መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እስካገለገለና ኑሮውን እስካሻሻለ ድረስ የኢትዮጵያን ይገባኛልነትና የሚሰሩ መሰረተ ልማቶች መቀበል
የኢትዮጵያውያን ግዴታ ነው። ዓባይ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥሪት መሆኑን አምናለሁ። ጎሳዊ ወይንም ክልላዊ ሃብት አይደለም።
ስለሆነም፤ ዓባይን የምንታደገው “ኢትዮጵያ ሃገሬ ናት፤ ዜግነቴ ኢትዮጵያዊ ነው” ብለን እንጂ በጎሳ መታወቂያችን አይደለም። ከዚህ ጋር
አያይዠ ለማሳሰብ የምፈልጋቸው ብዙ ትችቶች አሉኝ፤ ጥቂቶቹ። አንድ፤ የህወሓት መንግሥት ጎሳዎች እርስ በርሳቸው እንዲጨፋጨፉ
ዋና ቀስቃሽ መሆኑ፤ ጭፍጨፋዎችና ዛቻዎች ሲካሄዱ ችላ ማለቱ ኢትዮጵያን ወደ አደገኛ ስርዓት ሰራሽ የእልቂት ጎዳና እየመራት ነው።
አንዳንድ የውጭ መንግሥታት ለዚህ የእርስ በርስ ግጭት መጋቢ ሆነዋል። ሁለት፤ ዶር መረራ ጉዲና “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል
ጉዞና የሕይወቴ ትዝትዎች” በተባለው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሊያነቡት ይገባል ብየ በምገምተው መጽሃፉ ያቀረበው ትችት ከፊታችን
የተደቀነውን አስኳል የፖለቲካ ኃይሎች አሰላለፍ መጠላለፍ በግልፅ ያሳያል። ይኼም፤ ህወሓት ሆነ ብሎ ያገለላቸው አብዛኛውን
የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚወክሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥቃቅንና ከለውጥ በኋላ ሕዝብ ተወያይቶ ሊፈታቸው የሚችለውን ልዩነቶች
ወደጎን ትተው ሰብሳቢ ወደሚሆነው ወደ ማህል የሚስብ ዲሞራሳዊ አጀንዳ አለመቅረጻቸው ነው። አብዛኛውን ሕዝብ የሚወክለው
“የኦሮሞና የአማራ ልሂቃን ፖለቲካ በዋናነት በሁለቱ ጫፎች ላይ ቆሞ ገመድ ከመጎተት ወደ መሃል መጥቶ የጋራ ዲሞክራቲክ አጀንዳ
መቅረጽ አልተቻለውም። ብዙዎቹ ሂሳብ የመወራረድ ፖለቲካን የዛሬ 30 እና 40 ዓመታት ብቻ ሳይሆን፤ የዛሬ 130እን 140 ዓመታት
በፊት የነበረውም ጭምር እንተሳሰብ የሚሉ ይመስሉኛል። የኦሮሞ ልሂቃን ዋናው ችግራቸው የጋራ የፖለቲካ አጀንዳ ለመቅረፅ
ከመጣር ይልቅ ለብቻ የሚደረገው ትግልን የመንግስተ-ሰማያት አስተማማኝ መንገድ አድርግው ማምለካቸው ነው። የአማራው ልሂቃን
በሽታው በዋናነት በአማራ ልሂቅ የተፈጠረች የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እንደዛው እንድትቀጥል ነው። እምነታቸው መቀጠል ትችላለች ነው።”
ከዶር መረራ ትችት ዋና ትምሕርት ነው ብየ የተቀበልኩት የኦሮሞን ልሂቃን የመገንጠል አምልኮ፤ ወይንም የአማራን ልሂቃን
ኢትዮጵያን ወደ ነበረችበት ንጉሳዊ ወይንም ደርጋዊ ስርዓት የመመለስ ተልእኮ ሳይሆን የሁለቱ አንጋፋ ሕብረተሰብ ክፍሎች ልሂቃን
ኢትዮጵያን ከመገነጣጠልና ከእልቂት አደጋ ለመታደግናን ሕዝቧን ዘላቂና ፍትሃዊ ወዳለው የእድገት መሰላል ለማመቻቸት እየተነጋገሩና
እየተወያዩ የጋራ ዲሞክራሳዊ አጀንዳ ለመቅረፅ አለመቻላቸውን ነው። ይኼን ባለማድረጋቸው የውጭ ኃያላን መንግሥታት፤ በተለይ
አሜሪካ በተናጥል ለሚያደርጉት ሰላማዊ ሰልፍና ጠበቃነት ዋጋ አልሰጡትም። ወደፊትም ዋጋ የሚሰጡት አይመስለኝም።
የኢትዮጵያን የፖለቲካ ውጣ ውረድ በጥልቀትና በቀጥታ የሚያውቀው ዶር መረራ እንዲህ ይላል። “…ለታሪክም ለሕዝብም አስቀምጨ
ማብቃት የምፈልገው መሰረታዊ ነጥብ፤ አብዛኛው የትግራይ ልሂቃን “ስልጣን ወይም ሞት” ብለው ሥልጣን ላይ የሙጥኝ እስካሉ
ድረስ፤ አብዛኛው የአማራ ልሂቃን በአፄዎች ዘመን የንበረውን የበላይነት መልሼ አገኛለሁ ብሎ የሚገፋውን የሕልም ፖለቲካ
እስካልተወ ድረስ፤ ብዙሃኑ የኦሮሞም ልሂቅ ኦሮሚያን ለብቻ የማውጣቱን ሕልም እስካልተወ ድረስ ሃገራችን ከአደጋ ቀጠናና ቀውስ
የምትወጣ አይመስለኝም።” እኔም የማሳስበው ተመሳሳይ ነው። የሶስቱም (የትግራይ፤ የአማራና የኦሮሞ) ልሂቃን አገሪቱ ብትፈራርስና
እልቂት ቢፈጸም በታሪክ፤ በአብዝኛው የኢትዮጵያ ሕዝብና በተከታታይ ትውልድ ተጠያቂዎች ናቸው። “ጂብ ከሄደ ውሻ ጮኸ”
የሚለው እንዳይከሰት እፈራለሁ። ኢትዮጵያ “ከአደጋ ቀጠና”፤ ሕዝቧን ከእልቂት ለማዳንና ዓባይን ከግብጾች አደጋ ወዘተ ለመታደግ
ፍላጎት ካለ-- ያለ ይመስለኛ--የፖለቲካው አደረጃጀት፤ ውይይትና ድርድር ከጎሳ ፖለቲካ ወደ ኢትዮጵያውያን ፖለቲካ መሸጋገር
አለበት። የኦሮሞ፤ የአማራና በህወሓት “ስልጣን ወይም ሞት” ውጭ የተሰለፉ የትግራይ ልሂቃን ለኢትዮጵያና ለመላው ሕዝቧ ባለ
አደራ ሆነው አብረው የሚሰበሰቡበት ወሳኝ ወቅት አሁን ነው። አገሪቱ ከፈራረስችና እልቂት ከተካሄደ በኋላ የምናደርገው ጭኸት
ለማንም አይበጅም። አሁንም የዘገየን ይመስለኛል። ለዚህ ነው፤ የጉራጌ ሆነ የአማራ፤ የኦሮሞ ሆነ የትግሬ፤ የሶማሌ ሆነ የአኟክ ወዘተ
መፈክር “ኢትዮጵያ ሃገሬ ናት፤ ዜግነቴ ኢትዮጵያዊ ነው” ብለን ለሁሉም ዜድጎች ዲሞክራሳዊና ሰብዓዊ መብት መነሳት አለብን የሚል
አደራ ያቀረብኩት። የኢትዮጵያ ሕዝብ በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ድምፁን አሰምቶ የፈለገውን የመንግሥት ስር ዓት የመመስረት መብት
አለው። ለፍትህ የሚቆረቆሩ ልሂቃን፤ ጎሳና ኃይማኖት ሳይለዩ የዲሞራሳዊ ማእከል አጀንዳ የማመቻቸት የሞራል ግዴታ አለባቸው።
ሶስተኛ፤ በአብዛኛው፤ ስርዓቱን የምንቃወም ግለሰቦችና ስብስቦች በሙስና የተበከለው የህወሓት መንግሥት፤ ከሕግ ውጭ በዓመት
ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ከድሃው ሕብረተሰብ ተሰርቆ ወደ ውጭ እንዲጎርፍ ያመቻቸ ራሱን አገልጋይ የመንግሥት ስርዓት መሆኑን
ነው። የዛሬው ስርዓት ሙስና ተወዳዳሪ እንደሌለው አምናለሁ። እነደ ተሃድሶ ግድብ ግዙፍና የማይንቀሳቅሱ የመሰረተ ልማት ምሰሶዎች
ሲሰሩ፤ ቢያንስ እንኳን ለሃገርና ለሕዝብ ይጠቅማሉ። በኔ ግምት ሊባክን የሚችለው ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመተው የውጭ
ምንዛሬና የብር ኢንቬስትሜንቱ የተሃድሶን ግድብ ለመገንባት፤ ለኢትዮጵያውያን የስራ እድል ለመፍጠር መዋሉ ተቀባይነት ያለውና
የሚደገፈ የዘመናዊነት መለኪያ ነው። ይህ የኢትዮጵያ የዓባይ ይገባኛልነት ትችት ሕብረተሰቡን፤ በተለይ ዲያስፖራውን በይፋ ከማነጋገሩ
ቀደም ሲል፤ “Ethiopia: the deal of the century (የመሬት ነጠቃና ቅርሚት) በተባለው መጽሃፌ ስለ ዓባይ ኢትዮጵያዊነት፤ ስለ
ተሃድሶ ግድብ ብሄራዊና ማህበራዊ ጥቅም፤ የተያያዙ ጥያቄዎችና መሰረታው የፖሊሲ ሃሳቦች ባጭሩ አቀርባለሁ። 2
1. ማንኛውም ዘመናዊነትን ለመቀዳጀት የሚፈልግ አገር ዘላቂነትና ፍትሃዊነት ያለው ሕብረተሰቡን የሚያቆራኝ የልማት መሰረት
ለመጣል ለመሰረተ ልማት ቅድሚያ መስጠት ግዴታው ነው። መንገዶች፤ ድልድዮች፤ ግድቦች፤ የሃዲድ መረቦች፤ የአየር
መጓጓዣዎች፤ ትምሕርት ቤቶች፤ የጤና ጣቢያዎች፤ መፀዳጃዎች፤ የንፁህ ውሃ ጉድጓዶችና ቧምባዎች ወዘተ ማልማት ወሳኝ
ነው። የኢህአዴግ መንግሥት በእነዚህ ዘርፎች ዙሪያ ያደረገው የመዋእለ ንዋይ ፈሰስ የሚያስመሰግን ነው። አከራካሪውና
እስካሁን ያልታየው መሰረተ ልማት ከምርት ኃይሎችና ከስራ እድል ፈጠራ ጋር አለመያያዙ እና ጎሳዊ መሆኑ ነው።
2. የተሃድሶና ሌሎች ግዙፍ የመብራት ኃይልና የመስኖ ግድቦች ከዚህ አስፈላጊ ከሆነ መሰረተ ልማት አይለዩም። ሆኖም፤
ግድቦች ሲሰሩ ሁለገብ ጥናትና ምርምር ማድረግ፤ አካባቢው ለተከታታይ ትውልድ እንዲያገለግል ማመቻቸት ፤ ነዋሪዎች
እንዳይጎዱ ጥንቃቄ ማድረግ እና አማራጮችን ማቅረብ፤ መላው ሕብረተሰብ የሚጠቀምበትን እቅድ ማውጣት ግዴታ ነው።
3. በተለይ ለመስኖ የሚያገለግሉ ግድቦች በስፋት መሰራት ቁጥሩ እየጨመረ የሄደውንና የሚሄደውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የምግብ
ፍላጎትና ዋስትና ለማሟላት ያስችላሉ። እንዲያውም፤ የእድገቱ ዋና ትኩረት መጀመሪያ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና
እንዲኖራት ማድረግ ነው። ዛሬ ብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የሚመኩት ለጋስ አገሮች፤ በተለይ አሜሪካ በሚለግሰው
የምግብ እርዳታ ነው። ይህች አገር ዘላለም የምግብ ጥገኛ ሆና ከቆየች አስደናቂ እድገት አለ ለማለት አይቻልም። ዓባይን
ያህል ለመስኖ የሚያገለግል ወንዝ ይዞ ጥገኛ መሆን የአገዛዝ ድክመትን ያሳያል። የምግብ ራስን መቻልና የምግብ ዋስትና
ስኬታማ ሊሆን የሚችለው ለም መሬትን ለውጭ ኢንቬስተሮች በመቸርቸር አለመሆኑን ከላይ በተጠቀሰው በማስረጃ
በተደገፈ መፅሃፍ በሰፊው ያሳያል። የደርግ መንግሥትና የግራው ክፍል ዋናና ሲጠቀስ የሚኖረው ዲሞክራሳዊ አስተዋፆ
መሬትን ላራሹ ማድረጉ ነው። ለእያንዳንዱ ከተመኛ ድሃ ሆነ ሃብትም ቤተሰብ ለራሱ መኖሪያ አምስት መቶ ካሪ ሜትር
መሬት ሰጥቶ በሕግ እንዲከበር ማድረግ ዲሞክራሳዊ ውሳኔ ነበር። ህወሓት ይኼን የሰው ህይዎት የተከፈለበት የአብዮት
ውጤት የፖለቲካና የግል ትርፍ መጠቀሚያ ማድረጉ በታሪክ ያስጠይቀዋል። ወጣቱ ትውልድ ለዚህ ዲሞክራሳዊ መብት
መታገል ይኖርበታል። በገጠር ሆነ በከተማ፤ የመሬት ባላቤትነት እውቅና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ማንነት ጋር የተያያዘ ነው።
4. ከውሃ የሚገኝ የመብራት ኃይል ለአገር ወለድ ኢንዱስትሪ ልማት መስፋፋት ቁልፍ ነው። የአየሩ ሁኔታ ከፈቀደ ከሌላ ነዳጂ
በበለጠ ደረጃ ተከታታይና ራሱን የሚያድስ ጥቅም ይሰጣል። ለአካባቢ እውቅና ሰጥቶ ይኼን የተፈጥሮ ሃብት መንከባከብ
ለተከታታይ ትውልድ ዋስትና ያለው የውሃና ከውሃ የሚገኝ መብራት፤ የመስኖ እርሻና የመሳሰሉ ጥቅሞች ይሰጣል።
ኢትዮጵያ የእርሻ ሰብሎች፤ የእንስሳት ወዘተ ኃብታም አገር ናት። ይህ የተፈጥሮ ኃብት ለኢንዱስትሪ መጋቢ ነው። የአገሪቱን
የጨርቃጨርቅ፤ መጫሚያ፤ የምግብ ውጤትና ሌሎች የፍጆት እቃዎች ለማምረትና ፍላጎትን ለማሟላትና ለውጭ ገበያ
ከእርሻና ከእርሻ ጋር የተያያዙ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ያለው እድል ሰፊ ነው። ትኩረቱ ግን የአገር
ውስጥ ፍላጎትን በተቻለ መጠን ማሟላት ነው የሚል ሃሳብ እሰነዝራለሁ። ተራው ኢትዮጵያዊ የመግዛት አቅሙ
የሚፈቅደውን ማቅረብ የእድገት መለኪያ መሆን አለበት። ኢትዮጵያውያን በአገራቸው የሚመረቱትን የኢንዱስትሪ ውጤቶች
የመግዛት ባህልን ልምድ ማድረግ ዘላቂነት ላለው እድገት ወሳኝ ነው። እድገት “ስልጣን ወይም ሞት” ለሚል ቡድን አገልጋይ
መሆኑ ማቆም አለበት። የሚያቆመው ለዲሞክራሳዊ ስርዓት የቆመ የአንድነት ኃይል ነው እላለሁ።
5. የዓባይ ወንዝ ኢትዮጵያዊነት እውቅናና የተሃድሶ ግድብ መገንባት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተደገፈ ነው። ሕዝቡ
ቀደም ሲል ቅኝ ገዢዎች፤ በተከታታይ የግብጽና ሌሎች የአረብ መንግሥታት ሆነ ብለው ጠብ እየጫሩ ኢትዮጵያ በዚህ
ግዙፍ የተፈጥሮ ሃብቷ እንዳትጠቀምና ከድህነት ነጻ እንዳትወጣ ማድረጋቸውን ያውቃል።
6. የኢትዮጵያ ሕዝብ እንግሊዞች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ በወቅቱ በጥቁር አፍሪካ ብቸኛ የነጻነት “ደሴት” እና እውቅና የነበራትን
ኢትዮጵያን እንደሌለች አድርገው ወደጎን ትተው በ1929 እና በ1959 ዓባይን ለግብፆችና ለሱዳኒሶች አውርሰው መሄዳቸውን
ያውቃል። ሆኖም፤ እነዚህን የተዛቡ ውሎች ተከታታይ የኢትዮጵያ መንግሥታት አልተቀበሉም። አዲሱና ለሁሉም የተፋሰስ
አገሮች የሚጠቅም፤ የNile Basin Initiative የተባለው መመሪያ የተባበሩት መንግሥት የልማት ድርጅት፤ ዓለም ባንክ፤
የካናዳ ተራድዖ ድርጅትና ሌሎች የደገፉት መርህ የጥቁር አፍሪካ ተፋሰስ አገሮች በሙሉ ደግፈውታል። ከጣና በለስ
ፕሮጀክት ጀምሮ፤ የዓለም ባንክ አመራር ኢትዮጵያ ድህነትን ለመቀነስ የምትችለው የዓባይ ወንዟን ለመስኖ እርሻና
ለኢንዱስትሪ ልማት ስትጠቀም ነው የሚል መሰረታዊ የልማት ዓመራር እንደነበረው አውቃለሁ። ሆኖም፤ ይህ ድርጅት
ለኃይል ማመንጫ ግድቦች የሚሰጠው ብድር ከአገር ወደ አገር ይለያያል። የፖለቲካ ውሳኔ አለበት ማለት ነው። ቁም ነገሩ
ግን፤ ዓለም ባንክ የናየል መርህን ከተቀብለ በኋላ ከመወላወል ወደ እርግጠኛነት ተሸጋግሯል። የኢትዮጵያን የይገባኛል አቋም
በቀጥታም ባይሆን ውስጥ ለውስጥ ይደግፋል። በአፄ ኃይለ ሥላሴና በደርግ ዘመኖች ታላቁን የዓባይ ግድብ በሚመለከት
የዚህ አይነት ጥራት ያለው አቋም አልነበረውም። ዓለም ባንክ የሚወስዳቸው አቋሞች በአብዛኛው የሚያሳዩት የአሜሪካ
ድጋፍ እንዳለ ነው። ግብጾች ከጅምሩ የዓባይ ግድብ የትም እንዳይደርስ ሞክረዋል። የማያከራክረው፤ የዓለም ሁኔታ በፍጥነት
ተለውጧል። ይህ ለውጥ ኢትዮጵያ የተሃድሶን ግድብ ለመገንባት ሙሉ መብት እንዳላት ያመለክታል።
3
7. ይህን በሚመለከት የአፄ ኃይለ ሥላሴ፤ የደርግንና የኢህአዴግ መንግሥታት ተመሳሳይ አቋም ይዘው ይገኛሉ። የግድቡን
ቅድመ ሁኔታ ያመቻቹት የቀድሞዎቹ መንግሥታት ሲሆኑ፤ ህልሙንና ራእዩን ወደ ተግባር የተረጎመው የአሁኑ መንግሥት
ነው። ስርዓቱን ስለምንቃወም ብቻ ለሃገር የሚጠቅሙ፤ ማንም የማያንቀሳቅሳቸው ሃውልት የሚመስሉ ግድቦች ሲሰሩ
መደገፍ ገዢውን ፓርቲ መደገፍ አይደለም። በበኩሌ፤ ስርዓቱንና የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም እለያለሁ። ያለፈውን
የኢትዮጵያን ዘመናዊ አገዛዝ አመሰራረት ውጣ ውረድ ስናይ፤ በሃገር ማእከላውዊነት፤ በሃገር ታሪክ ተከታታይነትና የወደፊት
አብሮ መኖር፤ አብሮ ማደግ፤ አብሮ ሃገርን መታደግ የሚያምን መንግሥት መደገፍ አግባብ አለው። የመንግሥቱ የበላዮች
ቢለወጡ የአገር ዘላቂ ጥቅም አይለወጥም። የአገር ዘላቂ ጥቅምና ደህንነት እንደ ሸቀጥ አይሸጥም፤ አይለወጥም። ዓባያና
በዓባይ ላይ የሚሰራ መሰረተ ልማት አይሸጥም፤ አይለወጥም። የዓባይ ግድብ ከዚህ ያለፈ የኢትዮጵያ የማይሸጥ፤ የማይለወጥ
የማንነት ታሪክ ጋር ተመሳሳይነት አለው እላለሁ።
8. በማህበረሰብ ህይዎት አንጻር ሲታይ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እየተራበ፤ እየተሰደደ ሰማንያ ሶስት በመቶ የሚሆነው በኩራዝ
መብራት እየተጠቀመ ወዘተ ዓባይ አይገደብ ብሎ መበየን በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ መፍረድ ነው። የዚህ አይነቱ
አቋም የሚጠቅመው ግብፃችን ይሆናል። ይኼን ስል ሁለተኛውንና ዋናውን የዲሚክራሳዊ ስርዓት አስፈላጊነት እንዳንረሳ
አሳስባለሁ።
9. የግድቡ ጥቅም የመብራት ኃይል ብቻ አይደለም። አስዋን፤ የቪክቶሪያ ፏፏቴና ግድብ፤ ኢዋዙ ፏፏቴና ሌሎች ለሽርሽር
(ቱሪዝም) በየዓመቱ የሚስቡት የሰው ብዛት፤ የሚያስገኙት ገቢ፤ የሚቀጥሩት የሰራተኛ ብዛት ከፍተኛ ነው። የተሃድሶ
ግድብም ይኼን የመሰለ ጥቅም እንደሚስገኝ ለማሰብ አያዳግትም። አክሱምን፤ ጎንደርን፤ ላሊበላን ወዘተ ለማየት የሚመጣው
አገር ጎብኝ ተጨማሪ ሃውልት አገኘ ማለት ነው። የዘላለም የተፈጥሮ ሃብት የዘላለም የኢኮኖሚ መንቀሳቀሻ ይሆናል።
10. የተሃድሶ ግድብ እቅድ በድንገት የተፀነሰ አለመሆኑን ባለፈው ሃምሌና ነሃሴ በተከታታይ በእንግሊዝኛ ባቀርብኳቸውና በክፍል
አንድ በአማርኛ ባቀርብኩት መጻጽፍት አሳይቻለሁ። በግብፅ የተካሄደው የሕዝብ አመጽ የግብፆችን ትኩረት ለጊዜውም
ቢሆን በአገሪቱ እርጋታ ላይ እንዲያተኩር አድርጎታል። የኢትዮጵያ መንግሥት ያለውን ክፍተት መጠቀሙ አግባብ አለው።
በተጨማሪ፤ የአፍሪካ የተፋሰስ አገሮች መብታችን ይከበር እያሉ ነው። ሆኖም፤ ይህ ጊዜአዊ የሆነ የግብፅ ድክመት በመለወጥ
ላይ ነው። የግብፅ የመንግሥት ዓመራር ፍጹም ብሄርተኛ (ultra Egyptian Nationalist) ወደ ነበረው የናስርና ሞባርከ
አይነት ወታደራዊ አገዝዛ እየተሸጋገረ ነው። ይህ ወታደራዊና አምባገነናዊ ይዘት ያለው አገዛዝ በተሃድሶ ግድብ ላይ ኢላማ
ያደርጋል የሚሉ ብዙ ናቸው። ባለፈው ዓመት መጨረሻ ዶሃ በተደረገው የዓረቦችና የአፍሪካውያን ልሂቃን ስብሰባ አንድ
የታወቀ ግብጻዊ ያቀረበው ትንተናና ድምዳሜ አመልካች ነው።
11. “በአፍሪካ የሚካሄደው ግዙፍ የሆኑ የመብራት ኃይል አቅርቦት ግድቦች ስራ አዲስ የወንዝ ውሃ ኃያላን መንግሥታት
እየፈጠረ ነው (New Hydropoewer Hegemony).” ይህ ኃያልነት ከማን ላይ እንዳተኮረ ግልፅ ነው። ግብፅን የሚመለከት
ግዙፍ ግድብ የሚሰራው በዓባይ ወንዝ ላይ ነው። አዲስ ወይንም መጤ የወንዝ ውሃ መብራት ኃያል አገር ተብላ
የምትጠራው ኢትዮጵያ ናት። ምሁሩን “የዓባይን (ናየል) ወንዝ ለጋራ አገልግሎት ለማዋል የተጀመረው የኢትዮጵያና የሌሎች
የአፍሪካ ተፋሰስ አገሮች መብት ነው። ድሃና ኋላ ቀር የሆኑት አገሮቻቸው የማልማት መብት አላቸው። የዓለም ሕግ
ይፈቅድላቸዋል። ይህ መብት በስራ መተርጎሙ የማይቀር ነው። የሚጠቅመው የጥቁር አፍሪካ አገሮችን እየለያዩ “አዲስ
ኃያል” ማለት ሳይሆን በጋራ በሚሰሩ የአባይ ሁለ-ገብ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ነው” ወዘተ በማለት ለማግባባት ያደረግሁት
ጥረት የትም የደረሰ አይመስለኝም። ግብፃዊው የሚለው ይህ አዲስ ክስተት ተቀባይነት የለውም ነው። እኔ ደግሞ የምለው
ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች የሚጋሩትን ታላቅ ወንዝ ለራሳቸው ሕዝብ አገልጎሎትና ለሃገራቸው ልማት ለማዋል
መብታቸው ነው። ማንም ኃይል ሊያቆማቸው አይችልም የሚል ነው። ሚዛናዊ የሆኑ የግብፅ ልሂቃን ዓባይን ሚዛናዊ በሆነ
መንገድ መጠቀም አግባብ አለው ይላሉ።
12. ምንም እንኳን “ሃይድሮ ፖወር ሄጀሞኒ፤ የውሃ ኃይል የበላይነት” ሆነ ተብሎ የአፍሪካ አገሮች እንደ ኃያላን መንግሥታት
እየሆኑ ሂደዋል፤ “ደቡብ አፍሪካና ናይጀሪያ” አዲስ የጥቁር አገሮች የበላይ ጡንቻ ያሳያሉ” ወዘተ የሚል አፍሪካውያንን
የሚከፋፍል ሃሳብ ቢያሽከረክርም፤ አባባሉ አያዋጣም። አንድ አገር የተፈጥሮ ሃብቱን ተጠቅሞ ድህነትን ለመቀነስ፤ ቢቻል
ለማጥፋት ሲጀምር የዚህ አይነት ቅፅል ስም መስጠቱ አግባብ የለውም። ሰላም አይፈጥርም። የገልፍ አገሮችና ሳውዲ አረቢያ
የነዳጅ ኃብታቸውን አልምተው ሃብታም ስለሆኑ አዲስ ኃያላን ያላቸው የለም። ናይጀሪያ አዲስ ኃያል አገር ብትሆን ኑሮ
ሺብርተኞችን ለማደን የአሜርካ እርዳታ አያስፈልጋትም ነበር። ኃያል ስትሆን ደግሞ ማንም ሊኮንናት አይችልም።
ኢትዮጵያውያን ካወቅንበት ኢትዮጵያም ተገቢውን አህጉራዊ ኃያልነት ትቀዳጃለች የሚል እምነት አለኝ። ይህ በብልሃት፤
ሁሉን በሚያስትፍ ዲሞክራሳዊ ስርዓት ስኬታማ ይሆናል። አገሪቱ ከተበታተነችና እልቂት ከተካሄደ ይህም ህልም ይሆናል።
13. የዓባይን ግድብ ለማፍረስ የሚሞከረው የግብፆች የጦርነት “አለንጋ” አያስፈራኝም። የሚያስፈራኝ ህወሓት የፈጠረው
የሕብረተሰብ መከፋፈልና የሰብዓዊ መብቶች ሁሉ መገፈፍ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሃገሩ ቀና ነው። ብሄር፤ ብሄረሰብ፤ 4
ሃይማኖት፤ ሃብት፤ ጾታ፤ ስደተኛ፤ አገር ውስጥ ኗሪ የሚል ሳይለየው በአንድ ላይ፤ ለአንድ ብሄራዊ ዓላማና ለእውነተኛ
የሁሉም ዜጎች እኩልነት ከቆመ ማንም የሚያጠቃው ኃይል እንደማይኖር ሙሉ እምነት አለኝ። ደጋግሜ እንዳሳሰብኩት፤
ግብፆች በፖለቲካና በኃይማኖት የተለያዩ ዘርፎች አሏቸው። የሚዳኛቸው ግን ማንነታቸውን ማወቃቸው ነው። “ግብፅ
አገራችን ናት። እኛ ግብጻውያን ነን” የሚለው እውቅና በያንዳንዱ የግብፅ ዜጋ ደም ስር የገባ መሆኑን ተመላልሸ
ካነጋገርኳቸው ግብጻውያን ተምሬያለሁ። ግብጾች በአስተሳሰብና በኃይማኖት ከአንድ ፋብሪካ የወጡ አይመስሉም። በዓባይ
ጥያቄ ግን አንድ ወጥ ናችው ለማለት ይቻላል።
ግብጾች “ግብፅ ሃገሬ ናት፤ እኔም ግብጻዊ ነኝ” የሚሉት ለኢትዮጵያውያን አዲስ ክስተት አይደለም። ተስፋ የሚሰጠኝ እሴት እኛ
ኢትዮጵያውያን ከማንም ባላነሰ ደረጃ “አገሬ ኢትዮጵያ፤ ዜግነቴ ኢትዮጵያዊ” እያልን አድገናል። ባህላችንና መታወቂያችን ይኼው
ነበር። ለኢትዮጵያ ነጻነት፤ ለሁሉም ሕዝቧ ክብር ሲሉ ተዋግተው የሞቱት ኦሮሞዎች፤ ጉራጌዎች፤ ደቡቦች፤ ትግራዮች፤ ኤርትራዉያን፤
አፋሮች፤ አማራዎች፤ ሶማሌዎች፤ ክርስትያኖች፤ ሙስለሞች ወዘተ ለዚህ የሚያኮራ እውቅና አብቅተውናል። እንደዛሬው አይሁን እንጅ
በእኔ ትውልድ ያየሁት የፓስፖርት መታወቂያ፤ ከግንባሬ ላይ የተለጠፈ ጎሳየ አልነበረም። በተማሪው እንቅስቃሴ የማውቃቸው ከዚህ
ዓለም ያለፉና አሁንም በህይወት ያሉ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ከየት መንደርና ጎሳ እንደመጣን ተነጋግረን አናውቅም። አናስብውም
ነበር። አነጋጋሪያችን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚበጅ ፍትሃዊና ዲሞክራሳዊ ስርዓት እንዴት እናራምድ የሚል ነበር። በሃገር ቤትና
ከሃገር ውጭ ያለው ወጣት ትውልድ--ተማሪው፤ አስተማሪው፤ የቢሮ ሰራተኛው ወዘተ ቀና አመለካከት፤ ከራሱ ጥቅም በላይ ለሃገሩና
ለወገኑ የሚቆረቆር፤ ለነገው ትውልድ የሚያስብና የሚታገል ለመሆኑ የአይን ምስክር ነኝ። የዚህ ሰብሳቢ መልእክትና ማሳሰቢያ አንድ
ነው። “አገሬ ኢትዮጵያ፤ ዜግነቴ ኢትዮጵያዊ።” ይኼን እንደ አሮጌ ጨርቅ አውልቀን ጥለን ዓባይን ሆነ ሌላውን የኢትዮጵያ የተፈጥሮ
ሃብት ለመታደግና ለመላው ሕዝብ ጥቅም ለማዋል አንችልም። ዲሞክራሳዊ አማራጭም ለመመስረት የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መብት
መገፈፍ የራሴ መብት መገፈፍ ነው ወደሚል ሰብሳቢ ፖለቲካ ከሸጋገር መቻል አለብን።
አንዱ የወቅቱ ጥያቄ አገር ቤትና ውጭ ያሉ ተቃዋሚ ድርጅቶችና ግለሰቦች፤ የገዢው ፓርቲ አባላትና ሌሎች በዓባይ ይገባኛልነት
የሚያምኑ ሁሉ “አገሬ ኢትዮጵያ፤ ዜግነቴ ኢትዮጵያዊ” ብለው የመሰብሰብና ለአንድ ዓላማ የመቆም ግዴታቸውን ከተወጡ ግብፆች
ኢትዮጵያን ለማጥቃት አይችሉም እላለሁ። ይህን የምልበት ዋና ምክንያት ከኢትዮጵያውያ አስደናቂ ታሪክ፤ ከጀግኖⶩ ጀብዱ ልምድ
የተማርኩትን ምርኩዝ በማድረግ ነው። አፄ ምኒልክ የአድዋን ድል ለኢትዮጵያና ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ያበረከቱት ዘመናዊ መሳሪያ
ስለነበራቸው አይደለም። ክሁሉም ብሄር፤ ብሄረሰቦችና እምነቶች የተወጣጡ አርበኞቿ በአንድ ላይ፤ “አገሬ ኢትዮጵያ፤ ዜግነቴ
ኢትዮጵያዊ” ብለው በአንድ ላይ ስለተዋጉና ስለሞቷላት ነው። የፋሺስቶችን ወረራ አንቀበልም ብለው ለአምሥት ዓመታት በዱር
በገደሉ የተዋጉላትም አርበኞቿ ይኼን የተቀደሰ አርማ ተከትለው ነው። ስለሆነም፤ ከግብፅ የመሳሪያ የበላይነት የበለጠ አስተማማኝ
የሚሆነው ወሳኝ ኃይል የኢትዮጵያውያን ወንድማማችነት፤ እትማማችነትና አንድነት ነው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ከሕዝቧ
አንድነትና እውነተኛ እኩልነት ሊለይ አይችልም። ብሄራዊ አንድነቷን ለመጠበቅ የምትፈልገውና የምትችለው ኢትዮጵያ፤ የተባበረና
በሕግ ፊት እኩል የሆነ ሕዝብን ትጠይቃለች። የተባበረና መብቱ የተከበረ ሕዝብ መሳሪያ የማይተካው ኃይል ነው።
ለስልጣን ብቻ የቆመው ህወሓት ለዚህ ኃይል መበታተን ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ነው። በአንድ ቦታ፤ “እኔ ከሌለሁ አማራውን ኦሮሞው
ሊነሳብህና ሊጨፈጭፍህ ነው፤ ተጠንቀቅ” ብሎ ይቀሰቅሳል። በሌላ ቦታ፤ ኦሮሞውን “የአማራ ነፍጠኞችና የኢሰፓ አምባገነኖች
እንደገና ሊመጡብህ ነው። የዱሮውን መንግሥት ለመመለስ እየተዘጋጁ መሆናቸውን እናውቃለን።” በሌላ በኩል ደግሞ ለትግራይ
ሕዝብ “የሸዋ አማራ አሁንም እየዶለተብህ ነው።” በደቡብና ሌሎች ክልሎች “የራስክን ጥቅምና ማንነት ካላስከበርክ፤ አማራውና
ኦሮሞው ይጨፈጭፍሃል” ወዘተ እያለ ሕዝብን ከሕዝብ ሲለያይ ቆይቷል። ይህ የቅኝ ገዢዎች “ከፋፍለህ ግዛው” አይነት የውሸት
ዓመራር ግብፇችንና ሌሎች ኃያላንን ለመቋቋም ማነቆ ሆኗል። ሕዝቡ እውነቱን ከውሸቱ ለይቶ ለመብቱ በአንድ ላይ እንዳይነሳ
አድርጎታል። ለዚህ መልሱ የህወሓት የስልጣን መቆያ የሆነውን የመለያየት ዘዴ አውቆ በአንድ ላይ አገር አቀፍ በሆነ የሕዝብ ዓመጽ
መነሳት ብቻ ነው። መረዳት ያለብን ህወሓት ራሱን መርምሮ ወደ ፍትሃዊ ስርዓት ካላመራ አገሪቱን አጥፍቶ ራሱንም ያጠፋል።
ለስልጣኑ ቆይታ ያደረገው ስሌትና ስልት በተለይ ኦሮሞውና አማራው እርስ በርሱ ቢተላለቅ ደንታ የሌለው አመራር ነው። ወጣቱ
ትውልድ ከዚህ ባሻገር ማሰብ አለበት። እልቂት ለማንም አጥፊ ነው። መከላከል የሁላችንም ሃላፊነት ነው። ለጥላቻው መጋቢ የሆን
ሁሉ በታሪክ ተጠያቂዎች እንደምሆን አያከራክርም።
ያለው የከፋፍለህ ግዛው ችግር እንዳለ ሆኖ (ይኼን ለመፍታት አብሮ ከመታገል ውጭ አማራጭ ያለ አይመስለኝም)፤ ይህ ግዙፍ ግድብ
የኢትዮጵያውያን መታወቂያ ሃውልት መሆኑን ግን መካድ አደገኛ ነው። ሌሎች የኢትዮጵያ መንግሥታት ሊገነቡት የፈለጉትንና አቅም
ስለሌላቸውና ሁኔታዎች ስላልፈቀዱ ስኬታማ ያላደረጉትን የአሁኑ መንግሥት መስራቱ አያስነቅፍም። ደጋግሜ ለማስታወስ የምፈልገው
አስኳል ጉዳይ የኢትዮጵያ የዓባይ ይገባኛልነት ከሶስት ሽህ ዓመታት በላይ ከሚገመተው ተከታታይ የኢትዮጵያ ታሪኳ ጋር የተቆራኘ
ነው የሚል የፀና እምነት አለኝ። ይህ ዓለም ያደነቀውና አንድ የመፃሕፍት ቤት የሚሞላው የኢትዮጵያ ተከታታይነት ታሪክ ከጥያቄ
በላይ አልፏል። ይህ አዲስ የኢትዮጵያ ታሪክ አልባ ክስተት በስልጣን ስሜት፤ ባለፉት ሃያ ሶስት ዓመታት በህወሓት መሪዎች ጥላቻ
የተሽከረከረ እልቂት ያስከተለና ወደፊትም የሚያስከትል ሂደት ነው። የዓባይ ይገባኛልነት ጥያቄ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ከኢትዮጵያ
ህልውና ጋር የተያያዘ ጉዳይ መሆኑን ህወሓት መቀበል ግዴታ ሆኖበታል። ተወዳጅንት ለማግኘት መሆኑ አያከራክርም፡፡ ኢትዮጵያ
በረዢም ታሪኳ ይገባኛል ብላ ባትከራከርና የብዙ ዜጎቿን ህይዎት መስዋት ባታደርግ ኖሮ፤ ገዢው ፓርቲ የተሃድሶን ግድብ ለመስራት 5
አይችልም ነበር። በአንፃሩም ግብጾች የሚሉት ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ይገባኛልነት አግባብ ይኖረው ነበር። ለህወሓት መሪዎችና
ለኢህአዴግ አባላት ለማሳሰብ የምፈልገው ታሪኩን የካደ ሕዝብ በዓባይ ላይ ታሪካዊ መብት አለኝ ለማለት የሞራል ብቃት እንደሌለ
ነው። ዛሬ የማይካደው ክስተት የኢትዮጵያን ታሪክ የለም የሚለው ህወሓት ካልፈለገውና ካላሰበው የታሪክ ውጥንቅጥ ውስጥ ገብቷል።
ታሪክን አፈራርሶና ሰርዞ የታሪክ ጨለማን መፍጠር ለጊዜው የበላይነት ጥቅም ቢሸምትም ዙሮ ዙሮ ሁሉንም እንደሚያጠፋ እሰጋለሁ።
ስርዓቱ ሆነ ብሎ የፈጠርው ጎሳዊ ፖለቲካ የህልውና ጉዳይ ሆኗል። ጎሳዊው የፖለቲካ ዓመራር ህወሓት ለራሱ የስልጣን የበላይነትና
ቆይታ ሲል ለተባባሪ የጎሰኞች ቡድኖች (ethnic elites) ፤ በማስፈራራት፤ በመደለል፤ ጉርሻ በመስጠት ወዘተ በናንተ ተወካይነት
“ጭቁን ሕዝቦች” ለመጀመሪያ ጊዜ እፎይ ብለው የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት አግኝተዋል በሚል ከእውነቱ የራቀ ስሌት
የኢትዮጵያን ታሪክ፤ አንድነትና የኢትዮጵያን ሕዝብ የቆየ ጠንካራ ግንኙነት፤ ሏዓላዊነት አወቃቀር ከስሩ ንዶታል። ባጭሩ፤ ቢቀበልም
ባይቀበልም፤ ቢያውቅም ባያውቅም፤ የህወሓት ዓመራር የተከተለውና የሚከተለው የአገር ዘመናዊነት ዓመራር “ከተሃድሶ ግድብ”
ኢትዮጵያዊነት ጋር ሊጣጣም አልቻለም። ኢትዮጵያ “ከመቶ ዓመታት በላይ የሚሰላ ታሪክ የላትም። የዛሬይቷ ኢትዮጵያ በኃይልና
በጭፍጨፋ የተፈጠረች ናት። ከፈለጉ ብሄር/ብሄረሰቦች የመገንጠል መብት አላቸው” ወዘተ ከተባለ ኢትዮጵያውያን ከሚጋሯቸው
ይልቅ የሚለዩአቸው ያይላሉ ማለት ነው። ዓባይን ሆነ ሌላ የተፈትሮ ኃብት፤ የኢትዮጵያን ዳር ድንበርና ደህንነት አብሮና ተባብሮ
ለመከላከል ያስቸግራል ማለት ነው። የህወሓትን አፍራሽ አመራር ከተቀበሉና ስኬታማ ለማድረግ ከፈለጉ የሁሉም ክልሎች ነዋሪዎች
“ዓባይ የኢትዮጵያ ነው። የአሁኑ መንግሥት የሚሰራው ግድብ አግባብ አለው። የግብፆችን የጦር ዛቻ አንቀበልም” የማለት ግዴታ
የለባቸውም። የጎሳዊውን አቀራረጽ ከተቀበልን ( የተገኙ ዲሞክራሳዊ ድሎችን፤ ለምሳሌ የመሬት ላራሹን፤ የባህል፤ ቋንቋ፤ ታሪክ
እኩልነትን ወዘተ ተቀብለን)፤ ዛሬ ወሳኙ ክልልና ጎሳዊ ማንነት እንጂ ኢትዮጱያና ኢትዮጵያዊነት አይደሉም። ሌላው ቀርቶ፤ በነጻና
በድሎት በምእራብ አገሮች የምንኖረው ስደተኞች በኃይማኖት፤ በፀሎት ቤቶች፤ በሞያዎች፤ በምግብ ቤቶች ወዘተ የተሰበሰብነውና
የምንሰበሰበው ጎሳዊና መንደራዊ በሆነ አወቃቀር ነው። አንዱ ከሌላው ጋር የመወያየት፤ አንዱ ከሌላው የመማር፤ የጋራ በሆኑ ጉዳዮች
ዙሪያ ከብሄር፤ ብሄረሰብና ኃይማኖት ባሻገር በጋራ የመወያየትና ገንቢ ዓማራጮች የማቅረብ ልምድ ጠፍተዋል። ህወሓትና ተባባሪዎቹ
ከስራ ላይ ያዋሉት መርህ የምንጋራው ታሪክ፤ ልምድና ባህል የለም የሚል መልእክት የሚሰጥ ክስተት ነው። ከላይ እንዳሳየሁት፤
ዓባይን ለመታደግ ጭምር፤ የጋራ ታሪክ፤ ባህልና ልምድ ለኢትዮጵያና ለሕብረተሰቧ የወደፊት ታላቅነት ወሳኝ ነው።
የኢትዮጵያ ተከታታይ የሆነ የማይካድ ታሪክ የአንድ ብሄር ወይንም ኃይማኖት ትግል ውጤት አይደለም። በተለያዩ ቀውጢ ወቅቶች
ማንም ሳይስገድዳቸው፤ ለሃገራቸውና ለራሳቸው ክብር ሲሉ የሞቱላት ቁጥር በሚሊዮኖች ይታሰባል። ከሁሉም ብሄር፤ ብሄረሰቦችና
እምነቶች የተወጣጡ ጀግኖች መስዋእት እንደሆኑላት የኢትዮጵያና የውጭ አገር የታሪክ በላሞያዎች በማስረጃ አቅርበውታል። ጥቂቶቹን
በክፍል ሁለት አቅርቤአለሁ። የጎሰኞች የታሪክ ብረዛ ለሁሉም አደገኛ ደረጃ ይዞ ወጣቱን ትውልድ የተያያዘ ታሪክ እንደሌለውና እርስ
በርሱ ‘እንዲፋጭ’ ከመጋበዙና ከማመቻቸቱ በፊት ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚወክሏቸው ተቋሞችና ጀግኖች ከሚለያዩአቸው ያይሉ
ነበር። አገር ወዳዱና ለሃቅ የሚሟገተው አኩሪ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ “የአባቶች ስንብት” በሚል ወቅታዊ አርእስትና
ትንተና ላሰበበትና ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ለሚጨነቅ አግባብ አለው። እንዳሳሰብኩት፤ ዛሬ ታላቅ፤ ሃብታምና ዘመናዊ ናቸው ብለን
የተሰደድንባቸውና ወጣቱ ትውልድ የሚሰደድባቸው አገሮች ኢትዮጵያ የሄደችበትን ውጣ ውረድ መንገድ ሂደውበታል። እነዚህ አገሮች
ከኢትዮጵያ ያላነሰ እልቂት ተካሂዶባቸዋል። መሪዎቻቸው ያተኮሩት በእርስ በርስ መወነጃጀልና ለእልቂት በሚዳርግ መወነጃጀል
አልነበረም። ይህ ቢሆን ኑሮ የምናደንቃት አሜሪካ የዓለም ኢኮኖሚና የጦር ኃይል መሪ አትሆንም ነበር። በብዙ የእርስ በርስ ጦርነት
ያለፈችውና ዛሬም ከፍተኛ ውጥረት የገጠማት ናይጀሪያ ደቡብ አፍሪካን ቀድማ (በጠቅላላ ገቢ ሲመነዘር) የአፍሪካ የኢኮኖሚ መሪ
ሆናለች ባልተባለችም ነበር። ሁለቱም አገሮች ታሪካችውን አልበረዙም። ታሪክ የሌለው ሕዝብ የሚጎዳው የተከታታይ ትውልድን የጋራ
ደህንነትና ብልፅግና መሆኑን ተገንዝበዋል። የማሳስበው ከእነዚህም ልምድ እንድንማር ነው።
“በርካታ አሰቃቂ ጭፍጨፋዎች እና የማንነት ጭፍለቃዎች የማንክደው የታሪካችን አካል ቢሆንም፤ ሃገር በመታደግ ዘመቻው በመሰለፍ
ዛሬ ኢትዮጵያንን-ኢትዮጵያ ያደረጉት፤ (እኛን “ዜግነታችን ኢትዮጵያዊ” ነው ለማለት ያበቁን፤ የኒ ጭማሬ) ከራስ አሉላ አባነጋ እስከ
ራስ ጎበና ዳጩ፤ ከፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ እስከ ፊታውራሪ ገበየሁ፤ ከራስ መኮንን እስከ አሚር አብዱላሂ፤ ከደጃዝማች
ባልቻ ሰፎ እስከ ራስ መንገሻ ዮኃንስ…በአድዋ የፈጸሙት አኩሪ ጀብዱ ነው። በአናቱም እነዚህን ጀግና አባቶች ለአንድ ዓላማ አንድ
ግንባር ያዋላቸው ሃገራዊ አጀንዳ እንጂ፤ ንጉሳዊ ፍቅር ወይንም አድርባይነት አለመሆኑ ከማናችንም ባይሰወርም፤ በህወሓት የኑፋቄ
ስብከት ተነድተን በአንድነት የሚያቆሙንን መስተጋብሮች አፍርሰን፤ የተናጥል ማንነት የምንሻ ከሆነ፤ አባቶቻችንን አሰናብተን፤ አዲስ
ማንነት ፈጥረን ወደ ገደሉ አፋፍ መገፋታችን የጊዜ ጉዳይ ከመሆን የሚታደገው አለመኖሩን ማስታወስ እወዳለሁ” በማለት ከፊታችን
የምናየውን ለሁሉም አደጋ ፈጣሪና ኢትዮጵያን እንዳልነበረች የሚበታትን ሁኔት በግልፅ አስቀምጦታል። ይህ እንደ ግብፅ ላሉ
የኢትዮጵያን ፈጣንና ፍትሃዊ ልማት፤ የመላው ሕዝቧን በሕግ የተረጋገጠ እኩልነት ለማይፈልጉ ኃይሎች ሁሉ ሳይዋጉ በረከት
ይሰጣቸዋል የሚል ግምት አለኝ። በኤርትራ እንደታየው፤ የኢትዮጵያውያን የእርስ በርስ ግጭት ስኬታማ ሲሆን የሚጎዳው ማን
ይሆናል ብለን ብንጠይቅ መልሱ ቀላል ነው። የሚጎዳው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። ለምሳሌ፤ ህወሓት የፈጠረው ስርዓት የእርስ በርስ
ጦርነት ቢያስከትል የማይረሳና የማይቆም ግጭት ይፈጥራል። ዛሬ በዩክሬን የምናየው በኢትዮጵያም እንደሚሆን አልጠራጠርም።
ስለዚህ፤ መፍትሄውን የምንፈልግበት ወቅት ዛሬ እንጂ ነገ አይደለም እላለሁ። የዲሞክራሲ ማእከል አጀንዳ መቅረፅ ከሚመጣ ችግር
ሊያድነን ይችላል የሚል ግምት አለኝ። የዲሞክራሳዊ ስርዓት አማራጭ ትግል የሁሉም ትግል መሆን አለበት እላለሁ። 6
እሁሉም በላይ የሚጎዳው ከሁሉም ብሄር፤ ብሄረሰብና ኃይማኖት የተወጣጣው ከስድሳ በመቶ በላይ የሚገመተው በደርግ ጊዜና ከደርግ
በኋላ የተወለደው ወጣቱ ትውልድ ይሆናል። ዛሬ ከሃገሩና ከቤተሰቡ ተለይቶ በበረሃ፤ በውቅያኖስና በአረብ አገሮች የሚሰቃየው፤
የሚሞተው ለመስራት፤ ለመፍጠር፤ ለማምረት የሚችለው አማራ፤ አፋር፤ ኦሮሞ፤ ጉራጌ፤ ሶማሌ፤ ትግሬ ወዘተ ትውልድ ነው።
በማፈንና በስደት ስሌት ሲታይ ስርዓቱ ጎሳ፤ ፆታ፤ እድሜና ኃይማኖት አይለይም። ወጣቱ ትውልድ እውቀት አለው። ስርዓቱ
“በፈጠረልን የጥላቻ ወጥመድ ገብተን እርስ በርሳችን እንጨራረስ የሚል ጤነኛ ሰው ያለ አይመስለኝም። ብንሰደድም ምንም አይደል፤
የቀረው ያልፍለታል” የሚል ግለሰብ ያለ አይመስለኝም። እርስ በርሱ የመወያየት እድል ቢኖረው ወጣቱ ትውልድ በራሱ ላይ
አይፈርድም የሚል እምነት አለኝ። እየቆየ የሚከሰተው ሃቅ ወጣቱ ትውልድ እርስ በርሱ እንዳይተማመን፤ እርስ በርሱ ተደጋግፎ
ፍትሃዊና ዲሞክራሳዊ መንግሥት እንዳይመሰርት የፈረዱበትና ለአደጋ ያመቻቹት የህወሓትና ጥገኛ የጎሳ መሪዎች ናቸው። ሆኖም፤ ቀስ
በቀስ ወጣቱ ትውልድ የጎሳ ክፍፍልንና የማይታረቁ ልዩነቶችን አጋነው ለስልጣንና ለግል ኃብት ማካበቻ እንዲሆኑ ያደረጉና የሚያደርጉ
ከፋፋይና በታኝ ኃይሎች መሆናቸውን እየተገነዘበ ሄዷል። ወጣቱ ትውልድ እንዲገነዘበው የምመኘው የፍትሓዊ ለውጥ ኃይሎች ሁሉ
ኢላማቸው መብታችውን ከገፈፈው ፓርቲና ከስርዓቱ ላይ እንዲሆን ነው። የስርዓቱን እድሜ ያራዘመው የኢህአዴግ ፍትሃዊ አገዛዝ
አይደለም። የሌሎቻችን መበታተን፤ አለመተማመን፤ አለመከባበርና አለመደጋገፍ ነው። ህወሓት ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የበለጠ
የመበታተን፤ ሰርጎ የመግባት፤ የመደለል፤ የማስፈራራት እውቀትና ሃብት አለው። ይህ ጥንካሬ ከሕዝቡ ጥንካሬና ኃይል አይበልጥም።
የጋምቤላ፤ የኦጋዴን፤ የኦሞ ሸለቆ፤ የአማራ፤ የአፋር፤ የኦሮሞ ወዘተ ሕዝብ በተናጠል ሲጨፈጨፍ “ነግ በኔ” ብለን ለማውገዝ
አልቻልንም። ተራችን የምንጠብቅ እንመስላለን። ህወሓት እኛን እርስ በርሳችን አባልቶ ይገዛል፤ ራሱን እንድንመስል አድሮጎናል። ጠብ
ጫሪው ሌላ ነው እያለ ራሱን ከደሙ ንጹህ ነኝ የሚል ቡድን ነው። ሌላው ቀርቶ፤ የመንፈሳዊ ተቋሞችን የፖለቲካ ስልጣን መጠቀሚያ
አድርጓቸዋል። የመንፈሳዊ አባቶች እርስ በርሳቸው ጠላትነት ሲፈጥሩና ምእመናንን ጎጠኛና መንደረኛ ሲያደርጉ የሞራል ድክመት የት
እንደደረሰ ለመገንዘብ ቀላል ነው። በተመስገን ደሳለኝ አባባል፤ “ኢህአዴግ ያለፉትን ሁለት አስርታት ያለመንገራገጭ ማለፍ የቻለው
በጠብ-መንጃ፤ እንደ አሸን በፈሉ ሰላዮች፤ እንዲሁም ከሊቅ እስከ ደቂቅ፤ ከኃይማኖታዊ እስከ ዓለማዊ ማሕበራት ውስጥ በዘረጋው
የካድሬ ጥርነፋ ብቻ ሳይሆን፤ ለርእዩተ ዓለሙ ሳጋና-ማገር ያደረገው የሃገሪቱን ታሪክ ከልሶ፤ ደልዞ እና ፈጠራ አክሎበት በመስበክም
ጭምር መሆኑ በግላጭ የሚታይ እውነት ነው።” ለመጨመር የምፈልገው ህወሓት ሆነ ብሎ ሥስታምነትን እንደመመሪያ መፍጠሩን፤
እኛ በኢትዮጵያዊነታችን ሳይሆን በጎሳዎቻችን እንድናምንና በተናጥል እንድንታገል ማድረጉን ነው። ወደማይፈለገው ዝቅተኛ የትግል
መሰብሰቢያ ደረጃ ወስዶናል ማለት ነው። የእኛ ሰብሳቢ መመሪያ ጎሰኛነት ከሆነ ከምንቃወመው ከህወሓት ዓመራር የሚለየን ምን
እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም። በጎሰኛነት ፖለቲካ ወጥመድ ተይዞ የጎሰኛነት አገዛዝ ይውደም ሲባል አማራጩ ምን አይነት ስርዓት
እንደሚሆን ለማወቅ ልዩ ጥበበኛ መሆን ያስፈልግ ይመስለኛል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሰብአዊ መብትና ክብር አለው። ይህ መብት
አማራ፤ አፋር፤ ጉራጌ፤ ወላይታ፤ ኦሮም፤ ሶማሌ፤ አኟክ ወዘተ አይለይም። ካልለየ፤ አግባብና የሚያዋጣው፤ የዓለምና የኢትዮጵያ ሕዝብ
የሚቀበለው የትግል መንገድ በኢትዮጵያዊነታችን በአንድ ላይ ለፍትፍ-ርትአ፤ ለእውነተኛ እኩልነት፤ ለዲሞክራሲ በጋራ መታገል ብቻ
ነው። ይኼን ካላደረግን በራሳችንና እነወክለዋለን በምንለው ሕዝብ ላይ ፈረድን ማለት ነው። በቅርቡ የኦባማ መንግሥት ለአንድ
የታወቀ ኢትዮጵያዊ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የነገረው፤ “እናንት ኢትዮጵያን በአንድ ላይ፤ በአንድ ድምፅ ለመናገር እስካልቻላችሁ ድረስ
አዳማጭ የላችሁም” ነው። ይኼን መሳይ መልእክት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከአሜሪካ፤ ከካናዳ፤ ከአውሮፓ የጋራ ማህበር ወዘተ
ሰምተናል። እኛ ህወሓትን እንወቅሳለን እንጂ ችግሩም፤ መፍትሄውም በእኛው እጅ ነው።
የህወሓት ዓመራር ከፋፋይ ብቻ ሳይሆን የማባበል ችሎታ ያለው ነው። በቁሳቁስ ማባበል ታማኝነት የሚገዛ መሆኑን ስላወቀ፤
ስደተኛውን ጭምር አባብሎ የከተማ መሬት ፈቃድ ሰጥቶ ኪራይ ይሰበስባል። ገንዘብ ያለውን ስደተኛ በከተማ መሬት ብቻ ሳይሆን፤
በንግድና በቤት ግንባታ ፈቃድ አባብሎ ደጋፊው አድርጓል። የኢትዮጵያ እድገት አድናቂ ከሆኑት ተመልካቾች መካከል ስደተኛው
የመጀመሪያውን ደረጃ ይዟል። ከአገሪቱና ከአብዛኛው ወጣት ትውልድ ደህንነትና ውርደት የበለጠ የራሱና የቤተሰቡ ኑሮ መሻሻል
ይገዛዋል። ህወሓት ሰላዮችን በተቃዋሚው ስብስቦች ሰርጎ የማስገባት ችሎታ አለው። በውጭ አገሮች በሰላማዊ ሰልፎች፤ በፓልቶኮች፤
በመገናኛ ብዙሃን፤ በቤተክርስትያን፤ በመስጊድ ወዘተ ቀድመው ህወሓትን የሚያወግዙ የህወሓት ሰላዮች መሆናቸውን ብዙ ታዛቢዎች
ያውቃሉ። ሆኖም መንጥረው ለማጋለጥ አልቻሉም። ሌላው ቀርቶ የራሳችን ስብስቦች ለመቆጣጠር አለመቻላችን የሚያሳየው
የዲስፕሊን ጉድለትን ጭምር ነው። ተቃዋሚዎች ለዚህ ሰርጎ ገብነት መፍትሄ ማግኘት አለባቸው። ህወሓትን የሚደግፈው ክፍል
ከአምስት በመቶ በላይ የሚሆን አይመስለኝም። ዘጠና አምስት በመቶ የሚሆነው የት ሔደ???
የተወሰኑ ስግብግቦችንና የጥቅም ሰዎችን፤ በተለይ ወጣቶችን፤ ማባበልና መግዛት እስከተወሰነ ደረጃና ወቅት ያገለግላል። በተመሳሳይ፤
እሰከተወሰነ ጊዜ ወጣቱን ትውልድ ሰላይ ማድረግ ሕብረተሰቡን ለመከፋፈልና ለማሳፈራራት ይረዳል። ሆኖም፤ ሁሉም ወጣቶች
ሰላይ፤ ካድሬና ሃብታም ሊሆኑ አይችሉም፤ አይደሉም። የዛሬ ሰላዮች የነገ የህብረተሰብ ወገኖች የማይሆኑበት ሕግ የለም። ሁሉም
ወጣቶች የኢትዮጵያን እውነተኛ ታሪክ፤ የብሄር/ብሄረሰቦችን ታሪክ የመዘገበው ትሥስር አያውቁም ለማለት አንችልም። እውቀትን
የሚፈልግ ወጣት የሃገሩን ታሪክ እንደማንም ፈልጎ ያውቃል። ህወሓት ወጣቱን ትውልድ የታሪክ ደንቆሮ አድርጎ ለመቆየት አይችልም።
ታሪክ ለመቅበር ዘላለማዊነት ያስፈልጋል። አገዛዝ ዘላለማዊ የሆነበት አገር የለም። መለወጡ አይቀርም። ከጎሳ በላይ በአንድነት
ለዲሞክራሳዊ ስርዓት መነሳት ቀስቃሽ እንደሚሆን አልጠራጠርም። የፖለቲካ ልሂቅን ሚናም ይኼው ይመስለኛል። ወጣቱ ትውልድ
ደንቆሮ አይደለም። ከፍርሃት ዓለም እየወጣ ነው። ለራሱ የወደፊት እድል እየተቆጨ እንደሚሄድ አምናለሁ። የሁሉም የፖለቲካ
ስብስቦች ልሂቃን ሃላፊነት ይኼ ትኩስ ወጣት ኃይል ገንቢና ሁሉን ኢትዮጵያውያን ወደሚያስተናግድ ዲሞክራሳዊ አማራጭ
እንዲያዘነብል ማበረታት ይመስለኛል። 7
ቤተክርስቲያን ወይንም መስጊድ የሚያዘወትር ወጣት ከፀሎቱ ባሻገር ስለ እምነቱ ለማወቅ ይጣጣራል፤ እውቀቱ እየጠነከረ ይሄዳል።
እውቀት እንደ ተስቦ በሽታ ነው። አንዱ ወደ ሌላው ይመራል፤ ይዛመታል። በማውቀው ልቆጠብና ስለታቦት ምንንነት ባጭሩ ላቅርብ።
የታወቀው የኢትዮ-ኢዝራኤል የቆየ ግንኙነት ደራሲ “The Sign and the Seal—the quest for the Ark of the Covenant,”
ግራሃም ሃንኮክ የኢትዮጵያን ጥንታዊትነት፤ የክርስትና ኃይማኖት ጥንታዊ መንስኤ መሆንና የእስልምናን ኃይማኖት ማስተናገድ፤
የኢትዮጵያንና የኢዝራኤልን ግንኙነት ጥንታዊነት፤ የዓባይን ማእከላዊነት በማስረጃ አቅርቦታል። ቁም ነገሩ ኢትዮጵያ ጥንታዊ መሆኗን
ሲጠቅስ እንዲህ ብሏል። “ብሉይ ኪዳንም ሆነ አዲስ ኪዳንን ያስተናገደች ኢትዮጵያ ለአይሁዶች ሁለተኛ አገርና መጠጊያ” እንደነበረች
ነው። የኢዝራኤላውያን አባትና መሪ የነበረው ሙሴ “ኢትዮጵያዊት ሚስት አግብቶ በኢትዮጵያ መኖሩን አረጋግጧል። ከክርስቶስ በፊት በ
470 ዓም (የጣና ማርቆስ አባቶች በፃፉት መሰረት) የኢስራኤሎች መታወቂያ የሆነው “ታቦት/ጽላት ሙሴ” (Ark) ከኢየሩሳሌም ወጥቶ
ኢትዮጵያ እንደገባ ሃንኮክ ተዘዋውሮ ባገኘው መረጃ አረጋግጧል ይላል። ከዚህ የተማርኩት ትችት፤ በመፅሃፍ ቅዱስ፤ በኮራን፤ በጥናትና
በልምድ የተገኘ ሂደት በማያሻማ ሁኔታ የሚያረጋግጠው የኢትዮጵያን ታሪክ ተከታታይነትና የዓባይን ኢትዮጵያዊነት መሆኑን ነው።
የኢትዮጵያ ተከታታይነት ሲባል አንድ ወጥ፤ ላይና ታች የሌለበትና የረጋ ሕብረተሰብ ማለት አይደለም። ኢስራኤላውያን ለሁለት ሽህ
ዓመታት ተበታትነው ነበር። ተስፋ ሳይቆርጡ ታግለውና በምእራብ አገሮች ተደግፈው አዲሲቱን ኢስራኤል መስርተዋል። ኢትዮጵያ
ጥንታዊ ብትሆንም አንድ ወጥ (homogeneous) ሕዝብ የላትም። አስደናቂ አገር አድርጎ የሚለያት ይኼ የሕብና የእመነት ስርጭት
ጭምር ነው። የኢትዮጵያ የሕዝብ ስርጭት፤ የባህል፤ የንግድ፤ የመንፈሳዊ፤ የጆግራፊና ሌሎች ግንኙነቶችን ያሳያል። የኦሮሞ ሕዝብ
የማህል አገሩን አቋርጦ ወደ ምእራብ፤ ወደ ሰመኔንና ወደ ምስራቅ እንደተስፋፋ ታሪክ ያስተምረናል። የትግራይ ሕዝብ ከአክሱም በኋላ
በመላው ኢትዮጵያ ተስራጭቷል። አማራውም እንደዚሁ። ማንኛውም ስብጥር ሕዝብ ከአንዱ ወደሌላው ክፍል ሲሄድ በአዲሱ ቦታ ካሉ
ሕዝቦች ጋር ይቀላቀላል። እኛ ስደተኞች ተሰደን እንደ ደሴት ለብቻችን አንኖርም። እንቀላቀላለን፤ መብት አለን። ጥልቀት ጥናት ያካሄዱ
ባለሞያዎች የሚያስተምሩን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደዛሬው “በክልል ከዚህ ወዲያ አታልፉም” ያላቸው እንዳልነበረ ነው።
ከህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት በፊት ኢትዮጵያውያን እንደፈለጉት በማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የመኖር መብት ነበራቸው።
“እትዮጵያ ሃገሬ ናት፤ ዜግነቴ ኢትዮጵያዊ ነው” ይሉ ነበር ማለት ነው። የሃሳብ፤ የፖለቲካና የእምነት ልሂቃን ይኼን የሕዝብ ትሥስር
ለወጣቱ ትውልድ ማስተማር ግዴታችን ነው። እኛ ከማናውቀው ሕዝብ ጋር ለመኖር ከቻልን፤ ከምናውቃቸው ወገኖቻችን ጋር ለመኖር
እንችላለን የሚል እምነት አለኝ። ይኼን ፈረንጆች እስከሚነግሩን መቆየት አሳፋሪ ሆኖ አገኘዋለሁ።
አባይ የሁሉም ኢትዮጵያውያን መመኪያና መጠቀሚያ መሆን አለበት የምለው ከዚህ የታሪክ ሂደት በመነሳት ጭምር ነው። እስራኤሎች
ኢትዮጵያ የልዩ ልዩ ብሄር/ብሄረሰቦችና ኃይማኖቶች አገር መሆኗን ይቀበላሉ። ጥናቶች የሚያሳዩት አብዛኛዎቹ እስራኤሎች ኢትዮጵያ
ዓባይን የመጠቀም መብት እንዳላት ያምናሉ። ስለሆነም፤ አንዳንድ ተመልካቾች ኢትዮጵያን የሚጠቅማት ከእስራኤል ጋር ያላትን
ተከታታይ ግንኙነት ማጠናከር ነው ይላሉ። ይኼን ብንቀበል፤ ባንቀበል ኢስራኤል እንደሌሎች አገሮች ለማስከበር የምትፈልገው የራሷን
ደህንነትና ጥቅም መሆኑን መርሳት የለብንም። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን መመካት ያለባቸው በራሳቸው ላይ ነው። ከተከፋፈሉ
አይችሉም። ከሁሉም በላይ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚጠቅመው ጎዳና የአሁኑ አፋኝና ክልላዊ (አግላይ) ስርዓት ሕዝብን በሚወክል፤
በሕግ የበላይነት በሚያምን፤ የሕዝብ ተሳትፎና እኩልነት በሚቀበል፤ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥቅምና አገልግሎችት ሙሉ በሙሉ
የሚቆም ዲሞክራሳዊ ስርዓት ሲተካ ብቻ ነው። የፈለገው የውጭ እርዳታና ድጋፍ ቢገኝ፤ የፈለገው በያመቱ እጥፍ እድገት አለ ቢባል፤
የፈለገው ዲያስፖራ ቤት ቢሰራና የውጭ ምንዛሬ ቢልክ (አብዛኛው ውጭ ባንኮች ይቀራል) የሕብረተሰብን መተባብር፤ ጥንክርናና
የተፈጥሮ ሃብት ባለቤትነት ሊተካ አይችልም። በራስ መተማመን ወሳኝ ነው። በራስ ለመተማመን የትምሕርት አቀራረፅና አመራር ወሳኝ
መሆኑን በክፍል ሁለት አሳይቻለሁ። ፖለቲካዊ ትምሕርት በራስ መተማመንን ተቀዳሚ አያደርግም። ጥገኛነትን ያጠናክራል። የእስራኤል
ጥንክርና ከህብረተሰቡ አንድነትና ራስን የመቻል ጥረት ጋር የተቆራኘ ነው። እስራኤል በአረቦች የተከበበች አገር ብትሆንም፤ የራሷ
ጥንካሬና የምእራብ አገሮች ድጋፍ የማትደፈር አገር አድርጓታል። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን እንደ እስራኤልና ኢስራኤላውያን
አይደሉም። አስተማማኝ የሆነ የሚመኩበት አገር የለም። ባለፈው ታሪካቸው እንዳሳዩት ሁሉ በራሳቸው መመካት አስፈላጊ
ይመስለኛል። ታሪክን መቀበል ወሳኝ የሚሆነው ለዚህ ጭምር ነው።
አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን ዝቅ አድርገው በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ተከታታይ የሆነ፤ ለህብረ-ብሄር ግንኙነት መሰረት የሚሆን
ሂደት አልነበረም ሲሉ የሚያንፀባርቁት የውጭ አገር ሊቃውንትንና የጎሰኛውን ህወሓት እሴት ነው። “የጥቁር አቴና” ደራሲው በርናል
“የግብፅ ስልጣኔ የአባይ ወንዝ ውጤት ብቻ አይደለም…..የኢትዮጵያውያንና የሌሎች ጥቁር አፍሪካውያን በረከት ጭምር መሆኑ በባህል፤
በኢኮኖሚ፤ በግዙፍ ስራዎች ወዘተ ይታያል” ብሏላ። ኢትዮጵያ ግብፅን ገዝታ ነበር። ኢትዮጵያ ከግብፅ ያላነሰ ታሪክና ስልጣኔ አላት።
ለግብፅ አበርክታለች። በአይኔ ያየሁት፤ አስዋን ግድብ ላይ የተሰራው ታላቅ ሙዚየም የጥቁር ሕዝቦች አስተዋፆ እንዳለበት ምስክር ነው።
ይኼን ሃቅ በጥናት ተደግፎ ያሰመረው በርናል እንዲህ ብሏል። “የአውሮፓውያንና የአረቦች ዘረኛነት መሰረታዊ ዓላማ እንዳለው
አያከራክርም…. አንድ አፍሪካዊ (ኢትዮጵያዊ) ንጉሥ ወታደሩን ከኢትዮጵያ ይዞ ወደ ግብፅ፤ ወደ መካከለኛው ምስራቅ (Asia Minor)
እና በግብፅና በመከካለኛው ምስራቅ አድርጎ ወደ አውሮፓ መሄዱ እየታወቀ ይኼን ታሪክ የመዘገበውን የጥቁር አፍሪካ አስተዋጾ ሃቅ
እንደሌለ ማቅረባቸው ለህሊናው ለሚገዛ ሰው የሚታሰብ ሆኖ አላገኘውም።” እርሱ አልተቀበለውም። እነዚህና ሌሎች አስተዋፆዎች
የኢትዮጵያ ታላቅነት መስታወቶች ናቸው። የታሪክ ታላቅነት ያለው አገርና ህብረተሰብ ራሱን አድሶ የዘመናዊ ኢኮኖሚ መስርቶ ታላቅ 8
ማህበረሰብና ታላቅ አገር ለመገንባት እንደሚችል ምንም አልጠራጠርም። ይችላል። ቻይናዎች እያደረጉት ነው። ጃፓኒዎችና ኮሪያኖች
አድርገውታል ወዘተ። የኢትዮጵያ የትምሕርት ሂደት ለራሴና ለተከታታይ ትውልድ የራሳችን የሚኮራ ታሪክ፤ ባህልና ልምዶች እንድናውቅ
አላደረገም። ህወሓት ፈጽሞ አውድሞታል። ግብጾች በፖለቲካ ቢለያዩም የግብፅን ታሪክ፤ የግብፅን “የዓባይ ባለቤትነት፤ ማለትም
ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብት)፤ የጥቁር አፍሪካን ኋላ ቀርነት ለተከታታይ ትውልድ አስተምረዋል። አሁንም ያምኑበታል። ያስተምራሉ።
ትምሕርት ለሕዝብ መተዋወቅና ግንኙነት ወሳኝ ነው። ለዚህ ነው ማንኛውም አገር በአብዛኛው ወሳኝ የሆኑ የትምሕርት ግብአቶችን
ብሄራዊ የሚያደርጉት። የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ የሕዝብ መቆራኘት ወሳኝነት አያምንም። ወጣቱን ትውልድ የሚያስተምረው ወደ
“ጎሳው ገብቶ” የጥላቻ ቀንበር እንዲሸከም ነው። በነጻነት የምንኖርና ነጻነትንና ፍትህን የምንፈልግ ሁሉ፤ “ኢትዮጵያ ሃገሬ ናት፤ ዜግነቴ
ኢትዮጵያዊ ነው” ለማለት እስካልደፈርንና አብረን እስካልተሰለፍን ድረስ በአምባገነናዊ አገዛዝ አዙሪኝ እንደምንሺከረከር ማጤን
አስፈላጊ ነው። ስርዓቱ የፈጠረውን የብሄር/ብሄረሰብ መለያዎች አወቃቀርና መፈክሮች አንግበን ዲሞክራሳዊ ስርዓት ለመመስረት
አንችልም። በልዩነተቻችን እስከተሰበሰን ድረስ ተጠቃሚው የህወሓት “ስልጣን ወይም ሞት” አርማና የአገዛዝ ስልት ሆኖ እንደሚቆይ
አያከራክርም። የዓባይ ግድብ መሪ ተጠቃሚ የሚሆነው ይኼው ቡድን ይሆናል ማለት ነው።
ማጠቃለያ
ኢትዮጵያ የዓባይን የተፈጥሮ ሃብቷን ለራሷ ሕዝብ ኑሮ ለመሻሻልና ድህነትን ለመቀነስ፤ የዘመናዊ ኢንዱስትሪን ለማስፋፋትና የምግብ
ዋስትናን ስኬታማ ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት መደገፍ አግባብ እንዳለው በተከታታይ አሳስቢያለሁ። ይኼን ተከታታይ የኢትዮጵያ
መንግሥታት ስኬታማ ለማድረግ የሞከሩትን ግዙፍ የሆነውን የዓባይን የዘመናዊነት ልማት ፖሊሲ የግብፅ መንግሥትና ተባባሪዎች
እንዳይሳካ ለማድረግ እንደሚሞክሩ ይጠበቃል። በታሪኩ ደጋግሞ እንዳሳየው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ መብቱ ተከብሮ በአንድ ላይ የጋራ
ጥማድረግ የሞከሩትን ግዙፍ የሆነውን የዓባይን የዘመናዊነት ልማት ፖሊሲ የግብፅ መንግሥትና ተባባሪዎች
እንዳይሳካ ለማድረግ እንደሚሞክሩ ይጠበቃል። በታሪኩ ደጋግሞ እንዳሳየው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ መብቱ ተከብሮ በአንድ ላይ የጋራ
ጥቅሙን ለማስከበር ከተነሳ ምንም ኃይል ሊያቆመውና ሊገታው እንደማይችል እምነት አለኝ። ይህ ሃሳብ መንታ መንገድ ነው ብየ
ከጀመርኩት ሁለተኛ ዘርፍ ይወስደኛል። ይኼም የስርዓቱ ጎሳ-ተከል ከፋፋይነት ጉዳትና፤ የዲሞክራሳዊ ስርዓት አስፈላጊነት ዓላም
የአመራር ክፍተት ነው።
ባለፉት ሃያ ሶስት ዓመታት ህወሓት በበላይነት ለመግዛት የቻለው “ለጭቁን ሕዝቦች” ፍትህ ስለቆመና በድርጊት ጥቅሞችን ስላሳየ
አይመስለኝም። እኛ ስለተከፋፈልን ነው። መንግሥት፤ በልማት ስም፤ የጋምቤላን፤ የኦሞ ሸለቆን፤ የኦሮሞን፤ የአፋርን ወዘተ ሕዝብ
ከመሬቱ እያባረረና እየጨፈጨፈ ለጭቁኖች ቁሜአለሁ ለማለት የማይችል መሆኑን ማስረጃዎች ተጠቅመን በአንድ ድምፅ ለማጋለጥና
ድምፃችን ለማሰማት አልቻልነም። የኦሮሞን ወጣት እየጨፈጨፈ ለጭቁኖች መብት ለመቆም አትችልም ብለን በአንድ ላይ ለማውገዝ
አልቻልነም። የአማራን ድሃ ገበሬ ሕዝብ ከቤቱና ከመሬቱ በቀጥታም ሆነ በተወካዮች አማካይነት እያባረረ፤ አማራውን በገደል
እየወረወረና እየረሸነ፤ የምትኖርበት “ክልልህ አይደለም” ሲል በአንድ ላይ ሆነን እነዚህ ወገኖችህ ናቸው ለማለት አልቻልነም።
የትግራይን ሕዝብ ዲሞክራሳዊ መብት እያፈነ ለዲሞክራሲ ቁሜአለሁ ሲል በአንድ ላይ ሆነን መብታቸውን በመደገፍ ድምጻችን
አላሰማነም። የአፋር፤ የቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ፤ የኦሞ ሸለቆ፤ የኦጋዴን፤ የኦሮሚያ፤ የጋምቤላ ሕዝብ የተፈጥሮ ኃብት ለውጭና ለምርጥ
የውስጥ ለኢንቬስተሮች ሲቸረቸርና ነዋሪዎች ከቀያቸው ሲባረሩ በአንድ ድምፅ መብታቸው ይከበር አላልነም። የዓባይ ግድብ መገንባት
የኢትዮጵያ መብት መሆኑን ተቀብለን በአንድ ድምፅ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ የሚፈልገው ግድቡን ብቻ አይደለም። በተመሳሳይ
ሳይሆን፤ በመጀመሪያ ደረጃ ሕዝቡ የሚፈልገው፤ ሰብአዊ መብቱ መከበሩን ነው። ተቀዳሚውና ዋናው የሕዝብ ጥያቄ ይኼው ነው
እያልን አልተሟገትነም። የአሜሪካ መንግሥትና ሌሎች እርዳታ አበርካቾች የሚከተሉት ፖሊሲ ከቀጠለ “ከሁሉም ያጣ ጎመን”
እንደሚሆኑ በጥናትና ምርምር ተደግፈን በአንድ ድምፅ አቤቱታችን ለማሰማት አልቻልነም። ለአምባገነናዊው ህወሓት እርዳታ ሰጥቶ
ለሰብአዊ መብቶች መገፈፍ አጋር መሆን እርጋታን ለማረጋገጥና ከሽብርተኛነት ነጻ የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር አያስችልም
የምንልበት ወቅት አሁን ነው። የሚያዋጣው ሁሉን አቀፍ፤ ፍትሃዊና ዲሞክራሳዊ ስርዓት እንዲፈጠር መደገፍ ነው ብለን በመተባበር
ከተነሳን አዳማጭ እንደምናገኝ አልጠራጠርም።
ባጭሩ፤ ዓባይን ለመታደግ፤ የግድቡን ፍሬ ለመካፈልና ስርዓቱን ለመለወጥ ከተፈለገ፤ በጎሳ፤ በኃይማኖት፤ በሃብት፤ በስልጣን ወዘተ
መከፋፈላችን ለምንፈልገው ዓላማ ማነቆ መሆኑን መቀበል አለብን። ስለሆነም፤ ግብፆችን “ኢትዮጵያን አትንኩ” ብለን ህወሓትን አፋኝ
አገዛዝክን ቀጥል ማለት ሃላፊነት የጎደለው ትችት ነው። “ሕዝብን እየከፋፈለህ የምትጨፈጭፍበት ወቅት ያቁም፤ መከፋፈልን
አንቀበልም” ብለን በአንድ ላይ ለሁሉም ኢትዮጱያውያን ፍትህ፤ ሰብአዊ መብት፤ ዲሞክራሳዊ መንግሥት የምንታገልበት ወቅት አሁን
ነው እላለሁ። በተናጥል ታግለን የትም አንደርስም። የግብፅ መንግሥትና ህወሓት የሚፈልጉት የእኛን በጎሳ፤ በኃይማኖትና በስልጣን
መከፋፈል፤ የእኛን እልቂት መሆኑን በተደጋጋሚ ለማሳየት ሞክሬያለሁ።
ይቀጥላል
No comments:
Post a Comment