sourse abugida
የአንድነት ፓርቲ የአዲስ አበባ ስራ አስፈጻሚ አባልና የወጣቶች ጉዳይ ሰብሳቢ አቶ ስንታየሁ ቸኮል ትናንት ለምሳ ወደ መኖሪያ ቤቱ ሲያቀና ማንነታቸውን ባልለያቸው ሰዎች በድንጋይ መፈንከቱ ታውቋል፡፡ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ኳስ ሜዳ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ከቀኑ 8፡00 እንደደረሰ ሁለት ሰዎች ወደ እርሱ በመቅረብ ምንም ሳያነጋግሩት በድንጋይ ፈንክተውት መሰወራቸውን አቶ ስንታየሁ ለፍኖተ ነፃነት አስረድቷል፡፡ በድንጋይ ከተፈነከተ በኋላ ለደቂቃዎች ራሱን ስቶ የወደቀው አቶ ስንታየሁ በሰዎች እገዛ ህክምና አግኝቶ በአሁኑ ሰዓት በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛል፡፡ አንድነት ፓርቲ ‹‹የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት››የሚለውን ህዝባዊ ንቅናቄ መጀመሩን ተከትሎ አቶ ስንታየሁ ታላቅ አስተዋጽኦ ሲያበረክት ቆይቷል፡፡ፓርቲው በመስከረም 19 እና ሚያዚያ 26/2006 አዲስ አበባ ላይ ባደረጋቸው ሰላማዊ ሰልፎች ስንታየሁ እጆቹን በካቴና አስሮ በእስር ቤት የሚገኙትን የህሊና እና የፖለቲካ እስረኞች ትኩረት እንዲያገኙ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ በቅርቡ አንድነት ላደረገው ሰላማዊ ሰልፍ የቅስቀሳ ስራ ለመስራት ስንታየሁ ከሌሎች የፓርቲው አባላት ጋር ሲንቀሳቀስ በፖሊስ ተይዞ በህገ ወጥ መንገድ ታስሮ መለቀቁም አይዘነጋም፡፡
No comments:
Post a Comment