ግንቦት ፳፪(ሃያ ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከቀናት በፊት ከትምህርት ገበታው ታፍኖ ተወስዶ የነበረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 1ኛ አመት ተማሪ እና የአንድነት ፓርቲ አባል የሆነው መልካሙ አምባቸው በማእከላዊ ወንጀል ምርመራ መታሰሩ ታወቀ።
በጎንደር ምዕራብ አርማጨሆ ነዋሪ የሆነውና በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 6 ኪሎ የአካውንቲግ 1ኛ ዓመት ተማሪ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአንድነት መዋቅር ስራአስፈጻሚ አባል የሆነው ወጣት መልካሙ አምባቸው ሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2006 ዓ.ም ማታ ራት ከበላ በኋላ ከዩኒቨርስቲ ግቢ ባልታወቁ ኃይሎች ታፍኖ ተወስዷል።
ወጣት መልካሙ የአካባቢው ነዋሪ እንደመሆኑ መጠን በጎንደር ስለ ሚደረገው የድንበር ማካለል የሚያውቀውን መረጃ በመስጠቱ በመንግስ ሀይሎች ክትትል ይደረግበት እና አንዳንዴም ማስፈራሪያ ይሰነዘርበት እንደነበር ለፍኖተ ነፃነት በተደጋጋሚ ይገልጽ ነበር።
ተማሪ መልካሙ ሰሞኑን ከዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ታፍኖ የተወሰደው ከድንበር ማካለሉ ጋር በሰጠው መረጃ እንደሆነ በቦታው የነበሩ የዓይን ምስክሮች ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ቀናት አንድነትፓርቲ ወጣት መልካሙ ያለበትን ሁኔታ ለማጣራት በዩኒቨርስቲው አካባቢ ወደ ሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች ተወካዮችን በመላክ ጥረት ቢያደርግም፤የሚገኝበት ቦታ እና ሁኔታ ሊታወቅ አለመቻሉን መግለጹ ይታወሳል።
መልካሙን የሚያወቁት አብሮ አድጎቹ በሰጡት አስተያየት ከ 2001 አመተ ምህረት ጀምሮ ማለትም ገና በልጅነት እድሜው የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል በማለት የመኢአድ አባል ሆኖ መታገል እንደጀመረ ጠቅሰው፤ ሆኖም ላለፉት አመታት በደረሰበት ተደጋጋሚ እስር እና ድብደባ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለሁለት ዓመታት ለማቁዋረጥ ተገዶ እንደነበር አውስተዋል።
ታስሮ ሳለ የ 50 ሺህ ብር ዋስትና ሲጠየቅ የሚከፍለው በማጣቱ የ አካባቢው ህብረተስብ አዋጥቶ በመክፈል ከ እስር እንዳስፈታው የገለጹት አብሮ አደጎቹ፤ በስንት ስቃይና መከራ ውስጥ አልፎ ትምህርቱን ጨርሶ ወደ ዩኒቨርሲቲ በገባበት ዐመት እንደገና ለተመሳሳይ መከራ መዳረጉ እንዳሳሰኛቸው ተናግረዋል።
Source: Ethsat
Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of various information and content providers. The Website neither represents nor endorses the accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors.
No comments:
Post a Comment