sourse abugida
ከሰሞኑ ወያኔ መራሹ የአዲስ አበባ አስተዳደር ያወጣው አዲስ አበባ ዙርያ የኦሮሚያ ዞን ያካተተ ማስተር ፕላን እና የእዝ አስተዳደር ተግባራዊነትን በመቃወም በብዙዎች የኦሮሚያ ክልል ተወላጆችና ሃገር ወዳዶች ሰፊ ህዝባዊ የመብት ማስከበር ንቅናቄ ተቀስቅሶ በመንግስት ቅጥ ያጣ ግድያና እስር ለጊዜው ጋብ ቢልም አሁንም ቢሆን በህዝቡ ውስጥ ሞልቶ ሊገነፍል የደረሰ ቁጣ አለ፡፡ በሌላ በኩል በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ለረጅም ጊዜ ሲደረግ የነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ አሁንም ቢሆን የቀጠለ ቢሆንም እስካሁን ድረስም ቢሆን በሌሎች ማህበረሰቦች ዘንድ በሚፈለገው መልኩ ሊስፋፋ አልቻለም፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት ሁለት ሲሆኑ አንደኛው የመንግስት ህዝባዊ ተቃውሞን አቅጣጫ በማሳት እና በህዝቦች መካከል የተነሳ የዘረኝነት ወይም የሀይማኖት የበላይነት የተፈጠረ በማስመሰል በህዝቡ ውስጥ መከፋፈልን በመፍጠር “የእብድ ገላጋይ” እንደሚባለው እንዳስታራቂ መጥቶ በህዝቦችና በሀይማኖት መሀከል ለረጀም ግዜ የቆውን መዋደድ (ልብ አርጉ መቻቻል አላልኩም) እንዳልነበር አድርጎ የኢትዮጵያ ህዝቦች የተባበረ አንድነት እንዳይኖራቸው ማድረግ ሲሆን ሁለተኛወ ደግሞ የተቃዋሚዎች ሀዝባዊ ንቅናቄውን በማጠናከርና የጋራ አጀንዳ የሆነውን የወያኔን ጨቋኝ ስርዐት መገርሰስ የተለየ አትኩሮት በመስጠት እንዲሁም ህዝባዊ ንቅናቄው ሰፊ ሽፋን አንዲኖረው እምብዛም የጠነከረና የተቀናጀ ህዝባዊ የመብት ማስከበር ንቅናቄ አጠናክረው ባለማስቀጠላቸው ነው፡፡
በአብዛኛው ህዝባዊ ተቃውሞዎች ውስጥ የሚሳተፉ የወያኔ ካድሬዎች (Under Cover) እንደሚባለው በማዘጋጀት ዋና ተልዕኮዋቸው በህዝቦች መሀከል መቃቃር ሊፈጥሩ የሚችሉ አጀንዳዎችን በሰፊው እንዲሰራጩ እና በህዝባዊ ጥያቄዎች ውስጥ እንደ አንድ አጀንዳ እንዲካተቱ በማድረግ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን በማክሸፍ እንዲሁም ተቃውሞዎችን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ በመጠምዘዝ ውጤታማ እንዳይሆኑ በማድረግ ከጅምሩ የህዝብ ንቅናቄን ፈር ማሳት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የተቃዋሚወች በአቋም መግለጫ ብቻ መወሰን የተቃውሞ ንቅናቄዎቹ ስኬታማ እንደዳይሆኑ አስተዋጽዎ አድርጓል፡፡ ለዚህ በማሳያነት በቅርቡ የተደረጉት ህዝባዊ ንቅናቄዎች ምን አይነት ሙከራ እንደተደረገበት እንመልከት፡፡
የመጀመሪያው የሙስሊሞች ህዝባዊ ጥያቄ ሲሆን በመሰረቱ እስካሁን ከታዩት ህዝባዊ ንቅናቄዎች በተሻለ መልኩ የተደራጀ ቢሆንም በሚፈለገው መልኩ ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል አላካተተም (የሀይማኖት ነጻነት ሁሉንም ዜጋ የሚመለከት ቢሆንም) እንደውም ተደጋግመው በሚቀርቡ የመንግስተ መሰረተ ቢስ ፕሮፓጋንዳዎች (እስላማዊ መንግስት ማቋቋም በሚል ውሸት የታጨቀ) የሌላ ሀይማኖት ተከታዮች ሁኔታውን በጥርጣሬ የሚመለከቱበትና መንግስት የሚወስደውን ኢ-ፍትሀዊ እርምጃ በዝምታ ያለፉበት ሁኔታ የተፈጠረው፡፡ ለዚያውም ሙስሊም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በየአጋጣሚው ትክክለኛውን ጥያቄዎቻቸውን ለማስረዳት ጥረት እያደረጉ፡፡ በዚህ ረገድ ተቃዋሚዎች የመረጡት አካሄድ የጥያቄውን ትክክለኛነትና የገዠው ወያኔ መንግስት እርምጃ ትክክል አለመሆኑን አስመልክቶ መግለጫ መስጠት ብቻ ነው፡፡ጥያቄው የሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሆነ በማስረዳት በቂ የሆነ ቅስቀሳ ማድረግ እና ግንዛቤ ማስጨበጥ ሲገባቸው የተለሳለሰ አካሄድን በመምረጣቸው ተቃውሞው ሰፊ ህዝባዊ ተሳትፎ ሳይኖረው ቀርቷል፡፡ አሁንም ቢሆን ይህን ህዝባዊ ንቅናቄ ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እድሉ ስላለ ተቃዋሚዎች ህዝባዊ ተቃውሞውን ቅርጽ በማስያዝ የጋራ አጀንዳ ወደሆነው የወያኔን ጨቋኝ ስርዐት ገርስሶ ወደመጣል ሊመሩት ይገባል፡፡
በሁለተኛነት ማየት የፈለኩት የአሁኑ በኦሮሚያ ክልል ተወላጆችና ሃገር ወዳዶች የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞና ንቅናቄ ሲሆን፡ ህዝባዊ ተቃውሞውን እንደተለመደው ዋነኛው ጥያቄ የኦሮሚያ ክልል ህዝብን ብቻ የሚመለከት ተደርጎ ከመወሰዱም ባሻገር ችግሩ የጨቋኙ ስርዐት ያመጣው ሆኖ ሳለ እንደተለመደው የጥቂት ሀገወጦች እንደሆነና ችግሩም ከሌሎች ብሄረ ተወላጆች ጋር የተፈጠረ ግጭት ተደርጎ ቀርቧል፡፡
እውነታው ግን ዛሬ በኦሮሚያ ላይ እየተወሰደ ያለው ህገ ወጥ አፈና እና ጭፍጨፋ በተመሳሳይ መልኩ በአማራ ክልል (መሬት ተቀርሶ ለሱዳን ሲሰጥ)፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች በተለያየ ግዜ ሲወሰድ የነበረ መሆኑ ነው፡፡ እኔ የምለው ግን የብሄር ግጭት በኢትየጵያ ውስጥ ሆነ ተብሎ የሚጫር ነው ወይስ የብሔሮች አንድ ላይ ተከባበብሮ መኖር አለመቻል? የብሄር ግጭት የሚነሳው ወያኔ የመብት ማስከበር ጥያቄ ሲነሳበት ብቻ ነው እንዴ? በነገራችን ላይ የትኛው ብሄር ነው የእከሌ ብሄር ከክልሌ ይውጣልኝ ብሎ ሰልፍ የወጣው? ወያኔ ግን ሖነ ተብሎ አንዱን ብሄር ከሌላው የሚያጋጩ ነገሮችን በመቆስቆስና የተባበረ አጀንዳ እንዳይኖር በማድረግ የተባበረ ህዝባዊ ተቃውሞን ማጨናገፊያ ሁነኛ መንገድ አድርጎ ቀጥሎበታል፡፡
ስለዚህ የተቃዋሚዎች የቤት ስራም ማተኮር ያለበት ይህንን የወያኔ ሰይጣናዊ አካሄድ ማክሸፍን ዋና አጀንዳ አድርጎ መሆን አለበት ባይ ነኝ ፡፡ የሁሉም ህዝባዊ ጥያቄዎች መነሻቸውም መድረሻቸውም የወያኔ ጨቋኝ ስርዐት መሆኑ በገሀድ እየታወቀ እውነታው እየተድበሰበሰ ሌላ ቅርጽና ይዘት ሲሰጠው በቸልታ መመልከት ለወያኔ አገዛዝ መራዘም ዋነኛ ስትራቴጂ ከመመቻቸት ባሻገር ለወያኔ ህዝብን የመከፋፈል አጀንዳ ስር እንዲሰድ መፍቀድም ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ በአንድነት ጨቋኙን የወያኔን መንገስት ማስወገድ ዋና ዐጀንዳ አድርገን እንንቀሳቀስ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚነሱት ሁሉም ተቃውሞዎች የጋራ አጀንዳ የጭቆናው ስርአት መወገድ ነው ስለዚህ አዚህ አጀነዳ ላይ አናተኩር ያኔ የሁሉም ጭቆና ማብቂያና መቀበሪያ ይሆናል ተባብረን ወያኔን ከነአስከፊ ጭቆናው ጋር እናስወግደው!!!!
No comments:
Post a Comment