Monday, May 26, 2014

የኢህአዴግ የዝምታ ፍራቻ (Sedate-phobia) እና ስርወ-ምክንያቱ

May 26, 2014
ዳጉ ኢትዮጵያ (Dagu4ethiopia@gmail.com)
እመኑኝ ወዳጆቼ፣ ኢህአዴግ የዝምታ ፍራቻ በሽታ (በሙያዊ አጠራሩ ሴዳትፎቢያ – Sedate-phobia) ይዞታል! ዝምታ ሲሰፍን፣ ፀጥታ ሲረብ፣ እርጋታ ሲነግስ ይጨንቀዋል፡፡ ለዚህ ነው ያለማቋረጥ፣ ያለአንዳች ዕረፍት ግርግር የሚፈጥረው፡፡ ይህ የሥርዓቱ በሽታ ሥር የሰደደ ቢሆንም የለየለት ደግሞ ከምርጫ 1997 ማግስት ጀምሮ ነው፡፡ ስለዚህም አንዱን የቴሌቪዥን ጣቢያ በ14 ቻናል ከፍሎ 14 ስም እየሰጠ ያንኑ ጩኸት የሚጮኸው፡፡ ስሙን ኢቴቪ፣ አማራ ቲቪ፣ ትግራይ ቲቪ፣ ኦሮሚያ ቲቪ፣ ፋና፣ ዛሚ ወዘተ ብሎ ቢለያየውም ጩኸቱ ግን አንድ ነው፡፡ ዜማው፣ ቅኝቱ፣ ቀለሙ ልዩነት የለውም፡፡ ዋናው ፀጥታውን መስበሩ፣ እርጋታውን መግሰሱ ነው፡፡ሳስበው ሳስበው ኢህአዴግ ታሟል!
ለጩኸቱ ብዙ ብዙ ሰበብ ይፈልግለታል፡፡ ሚሊየነም፣ ህዳሴ፣ የብሔር ብሔረሰብ ቀን፣ የአባይ ግድብ፣ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት… ሌላም ሌላም፡፡ ዋናው ፀጥታው ይሰበር… ዝምታው በኳኳታ ይሸፈን… የቀረው ዕዳው ገብስ ነው፡፡
ይህ የዝምታ ፍራቻው ገፍቶ ገፍቶ ከመሠረታዊ ዕምነቶቹ ሳይቀር አቃቅሮታል፡፡ ባንዲራን “ጨርቅ ነው” ብሎ ያጣጣለ ፓርቲ የባንዲራ ቀንን ለምን ሊያከብር የተነሳ ይመስልሃል? ድንገት የባንዲራ ክብር ተገልጦለት? አይደለም ወዳጄ፡፡ ዝምታውን እስከ ገፈፈለት ድረስ ርዕሠ-ጉዳዩ ለኢሕአዴግ ሁለተኛ ነው፡፡ ዋናው ጩኸት ይፍጠርለት፣ አታሞ ያስደልቅለት፣ ቸበር ቻቻ ያንግስለት፣ ኳኳታ፣ ግርግሩን ያድምቅለት፡፡
መሪዎቹ ይሰበሰባሉ፡፡ አጀንዳ – “ቀጣዩ ጩኸት በምን ሠበብ ይሁን?” የብሔር ብሔረሠብ በዓል ግርግሩ ሳይበርድ የአባይ ግድቡ ይለጥቃል፡፡ የኢኮኖሚ እድገቱ ዳንኪራ ጋብ ሳይል የግንቦት ሃያው አስረሽ ምቺው ይጀመራል፡፡ ዕድሜ ግንቦት 20 ለተቆጣጠራቸው የፕሮፖጋንዳ አውታሮች፡፡ ዕድሜ የተሰጣቸውን ርዕስ ሳያላምጡ ውጠው አስረሽ ምቺውን ለሚያስተናብሩ ካድሬዎቹ፡፡ ዕድሜ የአበሉንና የኮሚሽኑን አወፋፈር እንጂ ይዘቱን መረዳት ለማይችሉ “ልማታዊ አርቲስቶች”፡፡ ሙዚቃው ይሞዘቃል፣ መነባንቡ ይነበነባል፣ ግጥሙ ይተረተራል…ጩኸት፣ ግርግር፣ ሁካታ ይሆናል፡፡ ያኔ ኢህአዲግም ለጸጥታ ፍራቻ በሽታው ማስታገሻ አገኘ ማለት ነው፡፡ በጩኸቱ ውስጥ ሆኖ ጩኸቱን ስለማስቀጠል መጨነቁ እንዳለ ሆኖ (ልክ እንደ ሌጋሲው)፡፡
አመክኒዮው ግልጽ ነው- ዕሳት በሌለበት ጭስ አይኖርም፡፡ ስለዚህ – “መቼም ይህ ሁሉ ጩኸት አንዳች ነገር ቢኖር ነው” የሚል ስዕል መፍጠር፡፡ “መቼም ይህ ሁሉ ዳንኪራ በባዶ ሜዳ አይሆን? – እኔ ያልታየኝ አንድ የሚያስጮህ፣ የሚያስፈነጥዝ ነገር ቢኖር ይሆናል እንጂ?” የሚል ጥርጣሬን በዜጎች አዕምሮ ማኖር፡፡ “ሌላው እየጮኸ እኔ ዝም ብል ምን ይባላል? ቀበሌ ስኳር ብከለከልስ? ግብር ቢጨምሩብኝስ? ከቀበሌ ቤቴ ቢያፈናቅሉኝስ?” ወዘተ የሚል ስጋት በዜጎች ልብ አኑሮ ጩኸቱን እንዲቀላቀሉ በዕጅ አዙር ማስገደድ፡፡ “አበል እስከተከፈለኝ፣ ብድር እስከተሰጠኝ… አብሬ ብጮህ ምን አገባኝ” ማሰኘት፡፡
ለዚህ ነው ጩኸቱ ዜማ የሚጎድለው፡፡ ሺዎች ተሰብስበው አዳራሹ ግን ባዶ የሚሆነው፡፡ ዜናው እየተተረተረ መረጃው ዜሮ የሚሆነው፡፡ ፕሮፖጋንዳው እየዘነበ ቅቡልነት ኢምንት የሚሆነው፡፡ ለዚህ ነው በየወንዙ መማማል… በየስብሰባው መገዘት ልማድ የሆነው፡፡ ግጥሙ ባዶ የቃላት ኳኳታ የሚሆንብህ፣ ዘፈኑ ባዶ ቀረርቶ የሚሆንብህ፡፡ ከስብሰባው፣ ኮንፍረንሱ፣ ሲምፖዚየሙ… ስትወጣ “ምን አገኝህ?” ብትባል ምን እንደምትል ግራ የሚገባህ – ለዚህ ነው፡፡ ግማሽ ሰዓት ዜና አዳምጠህ፣ አንድ ሰዓት ዶክመንተሪ ተከታትለህ፣ ሙሉ ቀን አውደ ጥናት ተካፍለህ አንዳች አዲስ ነገር የማትጨምረው ለዚህ ነው፡፡
ይብላኝ በዚህ ግዜ ለጠያቂ ነፍስ! ከዲሞክራሲው ግርግር ማዶ፣ ከዕድገቱ ጩኸት ባሻገር፣ ከፍትሕ ዜማው እልፍ ብሎ፣ ከዕኩልነቱ ኦርኬስትራ ጀርባ አሻግሮ የዲሞክራሲውን ቋት፣ የዕድገቱን ሌማት፣ የፍትሑን መንበር፣ የዕኩልነቱን መድረክ ባዶነት ላየ የጩኸቱን ከንቱነት መረዳቱ ቀላል ነው፡፡
ይብላኝ ያን ጊዜ ለራሱ ለኢህአዴግ፡፡ የአበሉ ሙቀት የበረደ ጊዜ፣ የፍርሐቱ ቆፈን የተገፈፈ ጊዜ፣ “የልማታዊ አርቲስቱ” ዜማ ዕጅ ዕጅ ያለ ጊዜ፣ ዜጎች ከቲሸርት ነፃነት፣ ከአበል እውነት ብለው የተነሱ ጊዜ፡፡
ፀጥታው ሲሰፍን የእውነት ድምጽ መሠማት ይጀምራል፡፡ ለራሱ ለኢህአዴግም፡፡ ያኔ የፀጥታ ፍራቻው ለዕውነት ፍራቻው ስፍራ ይለቃል፡፡ አዲዮስ!

No comments: