያለው ተመሳሳይነት አሳዛኝም አሳፋሪም ከመሆኑ የተነሳ ከእንግዲህ ሌላ ጥቃት እንዳይደገም፡ ኢትዮጵያውያን ተቀነባበና የተባበረ – ይህ የኦሮሞ ጉዳይ ነው፡ የለም የአማራ ነው ሳንል – በኢትዮጵያዊ አንድነት ስሜት ልንታገለው ይገባል!!
እስከዛሬ እንደታየው የኢትዮጵያውያን እንደባቤል መንደብ መከፋፈል፡ ውጤቱ አገራችንንና ወገኖቻችንን ለጥቃት ማጋለጥ፡ በግለስብም ሕሊና በሌላቸው ስግብግብ ወንበዴዎች መዋረድ ብቻ ነው! ይህም የኢትዮጵያ ሕዝብ አክ እንትፍ ብሎ ለተፋቸው ወንበዴዎች ዕድሜ መራዘም ረድቷል!
የሕወሃት ሰዎች ከኢትዮጵይዊነት ይልቅ፡ በጠባብነት፡ በግድያና በዘረፋ ሥልጣናቸውን ዘላለማዊ ለማድረግ ቀና ደፋ ሲሉ ይታያሉ፡፡ በዚህ በሁለት አሥርታት ውስጥ የታየው እነርሱ የፈለጉት ለውጥ ውጤት በሃገር፡ በሕዝቦች መፈቃቀድ፡ መተሳሰርና አንድነት፡ ታሪክና ባህል ላይ ክፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑ ነው።
ስለሆነም፡ የከፋ ሁኔታ አገራችን ላይ ከመድረሱ በፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን በተለመደው ይቅር ባይነንትና ዘብጥ የሌለው ትዕግሥት የሚያልፈውና የሚያሳልፈው ሳይሆን፡ እምቢ ለሃገሬ! እምቢ ለነጻነቴ! የሚባልበት በአንድነት የትብብር ክንዱን የሚያነሳበት ወቅቱ አሁን ነው!
ተዛማጅ ጽሁፎች:
Urban land lease legislation: the prime minister’s new front against urban dwellers
በአዲስ አበባ ዙሪያ ገበሬዎች የሚፈናቀሉት ያለ በቂ ዝግጅት ነው ተባለ

No comments: