ዛሬ በአዲስ አበባ ታትሞ ከወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ
ዶ/ር ሞጋ ፉሪሳ ይባላሉ። የፊትውራሪ ፉሪሳ ልጅ ናቸው። አያታቸው በአድዋው ጦርነት ከተሰው ጀግኖች ኢትዮጵያውያን አንዱ እንደነበሩ ይናገራሉ። አባ ሞርቲ ይባላሉ፡ በጅማ የጎማ ጎሳ አመራር አንዱ እንደሆኑም ይገልፃሉ። ዶ/ር ሞጋ ፉሪሳ ከአሁኑ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከቀድሞ የጎንደር ጤና ሳይንስ የሕክምና ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በመቀጠልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሳይንስ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በመቀጠል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሜዲካል ዶክተር በመሆን ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። ላለፉት 45 ዓመታት ሀገራቸውን በሕክምና ሙያ ሲያገለግሉ ቆይተዋል። እስከቅርብ ጊዜ የቀዶ ጥገና አማካሪ በመሆን አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። ጎን ለጎን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) የአማካሪ ም/ቤት አባል ናቸው።
ሰሞኑን ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በክልሉ አንዳንድ ከተሞች ያጋጠሙ ችግሮችን በተመለከተ ባልደረባችን ዘሪሁን ሙሉጌታ አነጋግሯቸዋል።
ሰሞኑን ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በክልሉ አንዳንድ ከተሞች ያጋጠሙ ችግሮችን በተመለከተ ባልደረባችን ዘሪሁን ሙሉጌታ አነጋግሯቸዋል።
ሰንደቅ፡- ሰሞኑን የአዲስ አበባ የተቀናጀ የማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ የተከሰተውን ችግር በተመለከተ ምን አስተያየት አለዎት?
ዶ/ር ሞጋ፡- ስለወቅታዊው ሁኔታ ከመናገሬ በፊት ቀደም ሲል ስለነበረው ነገር ብናገር ደስ ይለኛል። የነገሩን ፍሬ ነገር ማጥራትም የሚገባ ይመስለኛል። ጉዳዩ ከተፀነሰ ቆይቷል። አሁን እርግዝናው ከፍ በማለቱ ያጋጠመ ችግር ነው። እንደምታስታውሰው የኦሮምያ ዋና ከተማ ፊንፊኔ ከተባለ በኋላ ወደ አዳማ ሲዛወር ተቃውሞ ቀረበ። በዛን ጊዜ ሜጫና ቱለማ ሆነን ስንቃወም በተመሳሳይ ከ350 ያላነሱ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ተባረሩ። ልጆቹ ከትምህርታቸው በመባረራቸው በሽማግሌ ችግሩን ለመጨረስ በወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ለነበረው ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ አቤቱታ አቀረብን። እሱም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን አነጋግሬ እመልስላችኋለሁ ብሎ መልስ ስላልሰጠን መልሰን በቀጥታ ለአቶ መለስ ዜናዊ ደብዳቤ ፃፍን። በመጨረሻም ነገሩ ሊሳካ አልቻለም። እኛም በዚህ ቁጭት ተነሳስተን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) የሚባል ፓርቲ መሰረትን። እንግዲህ ያው ችግር ሽል ሆኖ ተፀነሰ፤ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
ሰንደቅ፡- ቀደም ሲል የነበረው ተቃውሞ ፊንፊኔ ወይም አዲስ አበባ የኦሮምያ ትሁን የሚል ነበር፤ አሁን ደግሞ አዲስ አበባ ወደ ኦሮምያ መስፋፋት የለባትም የሚለው ተቃውሞ እርስ በርሱ አይጋጭም?
ዶ/ር ሞጋ፡- ይህንንም ለማለት ከሕዝቡ ጋር መመካከር ያስፈልጋል። በማስተር ፕላን ስም መሆን የለበትም። እኛ መስፋፋቱን አልተቃወምነውም። በፕላን ሰበብ ግን ገበሬው እንዲፈናቀል ተደርጓል። ገበሬው የእርሻ መሬቱን እየተነጠቀ ድንጋይ ጠራቢ ሆኗል። ሰውን ሳያማክሩ መንቀሳቀሳቸው ብዙ ችግር እንዲያስከትል አድርጓል። መቼም ልማት አይጠላም። አዲስ አበባ በርካታ ክፍት ቦታ እያለም በዙሪያዋ የሚደረገው ልማት ምንድነው። ከአዲስ አበባ መሀል ቦታዎች ነዋሪዎች እየተፈናቀሉ በርካታ ቦታዎች ታጥረው እየተቀመጡ ነው። ይህንን ባዶ ቦታ ሳያለሙ ወደ ኦሮሞ ገጠር ቀበሌዎች መሄድ ያውም ሕዝብን ሳያማክሩ ተገቢ አይደለም። እስካሁንም የኦሮሞ ገበሬ ከቦታው እንዲነቀል ተደርጎ ሲሚንቶ ተሸካሚ፣ ለማኝ ተደርጓል። ኦሮሞ በባህሪው አራሽና ከብት አርቢ ማኅበረሰብ ነው። ከዚህ ቀደምም በአበባ ልማት እየተባለ በርካታ የኦሮሞ ገበሬ ባዶ እጁን እንዲቀር ተደርጓል። ስለዚህ ልማት ባይጠላም የኦሮሞን ገበሬ ጥቅምና መብት በማስጠበቅ ሊሆን ይገባል። እያፈናቀሉ ልማት ሳይሆን ጥፋት ነው የሚሆነውና መስተካከል አለበት። ልጆቹም (የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹ) መቃወማቸው ተገቢ ነው። ስለዚህ ሕዝቡ ሳይፈናቀል ልማቱ መካሄድ አለበት። ሕዝቡ ድንጋይ ተሸክሞ ከሚኖር የልማቱ አካል ማድረግ ያስፈልጋል።
ሰንደቅ፡- ማስተር ፕላኑን በመቃወም ሰበብ በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆችን ሕይወት፣ ሐብትና ንብረት የማውደም ሁኔታ እየታየ ነውና በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?
ዶ/ር ሞጋ፡- ይሄ ጉዳይ በጣም አጠራጣሪ ነው። ኦሮሞ ከጥንት መሰረቱ ከሌላ ኅብረተሰብ ጋር ተፋቅሮ የሚኖር ሕዝብ ነው። ኦሮሞ በባህሉ የማረከውን እንኳ የሚያሳድግ ቀና ሕዝብ ነው። ነገር ግን በተወላጁ (በኦሮሞው) ስም የሚነግዱ ጠባቦች አሉ። ይህንን ጉዳይ ካነሳን ዘንድ እኛ (ኦፌዴን) በነበርንበት ዘመን ከኦህዴድ አመራሮች ጋር በምስጢር እንገናኝ ነበር። አሁንም በአመራር ላይ ያሉ አሉ። እነ ጁነዲን ነበሩበት ጥለው ቢጠፉም። በምስጢር እየተገናኘን ከልማቱ የኦሮሞ ተወላጅ እንዴት መጠቀም እንዳለበት፣ በልማት ስም የኦሮሞ ገበሬ መሬቱን እየተነጠቀ ስለመሆኑ፣ ሕዝቡም በሕዝብ ቁጥር ከፍ ያለ በመሆኑ በፌዴራል ደረጃ የተሟላ ስልጣን እንዲያገኝ ከእነሱ ጋር እንመካከር ነበር። በመጨረሻ የሕወሓት አመራሮች ደርሰው ስብሰባው እንዲቋረጥ አድርገዋል። እና አሁን በክልሉ የሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆች ላይ ጥቃት የሚያደርሰው ሕዝቡ ሳይሆን የካድሬዎች ተግባር ነው። በኦሮሞ ባህል ሰው አይገፋም፣ ኦሮሞ የማረከውን ሁሉ ወተት አጠጥቶ እንደ ወገኑ የሚያኖር ሕዝብ ነው። በኦህዴድ ውሰጥ ያለው ተንኮል ካልሆነ በስተቀር ሕዝቡ የሰው ቤት አያቃጥልም፤ ንብረት አይዘርፍም። ለኦሮሞ ተቆርቁረናል እያሉ ሕዝቡን ወደሌላ አቅጣጫ የሚመሩት እነሱው ናቸው። እኔ ከኤርትራ ከረን ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ ኖሬያለሁ። እንደዚህ አይነት ነገር አልነበረም። አሁን የመጣ ነገር ነው። ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጨው የኦፒዲኦ ካድሬ ነው። እነዚህ ደግሞ ተላላኪዎች ናቸው። ለነፃነታቸው ሳይታገሉ የኦሮሞን ሕዝብ ከሌላ ኢትዮጵያዊ እንዲጋጭ የሚያደርጉ እነሱ ናቸው። ኦሮሞ በባህሉ ሰው ይወዳል፤ ድሮም አብረን ኖረናል አሁንም አብረን እንኖራለን።
ሰንደቅ፡- የኦሮሞ ሕዝብ የፖለቲካ ጥያቄ በምን መልኩ ነው ሊመለስ የሚችለው? አንዳንድ ወገኖች የመገንጠል ጥያቄ ሲያነሱ ይታያል?
ዶ/ር ሞጋ፡- መሆን ያለበት በሰጥቶ መቀበል መርህ በሰላማዊ መንገድ ተነጋግሮ የፖለቲካ ጥያቄውን መልክ ማስያዝ ይኖርብናል። ከተቻለ እንደነ ዴዝሞንቱቱ አይነት የሰላም አባት ያስፈልገናል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የፖለቲካ አለመግባባት የባልና የሚስት ጥል የቀለለ አይደለም እንዳሉት ቁጭ ብለን መነጋገር ያስፈልገናል። የኦሮሞ ሕዝብ በማንኛውም ሁኔታ ሌላ ጎሳ አይጠላም። የልማቱ አካል ሆኖ የሚገባውን ተካፍሎ እንዲኖር መነጋገር ያስፈልጋል። “እንገንጠል” የሚሉ አክራሪ ጠባቦች ናቸው። የኦሮሞንም ታሪክ ጠንቅቀው የማያውቁ ናቸው። ለምሳሌ የእኔ አባቴም ሆኑ አያቴ ለኢትዮጵያ የተሰው ጀግኖች አርበኞች ናቸው። ፊታውራሪ ፉሪሳ ከራስ እምሩ ጋር ጣሊያንን ሲዋጉ የወደቁ ናቸው። እና የኦሮሞ ሕዝብ ለኢትዮጵያዊነቱ ዋጋ የከፈለ ሕዝብ ነው። በእርግጥ በሁለቱም አቅጣጫ አክራሪዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እንገንጠል የሚሉትን ያህል በኢትዮጵያዊነታቸው ጠንካራ እምነት ያላቸው አሉ። ቁምነገሩ ግን ሕዝቡ ሰላም የሚፈልግ አርሦና ከብት አርብቶ የሚኖር፤ ከሰው ጋር ተስማምቶ የሚኖር ቀና ሕዝብ ነው። ስለዚህ ፖለቲካው ሊስተካከል የሚችለው አብረን ስንለማ ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍል እንዲኖር በማድረግ ነው። ኦሮሞ በኢትዮጵያዊነቱ ላይ ጥርጥር የሌለው ሕዝብ ነው። ሕዝቡ የኢትዮጵያ መሠረት ነው። አይገነጠልም፣ እንገንጠል የሚሉ ታሪክ የማያውቁ፣ ወይም ታሪክ የሚያዛቡ ግለሰቦች ናቸው።
ሰንደቅ፡- በአንዳንድ የኦሮምያ ወረዳዎች በምኒልክ ዘመን በደል ደርሷል በማለት ሐውልት መቆሙን የማይደግፉ ወገኖች አሉ። እርስዎ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?
ዶ/ር ሞጋ፡- በእኔ እምነት ሐውልት ማቆም የሚገባቸው እነዚህ ሰዎች [የኦህዴድ አመራሮች] አይደሉም። ኦህዴዶች ሐውልት የማቆም መብት የላቸውም። ሰዎቹ ምርኮኞች ናቸው። ምርኮኞች ስለሆኑም እነ ጀነራል ታደሰ ብሩን ከሜጫና ቱለማ ቢሮ ውስጥ ፎቶግራፋቸውን የረገጡ ግለሰቦች ስለሆኑ እኛን ወክለው ሐውልት ሊያቆሙ አይገባም። እኛ በሰላም መኖር ነው የምንፈልገው። ምኒልክም ሀገር አስጠብቆ አስረክቦናል። የእኔ አያትም በአድዋው ጦርነት ተካፍለዋል። አባ ሞርቲ ይባላሉ። ኃይለኛ ተዋጊና ለመንግስት ታማኝ ነበሩ። በጅማ ጎማ የታወቁ አምስቱ ጊቤዎች ከሚባሉ ታላላቅ የጎሳ አመራሮች አንዱ የነበሩ የአገሩ ጀግና ናቸው። አሁን ምኒልክ የኦሮሞን ሕዝብ በድሏል ተብሎ ሐውልት ከማቆም ይልቅ ለእነ አፄ ቴወድሮስ፣ እና ለእነ አፄ ዮሐንስ ሐውልት እንደቆመላቸው ሁሉ ለጀግናው ጀነራል ታደሰ ብሩ ሐውልት ማቆም በተገባቸው ነበር። እነ ጄነራል ታደሰ ብሩ በቅርብ የማውቃቸው ታላቅ ሰው ነበሩ ሌላ ጊዜ ስለሳቸው በስፋት ልነግርህ እችላለሁ።
ሰንደቅ፡- በኦሮሞነታቸው ላይ ለዘብተኛ አቋም የሚያራምዱ የኦሮሞ ተወላጆችን “ጎበና” በማለት የኦሮሞ ሕዝብን እንደካዱ አድርገው የሚፈርጁ ወገኖች አሉና ስለዚህ ጉዳይ እርስዎ ምን ይላሉ?
ዶ/ር ሞጋ፡- ጎበና ሀገርን ለፈረንጅ አልሸጠ፤ የግዛት ማቅናት ነው ያደረገው ጅማ አባጅፋርን አልነካ ጎበና የመንግስት አሽከር ቢሆንም፤ ለኢትዮጵያ የደከመ ሰው ነው። ከእነ ምኒልክ ጋር ሆኖ አገር ያሰባሰበ ነው። በዚያን ጊዜ ሰዎች ተጎድተው ሊሆን ይችላል። ዋናው ታሪኩን ለታሪክ ባለሙያዎች ትተን አሁን ስላለብን ችግር መነጋገር አለብን። በአግባቡ በገዳ ስርዓት እንዳንነጋገርም እነሱም በኦፒዲኦ ተፅዕኖ ስር ሆነዋል። ዋናውን ዓላማ እንዲስቱ አድርገዋቸዋል። በኦሮሞ ምድር ሌላ ሰው ችግር ላይ ሲወድቅ እውነተኛ የገዳ ስርዓት አራማጆች ቢኖሩ ችግሩ አይፈጥርም ነበር። በጉጂና በቦረና መካከል ጠብ እንዲፈጠር የቀሰቀሰው ማን እንደሆነ እናውቃለን። ወታደሩም ቢሆን የሀገር ድንበር መጠበቅ ሲገባው ከተማ ውስጥ ገብቶ ሰው መፍጀት የለበትም።
Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of various information and content providers. The Website neither represents nor endorses the accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors.
No comments:
Post a Comment