Tuesday, May 20, 2014

በዝዋይ ማረሚያ ቤት በፖለቲካ እስረኞች ላይ እየተወሰደ ያለውን ህገወጥ ድርጊት አጥብቀን እናወግዛለን!!! -ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሠጠ መግለጫ


May 20th, 2014

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የትንሳዔን በዓል ምክንያት በማድረግ በተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች እንዲሁም የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን በያሉበት እስር ቤቶች ፕሮግራም አውጥቶ በቡድን በቡድን በመሆን የእንኳን አደረሳችሁ መልእክቶችን ለማድረስ ችሎ ነበር፡፡ ከእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታችን በተጨማሪ ከፍተኛ አመራሩ አላማ ያሉበትን የአያያዝ ሁኔታ ለመረዳት ጭምር ነው፡፡
በዚህም መሰረት በተለይ በዝዋይ በፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈፀምባቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡ በዝዋይ ማረሚያ ቤት በሚገኙ የፖለቲካ እስረኞችን እና ጋዜጠኞችን ዝዋይ የተመደበው የልዑካን ቡድን ጎብኝቶ ከመጣበት እለት ጀምሮ ደግሞ በእስረኞቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ የአካል እንዲሁም የስነ ልቦና ችግሮች እየደረሱባቸው ይገኛል፡፡ ለዚህም የእስረኞች ቤተሰቦች ለጥየቃ በሚሄዱበት ጊዜ መጎብኘት እንደማይቻልና ይዘውት የሄዱትን ምግብ ይዘውት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡
እስረኞቹ የሚፈፀምባቸውን በደል ለማሳወቅ 3 ቀን የሚቆይ የርሃብ አድማ በማድረጋቸው የዝዋይ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ከአራት ወራት በፊት ማንኛውም ቤተሰብ እስረኞችን ለመጠየቅ ወደዚህ ቦታ ድርሽ እንዳይል የሚል ማስጠንቀቂያ በመስጠታቸው የእስረኞች ቤተሰቦች ምን አድርገዋቸው እንደሆነ አላወቅንም በማለት በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ እስረኞቹ ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸው ተጠብቆ ከቤተሰቦቻቸውና ከዘመዶቻቸው እንዲሁም ከጠበቆቻቸው ጋር የሚገናኙበት መንገድ በአስቸኳይ እንዲመቻች እንዲሁም በእስረኞች ላይ የተፈፀመው ሕገወጥ ድርጊት በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን እንጠይቃለን፡፡
በተለይም ጉዳዩ የሚመለከታችሁ ሀገር ዓቀፍና ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ደርጅቶች፤ ዲፕሎማቶች፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ኃላፊዎች፤ ጋዜጠኞችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ በእስረኞች ላይ እየተፈፀመ ያለውን ህገ-ወጥ ድርጊት ለማስቆምና የፖለቲካ እስረኞችን ለመታደግ እንዲሁም የህግና የሞራል ግዴታን ለመወጣት እንድንረባረብ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ በውጭ ሀገር የምትኖሩ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ይህንን አስከፊ ድርጊት በማውገዝ ድምፃችሁን እንድታሰሙ እንጠይቃለን፡፡
ድል የሕዝብ ነው!!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
ግንቦት 11 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባUDJ-SEALAbugida Ethiopian American Information Center

No comments: