የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ በጋዜጠኞች እና ብሎገሮች ላይ የፈፀመውን እስር ተከትሎ የኢቦኒ መፅሔት መስራች እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር የነበረው ጋዜጠኛ ተሰማ ደሳለኝ ሀገር ጥሎ ተሰደደ፡፡ ጋዜጠኛው በሀገሪቱ ያለው የፕሬስ ነፃነት አፈና ተጠናክሮ በመቀጠሉ እና መንግስት ሊወስደው ያሰበውን እርምጃ በመሸሽ እንደተሰደደ ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ዛሚ ኤፍ ኤም፣ እና በሌሎች የኢህአዴግ ደጋፊ ናቸው በሚባሉ እንደነ አይጋ ፎረም እና ሆርን አፌይርስ የመሳሰሉ ድህረ-ገሮች የተለያዩ ጋዜጠኞች እና የኢትዮጵያ ዞን 9 ብሎገሮች እንዲታሰሩ እና እንደሚታሰሩ ፍንጭ መስጠታቸው ለስደቱ ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ከመጪው ምርጫ 2007 ዓ.ም. በፊት የመንግስትን ብልሹ አሰራር እና ኢሰብዓዊ ድርጊት በመኮነን ያጋልጣሉ የተባሉ የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች እና ብሎገሮች እንደሚታሰሩ በተለያየ ጊዜ የተነገረ ቢሆንም፤ በቅርቡ 3 ጋዜጠኞች እና 6 ብሎገሮች መታሰራቸው ይታወቃል፡፡ በመንግስት የተወሰደው የጋዜጠኞች እና ብሎገሮች እስር ተከትሎ ሌሎችም ሊታሰሩ እንደሚችሉ በተዘዋዋሪ መንገድ መገለፁን ተከትሎ ከጋዜጠኛ ተሰማ ደሳለኝ በፊት ጋዜጠኛ በትረ ያዕቆብ እና ፍስሃ ያዜን ጨምሮ አራት ጋዜጠኞች መሰደዳቸው ታውቋል፡፡ ጋዜጠኞቹ ከሀገር ጥለው መሰደዳቸው በስተቀር እስካሁን ያሉበትን ሁኔታ ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የእንቁ መፅሔት ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ከስራው ጋር በተያያዘ በእንቁ መፅሔት በተፃፈ ፅሑፍ ከማዕከላዊ ቃሉን እንዲሰጥ በስልክ በተደረገለት ጥሪ ትናንት ሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2006 ዓ.ም. ወደስፍራው ቢያቀናም ማረፊያው እዛው ማዕከላዊ እስር ቤት ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬ በዋስ ይለቀቃል ተብሎ ቢጠበቅም እስር ቤቱ ፍርድ ቤት አቅርቦት የዋስ መብት ሳይከበርለት ለተጨማሪ 7 ቀናት እዛው ማዕከላዊ ታስሮ እንዲቆይ ተጠይቆበት በእስር ላይ ይገኛል፡፡
No comments:
Post a Comment